Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብኩን ንብረት!

በናታን ዳዊት

የመልካም አስተዳደር መጓደል አንዱ ማሳያ የአገርንና የሕዝብን ሀብት በአግባቡ አለመጠበቅና እንዳይጠበቅ ማድረግ ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ ሀብት በአግባቡ እንዲጠብቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት፣ የሥራ ኃላፊዎች ዝርክርክ አሠራር የሚፈጥረውን ብክነት መቆጣጠር አለመቻላቸው ነው፡፡  ነገሩን ከፍ አድርገን ካየነውም ለአገር ደንታ የሌላቸው ሹመኞች ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎችን በመያዝ እንደልባቸው በመፈንጨታቸው የሕዝብ ሀብት መና እንዲቀር ሆኗል፡፡

በአግባቡ ማቀድ፣ በዕቅዱ መሠረት መፈጸምና ይህ ሥርዓትም በተገቢው መንገድ ስለመተግበሩ የሚያረጋግጥ አሠራር መጥፋቱ ብቻም ሳይሆን፣ የተጠያቂነት ባህል አለማዳበሩ ጭምር የአገርን ሀብት የማባከንና የመበዝበዝ አባዜ እንዲስፋፋ መንገዱን ጠርጓል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም በጀቱን በአግባቡ ስለመጠቀሙ ጥርት ያለ መረጃ አቅርቦ ጥሩ የሠራው ሲወደስ፣ አጥፊውም ሲጠየቅ አለማየታችን ችግሩን አብሶታል፡፡

ሰሚ አጣ እንጂ በየዓመቱ የኦዲተር ጄነራል መሥሪያ ቤቱ ከሚያቀርበው ሪፖርት መረዳት እንደቻልነው፣ ጥቂት የማይባል የሕዝብ ገንዘብ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ አለማዋሉን ለዓመታት ይፋ ሲያደርግ መኖሩን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

ማሳሰቢያውም ማስጠንቀቂያውም ብዙም ፋይዳ ስላላመጡ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን የማባከን ድርጊቱ እየሰፋና እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ በግብታዊነት ተገዝተው ያለሥራ የተከማቹ፣ በዕታቀደው መሠረትም ተገዝተው ለሚፈለገው ዓላማ ሳይውሉ በየመጋዘኑ የታሸጉ ዕቃዎች በርካታ ናቸው፡፡ መጠነኛ እክል በሚገጥማቸው ወቅት በቀላሉ ተጠግነው መስተካከል የሚችሉ ተሸከርካሪዎችና ማሽኖች እንደ ጠላት ንብረት በአልባሌ ወዳድቀው ይታያሉ፡፡ በአገር ልጅ ጉልበትና ዕውቀት ተገጥጣጥመውም ተመርተውም ለስንት ሥራ ሲጠበቁ፣ ተገልጋዩ እጅ ከመድረሳቸው በፊት በትላልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቅጥር ግቢ ተጥለው ቦታ ያጣበቡ ስንትና ስንት ንብረቶች እንዳሉ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡ ይሁንና ግን ስንትና ስንት ገንዘብ የወጣባቸው ትራክተሮች፣ የግብርና መሣሪያዎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ብዛት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ለስንቱ አገር ይተርፋሉ የተባሉ ትልልቅ ተቋማት አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥመው ሲያበቁ ያለ አገልግሎት አጉረው በማስቀመጥ ምን አንደሚጠብቁ ለማወቅ አስቸግሯል፡፡ በመከላከያው የብረታ ብርትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የተገጣጠሙ ትራክተሮች በተለያዩ አካባቦቢዎች እንዲሁ ተመልካች በማጣት ተከማችተው ይታያሉ፡፡ እነዚህ ንብረቶች በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ መሆናቸው ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡

በማይረባ ብልሽት ምክንያት የቆሙ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች በየመሥሪያ ቤቱ መጋዘኖች ጥጋጥግና በየሜዳው ተጥለው  ሣር በቅሎባቸው ማየት ያሳምማል፡፡ ይህም ንብረት በማስተዳደርና በማስወገድ ረገድ አገሪቱ ያለባትን ሰፊ ችግር ያሳያል፡፡ ችግሮቹ ለአገርና ለሕዝብ ንብረት ተቆርቋነት የጎደለን ስለመሆናችንም የሚያሳብቁ ናቸው፡፡

በተለያዩ መጋዘኖች ውስጥ ታሽገው የመገልገያ ጊዜያቸው የሚያልፍባቸው እንደ መድኃኒትና ኬሚካል ያሉትን አደገኛ ንብረቶች እንቁጠር ካልንም ብዙ ጉድ እናወጣለን፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መጋዘኖች ጎራ ያለም ከየመቆጣጠሪያ ጣቢያና ኬላው የሚወረሱ ንብረቶች ቦታ አጣብበው መኖራቸው ማንን እንደሚጠቅም  ግልጽ አይደለም፡፡ እርግጥ ሕገወጥ ንብረት አይወረስ ለማለት ሳይሆን፣ ሌሎች አዋጪ መንገዶች ግን ሊፈለጉ ይገባቸዋል፡፡

ከውጭም ከአገር ውስጥም ከውጭም ንብረት እያግበሰበሱ የመግዛት አባዜ የተጠናወታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ በእጃቸው የሚገኘውን ንብረት እንኳ መላ ሳይፈልጉለት አዲስ ለመግዛት ላይ ታች ሲሉ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ንብረቶች እንዴትና በምን አግባብ ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ የሚጠይቅና የሚቆጣጠር ቆራጥ አካል ወይም ተቋም አለመኖሩም ሁሉም እንዳሻው የሚፈነጭበትን ሜዳ አስፋፍቶለታል፡፡

ይሁን እንጂ ስንት ጥሪት ተሟጦባቸው የተገዙ ንብረቶች ያለጥቅም ለዓመታት ፀሐይና ዝናብ ሲፈራርቅባቸው፣ በመጋዘን ሳሉም የሚዝጉና የሚሻግቱ፣ ስንቱ እየፈለጋቸው የማያገኛቸው መሆናቸው ሳያንስ ለዝርፊያም ጭምር የተጋለጡ ናቸው፡፡ አንዳንድ ንብረቶች ጠቃሚ የሚባለው ውስጣዊ አካሎቻቸው ተቦጥብጠው ባዷቸውን ሲቀሩ እያየን አይ የመንግሥት ንብረት እንላለን፡፡

እንዲህ ላሉት ንብረቶችና ባለንብረቶቹ መሥሪያ ቤቶች መላ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ ንብረቶቹን የሚያስተዳድር፣ ያለውንም አቅምና ብቃት የሚያጠናክር ጠንካራ አካል ማዋቀር ያስፈልጋል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሚገኙ ንብረቶች አንድ በአንድ መቆር አለባቸው፡፡ የሚጠገኑት ተጠግነውና ታድሰው በምን መልኩ ሥራ ላይ መዋል አንዳለባቸው ውሳኔ መሰጠት አለበት፡፡

እነዚህን ንብረቶች ዋጋ እንዲኖራቸው በሚድረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻልም መገመት ይችላል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ሜቴክ፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ የተለያዩ የልማት ድርጅቶችና ሌሎችም ተቋማት በየቦታው ያከማቿቸው ዕቃዎች ብቻ በዋጋ ቢተመኑ፣ ለምን እንደተከማቹ ቢታይ፣ የአገር ንብረት ምን ያህል እየባከነ እንደሆነ ስለምንረዳ እንደ አልባሌ የተጣሉ ንብረቶች የፈሰሰባቸው ሀብት እንባችንን ባፈሰሰው ነበር፡፡

ስለዚህ ከሕዝብ ጋር በመተባበር እነዚህን ንብረቶች በመጠቆምና ንብረቶቹን ለማስተዳደር ለሚችለው ተቋም በማሳወቅ፣ ንብረት እንዲሰበሰቡ ወደ ዋጋ በመለወጥም ጠቃሚ የንብረትና የሀብት ማዳን ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ከዚህ በኋላም ንብረቶች ያለአግባብ ተገዝተው እንዳይከማቹ፣ ወዲያው ለተፈለጉበት ዓላማ እንዲውሉ በሚያስችል አካሔድና በዕቅድ መሥራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አወጋገዱንም በተመለከተ ጠንካራ የአሠራር ሥርዓትን በመተግበር ብክነትን ማስቀረት የግድ ይላል፡፡

ሰርክ ከምናደምጣቸው ማስታወቂያዎች ውስጥ፣ በደረቅ ወደቦችና በጅቡቲ ወደብ  የተከማቹ ንብረቶችን የማንሳት ፈተና ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው፡፡  ንብረቶቹ  የአገር ሀብት የወጣባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲነሱ ማድረግ፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በመሥራት ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር መንቀሳቀስ ለአገርና ለሕዝብ ብዙ ይጠቅማል፡፡ ሀብትን ማባካን በምንም ምክንያት ይሁን በአገር የውጭ ምንዛሪ የገቡ ንብረቶች ከወደቦች መነሳት አልቻሉም ተብሎ ሌላ ተመሳሳይ ዕቃ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ መቀራመትና ስንቱን ድሃ እያስለቀሱ በሚሰበሰብ ታክስ ያለ ከልካይና ተመልካች በገፍ የሚከሰከሰው ገንዘብ ጡር አለውና ለሕዝብ የሚገደው አካል አደብ ይግዛ ማለት የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት