Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትናንትና ዛሬ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትናንትና ዛሬ

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በበኃይሉ በላይ

በዚህ ክፍል ሁለቱን ተጨማሪ ዘርፎችና ማጠቃለያውን እንመልከት፡፡ መጀመርያ ጉልበተኛውን የአገልግሎቱን ዘርፍ እናስቀድም፡፡

የአገልግሎቱ ዘርፍ

በፊውዳሉ ኢኮኖሚ ተጀምሮ በቀጣዮቹ ሥርዓቶች ስለሚዘምነውና ስለሚስፋፋው የአገልግሎት ዘርፍ፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት ከላይ ተገልጧል፡፡ ይኼም የራሱን የመንግሥትን አገልግሎት ጨምሮ ከግብርናውና ከማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጪ ያለውን ሥራ ሁሉ ይጠቀልላል፡፡ ህልውናው፣ ዓላማውና ግቡ በሁለቱ ዘርፎች በመንግሥት አስተዳደርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ  ከውጭ አገር ኢኮኖሚዎች ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ብቻ ነው፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን ንግድ ተኮር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ በአገራችን ሥራ (Business) የሚለው ሐሳብ የሚገለጸውም ንግድ በሚለው ቃል ነው፡፡ የሚለየው ኢንዱስትሪ የሚባለው ሥራ ብቻ ይመስላል፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ወይም ቢሮ ስንል ለሁሉም ሥራዎች ፈቃድ የሚሰጠውን መንግሥታዊ አካል ነው፣ እርሻን ጨምሮ፡፡ ንግድና ምጣኔ ሀብት ማለት በእንግሊዝኛው ቢዝነስና ኢኮኖሚ፣ በአማርኛው ሥራና ምጣኔ ሀብት ማለት ይመስላል በአገራችን፡፡

ከመንግሥት አገልግሎቶች በተጨማሪ የአገልግሎት ዘርፉ የአገር ውስጥ አቀባባይ ነጋዴዎችን፣ ሥራ ተቋራጮችን፣ የሙያ አማካሪዎችንና ተቀጣጣሪዎችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን (ባንክና ኢንሹራንስ)፣ አስመጪዎችን፣ ላኪዎችን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎችን፣ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎችን፣ የሪል ስቴት ገንቢዎችንና ባለቤቶችን፣ ወዘተ. ይጨምራል፡፡ በአገራችን መንግሥት፣ ፓርቲ፣ ግለሰብ፣ ወይም የእነዚህ ማኅበራት ባለቤቶቻቸው ናቸው፡፡ በመካከላቸው ግን ልዩነቶች የሉም፡፡ የመጀመርያ ህልውናቸው፣ ቀጣይነታቸው፣ ዕድገታቸውና ኪሳራቸው ከሥልጣንና ከፖሊሲ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ በከተሞች ይገኛሉ፡፡ የሥራና የአደጋው (Business Risk) ተጋላጮች አይደሉም፡፡ ወይም መጠኑ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ህልውናቸው ለመንግሥት ካላሠጋ፣ ከተሞዳሞዱና ከተፈቀደላቸው እያተረፉ ለመቀጠል አይቸገሩም፡፡

በባህሪያቸው አስገባሪዎች ስለሆኑ ለትርፍ ብቻ እንጂ ለተቋቋሙበት ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ፣ ለልህቀትና ለልዩነት አይደክሙም፡፡ በዚች አገር ኢኮኖሚም ይነካካቸዋል እንጂ ድርቅና ዝናብም አያደርቃቸውም፣ ወይም አያበሰብሳቸውም፡፡ ስለዚህ ማን ሞኝ አለ ብለው ከዚህ ጮማ ከሆነ ዘርፍ ወደ ሌሎች አኞ ወደሆኑ ዘርፎች ለመሸጋገር አይፈልጉም አይፈረድባቸውም፡፡ እርስ በርስ ይደጋገፋሉ፡፡ ከኢኮኖሚ፣ ከብዙኃኑና ከግብርናው ዘርፍ ጋር ያላቸው ግንኙነት ግን የቀጥታም ይሁን የተዘዋዋሪ በመሠረታዊ ባህሪው ጥገኝነት ነው፡፡ ቢመቻቸውም በዚህ መንገድ ግን መቀጠል አይችሉም፡፡ ወቅቱ የሚያስገነዝበን ይህንን ነው፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣን ጀምሮ ምቾታቸው ደግሞ በዝቷል፡፡ የእያንዳንዳቸውን ሥራ መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ግን አይቻልም፡፡ አጠቃላይ ምሳሌ ከመሬት ላይ እንመልከት፡፡

አንድ ቀን አዲስ አበባ ከተማ ለቡ ቀለበት መንገድ አካባቢ ድንገት የገባሁበት የቢሮና የቤት ዕቃዎች አቅራቢ የቻይናውያን ነበር፡፡ ይህ አቅራቢ ካሉት የቤት ዕቃዎች መካከል አንድ ስፋቱ ሁለት ሜትር የሚሆን አልጋ ላይ የተለጠፈው ዋጋ ትኩረቴን ሳበው፡፡ አላመንኩም ጠጋ ብዬ አየሁ፣ ጠይቄም አረጋገጥኩ፡፡ ድርስ ያለውን ተናገር፣ ኧረ መሻጫውን ምናምን በሌለው ፊክስድ ዋጋ የአልጋው ዋጋ 575,000 ብር ነበር፡፡ የአምራቹን አርሶ አደርና አርብቶ አደርን መደብ፣ ቆጥአጎዛና ጀንዲ ከጎጃም አዘነው (የቻይና ፎጣ እየተካው ነው) ጋር ዋጋውን በአምስት መቶ ብር ገምታችሁ ከዚህ አልጋ ዋጋ ጋር ስታወዳድሩት በአንድ ቤተሰብ  ከ1,150 ቤተሰብ ጋር እኩል ይሆናል፡፡ ባለቤቱ ማንም ቢሆን በባንክ፣ በኪስ ያለ ወይም ለፍጆታ የሚወጣ ገንዘብ የሥራ መለኪያ ነው ይሉናል ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፡፡ በመዲናችን ይህን አልጋ የሚገዛ (ኢንዱስትሪ ስለሌለን) የአንድ ላኪ (ኤክስፖርተር)፣ አስመጪ (ኢምፖርተር)፣ ወይም ሥራ ተቋራጭ (ኮንትራክተር) ወዘተ. ቤተሰብ የሥራ ዋጋ ከ1,150 አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ቤተሰብ የሥራ ዋጋ ጋር እኩል ይሆናል ይላል ኢኮኖሚያችን ሲተረጎም፣ ምንም ሳይጋነን፡፡ ይህን ያየሁት ቦሌ መደኃኔዓለም ባለ የገበያ ሕንፃ (ሞል) አይደለም፡፡ ገበያው ደርቶ ለቡ ቀለበት መንገድ ደርሶ ነው፡፡ ለነገሩ የዓለም ውድና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች፣ ሸቀጦች፣ መብልና መጠጦች በከተማዋ ብርቅ አይደሉም፡፡ አንባቢ የሚጠበቅበት ዘወር ዘወር ማለትና ማስተዋል ብቻ ነው፡፡ ይኼው ወደ ሌሎች ከተሞች እንደ አቅሚቲ ይቀጥላል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉ አያስፈልግም ወይም ጨርሶ ፋይዳ የለውም እያልኩ አይደለም፡፡ በተገኘው አንፃራዊ ሰላም እንደ ወጉ በተጀመረችው ድጋፍ የተገኘውን በግብርናው ዘርፍ ምርት ላይ የተመሠረተ ጥቂት የኢኮኖሚ ዕድገት ያለ አግባብ የዘረፈና ያበጠ ዘርፍ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ የተመረተ ምርት በተለያየ መንገድ ለገበያ መቅረብ የሚችልና መቅረቡም የማይቀር ቢሆንም፣ መንግሥት ኤክስፖርትን ለመደገፍ ብሎ የሚሸልመው ላኪዎችን ነው፡፡ አምራቾችን አያውቃቸውም፡፡ በብሔራዊ ባንክ ፊታውራሪነት በዶላር ሀራራ ላይና ንግድ ተኮር በሆነው ፖሊሲ ላይ ተመሥርቶ የዘለቀው የአገሪቱ የፋይናንስ ሴክተር ያለምንም ማስያዣ፣ ከውጭ ገዥ ጋር ውል ይዘው ስለቀረቡ ብቻ 90 በመቶ ብድር የሚሰጠው ለላኪዎች ብቻ ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ አምራቹ አምርቶ ላኪዎች ሲነግዱ አገር ባገኘችው የውጭ ምንዛሪ ከውጭ አገር ሸቀጥ የማስገባት (ኢምፖርት የማድረግ) ቅድሚያ መብት አላቸው፡፡ ለሚገኘው የባንክ ብድር ከኢምፖርት በሚያገኙት የደለበ ትርፍስ ለሚያካክሱት እንጂ፣ ላኪዎች የላኪነት ሥራቸውን የሚሠሩት በኪሳራ እንደሆነ በኩራት ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ኤክስፖርት ለማድረግ ውል የሚይዙት ደጅ ጠንተው እንጂ፣ በአገሪቱ ምርት ጥራትና ዋጋ ላይ ተደራድረውና ገበያ አማርጠው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ወደ ውጭ ለሚላኩና ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ለሚያመርቱ የእርሻ ፕሮጀክቶች ብድር ያቀርብ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሥጦታውን ለሚሰጠው ሰጥቶ (በጋምቤላ)፣ አበደርኩ ያለውንም እንደ ነገሩ በትኖ ከሰርኩ በማለት ዛሬ ማበደሩን አቁሟል፡፡ ለንግድና ለውጭ ምንዛሪ ብቻ ታጥቆ የቆመው ኢኮኖሚ በሚንሰፈሰፍለት የውጭ ምንዛሪ ማዳበሪያና ስንዴ ሲሸምት ሌላውን ትተን በአገር ውስጥ ገበያ ከአሥር ብር በታች ዋጋ ያላቸውን ጥርሳችንን የምንኮረኩርበት ስቲክኒና የቁማር መጫወቻ ካርታ. . . ወዘተ.  ከቻይና እያስገባ፣ ሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች በውጭ ምንዛሪና በውጭ ኮንትራክተር ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ በመገንባት እየተወዳደሩ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ደካማ የኤክስፖርት አፈጻጸም ሲባል ዛሬም አምርቶ ሲሸጥ የሚተረፍበትና ሲሸምት የሚተረፍበት ጭሰኛ የሚፈል ግን ፊውዳል እንጂ ማንን ያስታውሳል እያልን፣ በአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ የታየው ዕድገት በአገልግሎት ዘርፉ መቅረቱን ከሚከተለው ማስረጃ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ሦስተኛውን ዘርፍ እንመልከት የማምረቻ ኢንዱስትሪውን፡፡

የማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ

ቀለል ካለ ውጤታማ የመንግሥትና የግል አገልግሎት ዘርፍ ጋር የማምረቻ ኢንዱስትሪ ትክክለኛውና ጤናማው የከተማ ኢኮኖሚ መስክ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በአገራችን ከቱሪዝም፣ ከፊልምና ሌሎችም ቀጥሎ ኢንዱስትሪ የሚለው ቃል ይገለጻል፡፡ መፅናኛ ይመስላል፡፡ ከላይ በአገራችን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስለሌለን ያልኩት የዘርፉ ጅምርም ቢሆን አነስተኛ ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ ጉስቁልና፣ በአገልግሎት ዘርፉ እብጠትና ይኼው እስካሁን አማላይ ሆኖ በመቀጠሉና ሌሎች ተግዳሮቶች ምክንያት፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በታሰበለት የመዋቅር ለውጥ መራመድ ስለማይችልና ተስፋም ስለሌለው ነው፡፡

እመርታን ማሳየት ያልቻለው ግብርናችን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ የሚጎዳው በሦስት መንገዶች ነው፡፡ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር፣ በአገር ውስጥ ሰፊ የገበያ እጥረትና ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ በሚፈልገው የመዋዕለ ንዋይ ድርቅ ነው፡፡ ጉልበተኛው የአገልግሎቱ ዘርፍ ደግሞ በከፍተኛ ወጭ (ከአገር ውስጥ ግብርና አንፃር) ግብዓቶችን ከውጭ ገበያ ሊያቀርብለት ቢችልም፣ በኢኮኖሚው ያለውን አነስተኛ መዋዕለ ንዋይና የአገር ውስጥ ገበያውን በጡንቻው ይሻማዋል፡፡ ኢኮኖሚያችንና ዘርፉ በዚህ ሁኔታ ላይ ሲሆን፣ መንግሥት ድንገት ተነስቶ በብድርና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ አቅርበው ውጤታማና ቀጣይነት ያለው ዕድገት የሚያስመዘግቡ፣ ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ኢኮኖሚውን ወደ ኢንዱስትሪ መር በማሸጋገር የውጭ ምንዛሪ ችግርን እቀርፋለሁ ብሎ ተነስቷል፡፡ የአገሪቱ ተመሳሳይ በእጅ ያለ የተጨበጠ ገበያ በውጭ አገር በተመረተ የኢንዱስትሪ ውጤት እየተሸፈነ፣ ከቁጥጥራችን ውጪ በሆነ የዓለም ገበያ ተወዳድረው ውጤታማ የሚሆኑ ተቋማትን ማለም በንግድ ተኮር አቅጣጫ የተንሸዋረረ ዶሮዋን በምን የመቀየር ዕይታ ይመስላል፡፡

የውስን መዋዕለ ንዋይ ሀብት ባለቤቶች፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕውቀት፣ ልምድና ባህል ጀማሪ መሆናችንን ትተን በተለይ ከጥሬ ዕቃውና ከምርቱ ገበያ የራቀ፣ የወደብ ኪራይና ወጪ ያለበት አምራች ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችል ሁልጊዜ የቦታ፣ የጊዜና የወጪ (Time, Place and Cost)  ተግዳሮቶች እንዳሉበት መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ይህንን በርካሽ የሰው ጉልበት ብቻ ደግሞ ማካካስ ዘላቂ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ አንድ አገር ከዓለም የተነጠለ መሆን ባይችልም፣ የውጭውን ተፅዕኖ የሚሸከም በቂ የአገር ውስጥ አቅም ግዴታ ነው፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪውና ካፒታሊዝም ተወልደው ባደጉባቸው አገሮችም ቢሆን ጥቂት ባለሀብቶችና ብዙኃኑ ሠራተኛ የጎሪጥ የሚተያዩበት ሥርዓት እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሁኔታው እንዳለ በባዕድ ጥቂት ባለሀብቶችና በብዙኃኑ አገሬው መካከል፣ በአገራቸው ላይ ሲቀጥል ልዩነትን መጠበቅ ሞኝነት አይሆንም፡፡ በቅርቡ በአገራችን የታየው የሕዝብ እንቅስቃሴ ብዙ ተቋማትን ሲያወድም የፖለቲካ ተቃውሞ ብቻ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የእኛ ነው፣ የእኔ ነው ብሎ ቢያስብና ተጠቃሚ ቢሆን ለፖለቲካው ብቻ ሕዝብ ቆም ብሎ አስቦ መላ አያጣም ነበር፡፡ የራሱን ችግር ማስታመም እንጂ ለባዕድ ብዝበዛ፣ ጥቃትና የበላይነት ትዕግሥትና ልምድ የሌለውን ሕዝብ በተለየ ዓይን መመልከትም ይገባል፡፡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስኪያጅ ግድያ ወንጀል ቢሆንም መንስዔውን መመልከትም ይጠቅማል፡፡ ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች የውጭ ኢንቨስትመንትንና ገበያን ያለመው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀጣይ ተስፋ አይታየኝም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሀብትና ጊዜም መባከን የለበትም፡፡

ለአገር ውስጥ ገበያ በሥራ ላይ ያሉ ጅምሮችም ቢሆኑ ጥቂት በሆነው በከተሜው ፍላጎትና ገበያ ላይ የተወሰኑ ናቸው፡፡ የቢራ፣ የመጠጥ ውኃ፣ የምግብ ማቀነባበሪያዎች፣ የግንባታ ግብዓት ማምረቻዎችና ሌሎች ፋብሪካዎች ለጊዜው ብቅ ብቅ ብለው ትርፋማ ቢሆኑም ከሰፊው ገበያ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ፍላጎት፣ የመግዛት አቅም ጋር በምርት ዓይነትና ዋጋ የሆነ ቦታና ጊዜ ካልተገናኙ ዘለቄታዊ የኢንዱስትሪ የዘርፉን ዕድገት በተለይ በኢኮኖሚው የሚኖረውን ዓብይ ድርሻ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ በሒደት ወደ ዓለም ገበያ ለመጓዝም ከዚህ በኋላ ይቀላል፡፡

ማጠቃለያ

መንግሥትም ይሁን አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በአገራችን ለ27 ዓመታት የባጀው የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ውጤታማ እንደነበርና የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡን ሁለቱም ገልጻሉ፡፡ አቶ ኤርሚያስ ከፍተኛ የብድር ጫናንና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የመሳሰሉ የወቅቱ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተፈጠሩት መንግሥት ሲጀምር ትክክል ቢሆንም፣ ዕድገቱ የሚፈልገውን የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ ማሻሻ በየጊዜው ባለማድረጉ በተለይ በፋይናንስ መሠረተ ልማት ፖሊሲው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥትም ለወቅታዊ ችግሮች የታቀዱ የልማት ፕሮጀክቶች (በተለይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ የተባሉት) አፈጻጸምን እንደ ምክንያት በማስቀመጥ፣ የገጠመውን የኢኮኖሚ ፈተና ለማለፍ በመንግሥት እጅ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ለአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ለማስተላለፍ ወስኗል፡፡ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስም ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብም ተመሳሳይ ሲሆን፣ ዕርምጃው የወቅቱን የውጭ ምንዛሪና የዋጋ ንረትን ችግር ከመቅረፍ አልፎ ደካማ አፈጻጸም ያላቸውን የመንግሥት ድርጅቶች አቅም በማጎልበት ለአገሪቱ የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሚና ማሳደግና ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚያስችል ሁለቱም ይስማማሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮምንና ንግድ መርከብን በመጥቀስ፡፡

በኋላ ቀሩ የኦኮኖሚ ሥርዓት አማራጮች አልነበሩም፡፡ ውጤታማነትም ደካማ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ዘመናዊው ኢኮኖሚ የተደረገው ሽግግር በውድድር፣ በገበያና በአማራጮች ውጤታማ መሆን ወይም ደግሞ ይህን በሚያካክስ ዘመናዊ የመንግሥት አሠራር ውጤታማነትን በየጊዜው በማረጋገጥ ነው፡፡ በአገራችን ከሁለት አንዱን አማራጭ በትክክል መፈጸም ስላልተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ ቴሌኮምንና የንግድ መርከብን የአፈጻጸም ድክመቶች ማስረጃዎች አቅርበው፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር አስገንዝበዋል፡፡ ችግሩ ግን መንግሥት በባለቤትነት በያዛቸው የልማት ድርጅቶች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በፓርቲ፣ በግለሰብ፣ በዜጎች፣ በማኅበራትና በውጭ ባለሀብቶች በተያዙ በአገልግሎት ዘርፉ ተቋማትም በተለያየ መጠን ይቀጥላል፡፡

ከዚህ የሚለየው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን ውጤታማ መሆን የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ይሆናል፡፡ ስኬቱም የሚያያዘው ከፈተናውና ከውድድሩ ጋር መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሌሎችን ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ድርጅቶች ከፍተኛ ገቢና ትርፍ የሚያጋብሱ ተቋማት ቢሆኑም፣ በሥራቸው (Business) ልክ ግን አይደለም፡፡ ስለዚህ በባህሪያቸው ዘመናዊ የንግድ ድርጅቶች አይደሉም፡፡ እንዲያውም አንድ ለእናቱ የሆኑ የአስገባሪዎች ባህሪ የሚጎላባቸው ናቸው፡፡ ስለማያስፈልግ፣ ግዴታ ስላልሆነና የተያያዙ ስላልሆኑ ከአስገባሪ ብቃትን መጠበቅ ከባድ ነው፡፡  በግለሰብም ይሁን በመንግሥትና በፓርቲ ባለቤትነት ሥር ያሉ ሌሎች መሰል ተቋማትም በተለያየ መንገድ ተመሳሳይ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ቆም ብሎ ማሰብ፣ የኢኮኖሚውን እንቆቅልሽ መረዳትና ነባራዊ ሁኔታውን መቀየር ተገቢ ነው፡፡

መረጃው የሚጠቁመው በግብርናውና በኢንዱስትሪው በ2003/04 በጀት ዓመት የተመዘገበው ከፍተኛ ዕድገት፣ በ2004/05 በጀት ዓመት የአገልግሎት ዘርፉን ዕድገት ከነበረበት 6.3 በመቶ ከእጥፍ በላይ አሳብጦ ወደ 12.8 በመቶ ማድረሱን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የሁለቱ ዘርፎች የዕድገት ምጣኔ ሲቀንስ፣ የአገልግሎት ዘርፉ ዕድገት ግን ዋናው የኢኮኖሚ ዘርፍ ዝቅተኛ ዕድገት ባስመዘገበበት ወቅትም ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡ ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ በአንድ ዓመት መቶ በመቶ በሆነ ምጣኔ ያደገው የአገልግሎት ዘርፍ ከዚያ በኋላ ተመሳሳይ ምጣኔ ያለው ዕድገት ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ ከየት ያመጣዋል ባትሉኝ ከ12.8 በመቶ እየተንፏቀቀም ቢሆን አማካይ ዕድገቱ ከሁለቱ ዘርፎችና ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው አማካይ ዕድገት ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ጤናማ ባይመስልም በአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የነበረው ድርሻም ለውጥ አሳይቷል፡፡

ስለዚህ ከመንግሥት ከመሠረተ ልማት በጀት በተጨማሪ በማንኛውም ሁኔታ በአገልግሎት ዘርፉ በከተማ የተወሰነውን መዋዕለ ንዋይ (Capital) እና የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ አገልግሎቶችን (Services) ወደ ገጠርና ግብርናው ማንቀሳቀስ (Moblise) ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ማነጣጠር አማራጭ ያለው አይመስልም፡፡ የባከነው ጊዜ የሚያስቆጭ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ኋላ ቀር ዘርፍ ላይ አሁንም መረባረብ የመጀመርያው የቤት ሥራ ሲሆን፣ ቀዳሚው ደግሞ ገጠሩን በተለይ ለግብርና መሠረተ ልማቶች ግንባታ (ለመስኖና ለከርሰ ምድር ውኃ. . . ወዘተ. በአጠቃላይ ለግብዓቶችና ምርቶች የተሳለጠ እንቅስቃሴ) ምቹ ማድረግ ነው፡፡

ክረምትና በጋ ከዋና ዋና መንገዶች ወደ ሰፊው አርሶ አደርና አርብቶ አደር ቀበሌዎች የሚያደርሱ የመንገድ ግንባታዎችን ዕውን በማድረግ የሰብል ልማቱን፣ ሰፋፊ እርሻዎችንና የእንስሳት እርባታውን ካሉበት ከተፈጥሮ ጥገኝነት ለማላቀቅ፣ ለማዘመንና የምርት ዕድገትን ብቻ ሳይሆን እመርታን በአጭር ጊዜ እንዲያስመዘግቡ የአገሪቱን ውስን ዕውቀትና መዋዕለ ንዋይ ሁሉ ያለውን ከኩባንያዎች ሽያጭና በየትኛውም መንገድ የሚገኘውን በዚህ ዘርፍ መሠረተ ልማቶች ላይ ቅድሚያ ማፍሰስ (Invest) ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ለሐዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ ተብሎ የሚገነባው የፍጥነት መንገድ ወጪ ለአገሪቱ ግብርና ዘርፍ ቢውል ዘርፉን በመስኖ ማጥለቅለቅ ይችል ነበር፡፡ የፍጥነት መንገዱ፣ የኃይል ማመንጫው፣ ወዘተ. ከዚህ በኋላ ይከተላሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ልማቱን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየጠየቁን ባሉ የዚህ ዘርፍ ግብዓቶችና በመሠረታዊውና ሰፊው የአገር ውስጥ ሸቀጦች ገበያ ላይ አነጣጥሮ መጀመር ተገቢ ይሆናል፡፡ ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለጊዜው መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ ሀራራውን ማስታገስና ወደ ትክክለኛ ፍላጎት ማስተካከል እንጂ፣ አሁን ባለበትና በሚቀጥልበት ሁኔታ አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት በምንም መንገድ ማርካት እንደማይቻል ጥናቶች እንደሚያሳዩ መረዳት ተገቢ ነው፡፡

መንግሥት በእጁ ያለውን ሀብት በዚህ ሁኔታ ለመጠቀም የሚችል ቢሆንም፣ በሁሉም ርብርብ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ለመሆን ግን የግል ባለሀብቱን ተሳትፎም ይፈልጋል፡፡ ለተጨማሪ አቅም ብቻ ሳይሆን ለልዩነትም ጭምር፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንደሚለው በተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ፣ አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት በፋይናንስ ፖሊሲው ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን በከተማና በአገልግሎት ዘርፍ ያለውን እብጠት የሚበልጡ፣ የሚቀንሱ፣ የግብርናውንና የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ዘርፎች ምርታማነት፣ የአምራቾችን ውጤታማነት፣ ትርፋማነትና ተጠቃሚነት የሚያስጠብቁ አዳዲስ አቅጣጫዎችና ፖሊሲዎች ግዴታ ናቸው፡፡ በየክልሉ ተጠርንፈው በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የኢኮኖሚ ሀብቶች (Economic Resources) ለምሳሌ የሰው ጉልበትና ልምድ፣ የእርሻ መሬትና መዋዕለ ንዋይ (Labour, Land and Capital) ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚገናኙበት፣ ምርት የሚያመርቱበትን ሁኔታ ዕውን የሚያደርግ፣ ከኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ማሻሻያም በላይ የፖለቲካም  ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ በኋላ በአጠቃላይ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም ገበያ ድረስ አጭር፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ፣ ግልጽና በሒደት በተፎካካሪዎች የሚደምቅ፣ ለተለያዩ ሐሳቦችና አሠራሮች ክፍት የሆነ፣ በመውደቅና በመነሳት፣ በትርፍና በኪሳራ የታጀበ፣ የተሻለው የሚነግሥበት፣ ሌላው ከተሻለው የሚማርበት፣ በቅብብሎሽ አጠቃላይ ቀጣይ ዕድገት የሚመዘገብበት ገበያና አጠቃላይ ኢኮኖሚ በሦስቱም ዘርፎች ያስፈልገናል፡፡ በባህሪው ከፊውዳሊዝም የተላቀቀ፡፡ የፖለቲካችን ለውጥ የሚሰምረው በኢኮኖሚ ለውጡ ከታጀበ ስለሆነ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አመሠግናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው     [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...