Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲሱ በጀት ዓመት ለዕዳ ክፍያ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቧል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ሐዋላ ገቢ ቆሞ እንደነበር ተገለጸ

ገቢ ንግድ ከ55 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል

እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ዕዳ ወደ ከፍተኛ አሳሳቢ የዕዳ ጫና ደረጃ አገሪቱን በመክተቱ በዚህ ዓመት የአጭር ጊዜ ብድሮችን እንዳቆመ ያስታወቀው መንግሥት፣ ለዕዳ ክፍያ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስታወቀ፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ የዕዳ መጠን ከ24 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመድረሱና የዕዳ ጫናው መጠን ከፍተኛ ሥጋት ደረጃ አገሪቱን በማስገባቱ የተነሳ መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከፈሉ፣ ከፍተኛ ወለድ የሚታሰብባቸውና የችሮታና የእፎይታ ጊዜያቸው አነስተኛ የሆኑ የብድር ዓይነቶችን (ኮሜርሺያል ሎንስ ወይም ነን ኮንሴሽናል ሎንስ) ማቋረጡን አስታውቋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ማክሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፣ የአገሪቱ የዕዳ ጫና መብዛት ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ ሳቢያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የአጭር ጊዜ ብድር እንዳይበደሩ ተከልክለዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ለዕዳ ክፍያ መዋሉን አቶ ሐጂ ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት በ2010 ዓ.ም. በመንግሥት ግምጃ ቤት አማካይነት ከውጭ የተገኘው ብድር 2.6 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አስታውሰው፣ ከዚህ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥት የብድር ድርሻ 1.45 ቢሊዮን ዶላር ወይም 55.8 በመቶ እንደነበር፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች (በአብዛኛው የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ) ድርሻ 1.16 ቢሊዮን ዶላር ወይም 44.2 በመቶ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ አገሪቱ ላለባት የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ400 ቢሊዮን ብር ወይም ከ14 ቢሊዮን ዶላር (በወቅቱ ምንዛሪ ሲሰላ) በላይ ዕዳ እንዳለባቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በመሆኑም መንግሥት  በልማት ድርጅቶች በኩል አገሪቱ ያለባትን ዕዳ በራሳቸው በልማት ድርጅቶቹ እንዲሸፈን ማድረጉን፣ የሰጠውንም የብድር ዋስትና ኃላፊነት ወደ ተቋማቱ ማዛወሩን ይፋ አድርጓል፡፡

የአገሪቱን የዕዳ ጫና ብቻም ሳይሆን አገሪቱን የክፍያ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ ካዛቡት መካከል የወጪ ንግዱ እየተዳከመ መምጣት አንዱ ነው፡፡ እስከ አሥር ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ሲነገርለት የቆየው የወጪ ንግዱ ዘርፍ፣ በ2010 ዓ.ም. በ2.8 ቢሊዮን ዶላር ተገድቧል፡፡ ካለፈው ዓመት አኳያም ቢሆን በ79 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያነሰ አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ የገቢ ንግዱ ከ55.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመሆኑ፣ ከፍተኛ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን ጉድለት እንዲታይ ምክንያት ሆኗል፡፡ የገቢ ንግዱ ከ2009 ዓ.ም. አኳያ እንኳ የ30 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ79 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ሚኒስቴሩ ይፋ አድረጋል፡፡

የወጪ ንግዱ መዳከም ብቻም ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በባንክ በኩል እየተላከ እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ሐዋላ ገቢ የሚስተናገድበት የውጭ ምንዛሪ መስክም በ2010 ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ተቋርጦ እንደነበር አቶ ሐጂ ገልጸዋል፡፡ ይህ የሆነውም በውጭ በተለይም በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ዜጎች ይላክ የነበረው የሐዋላ ገቢ በፖለቲካ ተቃውሞ ምክንያት በባንክ መላክ እንዲቋረጥ ግፊት በመደረጉ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና የወጪ ንግዱ ገቢ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ሥራ በሚጀምሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንቅስቃሴ እንደሚታገዝ መንግሥት ተስፋ እንዳለው ያስታወቁት አቶ ሐጂ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም በመደበኛው የሐዋላ መላኪያ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር ቤት ለመላክ መወሰናቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን እንደሚያስታግሰው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የዳያስፖራው ትረስት ፈንድና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ግኝት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ በበጀት ረገድ በ2009 ዓ.ም. ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደው ገቢ ታክስና ታክስ ነክ ያልሆኑትን ብድርና ዕርዳታን ጨምሮ፣ ከ280 ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሐጂ፣ ከታክስና ታክስ ነክ ካልሆኑ የገቢ ምንጮች 180 ቢሊዮን ብር ሊሰበሰብ መቻሉን፣ ከ53 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጉድለት ማጋጠሙን፣ በታክስ ይሰበሰባል ከተባለው ገቢ ውስጥ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ሳይሰበሰብ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ከ346 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚሰበሰብ መታቀዱ ይታወሳል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች