Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሁለት ቡሔዎች ወግ

የሁለት ቡሔዎች ወግ

ቀን:

ቡሔ ማለት ብርሃን፣ ገላጣ ወይም የብርሃን መገለጥ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ደብረ ታቦር ተብሎ የሚታወቀው ዓመታዊ በዓል በአውሮፓ ቋንቋዎች ‹‹ትራንስፊጉሬሽን›› (Transfiguration) ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ ነሐሴ 13 ቀን፣ በአውሮፓዎች ኦገስት 6 ቀን ሲከበር ከወቅት አንፃር የኢትዮጵያው በክረምት አጋማሽ የአውሮፓው በበጋ አጋማሽ  ይውላል፡፡

ድርሳናት እንደሚያሳዩት የቡሔ በዓል መጀመርያ የተከበረው በአራተኛው ምዕት ዓመት በሶሪያ ሲሆን፣ በምዕራብ ቤተ ክርስቲያን መከበር የጀመረው  በአሥረኛው ምዕት ዓመት በፈረንሳይ ነው፡፡

ምሥራቆቹ ኦርቶዶክሳውያን በሚከተሉት የጁሊያን አቆጣጠር መሠረት ‹‹ኦገስት 6›› የሚውለው (የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንዷ ነች) በኢትዮጵያው ነሐሴ 13 ቀን ላይ ነው፡፡ ምዕራቦቹና ከምሥራቅ የተወሰኑት በሚከተሉት የግሪጎርያን አቆጣጠር መሠረት ‹‹ኦገስት 6›› የሚውለው ሐምሌ 30 ቀን (በጁሊያን ጁላይ 24 ቀን) ነው፡፡

የምሥራቁን የቢዛንታይን ግሪክ ኦርቶዶክስ ሥርዓት የምትከተለው በሮም የምትገኘው የቅድስት ማርያም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቡሔዋን ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. አክብራለች፡፡

የበጋው ቡሔ

ካርዲናል ቲሞቲ ዶላን እንደሚገልጹት በበጋማው የኦገስት ወር በቤተ ክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ የደስታ ብርሃን የሚንፀባረቅባቸው የበዓላት ቀኖች ቡሔና ፍልሰታ ናቸው፡፡ አንደኛው ቡሔ ኦገስት 6 የሚውልበት ቀን የበጋ ወቅት አጋማሽ (ሚድ ሰመር) ላይ የሚውልበት ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአውሮፓው ባሕረ ሐሳብ መሠረት በጋ (ሰመር) የሚቆየው ከጁን 21 ቀን እስከ ሴብቴምበር 23 ቀን ድረስ ሲሆን፣ አጋማሹም ኦገስት 6 ላይ ይሆናል፡፡ በዚህ የበጋ አጋማሽ ላይ ነው እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ታቦር ተራራ ላይ ከሐዋርያት ጋር ከወጣ በኋላ መለኮታዊ ብርሃኑ የተገለጠው፣ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነውና እሱን ስሙት›› የተሰማው፡፡

አውሮፓውያኑ ለበጋው አጋማሽ ልዩ ሥፍራ ይሰጡታል፡፡ ዕረፍት የሚወጡበት፣ ቤተሰብና ጓደኛን የሚጎበኙበት የደስታና የመዝናናት ጊዜን ያሳልፉበታል፡፡

ቡሔ ከሚከበርባቸው አገሮች አንዷ ስለሆነችው ቡልጋሪያ አልቤና ቤዞቭስካ እንደጻፉት፣ የቡሔ ዕለት ማለዳ ላይ ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያቀኑት በወቅቱ የደረሰ የወይን ዘለላን ይዘው ነው (በጃፓን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በቡሔ ዕለት የደረሰውን ፍራፍሬ ይዘው ይቀርባሉ)፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ቡራኬ ከተሰጠ በኋላ ሴቶች ወይኑን ለቤተሰቦቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ያድላሉ፡፡ እነሱም ያጣጥሙታል፡፡ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የተለያዩ ፍራፍሬዎች እንደ አፕል፣ ሃብሃብ (ወተር ሜለን) ያሉትም ከቤተ ክርስቲያን ይዘልቃሉ፡፡

የሁለት ቡሔዎች ወግ

በራዝግራድ ክፍለ አገር ያሉት ካፓንትሲዎች (Kapantsi) እምነት ቀያይ ወይንና ሃብሃብ በዕለቱ መቋደስ እኩይ ነገርን ይከላከልላቸዋል፡፡ በስሞሊየን አካባቢ ፔትኮቭ መንደር ስለሚኖረው ማኅበረሰብ የጻፈው ዲሚትሪ ማሪኖቭ እንደገለጸው በዓሉ ባህላዊ ሥርዓት አለው፡፡ በቡሔው ቀን ኅብረተሰቡ ሆሮ የሚለውን ዳንስ ይደንሳል፡፡ በቄስ ያስባረከውን ማርና የበዓሉ መገለጫ የሆነውን ዳቦ በማሩ እየተቀባ ይታደላል፡፡

በበጋ አጋማሽ ኦገስት 6 ቀን ተፈጥሮ ለውጥ ታሳያለች ብለው ያምናሉ፡፡ በዚሁም ሰውም የለውጥ ሐሳብ ያድርበታል፡፡ በድርሳናቸው እንደተገለጸው በዕለቱ የሰማይ መስኮት ሲከፈት እግዚአብሔር ለቀናዎች፣ ለጻድቃን ምኞታቸውን ይፈጽምላቸዋል፡፡ ቅዱሳኑ ብቻ የሰማይ መስኮት መከፈተን ያያሉ፣ ምኞታቸው እንዲፈጸምላቸው ፀሎት ያደርሳሉ፡፡ ይህ እምነት ኤጲፋኒ (ጥምቀት) ከሚከበርበት (ጃንዋሪ 6 ቀን) ጋርም ይያያዛል፡፡ በአገሩ በርካታ አካባቢዎች በዋዜማው ምሽት ወደ ሰማይ አንጋጠው የሰማዩ መስኮት ሲከፈት ለማየት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ (በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት በዓመት ውስጥ የሰማይ መከፈት የሚሆነው በየ52 ቀኑ ለሰባት ጊዜ መሆኑን አንዱም ጳጉሜን 3 ቀን መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡

ግሪክ ኢትዮጵያ በምታከብርበት ዕለት በዋዜማውና በዕለቱ የምታከብረው በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ነው፡፡ ተከታዮቿ የዓረብ ክርስቲያኖች በዋዜማው ምሽት በቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ሆነው እንጨት ከምረው በማንደድ በዙርያው ሆነው በዓሉን በማሰብ ያሳልፋሉ፡፡

የክረምቱ ቡሔ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓሉ በዋናነት ደብረ ታቦር መባሉ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን የገለጠበት ሥፍራ ደብረ ታቦር በመሆኑ ነው፡፡ መምህራን እንደሚገልጹት ቡሔ የሚለውም ብርሃንን ይጠቅሳል፡፡ በደብረ ታቦር ብሎ የተገለጠውን የፊቱን ብርሃን ጸዳል፣ የልብሱንም እንደ ነጭ በረዶ መሆን ያስረዳል፡፡

 በኢትዮጵያ ቡሔ የሚከበረው በክረምት ወቅት ነው፡፡ ክረምት እንደሚታወቀው ከሰኔ 26 ቀን እስከ መስከረም 25 ቀን ድረስ ባሉት 95 ቀናት ውስጥ ይዘልቃል፡፡ የቡሔው ዕለት የሚውልበት ነሐሴ 13 ቀን ደግሞ የክረምት አጋማሽ ነው፡፡ (ዘንድሮ ቡሔ ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በጁሊያን አቆጣጠር ኦገስት 6 ቀን 2018 ሲሆን፣ በግሪጎሪያን ቀመር ኦገስት 19 ቀን 2018 ይሆናል)፡፡

እንደ ካሕሣይ ገብረ እግዚአብሔር አገላለጽ ነሐሴ የተስፋ ምልክት፣ የምሥራች ዋዜማ፣ የብርሃን ተምሳሌት ናት፡፡ እሸት አዝላ፣ አበባ ታቅፋ፣ ብቅ ስለምትል ለገበሬው የተስፋ ምልክቱ ናት:: ነሐሴ ደግሞ በቡሔዋ ትለያለች:: የቡሔ በዓል አከባበር በመጠኑም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይለያያል:: በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከዋዜማው ነሐሴ 12 ቀን ጀምሮ የሚከበረው ምሽቱ ላይ ችቦ የሚለኮሰው የነሐሴ 12 ማታ በሥርዓተ አምልኮ ቀን (ሊተርጂካል ዴይ) አቆጣጠር የነሐሴ 13 መነሻ ነውና፡፡

የሁለት ቡሔዎች ወግ

 

በየአካባቢያቸው ልጆች የቡሔ ጨዋታን ይጫወታሉ፡፡ ያቀጣጠሉትን ችቦ ይዘው በየመንደሩ የሚጨፍሩም አሉ፡፡ ከኅብረተሰቡም እንደየባህሉ የቡሔው መገለጫ የሆኑ ሙልሙል፣ አምባሻ፣ አነባበሮሃንዛ ወዘተ ይበረከትላቸዋል፡፡

‹‹ቡሄ በሉ ቡሄ በሉ ልጆች ሁሉ

 አጨብጭቡ ዝም አትበሉ፣

 አንዱን አምጪው አታማርጪው

ወደ ጓዳ አታሩጭው፣

አንዱን አምጭው ያንን መላጣ

ቅቤ ቀቢው እንዳይነጣ፣

ደስ አለኝ ደሴ ዳቦ ደንደሴ፤›› ከሚጨፍሩት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡

እንደ ባህል አጥኚው ካሕሣይ ገብረ እግዚአብሔር አገላለጽ፣ ከቡሔ ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነገር፡– ‹‹ቡሔ ካለፈ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› የሚል ብሂል የሚሰማው ክረምቱ እየቀለለ ስለሚሄድና ፀሐይ ስለምትገለጥ ነው፡፡ በትክክለኛው የጊዜ ቀመር  ግን ክረምት የሚያበቃው መስከረም 25 ላይ ነው፡፡ ዶሮ ከጮኸ በኋላም ቢሆን ሌሊት አለ:: ከነብሂሉ ‹‹ቡሔ ካለፈ አለ ክረምት እነ እኝኝ ብላ እነቋግሚት፣

ዶሮም ከጮኸ አለ ሌሊት እነቁርቁሪት እነ ድንግዝዚት›› ሲልም ያክልበታል፡፡

መምህር መኩሪያ ተስፋዬ እንደጻፉትም፣ ‹‹ቡሔ ከዋለ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› መባሉ በኢትዮጵያክረምት መውጫ ዋዜማ ስለሆነ የክረምቱ አፈናው ተወግዶ /ተጋምሶ/ የብርሃን ወገግታ የሚታይበትበዶፉና በጎርፉ ተሸፍና የነበረች መሬት የምትገለጥበት በመሆኑ ነው፡፡

መምህሩ አያይዘውም ችቦ የመብራቱ፣ የሙልሙል ዳቦ የመጋገሩና የጅራፍ ማጮኽ ምክንያት ያብራራሉ፡፡ ‹‹የጌታችን ክብሩ በተገለጠበት ጊዜ ብርሃኑ የሌሊቱን ጨለማ ገፍቶት ነበር፡፡ የችቦው ብርሃን የጌታ ክብር መገለጡን፣ የጅራፋ ጩኸት ሐዋርያትን ያስደነገጣቸው የአብ የምስክርነቱ ቃል ምሳሌ ሲሆን፣ ኅብስቱ ጌታችን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የመሆኑ (የሥጋ ወደሙ) ምሳሌ ነው፡፡››

‹‹ፊቱ እንደ ፀሐይ … ሆ…    በርቶ የታየው

ልብሱ እንደ ብርሃን  ሆ…     ያንፀባረቀው

ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና

የቡሔው ብርሃን ለኛ መጣልን…›› እያሉ የሚጨፍሩት ልጆች ከቡሔያዊ ጨዋታቸው ማብቂያ ላይም ሙልሙል እንዲሰጣቸው የሚጠይቁት በሚከተለው መልኩ ነው፡፡

‹‹የዓመት ልምዳችን ሆ… ከጥንት የመጣ

ከተከመረው ሆ… ተመሶብ ይውጣ

የተጋገረውሆ… ሙልሙሉ ይውጣ››

 

በሔኖክ ያሬድ፣ ሮም፣ ጣሊያን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...