Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በጥቂት የፖሊሲ ማስተካከያ ብቻ አገሪቱ የምትለወጥባቸው ዕድሎች ብዙ ናቸው››

አቶ ጌታቸው ረጋሳ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ጌታቸው ረጋሳ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ናቸው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ በፕራይቬት ሴክተር ግሮውዝ ትምህርት ከስዊድን ዲፕሎማ ያገኙ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለ21 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴርም በምክትል ሚኒስትርነት ሠርተዋል፡፡ ከዚያም የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ምክትል ጸሐፊ በመሆን ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ  የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በመሆን እያገለገሉ ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ እንቅስቃሴና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል ቀዳሚ የሚባል ተቋም ነበር፡፡ ወቅታዊ አቋሙ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጌታቸው፡- ምክር ቤታችን እንደሚታወቀው ረዥም ዕድሜ ያለው ነው፡፡ አንጋፋ ነው፡፡ በእኛ አገር የንግድ ምክር ቤት አባል መሆን የሚቻለው በፈቃደኝነት ነው፡፡ እንደ አንዳንድ አገሮች ግዴታ አይደለም፡፡ ከ17 ሺሕ በላይ አባላት አሉን፡፡ ከ17 ሺሕ በላይ አባላት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ትልልቅና በአገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ኩባንያዎችን በአባልነት ይዟል፡፡ ከ60 እስከ 70 የሚሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችንም በአባልነት ይሳተፋሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኢትዮ ቴሌኮም ይጠቀሳሉ፡፡ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ 400 የሚደርሱ የውጭ ኩባንያዎች አባላት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በአዲስ አበባ ካሉት የንግዱ ማኅበረሰብ ቁጥር አንፃር ሲታይ አንዳንድ ሰዎች ቁጥሩ ትንሽ ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ትልልቅ የሚባሉ ኩባንያዎችን በአባልነት የያዝን ስለሆነ እነዚህ አባላቶቻችን በያዙዋቸው ሠራተኞች፣ በታክስ ክፍያ አፈጻጸማቸውና በኢኮኖሚ ውስጥ ባላቸው ሚና ዋነኛ ተዋዮችና ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ናቸው፡፡ ከአገሪቱ ኤክስፖርተሮች ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት አባላቶቻችን ናቸው፡፡ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም 40 በመቶ የሚሆኑት አባላቶቻችን ናቸው፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ አብዛኛዎቹ አባላቶቻችን ናቸው፡፡ ስለዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አባላትን ይዘናል፡፡ ከአባላት መዋጮ ከተመለከትነውም በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚሰበስብ ትልቁና ብቸኛው ንግድ ምክር ቤት ነው፡፡ ዓመታዊ በጀቱም እስከ 100 ሚሊዮን ብር እየተጠጋ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከንግድ ምክር ቤቶች አንፃር ስትገመግመው በምንም ሁኔታ የሚገናኝ አይደለም፡፡ በአፍሪካ ካሉ አምስት ትልልቅ ንግድ ምክር ቤቶች አንዱ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም ነው ብለን እናምናለን፡፡    

ሪፖርተር፡- ተፅዕኖ ፈጣሪ ብትሆኑም መንግሥት ይሰማችኋል ወይ?

አቶ ጌታቸው፡- በሕጎችና በደንቦች ላይ በምንሰጣቸው አስተያየቶች ልክ ድጋፍና ምላሽ አናገኝም፡፡ እንዲስተካከሉ ከምናቀርባቸው ሐሳቦች መንግሥት አንዳንዶቹን ሲቀበል ብዙዎችን አይቀበላቸውም፡፡ መንግሥት የራሱ የሆነ ልማታዊ አካሄድ ስላለውና የንግዱን ኅብረተሰብ ለማሳደግና ለማጎልበት ያለው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ምክንያት፣ የሚፈለገውን ተፅዕኖ ማምጣት አልቻልንም፡፡ ለምሳሌ የንግድ ምዝገባ አዋጅ ወጥቶ ልክ አለመሆኑና መስተካከል እንዳለበት ብዙ ጊዜ ነው ሐሳብ አቅርበን ያንን ለማሻሻል ብዙ ጊዜ የወሰደው፡፡ የታክስ አስተዳደርና ተመንን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚያወጣቸው ደንቦችን ብንወስድ ትክክል አይደሉም፡፡ ሊስተካከሉ ይገባል የምንላቸው ብዙ ሐሳቦች አሉ፡፡ ግን በመንግሥት ፈጣን ዕርምጃ ባለመውሰዱ የንግዱ ማኅበረሰብ ከዚህ ለውጥ ሊያመጣልን አልቻለም ይላል፡፡ ማለቱ ትክክል ነው፡፡ እኛም መድከማችን አልቀረም፡፡ ስለዚህ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለው የጋራ ትስስርና ግንኙነት አለመጠናከር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ኩባንያዎች የምክር ቤታችን አባላት ጭምር በሥራ ሒደታቸው ሌሎች አማራጮችን ይጠቀማሉ፡፡  በግል ግንኙነት ወይም ደግሞ በልዩ ልዩ ግንኙነቶች ጉዳዮችን የማስፈጸም፣ እንዲያውም በግል የመሄዱ ነገር አንዳንዴ የበለጠ ጠቃሚ መሆኑን የሚረዱበት ጊዜ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው አካሄድ ተገቢ ነው?

አቶ ጌታቸው፡- ሁኔታውን የፈጠረው ችግራቸውን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ ግን መሆን የነበረበት ንግድ ምክር ቤቱን በማጠናከር የጋራ ድምፅ ማሰማት ነበር፡፡ አንድ ሆኖ በመቅረብ ተቋሙንም ያሳድጉታል፡፡ ድምፃቸውን በጋራ ማሰማት  መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል፡፡ ይኼ አልሆነም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሙስና ግልጽነት መጥፋትና የብዙ ነገሮች ውጤት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ዘርፉ በኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ ምን ያህል አድጓል?

አቶ ጌታቸው፡- ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ኢኮኖሚ መንግሥት መር ነው፡፡ የግል ዘርፉ እያደገ የመጣ ነው፡፡ የሚገባውን ያህል አድጓል አላደገም የሚለው እንደ ጥያቄ የሚነሳ ቢሆንም፣ አሁን ባለበት ሁኔታ የግል ዘርፉ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት አስተዋጽኦ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአባላት ጋር በተያያዘ በቂ አባላት ያልኖሩዋችሁ ወይም 500 ሺሕ ነጋዴዎች ባሉበት ከተማ 17 ሺሕ ብቻ መያዛችሁ፣ የእናንተ አገልግሎት ውስን በመሆኑ ነው የሚለው አስተያት የጎላ ነው፡፡ አባልነት በፈቃደኝነት ላይ ስለመሠረተ ብቻ አይደለም ይባላል፡፡

አቶ ጌታቸው፡- ምክር ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎት በመሠረታዊነት በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ አንደኛው አገልግሎት መንግሥትንና የንግድ ኅብረተሰቡን እንደ ድልድይ ማገናኘት ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎችና ፖሊሲዎችን በሚመለከት እየተከታተለ ለንግዱ ኅብረተሰብ ምቹ ናቸው? ምቹ አይደሉም? የሚለውን አስተያየት እየሰጠ፣ በአጠቃላይ የንግዱን ኅብረተሰብ አስተዋጽኦ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ሕጎችና ደንቦች እንዲወጡ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የግል ዘርፉ ሊያድግ የሚችልባቸውን መሠረታዊ የሆኑ የቢዝነስ ልምምድ አገልግሎቶችን መስጠት ነው፡፡ ከሁለቱ አገልግሎቶች አንፃር መመዘን እንችላለን፡፡ መንግሥት በሚያወጣቸው ደንቦች ላይ፣ በታክስና በንግድ ሕጎች ላይ፣ በኩባንያ አመሠራረትና ፈቃድ አሰጣጥ ደንቦች ላይ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ግን በመንግሥት ዘንድ ተደማጭ ለመሆን ምክር ቤቱ የተጠናከረ መሆን አለበት፡፡ የተጠናከረ ከሆነ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለንግድ ማኅበረሰቡ ሲነሳ የከተፋፈለ ነገር ይታያል፡፡ ለምሳሌ የንግድ ምክር ቤቶች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የህዳሴ ነጋዴዎች ማኅበርና የነጋዴ ፎረም አሉ፡፡ ልማታዊ ባለሀብት የሚባሉም አሉ፡፡ ይህ የንግድ ማኅበረሰቡን ከፋፍሏል ይባላል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ መበታተኑስ ለምን አስፈለገ?

አቶ ጌታቸው፡- ይኼ ንግድ ምክር ቤቱ ብዙ ጊዜ የሚያነሳው ጉዳይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ማንም የመደራጀት መብት አለው፡፡ ነገር ግን ንግድ ምክር ቤቶች በአዋጅ በመንግሥት ሕግ የተቋቋሙ ሕጋዊ ተቋማት ናቸው፡፡ በሕግ እነሱን የሚተካ የለም፡፡ ህዳሴ  ፎረም፣ ደጋፊም ባላቸው ወይም ደግሞ ፎረም መንግሥት በአንዳንድ ምክንያቶች እየተደራጁ ሲመጡ ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸው ናቸው እንጂ፣ አዋጅን መሠረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ይኼ የንግዱን ማኅበረሰብ ከፋፍሎታል፡፡ በጋራ አንድ ሆኖ ድምፁን ለማሰማት ያላስቻለው አንዱ የአደረጃጀት ማነቆ ይኼ ነው፡፡ ተደራጅቶ አንድ ወጥ ሆኖ መቆም አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሦስት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የንግድ ማኅበረሰቡን ለማወያየት ፕሮግራም ሲያዝ ንግድ ምክር ቤቶች በአንድ በኩል፣ ሌሎቹ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ደግሞ በሌላ በኩል፣ ለዝግጅቱ ኃላፊነት ለመውሰድ ሲከራከሩ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ልዩነት እንዳለ ያሳያል፡፡

አቶ ጌታቸው፡- የንግዱ ማኅበረሰብ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ቢኖረው ኖሮ ለመደራጀትና ከመደራጀት የሚገኘው ጥቅም ላይ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ሁሉም በተለያዩ ትስስሮች የራስን ጉዳይ ማስፈጸምና ውድድርን መሠረት ያላደረግ እንቅስቃሴ በመኖሩ፣ ወደ ንግድ ምክር ቤት መምጣት የማያስፈልጋቸው አሉ፡፡ አሁን ወደፊት ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ግን ተስፋ አለ፡፡ ሰፊ የሆነ የውድድር መንፈስ ስለሚፈጠር በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሁሉ በውድድር ብቻ የጋራ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮችን ሊቀይር የሚችል ድምፅ ማሰማት ስለሚያስፈልግ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ የግድ ወደ ምክር ቤቱ በጋራ ችግሩን ለመፍታት ስለሚመጣ ነገሮች ይለውጣሉ፡፡ ስለዚህ ወደፊት በጋራ ድምፅን ማሰማት ይቻላል የሚል ትልቅ ተስፋ አለን፡፡ አሁን ያሉት መከፋፈሎች ተወግደው ወደ አንድነት እንመጣለን ብለን እናምናለን፡፡ የውድድር ሥርዓት ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ በውድድር ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱ ኩባንያ ራሱን አደራጅቶ፣ ራሱን አዘጋጅቶ የሚወጣው ይሆናል፡፡ ለዚህ ውድድር ደግሞ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚደግፈው ተቋም የግድ ስለሚያስፈልገው ወደ ምክር ቤቱ ይመለሳሉ ብለን እንገምታለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በለውጥ ላይ ነች፡፡ ነገር ግን አሁንም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር አለባት፡፡ አሁን እየተከናወነ ያለው ለውጥ ለንግድ ማኅበረሰቡ ምን ያመጣል ብለው ያምናሉ? በእርስዎ ዕይታ አሁን ያለው ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ጌታቸው፡- እንግዲህ የአገራችንን ኢኮኖሚ በምንመለከትበት ጊዜ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ በመንግሥትም በኩል ይፋ የሆኑ አሉ፡፡ በተግባር በንግድም ሆነ በኢንቨስትመንት ሥርዓቱ በግልጽ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አገሪቱ ካለባት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፡፡ የኤክስፖርት ዘርፉ ተዳክሟል፡፡ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአብዛኛው ግቡን መምታት እንዳልቻለ ታይቷል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ የግብዓትና የውጭ ምንዛሪ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ከሎጂስቲክስ፣ ከሞኒተሪ፣ ከፖሊሲና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አሁን እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴ ወደፊት የምናየው ነገር ጥሩ ነው የሚል ግምት አለኝ፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ችግሮቹን መረዳታችን ነው፡፡ ችግሮቹን ከተረዳን ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት መንግሥትም የግሉም ዘርፍ የየራሳቸውን ሚና ቢወጡ ወደ ተሻለ ሁኔታ እንመጣለን፡፡ አሁን እያየናቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች ጠቃሚ ናቸው፡፡ የውጭ ገንዘብ ወደ ባንክ አምጥታችሁ መንዝሩ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባደረጉት ጥሪ መሠረት፣ ብዙዎች ወደ ባንክ ሄደው መመንዘራቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡ በተደረገው ጥሪ መሠረት ሕዝቡ ለውጡን በመደገፍ ለአገሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ ባለው ፍላጎት፣ ጥሪውን ተቀብሎ እያስገባ ነው ያለው፡፡ ነግር ግን ይህንን ቀጣይ ለማድረግ ደግሞ የገንዘብ ፖሊሲ ማስፈጸሚያዎች ሥራ ላይ መዋል አለባቸው፡፡ አንድ ሰው ሄዶ ሲመነዝር ወይም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ይኖራል፡፡ አንድ ነጋዴ እንደ ባለሀብት ከኢኮኖሚ አንፃር ጥቅሙ ምንድነው? ብለህ ስትጠይቅ  የገንዘብ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚባሉት ሥራ ላይ ሲውሉ የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ ማስተናገድ ይቻላል እንጂ፣ በአገር ወዳድነት ብቻ ልታስቀጥለው አትችልም፡፡ ዞሮ ዞሮ አሁን ያለው ሁኔታ የበለጠ ለቀቅ ያለ እየሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት ስትራቴጂካዊ ተቋማት የግል ዘርፉ እንዲገባ መፈቀዱ የውድድር መንፈስ ይፈጥራል ተብሎ በሰፊው የሚጠበቅ ነው፡፡ ይኼ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ለንግዱ ማኅበረሰብ ትልቅ የምሥራች ነው፡፡ ነገር ግን ኃላፊነትን ይዞ መምጣቱም መታሰብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ኃላፊነት?

አቶ ጌታቸው፡- እያንዳንዱ የግል ዘርፉ ተዋናይ በተጠያቂነት መንፈስ በውድድር ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ ከውጭ የሚመጡ ኩባንያዎች ይኖራሉ፡፡ በአገር ውስጥ ላሉም የመወዳደሪያ ሜዳው እየሰፋ ሲመጣ፣ ሁሉም በውድድር አሸናፊ የሚሆንበት ሥርዓት ያመጣል፡፡ ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የንግዱ ማኅበረሰብ መዘጋጀት አለበት፡፡ አንደኛ የንግድ ባህሉን ዕውቀቱን፣ ሲስተሙንና ማኔጅመንቱን መቀየርን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቅ ኃላፊነት መውሰድ የሚገባው ምክር ቤቱ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በሚፈጠረው የውድድር መድረክ የንግዱ ኅብረተሰብ ተዋናይ ሆኖ ውጤታማ መሆን የሚችልበትን በቂና ዘመናዊ የሆነ ድጋፍ መስጠት አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ዳያስፖራዎች እዚህ መጥተው ኢንቨስት እናድርግ እያሉ ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት በጋራ እናመጣለን እያሉ ነው፡፡ ለእነሱ የሚሆን በቂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቋም ንግድ ምክር ቤቱ ይዞ መገኘት አለበት፡፡ አለበለዚያ ታሪክ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህም ነው ከወቅቱና ከጊዜው አንፃር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሥራዎች እየሠራ፣ ራሱንም እያደራጀ ነው የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማትን በከፊል ወደ ግል ለማዛወር ተወስኗል፡፡ ወደ ግል በከፊል ይዞራሉ ከተባሉት ውስጥ ቴሌ፣ ኤሌክትሪክ ኃይልና አየር መንገድ የንግዱ ምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡ የእነዚህ ተቋማት በከፊል ወደ ግል መዛወር ምን ያስገኛል? ምንስ ያስቀራል?

አቶ ጌታቸው፡- ፕራይቬታይዜሽን እንደ ጽንሰ ሐሳብ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1985 በማርጋሬት ታቸርና በሬጋን ጊዜ ነው፡፡ ፕራይቬታይዜሽኑን በሁለት ገጽታዎች እናየዋለን፡፡ በለሙ አገሮች ውስጥ ፕራይቬታይዜሽን ውስጥ የሚገባው የመንግሥት  ኩባንያዎች ብዙ ጊዜ ውጤታማ ስለማይሆኑ ወደ ግሉ ዘርፍ ቢዛወሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፣ ምርታማነታቸው ይጨምራል በሚል አሠራር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓውድ በለሙ አገሮች ውስጥ ፕራይቬታይዜሽን ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም ገበያው ቀልጣፋ ነው፡፡ ተወዳዳሪ የሆነ ገበያ አለ፡፡ ብዙ ባለ ሀብቶች ስላሉ የገዥዎች ችግር የለም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በሚሸጡበት ጊዜ ጥሩ የሆነ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ለዚህ ዓይነት ሽያጭ ደግሞ የፋይናንስ ምንጮች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ፋይናንስ እንደ ልብ ያለበት ኢኮኖሚ ነው፡፡ ካፒታል ማርኬት ያደገበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሽግግር ኢኮኖሚ የሚባሉ አሉ፡፡ እኛ ከሶሻሊዝም አሁን ወዳለንበት ስንመጣ ፕራይቬታይዜሸን ማድረግ ለተሻለ ምርታማነት ብቻ ሳይሆን፣ የግል ባለሀብቶች የመፍጠሪያ መንገድ ጭምር ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ለምሳሌ እኛ የመንግሥት ኩባንያዎችን ፕራይቬታይዝ አድርገናል፡፡ ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን አዲስ አይደለም፡፡ እስከ 2003 ዓ.ም. ከ225 በላይ ኩባንያዎች ተሸጠዋል፡፡ ይህ ሲሆን ዓላማው አንድ ገቢ ለማግኝት ነበር፡፡ ሁለተኛው ከመንግሥት ይልቅ በግሉ ዘርፍ ቢያዙ የተሻለ ይሆናል በማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ፕራይቬታይዝ በማድረግ የግል ዘርፉን ማሳደግና ማስነሳት ይቻላል ከሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ኩባንያዎች ሲሸጡ ግን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታሳቢ ተደርጎ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

አቶ ጌታቸው፡- ቅድም ገቢ ያልኩህ በዚህ ይጠቀሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማግኘትም አንዱ ዓላማ ነበር፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ በዚያን ጊዜ በሽግግር ኢኮኖሚው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲገባ ለማድረግ ነው፡፡ የግል ዘርፉ ከሌለ የውጭ ኩባንያዎች እንዴት ገብተው ይሠራሉ ይባል ስለነበር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፕራይቬታይዝ በምታደርግበት በዚያን ጊዜ ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንዱ ችግር ተወዳዳሪ ገበያ የለም፡፡ ማን ይግዛው? በዚያን ጊዜ ሀብታም የለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ኩባንያዎቹን ለሽያጭ ሲያወጣ ሊገዙ የሚችሉት በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች ፕራይቬታይዝ የተደረጉት ኩባንያዎች በጥቂቶች የተያዙ ናቸው የሚባለው፡፡ ተወዳዳሪ አካባቢ ባለመኖሩ ትክክለኛውን ውጤት አምጥቷል ወይ የሚለውን ጥያቄ ያመጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በሽያጩ ማግኘት የሚገባውን ያህል ገቢ ተገኝቷል ወይ የሚለውንም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ምክንያቱም ገበያው የለም፡፡ ካፒታል ማርኬት የለም፡፡ ፋይናንሱም የለም፡፡ በአጠቃላይ የራሱ የሆነ ክፍተት ነበረው፡፡ እና ያን ጊዜ ስትራቴጂካዊ ሴክተር የሚባሉት መቆየታቸው ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ለፕራይቬታይዜሽን ምቹ ሁኔታ አለ?

አቶ ጌታቸው፡- አሁን ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ ስለመጣ ገበያው እየሰፋ ብዙ ባለሀብቶች ተፈጥረዋል፡፡ እንዲሁም ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ፕራይቬታይዝ ለማድረግ ጊዜው የበለጠ ጥሩ ነው፡፡ አንደኛ አገሪቱ በብድር ዕዳ ውስጥ ስላለች የውጭ ምንዛሪ ችግሯንም ለማቃለል ይረዳል፡፡ አንዳንድ ዘርፎች ደግሞ በግሉ ዘርፍ ቢያዙ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ በቴሌ ኮሙዩኒኬሽን አካባቢ በተለይ የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ብትመጣ ፕራይቬታይዝ ማድረጉ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የቴሌን ካነሳህ የመሠረተ ልማት ወጪ የሚባል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ኦፕሬሽኑ ላይ የበለጠ ለቀቅ በምታደርግበት ጊዜ ውጤታማነቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ስትወስድ ደግሞ አትራፊ ናቸው፣ በጥሩ ሁኔታ እየሠሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነሱን ደግሞ የውጤታማነት ሳይሆን በሌላ ዓላማ ታስተናግዳቸዋለህ፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ዕርምጃው ወቅታዊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለግል ዘርፉ መምጣት ጠቃሚ ነው፡፡ በአየር መንገዱ አስተያየት እንደተሰጠበት አትራፊ ነው፡፡ ውጤታማ ነው፡፡ በእሱ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ትንሽ ጊዜ የሚሰጥና ሊጠበቅ የሚችል በመሆኑ፣ በመሠረታዊ ጉዳዮች ምክንያት ቢዘገይ ጠቃሚ ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ተቋማት ፕራይቬታይዝ ለማድረግ ግን ቀድሞ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡  ከዚህ አኳያ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ጌታቸው፡- ፕራይቬታይዜሽን ውስጥ ከመግባት በፊት መሟላት ያለባቸው መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ፕራይቬታይዜሽን ሲካሄድ ቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ዝግጅት የሚባል ነገር አለ፡፡ ቅድመ ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የትኛውን ላስቀድም? በየትኛው ቶሎ ገዥ አገኛለሁ? የትኛው ክፍል ነው የሚሸጠው? የሚለውን ማሰላሰል ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛ የፋይናንስ ምንጭ የት ነው መባል አለበት፡፡ ለምሳሌ ካፒታል ማርኬት ያስፈልጋል፡፡ አክሲዮን እንዴት ይሸጣል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ስለሆነ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ነገር ይጠይቃል፡፡ ቀላል ነገር አይሆንም፡፡ ሌላው ሕጎችና የአሠራር ሒደቶች ይኖራሉ፡፡ ፕራይቬታይዝ ሲደረግ ግልጽ የሆነ አሠራርን መዘርጋት ያሻል፡፡ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኃን ሚና አላቸው፡፡ ለሕዝብ የሚሰጠው መረጃም ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ሒደቱ ቀላል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ በተገቢው ሁኔታ መሠራት አለበት፡፡ ድርጅቶች ከተሸጡ በኋላ የተሻሉ እንዲሆኑ ለማድረግ እንጂ ሸጦ ለመብላት ስለማይሆን መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ መሟላት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ደረጃ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ጌታቸው፡- መንግሥት በጥሩ ዝግጅት ለመግባት የሚንቀሳቀስ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አኳያ አማካሪ ምክር ቤት መደራጀቱ በጣም የሚደገፍና ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብሎም ሆነ በአሁኑ ወቅት የንግድ ማኅበረሰቡ መሠረታዊ ጥያቄ ሆነው እየቀረቡ ካሉ ጉዳዮች መካከል የፋይናንስ አቅርቦት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግሩም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤት አባላት በዚህ ችግር ውስጥ ናቸውና እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው? ሊደረግ ይገባል የምትሉት ነገር አለ?

አቶ ጌታቸው፡- ፋይናንስ በቂ ሁኔታ የሚገኝበት አገር የለም፡፡ ፋይናንስ ሁልጊዜ የቢዝነስ ተቋማት ችግር ነው፡፡ አሁን ያለውን የፋይናንስ ሥርዓት ስናይ በግልና በመንግሥት ባንኮች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የፋይናንስ ዘርፉ ራሱ ማደግ አለበት፡፡ አቅም ማጎልበት አለበት፡፡ ንግዱን ለማሳለጥና የግል ዘርፉ እንዲያድግ ለማድረግ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በፖሊሲ፣ በደንብና ከባቢውን በማመቻቸት መሥራት አለበት ብለን እናስባለን፡፡ የግል ዘርፉ ሊንቀሳቀስ የሚችልባቸው የተለያዩ አማራጮች በጥናትና በፖሊሲ ተሰናድተው መቅረብ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ አኳያም የንግድ ምክር ቤቶች የተለያዩ ሐሳቦችን እየሰነዘሩ ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪን ብትወስድ ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ ፍራንኮ ቫሉታ፣ ክሬዲት ሴልና የመሳሰሉት አሉ፡፡ ከውጭ የሚመጡ የባንክ አሠራሮችን ለማስፈን የሚረዳ ምኅዳር ማስፋት ጭምር ይጠይቃል፡፡ ዋናው ግን መንግሥት በፋይናንስ ዘርፍ የፖሊሲ ለውጥና ማስተካከያ ሥራዎችን ማከናወን አለበት፡፡ 

ሪፖርተር፡- የፖሊሲ ለውጡ እንዴት መቃኘት አለበት ብለው ያምናሉ? የውጭ ባንኮች መግባት አለባቸው የሚሉ ሐሳቦችም እየቀረቡ ነው፡፡

አቶ ጌታቸው፡- አዎ የውጭ ባንኮች መግባትን ያጠቃልላል፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ኢኮኖሚና ያለው ለውጥ ግድ ይላል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገና ከውጮቹ ጋር ግንኙነቱ እየሰፋ ከሄደ፣ የውጭ ኩባንያዎች እየበዙ ከመጡ የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሻላል አይሻልም ሳይሆን መዋቅራዊ እንቅስቃሴው ራሱ የግድ የሚመጣ ነው ብሎ መወሰድ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ካለው ሁኔታ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ይሄዳል ብለው ያስባሉ?

አቶ ጌታቸው፡-  አዎ በጣም ያድጋል፡፡ በጣም ተስፋ አለው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት አገሪቱ ያለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ የተጀመረው እንቅስቃሴም ሆነ አጠቃላይ ያላት ሀብት መልካም ነገር አመላካች ነው፡፡ ስለዚህ የነፃ ኢኮኖሚ የውድድር ሥርዓትን ብናጎለብት የተሻለ እመርታ ማምጣት እንችላለን፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብም መንግሥትም በፖሊሲ ደግፎት በአገራችን ውድድር የሚሰፋበት፣ ነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚጎለብትበትና ኢንቨስትመንቶችን የሚስቡ ተጨማሪ ማበረታቻዎችና አሠራሮች ቢፈጠሩ የበለጠ በፍጥነት እናድጋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌላው አመላካች ነገር ደግሞ በውጭ በምንቀሳቀስበት ጊዜ ብዙ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹም በብዙ ጉዳዮች ለመምጣት ዝግጁ ናቸው፡፡ በጥቂት የፖሊሲ ማስተካከያ ብቻ አገሪቱ የምትለወጥባቸው ዕድሎች ብዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አገሪቱ 24 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግሩም አለ፡፡ የፋይናንስ ችግሮች ሁሉ ባሉበት ሁኔታ እንዲህ በቀላሉ ማደግ አያስቸግርም?

አቶ ጌታቸው፡- አሁን እንደ ችግር ያነሳናቸው ችግሮች ጊዜያዊ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ያህል ዕዳ ይዞ ችግሩን ጊዜያዊ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ጌታቸው፡- ለዚህም ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛ ፖሊሲ በምናሻሽልበት ጊዜ የዕዳ ክፍያ ማስተካከያ አለ፡፡ ዕዳ ስረዛ አለ፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ ሲመጣ ዕዳውን መክፈል ይቻላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ያልካቸው ነገሮች ብዙ ችግሮች አይደሉም፡፡ ኅብረተሰቡ በአንድነት ተያይዞ፣ መንግሥትና የግል ዘርፉ ተያይዘው ከሠሩ ችግሩ ትንሽ ነው፡፡ ጊዜያዊ ነው፡፡ አገሪቱ ያላት ሀብት ከዚህ ሁሉ ችግር ያለፈ ነው፡፡ በሰውም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ባሏት ዕድሎች ችግሮቿን ለመወጣት ትላለች፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...