Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአሁኑ ወቅት ያለው የስካውት ሥርዓት በዘፈቀደ የሚከናወን ነው››

አቶ ዓለሙ ምትኩ፣ የካቶሊክ ልደታ ልጃገረዶች መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የዲሲፕሊን ጉዳዮች ኃላፊ

አቶ ዓለሙ ምትኩ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የስካውት አባል የነበሩ ሲሆን፣ በተለይ በቀድሞ ሥርዓት የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች፣ የስካውትና የተማሪዎች ጉዳይ ጽሕፈት ቤትን በኃላፊነት መርተዋል፡፡ በተጨማሪም በቀድሞው ወወክማ ውስጥ የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ መሥራች ሲሆኑ፣ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ በየካቲት 12 (እቴጌ መነን) ትምህርት ቤት በስፖርት መምህርነትም አገልግለዋል፡፡ በተለያዩ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ተዘዋውረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሙያ ቀስመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የካቶሊክ ልደታ ልጃገረዶች የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የዲሲፕሊን ጉዳይ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በስካውት እንቅስቃሴ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የስካውትን ጽንስ ሐሳብና የሚመራበትን ሕጎች በዝርዝር ቢያስረዱን?  

አቶ ዓለሙ፡- ስካውት ማለት በአጠቃላይ ትምህርታዊ የሆነ የሕፃናትና ወጣቶች እንቅስቃሴ ነው፡፡ በአዕምሮ እንዲበለፅጉ፣ በመንፈስ እንዲጠነክሩ፣ በአካል እንዲዳብሩና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ድርጅት ወይም ማኅበር ነው፡፡ ቀደም ሲል ስካውት የተለያየ ትርጉም ነበረው፡፡ አንደኛው ትርጉም ቃፊር ወይም ሰላይ የሚል ሲሆን፣ በውትድርና ሙያ ውስጥ ደግሞ ሲግናል ወይም መልዕክት የሚያስተላልፉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የመጣው ትክክለኛው ስሙ የሕፃናትና የወጣቶች እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስካውት የሚመራበት አሥር ሕጎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹና መሠረታዊ የሆኑት ሦስቱ ሕጎች ናቸው፡፡ አንደኛው ለእግዚአብሔር ሊደረግ የሚገባውን ማድረግ ወይም እግዚአብሔር የሚወደውን ሥራ መሥራት፣ ሁለተኛው ለአገርና ለሕዝብ ማድረግ የሚገባውን ማከናወን ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ የራስን ግዴታ የሚወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ስካውት በእነዚህ ሦስት መሠረታዊ ሕጎች ተመሥርቶ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡

ሪፖርተር፡- ስካውቶቹ ለኅብረተሰቡ ወይም ላሉበት ትምህርት ቤት የሚሰጡት አገልግሎት ምን ይመስላል?  

አቶ ዓለሙ፡- በመጀመርያ ስካውት የሆኑ ሁሉ የቀይ መስቀል ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ትምህርቱም የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ያተኩራል፣ ሥልጠናም ይቀስማሉ፡፡ በቀሰሙትም ሙያ የየአካባቢያችውን ማኅበረሰብና ትምህርት ቤታቸውን ያገለግላሉ፡፡ በየትምህርት ቤታቸው የራሳቸውንም ክሊኒክ ያላቸው ስካውቶች ነበሩ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ጠዋት በክብር ይሰቅላሉ፡፡ ከምሸቱ 12 ሰዓት ላይ በክብር ያወርዳሉ፡፡ ሰንደቅ ዓላማው ሲወጣና ሲወርድ ራሱን የቻለ መዝሙር አለው፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በስካውቶች ዘንድ ትልቅ ክብር አለው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ታሪክና ምልክት እንደመሆኑ መጠን መንከባከብ፣ ማክበርና መጠበቅ የስካውት ግዴታው ነው፡፡ ከጠዋት ፀሎት በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመዝሙር ታጅቦ በክብር መስቀልና ሲወርድም ራሱን በቻለ መዝሙር እየታጀበ ማክበር በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ትልቅ ቦታ የተሰጠውም ነበር፡፡      

ሪፖርተር፡-አፄይለ ሥላሴ ሥርዓት የነበረው የስካውት መዋቅር ምን ይመስል ነበር?  

አቶ ዓለሙ፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት በመጀመርያና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ስካውት መዋቅርና ተጠሪም ነበረው፡፡ የተጠሪው ጽሕፈት ቤት ወይም ቢሮ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ውስጥ ተቋቁሞ ነበር፡፡ የራሱ በጀትና የሰው ኃይልም ነበረው፡፡ በየትምህርት ቤቱም ተጠሪዎች ነበሩት፡፡ ያለ ምንም አስገዳጅነት ፍላጎት ያላቸው ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች የስካውት አባል የመሆን መብት ነበራቸው፡፡ ስካውት ውስጥ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የጎሳ ወይም የዘር ልዩነት የለም፡፡ አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣት ስካውት ለመሆን ከፈለገ በአላህ፣ ክርስቲያን የሆነ ደግሞ በእግዚአብሔር ስም ቃለ መሃላ ፈጽሞ ስካውት ሊሆን ይችላል፡፡ ባጅ (ምልክት) ይሰጠዋል፡፡ አንድ ጊዜ ስካውት ከሆነ ደግሞ ሁልጊዜ ስካውት ነው፡፡ ይህም ማለት ከአገር ውጭ የትም ዓለም ቢሄድ የስካውት አባል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስካውት ከሆነ በአፍሪካም ከዚህም ባለፈ የዓለም ስካውት አባል ይሆናል፡፡ ለዚህም በየሄዱበት አገር ሁሉ ባጁን ማሳየት ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በአሁኑ ሥርዓቶች መካከል ያለውን የስካውት እንቅስቃሴን እንዴት ይመለከቱታል?  

አቶ ዓለሙ፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የስካውት እንቅስቃሴ በደንብ ይካሄድ ነበር፡፡ የስካውት አወቃቀሩም በመላ ኢትዮጵያ እጅግ በተጠናከረ ሁኔታ ይገኝ እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የስካውት የበላይ ጠባቂ መጀመርያ ልዑል መኮንን ኃይለ ሥላሴ ቀጥሎ ደግሞ አፄ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡ በተለያዩ ዓለም ከሚገኙ ስካውቶች ጋርም ጥሩ ግንኙነት ነበር፡፡ የወንድና የሴት ስካውት በሚል ተለይቶ በሚገባ ተደራጅቶና ተገቢ በጀትም ተበጅቶለት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ደርግ ሥልጣን ላይ ወጥቶ አገሪቱን በሶሻሊስት ሥርዓት መምራት ጀመረ፡፡ በስካውት ሥርዓት ውስጥ ደግሞ መፍረስ የማይገባቸውና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉት፡፡ ከእነዚህም መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ‹‹ለእግዚብሔር ላደርግ የሚገባኝን ተግባር መፈጸም›› የሚል ይገኝበታል፡፡ ደርግ ያራምደው የነበረው ሥርዓት ደግሞ እግዚብሔር የሚለውን ቃል ማየት ቀርቶ መስማት አይፈለግም፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ሰርዙት ብሎ አሳስቦ ‹‹ሊሰረዝ አይችልም› የሚል መልስ ተሰጠው ‹ለምን?› በሚልበት ጊዜ ‹‹የዓለም የስካውት ማኅበር ራሱን የቻለ ከፖለቲካ ውጭ ስለሆነ ቃሉን ልንሰርዘው አንችልም›› የሚል መልስ ተሰጠው፡፡ ይህ ከሆነ እንግዲያውስ ልትቀጥሉ አትችሉም ብሎ የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር ጽሕፈት ቤትን ዘጋና ሠራተኞቹን በተነ፡፡ በምትኩ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር (አኢወማ) አቋቋመ፡፡ በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር ስሙ እንኳን መወራቱ ቀረ፡፡

ሪፖርተር፡- ስካውት እንደተዘጋ ቀረ ወይስ እነደገና አንሠራራ?

አቶ ዓለሙ፡- ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ ከምባታና ሐዲያ ውስጥ አንድ የካቶሊክ ቄስ ስካውት የሚለውን ስም ቀይረው ‹‹የወጣቶች በጎ ሥራ›› በሚል መጠሪያ በድብቅ የስካውት ተግባር ሲያከናውኑ ነበር፡፡ ክንውኑም የአቅመ ደካማ ሰዎችን መኖሪያ ቤት መጠገን፣ እርሻቸውንም መንከባከብ የመሳሰሉና ሌሎችም ሥራችዎች ይገኙበታል፡፡ ይህም ሥራቸው አካባቢው በነበሩ የኢሕአዴግ አባላት ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ በመምጣቱ እንቅስቃሴው ወደ ስካውትነት እንዲሸጋገር ተደረገ፡፡ ከዚያም ቄሱ ከነበሩበት አካባቢ ተነስተው አዲስ አበባ በመምጣት በአሥር የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች የስካውት እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ አደረጉ፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ 300 ወጣቶች ሠልጥነው ስካውት ለመሆን በቁ፡፡ ይኼው እንቅስቃሴ በናዝሬት፣ በመተሐራ፣ በሻሸመኔ፣ በድሬዳዋ ከተሞች፣ እንዲሁም በአማራና በትግራይ ክልሎች ተዛመተ፡፡ በዚህም 1,000 ያህል ስካውቶችን ለማፍራት ተቻለ፡፡ እንቅስቃሴው በዚህ ሳይገታ አዲስ አበባ ውስጥ በስፋት የሰረፀ ሲሆን፣ በደቡብ ክልል በሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ተስፋፍቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ስካውት በዚህ መንገድ መቋቋሙ በጎ ጅምር ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያለው አቋም ምን ይመስላል? ራሱን የቻለ ቢሮስ አለውን?

አቶ ዓለሙ፡- በቀድሞ ባንኮዲሮማ ሕንፃ ውስጥ ቢሮ ተከፍቶ ነበር፡፡ የቢሮውም ኪራይ ሆነ ለሥራ አገልግሎት የሚውሉ ወጪዎችን ሁሉ የሚሸፍኑ እኚሁ የካቶሊክ ቄስ ነበሩ፡፡ ቢሮው ሲቋቋም ወንበርና ጠረጴዛ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን በቀድሞ ጊዜ የስካውት አባል የነበሩት አንድ በጎ አድራጊ ጠረጴዛና ወንበር የመሳሰሉ መገልገያ ዕቃዎችን በመለገሳቸው ችግሩ ሊቀረፍ ቻለ፡፡ እንቅስቃሴውም ተጠናከሮ በአሁኑ ጊዜ ቢሮው ቀድሞ ከነበረበት ሕንፃ ተነስቶ አራት ኪሎ በሚገኝ ኪራይ ቤት በመዛወር እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀድሞ ሥርዓትና በአሁኑ ሥርዓት የስካውት እንቅስቃሴን እንዴት ይነፃፀራል?

አቶ ዓለሙ፡- በቀድሞ ሥርዓት የነበረው የስካውት ማኅበር ባለቤት ነበረው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ሥር በመደራጀት ወይም በመዋቀሩ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቶች የነበሩ የሰውነት ማጎልመሻና ስፖርት መምህራንም የስካውት  እንቅስቃሴን የመከታተል ኃላፊነት ነበረባቸው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ራሱን የቻለ ክፍል ነበረው፡፡ በዚህም መሠረት ስካውቱ ጎልቶ ታይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የስካውት ሥርዓት በዘፈቀደ የሚከናወን ነው፡፡ ሕፃናትና ወጣቶች የሚገኙት ትምህርት ቤት እስከሆነ ድረስ ትምህርት ሚኒስቴር ባለቤት ሆኖ ይህንን እንቅስቃሴ ማስተዳደር አለበት፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ እንቅስቃሴው በተፈለገው መንገድ ይሄዳል ማለት ዘበት ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባለቤት እንዲሆን ያስፈለገው አንዱና ዋነኛው ምክንያት በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል ስለሚያመጣ ነው፡፡ ለእንቅስቃሴውም በጀት ሊመደብለት ይችላል፡፡ የክልል ትምህርት ቢሮዎች የሚኒስቴሩን አካሄድ በተከተለ መልኩ ሊያደራጁት ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አልፎ አልፎ ጥቂት ትምህርት ቤቶች ናቸው በባለቤትነት መንፈስ እየተንቀሳቀሱ ያሉ፡፡ ለዚህም በጀት የላቸውም፡፡ የሚንቀሳቀሱትም የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራንና በጎ ፈቃደኛ የሆኑ አንዳንድ መምህራን በሚሰጡት ዕርዳታ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...