Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሒደት ራሱን ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውጪ እንደሚያደርግ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሒደት ራሱን ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውጪ እንደሚያደርግ አስታወቀ

ቀን:

በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ እየተፈተነ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደሚያወጣና ግንባታውን የግሉ ዘርፍ እንዲያካሂድ ማድረግ የሚያስችል አሠራር እንደሚዘረጋ አስታወቀ፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ቅዳሜ ነሐሴ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት አጠር ያለ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ አስተዳደሩ የተጀመሩ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችን በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ዕቅድ አውጥቷል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ሁሉንም የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች መንግሥት አያካሂድም፡፡ ኅብረተሰቡ የመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚካሄድበትን ቦታ ከመምረጥ ጀምሮ በግንባታው በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆን ይደረጋል፤›› ሲሉ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2005 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው አራት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች፣ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ተመዝግበው አብዛኞቹ በየወሩ ባንክ እየቆጠቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ይፋ ከተደረገው የመኖሪያ ቤት ፕሮግራም 10/90 በመጀመሪያው ዙር ግብ መቶ ሲጠናቀቅ፣ 20/80 እና 40/60 ፕሮግራሞች በተለያዩ ችግሮች ተተብትበው ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ ወደ ኋላ እየተጎተቱ ነው፡፡

በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተጀመረው መርሐ ግብር የተለያዩ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ወደ ፊት መሄድ እንዳልቻለ እየተገለጸ ነው፡፡

ከአራት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሥልጣን የተረከቡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት ለኅብረተሰቡ ባሰሙት ንግግር፣ ከዚህ በኋላ መንግሥት የሚከተለውን አሠራር ግልጽ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ መንግሥት የመኖሪያ ቤት እየገነባ ለነዋሪዎች የማቅረብ አሠራር ችግሩን ይፈታዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከዚህ ይልቅ የግሉ ዘርፍ በስፋት መኖሪያ ቤቶችን እየገነባ ግልጽ በሆነ አሠራር ለኅብረተሰቡ በሽያጭና በኪራይ የሚያቀርብበት አሠራር ይመቻቻል ብለው ነበር፡፡

 የፌዴራል መንግሥት ከያዘው ዕቅድ በመነሳት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን ከመኖሪያ ቤት ግንባታ በሒደት በማውጣት፣ የመኖሪያ ቤት ፈላጊው ሕዝብ የራሱን ቤት ራሱ የሚገነባበት መንገድ ለማመቻቸት የተለያዩ አማራጮችን እያየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በ1996 ዓ.ም. በተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ግንባታ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ለተጠቃሚዎች የተላለፉት 175 ሺሕ ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ የ40/60 ቤቶችን ጨምሮ ከ132 ሺሕ በላይ ቤቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ የቤቶች ግንባታ የሥራ አፈጻጸም በየጊዜው ደካማ ሲሆን፣ የቀድሞው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የ2010 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሥራ አፈጻጸም ደካማ የሆነበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡

‹‹በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የፋይናንስ እጥረት ተከስቶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአንዳንድ ኮንትራክተሮች ደካማ መሆን ለሥራ አፈጻጸሙ ዝቅተኛነት አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...