Sunday, June 23, 2024

በጅግጅጋና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች የተቀሰቀሰው ግጭት የፈጠረው ውጥረት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት በቀብረ ደሃር፣ በጎዴና በደገሃቡር ከተሞችም በመስፋፋት የክልሉ ብሔር አባላት ባልሆኑ ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጉዳት ደርሷል፡፡

የተደራጁ ናቸው የተባሉ ወጣቶችና የታጠቁ ኃይሎች በእነዚህ ነዋሪዎች ላይ የአካል ጉዳት በማድረስና ንብረታቸውን በማውደም ለዓመታት ከኖሩበት መኖሪያዎቻቸው እንዲፈናቀሉ፣ በእምነት ተቋማትና በትምህርት ቤቶች ተጠልለው በምግብና በመጠጥ ውኃ ችግር እጥረት እየተሰቃዩ ሕይወታቸውን እንዲገፉ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በርካቶች ሕይወታቸው በግጭቱ ወቅት ማለፉም ይታወቃል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩት ነዋሪዎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የመንግሥትን እጅ እየጠበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ከሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ግጭቶች በመቀነሳቸው አንፃራዊ ሰላም የሰፈነ ቢመስልም፣ በማንኛውም ሰዓት ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል የጠረጠሩት ነዋሪዎች በመጠለያዎቹ መቆየትን መርጠዋል፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ዘላቂ ሰላም በጅግጀጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈጠራል የሚል እምነት በማጣታቸው፣ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ከሶማሌ ክልል ወደ ድሬዳዋና ሐረር ከተሞች ለደኅንነታቸው በመሥጋት በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከስድስት ዓመታት በላይ በጅግጅጋ የክልሉ መስተዳድር ተቋም ውስጥ በባለሙያነት ተቀጥሮ በመሥራት ላይ የነበረው ቢንያም ኃይሉ፣ ከእነዚህ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

‹‹አሁንም የተረጋጋ ሁኔታ በጅግጅጋ አይታይም፡፡ በዚህ ምክንያት በከተማው መቆየትን ሥጋት ስለፈጠረብኝ ያገኘሁትን አጋጣሚ በመጠቀም ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሐረር ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመግባት ችያለሁ፤›› ሲል ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በጅግጅጋም ሆነ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ለሚገኙ የሶማሌ ብሔር ላልሆኑ ነዋሪዎች ኑሯቸውን ለመቀጠል አስተማማኝ የሰላም አየር አለ ለማለት እንደማይቻል ተናግሯል፡፡

ጥቂት የሲኖትራክ (የጭነት ተሽከርካሪ) አሽከርካሪዎች ትውውቅን መሠረት በማድረግ እነዚህን ነዋሪዎች በማውጣት ላይ መሆናቸውን የሚናገረው ቢንያም፣ እሱም ይኼንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ሐረር ከተማ መግባት መቻሉን ገልጿል፡፡

በተለያዩ የእምነት ተቋማት ተጠልለው የነበሩ ነዋሪዎችን አሳፍሮ እርሱ ከነበረበት ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ቀድሞ ሲጓዝ የነበረ ተመሳሳይ ተሽከርካሪ፣ ከጅግጅጋ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር እንደራቀ የመገልበጥ አደጋ እንደደረሰበት ማየቱን ገልጿል፡፡

‹‹እኛ የነበርንበትን ተሽከርካሪ በደረሰበት ወቅት የሦስት ሰዎች ሕይወት በአደጋው ማለፉን አይቻለሁ፡፡ በርካቶችም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እኛም አደጋ የደረሰባቸውን ለመርዳት ጉዟችንን ለተወሰኑ ሰዓታት እንዲዘገይ በመስማማት ተጎጂዎችን ስንረዳ ነበር፤›› ሲል የገጠመውን አሳዛኝ ክስተት ተናግሯል፡፡

በጉዟቸው ወቅትም ከፍተኛ የሆነ እሱ ጅግጅጋ ከተማ በነበረበት ወቅት ካስተዋለው የመከላከያ ሠራዊት በእጅጉ የሚበልጥ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ ሲገባ ማስተዋሉን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

እስከ ሐሙስ ዕለት የክልሉ የመንግሥት ተቋማት ሥራ አለመጀመራቸውን፣ የንግድ ተቋማትም እንደዚሁ ዝግ መሆናቸውን ቢንያም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ያደርግ የነበረውን በረራም ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ካለፈው ቅዳሜ ቀን ጀምሮ ማቋረጡን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ በርካታ ለጥቃት የተጋለጡ ነዋሪዎች ከክልሉ ለመውጣት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎትን እየጠበቁ እንደሚገኙ፣ ስልክ በመደወል የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመወትወት ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመቀልበስ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መረጋጋት በክልሉ መስፈኑን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ የተሻለ መረጋጋት በአብዛኞቹ አካባቢዎች የሰፈነ ቢሆንም፣ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የመመለሱ ተግባር ውስብስብና ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንፃራዊ መረጋጋት በሶማሌ ክልል እየሰፈነ መሆኑን እንደሚረዱ ለሪፖርተር የገለጹት የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ በዚህ ሳምንትም ከሶማሌ ክልል በመነሳት በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት የመሰንዘር እንቅስቃሴ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በጭናክሰን ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር፣ እንዲሁም በድሬዳዋ በኦሮሞዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸዋል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ ጋር ረዥም ድንበር የሚጋራ በመሆኑ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ይኼንንም የሰላም ሁኔታ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት እንደሚፈጥሩት በማመን፣ ክልሉ ኃላፊነቱን ለፌዴራል መንግሥት እንደተወ ነገር ግን አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመጠለያዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የገጠማቸውን ሌላው ከፍተኛ ችግር የምግብና የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ነው፡፡ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋትና መከላከል ኮሚሽን ከሐሙስ ነሐሴ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ቢታወቅም፣ አቅርቦቱ የሚፈለገውን ያህል ባለመሆኑ በመጠለያዎች በሚገኙት ላይ ከፍተኛ ሥጋት መደቀኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

የመከለካያ ሠራዊት ባለፈው ሐሙስና ዓርብ ወደ ክልሉ መግባት መቀጠሉን ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በተለይም ከጅግጅጋ ውጪ በቀብሪ ደሃር፣ በጎዴና በደገሃቡር ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር በመግባት ላይ መሆኑን ታውቋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮችም ከሶማሌ ክልል የፀጥታ አመራሮች ጋር ባለፈው ሐሙስና ዓርብ ውይይት ሲያደርጉ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የውይይቱ ዓላማም በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በቅንጅት መሥራት የሚቻልበት ሁኔታና አፈጻጸሙ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ዓርብ ነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ላይ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የክልሉን ሰላም በትብብርና በቅንጅት ለመሥራትም ከመከላከያ፣ ከፌዴራልና ከክልሉ ልዩ ኃይል የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡

በዋናነት በጀግጅጋ ከተማና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች ከቅዳሜ ጀምሮ የተከሰተው ቀውስ፣ በክልሉ መንግሥት ጥቂት አመራሮች እነሱ ያደረጁት ቡድንና የፀጥታ ኃይሉ የፈጠረው መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ አስረድተዋል፡፡

ምክንያቱን ሲያብራሩም የሶማሌ ክልል ተወላጆች በድሬዳዋ ከተማ ባካሄዱት ስብሰባ የሶማሌ ክልል አመራሮች ከሥልጣን እንዲለቁ የታቀደ እንደሆነ በመገመት፣ ‹‹ሥልጣን ልቀቅ ተብያለሁ በማለት የክልሉ አመራር›› የቀሰቀሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ተግባር ውስጥም የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በግጭቱ እንዲሳተፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ አመራሮች በሙሉ ሳይመክሩበትና ስለጉዳዩ አስፈላጊነት እንኳን ሳይገነዘቡ፣ የሶማሌ ክልልን የመገንጠል እንቅስቃሴ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ሥልጣኔን ከምለቅ ሞት እመርጣለሁ›› በማለት በቀውስ ውስጥ የመሸሸግና አገርን የማፍረስ አደጋ ያዘለ እንቅስቃሴ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ የኢሶሕዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ እድሪስ ኢብራሂም በተደጋጋሚ መረጃ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ይሁን እንጂ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ፕሮግራም ቅዳሜ ቀን በሰጡት አስተያየት ክልሉን የመገንጠል እንቅስቃሴ መኖሩን አስተባብለዋል፡፡

‹‹ለጊዜው ለመገንጠል አላሰብንም፣ በፌዴራል ሥርዓቱ እንተዳደራለን፡፡ ነገር ግን መገንጠል ምንም ሐሳብ አይደለም፣ ሕገ መንግሥቱም ለዚህ ዋስትና ይሰጣል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የመከላከያ ሠራዊቱ በሕገወጥ መንገድ ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ፣ የሶማሌ ክልል ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳያቀርብለት በጅግጅጋ ከተማ መሰማራቱን ኃላፊው አውግዘዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ክልሉን ከሚመራው ኢሶሕዴፓ አመራሮች ጋር የተፈጠረውን ቀውስ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲመክር ቆይቶ፣ ከውሳኔ ላይ መድረሱ ይታወሳል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ የፀጥታ ማስከበር ተግባር ለመፈጸም፣ በፍጥነትም በጅግጅጋ ከተማ መሰማራቱን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡

ሌላው ጉዳይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ አሌ) ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ የሥልጣን መልቀቂያ እንዲያቀርቡና በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር በጊዜያዊነት ርዕሰ መስተዳድሩን ተክተው እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት የሶማሌ ክልል የፋይናንስP ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዲ መሐመድ ተሰይመዋል፡፡

ይህ ውሳኔ ተደፈጻሚ የሆነው በክልሉ ፓርቲ አማካይነት በመሆኑ፣ የሕጋዊነት ቅደም ተከተሉ በቀጣዮቹ ጊዜያት በክልሉ ምክር ቤት እንደሚፈጸም ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ይኼንንም የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ እድሪስ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ተቋማትን የማጠናከርና የሕግ ተጠያቂነትን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጅግጅጋ ከተማ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ ነዋሪዎች አሁንም ፍራቻ እንዳላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ሰላም ማስፈን መጀመራቸው ግን ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የምግብና የተለያዩ አቅርቦቶች ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ከጅግጅጋ ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ግን አሁንም ችግር መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በማረጋጋት ላይ ናቸው፡፡ በሌሎች የክልል ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት በማረጋጋት ላይ መሆኑንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -