Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአሁን በአግባቡ ሊፈተሽ የሚገባው የኮንስትራክሽን ዘርፍ

አሁን በአግባቡ ሊፈተሽ የሚገባው የኮንስትራክሽን ዘርፍ

ቀን:

በብሩክ ፈለቀ

ዓለማችን ያላትን ከፍተኛ አንጡር ሀብት በመሠረተ ልማት ወይም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ ታፈሳለች፡፡ የዓለማችን ወጪም ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሰባትና ስምንት ዓመት ዓለማችን ለእዚሁ ኢንዱስትሪ በዓመት ከሰባት ትሪሊዮን ዶላር በላይ ታወጣ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ግን በብዙ እጥፍ ጨምሮ ከሃያ ስምንት ትሪሊዮን ዶላር በላይ እያወጣች እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያም ከአጠቃላይ በጀቷ 60 በመቶ የሚሆነውን ለእዚሁ ኢንዱስትሪ እንደምታውል ይታወቃል፡፡ አብዛኛውን የዘርፉ በጀት፣ በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቀውን ዘርፍ በአዲሱ መንገድ በአግባቡ መፈተሽ ካልተቻለና በነበረው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይኼንንም ከፍተኛ ሀብት የሚጠቀምን ዘርፍ በአግባቡ በጥራት፣ ሁሉን አሳታፊና ወጪ ቆጣቢ፣ በዕውቀትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በብልኃት የምንመራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ጸሐፊው የኮንስትራክሽን ባለሙያ ባልሆንም በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች ላለፉት አሥር ዓመታት ዘርፉን ለመመልከት የሚያስችል ዕድል ገጥሞኛል፡፡ እናም እንደ ዜጋ አገሪቱን በለወጡ ሒደት ውስጥ በመሆኗ ዕይታዬን ለሚመለከታቸው አካላት ለማካፈል ሞክሬአለሁ፡፡

ዕቅድና የአዋጭነት ጥናት

አገሪቱ ከትልልቅና ከሜጋ ፕሮጀክቶች ጀምሮ እስከ ትንንሽ የሕንፃ፣ የመንገድ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ድረስ ግንባታ እያከናወነች ትገኛለች፡፡ እነዚሰህ ሁሉ ፕሮጀክቶች መጀመሪያ በዕቅድ ተይዘውና በጀት ተፈልጎላቸው ሲልም፣ የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶላቸው ወደ ትግበራ ይገባሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ ካለኝ መረጃ ላለፉት ዓመታት ወደ ትግበራ የገባንባቸው ፕሮጀክቶች መነሻ ሁለት ነገሮች ይመስሉኛል፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ምንጫቸው የኢትዮጵያ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድና ሁለት ሲሆኑ፣ ሌላው ደግሞ በድንገቴና በፖለቲካ ውሳኔዎች ካለ ዕቅድ የተተገበሩ፣ የአገሪቱን አቅም ግራ ቀኝ ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያላገናዘቡ ናቸው፡፡ እንደ አገር ከፍተኛ የሆኑ ዕቅዶችን ማቀድ መልካም ሆኖ በግምትና በስሜት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ትልቁ ስህተትና ችግር ነው፡፡ በአንድ አውደ ጥናት ላይ አንድ አንጋፋ መሐንዲስ በጃንሆይ ጊዜ የነበረውን ልምድ ሲነግሩን፣ ዕቅዶች መጀመሪያ የተለያየ ሙያ ባላቸው ሰዎች የተዋቀረ ኮሚቴ ማለትም መሐንዲሱ፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ስታትስቲክስና የሚመለከተውን ዘርፍ የሚወክሉ ባለሙያዎች ዘንድ ይወርዳሉ፡፡       እነዚህ ባለሙያዎች የወረዱትን አገራዊ ዕቅዶች ለአገሪቱ ካላቸው ጥቅሞች አንፃር ደረጃ ይሰጧቸዋል፡፡ የአዋጭነት ጥናትም ይሠሩላቸዋል፡፡ በዚህም ከስሜት፣ ከፖለቲካዊ ጠቀሜታ አንፃርና በመሳሰሉት ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ ግምገማ አካሂደው በወንፊት ይነፏቸዋል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከአቅማቸው በላይ ዕቅድ በማቀድ፣ ከእዚሀ በፊት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ማኒስቴር በአሁኑ ጊዜ ግን ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አቅርበው ያፀድቃሉ፡፡ ምን ያህሉ ፕሮጀክቶቻችን በወቅቱና በሰዓቱ ለማኅበረሰቡ ጠቀሜታ ዋሉ? ለሚለው ጥያቄ ግን መልሱ የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም ከራስ ጠቀሜታ አልፈው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ የተባሉት ስኳር ፕሮጀክቶቻችን ትልቅ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡

በተለይም የአዋጭነት ጥናትን በተመለከተም ፕሮጀክቶች በሚካሄዱበት አካባቢ በመሄድ፣ ትክክለኛ ጥናት የሚካሄድባቸው ፕሮጀክቶች ያሉም አይመስልም፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የመጀመሪያው በምንም ሁኔታ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ይገባል የሚለው ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የአዋጭነት ጥናቶች በአብዛኛው ከሌሎች ፕሮጀክቶች ኮፒ ተደርገው በመቅረባቸው ነው፡፡ በዘርፉ የተለመዱ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ያፋጥናል፣ ገበሬው የሚያመርተውን ምርት በቀላሉ ለማድረስ የሚያስችሉ በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፣ የቱሪዝም ፍሰቱን ያፋጥናል የሚሉና የመሳሰሉት መላምቶች እንዲይዙ በማድረግ፣ ጥሩ ልብስ እንዲለብሱ ይደረጋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት ተወላጅነት፣ ብሔርተኝነትና በአካባቢው ማኅበረሰብ ተቀባይነት ለማግኘት ብቻ ተብሎ የሚዘጋጅ በመሆኑ ነው፡፡

በነገራችን ላይ በፕሮጀክቱ ላይ የሚወጣው ገንዘብና ማኅበረሰቡ የሚፈልገው አገልግሎት አልተገናኝቶም ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ በአንድ ወቅት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ፕሮጀክት ከኮንትራክተሩ ጋር ባጋጠመው እሰጥ እገባ ለኮንትራክተሩ የይገባኛል ጥናት ሊያደርግ በቦታው የተገኘው መሐንዲስ በአካባቢው ባሳለፈባቸው ሦስትና አራት ቀናት መንገዱ ያረፈበትን ቦታና ማኅበረሰቡን ለማናበብ ሞክሮ ነበር፡፡ ከዚያም ባለፈ ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ችሎ ነበር፡፡ እናም የማኅበረሰቡን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ያገኘው በመድኃኒትና በሕክምና መሣሪያ የተሟላ ጤና ጣቢያ፣ የተወሰኑ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም በቂ አለመሆናቸውንና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢው ጨርሶ አለመኖሩን ነበር፡፡ ይኼን ሲመለከት በከፍተኛ ወጪ ይኼን መንገድ ከመገንባት ይልቅ፣ የመንገዱን ደረጃ ዝቅ በማድረግ በሚተርፈው ሁለትና ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር የአካባቢውን ማኅበረሰብ የቅድሚያ ፍላጎቶች ማሟላትና የገበሬውንም ኑሮ የሚያሻሽሉ ተግባራት መፈጸም ያስችል ነበር በማለት፣ በአንድ ዓውደ ጥናት ላይ ሲናገር አድምጨዋለሁ፡፡ ‹‹እንዲያውም መንገዱ የዛሬ ሃያ ዓመት ሃያና ሰላሳ መኪኖች ማስተናገድ ከቻለም እንጃ!!›› የሚል ንግግር ጣል በማድረግ አስገርሞናል፡፡

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በተለይ ባለሥልጣኖቻችን በክልሎች ጉብኝት ሲያደርጉ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች ጋር ከልብ ያልሆነ ውይይት ያደርጉ ነበር፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ላይም የየአካባቢው ማኅበረሰቦች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ነበር፡፡ ጥያቄዎቻቸው አንዳንዴም የአገሪቱም ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነበር፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ሆስፒታል፣ ፋብሪካ፣ ወዘተ. . . ይገንባልን የሚል ነበር፡፡ ባለሥልጣኖቻችን ግን በተወላጅነት፣ በብሔርተኝነት፣ ለአፍ ማዘጊያና ለጊዜያዊ ጭብጨባ ሲሉ ብቻ ቃል ገብተው ይመለሳሉ፡፡ ይኼንንም ቃል የማይረሳው ማኅበረሰብ ከአስተዳዳሪዎቹ ጋር የሚሠራ ኮሚቴ ያዋቅርና ለፌዴራል መንግሥት ቃል የተገባልን ጉዳይ ምን ደረሰ? እያለ ጉትጎታ ይጀምራል፡፡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትም ጉዳዩ ይቀርብና ማን ነው ቃል የገባው? ፕሮጀክቱ በምን የገንዘብ ምንጭ ሊሠራ ነው? በሚሉ ማለቂያ በሌላቸው ጥያቄዎች አተካራ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ወጣም ወረደም ግን ማለቂያ የሌላቸው ፕሮጀክቶች መጀመራቸውና የመሠረት ድንጋይ መቀመጣቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ከሦስተኛ ትውልድ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ግንባታ በማቆም የትምህርት ጥራት ላይ እንሠራለን ከተባለ በኋላ፣ በሁለት ክልሎችና ሥፍራዎች ሁለት የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጊዜው ያለፈበት እንገነባለን የሚል ከአንገት በላይ ቃል በመግባታቸው የተፈጠረውን አተካራ ልብ ይሏል፡፡

የኮንስትራክሽን ጨረታዎች

በዘመናችን የኮንስትራክሽን ጨረታዎች መልከ ብዙ ጦርነቶች የሚካሄዱበት አውድማ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሞተረኛው ለተወሰኑ ሰዓቶች ባልታወቁ ኃይሎች ተጠልፎ ተለቀቀ፤›› የሚል ዜና ቢሰሙ፣ የመጠለፉን ምክንያት ለማወቅ አይጓጉም? የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ በአንድ አነስተኛ የውይይት መድረክ ስለጨረታ ጉዳይ ስንወያይ የሰማነው ታሪክ ነበር፡፡ አንድ ደረጃ አራት የነበረ ጠንካራ ኮንትራክተር በልፋቱ ደረጃ አንድ ኮንትራክተር ለመሆን ይበቃል፡፡ ይኼም ኮንትራክተር ለሦስት ኮንትራክተሮች ተከፋፍሎ የሚሰጥ (Lot1,Lot 2,Lot 3) ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ሰነድ ይገዛል፡፡ ይኼንንም ሁኔታ በመመሳጠር ሦስቱን ሎቶች ለመከፋፈል አሰፍስፈው የነበሩ ኮንትራክተሮችን ያስደነግጣል፡፡ እነዚህ ኮንትራክተሮች ይኼንን ሁኔታ በአግባቡ ክትትል ለማድረግ ያስችላቸው ዘንድ መረጃ አቀባይ የሆነ ባለሙያ ከድርጅቱ ውስጥ ይገዛሉ፡፡ የሚደርሳቸው መረጃ ግን አስፈሪ ነበር፡፡ ድርጅቱ የጨረታ ሰነዱ (Tor) የሚጠይቀውን መሥፈርት ከበቂ በላይ ማሟላቱን፣ ቴክኒካል ዕቅዱም (Technical Proposal) ምርጥ የተባለ እንደሆነና ሊያስገባ ያሰበውም ዋጋ እነሱ ያለመዱትና ያነሰ ዋጋ እንደሆነ ይነገራቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሆነ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ይወስናሉ፡፡ በነገራችን ላይ ኮንትራክተሮች የጨረታ ሰነዶቻቸውን ባለመተማመን ምክንያት ሰነዱ ሲከፈት በዚያው ለመገኘት በማሰብ፣ የጨረታ ማስገቢያ ሰዓት ማብቂያው አሥርና አሥራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ያስገባሉ፡፡ ያላሰቡት ባለጋራ የሆነባቸው ኮንትራክተርም በእዚሁ ቀመር መሠረት ባለቀ ሰዓት በሞተረኛ ተላላኪ የጨረታ ሰነዱን ይልካል፡፡ ይኼም ጉዳይ ቀድሞ የተነገራቸው አካላት ሞተረኛውን መከታተል ይጀምራሉ፡፡ የትራፊክ መጨናነቅና ብዙ እንቅስቃሴ ያልበዛበት ቦታ ላይም አንድ ፒክአፕ መኪና ሞተረኛውን ዳር ይዞ እንዲቆም ያስገድደዋል፡፡ የፖሊስ ደንብ የለበሱ ሰዎች ወርደውም ሞተሩ ሕገወጥ እንደሆነና እንደሚፈለግ ይነግሩታል፡፡ ሞተረኛውንም የሚያዳምጠው ይጠፋል፡፡ ‹‹ብትቸኩልም ከሕግ የሚበልጥ ጉዳይ የለም፤›› ይባላል፡፡ ሞተሩም ፒክአፕ መኪናው ላይ ይጫንና ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ጉዞውም ግን ማለቂያ አልነበረውም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ግን ልቀቁት የሚል መልዕክት ደርሶናል የሚል ምክንያት በመስጠት አውላላ ሜዳ ላይ ይለቁታል፡፡ ሞተረኛው የፈለገ ቢሮጥም የጨረታ ሰዓቱ አልፎበት ነበር፡፡ የኮንስትራክሽን ጨረታዎች የጦርነት ትኩሳትን በዚህ ምሳሌ ብቻ የምንለካው አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ ኮንስትራክሽን ሴክተር ትራንስፓረንሲ ኢንቬቲቭ ኢትዮጵያ (Construction Sector Transparency Initiative Ethiopia) ያዘጋጀው የጋዜጠኞች ፎረም ላይ ይኼንን ታሪክ አጫውቻቸው ነበር፡፡ በሻይ ሰዓት ላይ ታሪኩ የገረመው አንድ ጋዜጠኛ ሐዋሳ የጨረታ ሰነድ ሊያስገባ የሄደ ግለሰብ ያደረበትን  ክፍል ከውጪ በመቆለፍ ሰዓቱን እንዳሳለፉበት የሚተርክና የሚያስገርም ገጠመኝ አጫውቶኛል፡፡ እናም መመሳጠር (Collusion) በኮንትራክተሮች በአሠሪው አካል፣ በኮንትራክተሩና በአማካሪ ድርጅቶች መሀል ሲልም በኮንትራክተሩና በአማካሪው መሀል ብቻም ይደረጋል፡፡

ይኼም መመሳጠር ጨረታውን በተመሳጣሪው ኮንትራክተር ቁምጣ ልክ በመስፋት፣ ቀድሞ መረጃን በመስጠት፣ የጨረታ ሰነዱ ላይ የማይገለጽና የጨረታ ኮሚቴዎች ብቻ በሚስጥር ሊያውቋቸው የሚገቡ ነጥብ መስጫ መሥፈርቶችን መስማት፣ በቡድን ጨረታ ሰነዱን በመግዛትና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመተሳሰር እጀባ በማድረግ፣ አንዱ እንዲያሸንፍ ማገዝና የመሳሰሉት ተግባራት ይፈጸማሉ፡፡ የጨረታ ሰነዱ ሲዘጋጅ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁ የሥራ ክንውኖች እንዳይገቡ በማድረግ፣ ወደ ሥራ ሲገባም መሬት ላይ የማይገኙ የሥራ ክንውኖች ሰነዱ ላይ እንዲገቡ በማድረግና ተመሳጥረው ድርጅቱ የተሻለ ዋጋ እንዲያስገባና ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ይኼም ሁኔታ በዘርፉ ላሉ ሰዎች የሚደንቅ ባይመስልም እንደ ማኅበረሰብ ግን ያላአግባብ የተወሰኑ ድርጅቶች ጡንቻቸው እንዲፈረጥም ያደረገ ስህተት ነው፡፡ ሌላው የኮንስትራክሽን ጨረታዎች ክፍተት ክልላዊነትና የባለሥልጣናት ተፅዕኖ ይመስለኛል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ጨረታዎች ሲወጡ ‹‹ያ ክልልማ የእነ እንትና ነው›› የሚልና በእውነትም ትንሹንም ትልቁንም ሥራ የተወሰኑ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ከክልሉ የተለያዩ አካላት ጋር ሲመሳጠሩ፣ እንደ ነውርና ሙስና የማይቆጠርባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በቀጥታ የፌደራልንም ሆነ የክልል ባለሥልጣናትን ጡንቻ በመመርኮዝና ጥቅምን በመጋራት የሚሠራበት ሁኔታ እንዳለ ያለፈው ሃያ ሰባት ዓመታት ታሪካችን መሆኑን፣ የተለያዩ ጥናቶችና የፌደራል ዓቃቤ ሕግ መዝገቦችን መመርመር በቂ ይመስለኛል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱ ችግሮች ባሻገር እንደ አቅሜ በጨረታ ዙሪያ ሳላነሳ የማላልፈው የቀጥታ ግዥ (Direct Award) አፈጻጸምን በተመለከተ ነው፡፡ በእርግጥም የቀጥታ ግዥ አዋጁ የሚፈቅደው አካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን  አዋጁ ላይ ይኼን ሒደት ለመፈጸም የሚያስችሉና መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይኼም ቢሆን ግን በአስቸኳይ ፕሮጀክቱን ለመፈጸም በደኅንነት ችግር፣ በፕሮጀክት ጥራትና ልምድ፣ ከዋጋም አንፃር በሚሉና በተለያዩ ምክንያቶች ይኼ ሒደት ሲፈጸም እናስታውሳለን፡፡ ቢሆንም ግን ፕሮጀክቶች በተባለላቸው ጊዜ ማለቅ ሳይችሉ፣ የሥራ ጥራትም ቢሆን ሳይጠበቅ፣ ዋጋም ቢሆን ከገቡበት ውጪ በዋጋ ማስተካከያ፣ በተጨማሪ ሥራ ሰበብና በመሳሰሉት ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍሉ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ ይኼም ሒደት አወዳዳሪና አሳታፊ ሳይሆን፣ አገሪቱም በተሻለ ዋጋ የተሻለ ጥራት ያላቸውን ፕሮጀክቶች ሳታገኝና ሳታረጋግጥ ከፍተኛ አዙሪት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ በዚህ ሒደት በተለይም የውኃና የመንገድ ግንባታዎች ሲወድቁ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይም በኮንስትራክሽን ላይ የሚሠሩ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችና የተመረጡ ኮንትራክተሮች ተጠቃሚ መሆናቸው ብዙ ጊዜ ሲወራ ይደመጣል፡፡

የኮንትራክተሮቻችንና የአማካሪ ድርጅቶቻችን አቅምና ነባራዊ ሁኔታዎች

በእርግጥም በአገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ዘርፉ ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ የገንዘብ አቅም እስካለው ድረስ የሚገባበት ነው፡፡ ባደጉት አገሮችም ቢሆን ባለሀብቶች የሚያስፈልጉትን ብቁ ባለሙያ፣ ቴክኖሎጂና ማሽነሪዎች በማሟላት ጠንካራና ግዙፍ ድርጅቶች ይመሠርታሉ፡፡ የእኛን የሚለየው ግን በዕውቀት፣ በገንዘብና በመሣሪያ ሳይደረጁ በቀላሉ ዘው ብለው የሚገቡበት ዘርፍ መሆኑ ነው፡፡ ሥራዎችን እየሠሩ ወደ ላይ እያደጉ በሄዱ ቁጥር ፕሮጀክቶችን ከማሳደድ ውጪ ራስን የማዘመን፣ ሥራዎችን የመመጠንና ትልቅ ዕራይን ለማሳካት የሚደረገው ሩጫም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ኮንትራክተሮቻችን ከዚህም ባለፈ ለሥራቸው ድጋፍ የሚሰጧቸውን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከመንደፍ ይልቅ፣ የተለየ ኢንቨስትመንት ውስጥ ሲዘፈቁ ይታያሉ፡፡ ወደ ውጭ አገር ሀብትን በማሸሽ ላይም ሲታሙ ይሰማል፡፡ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶችን ደጋግመው ማግኘት ችግር ቢሆንባቸው፣ በእጃችሁ ላይ ያሏችሁን ሥራዎች ሳታጠናቅቁ ሌላ ሥራ መቀበል አትችሉም ቢባሉ ድርጅታቸውን ከመፍረስ አደጋ ሊታደጉት አይችሉም፡፡

ብዙ ትልልቅ ኮንትራክተሮች ዋና መሥሪያ ቤታቸውን የራሳቸው በሆነ ዘመናዊ ሕንፃ ውስጥ ማድረጋቸውን እየተመለከትን ነው፡፡ ነገር ግን የሚያምረው ሕንፃቸው ውስጥ ብትገቡ የፕሮጀክት አስተዳደራቸው፣ የገንዘብ አስተዳደራቸው፣ ዶክመንቴሽንና የመሳሰሉትን ለመፈተሽ የሚቻልበት ዕድል ቢገኝ አብዛኞቹ ፈተናውን ወዳቂ ናቸው፡፡ በእርግጥም ለአንድ ጥናት የፕሮጀክቶቻቸውን መረጃ ፈልገን የሄድንባቸው መሪ ኮንትራክተሮች፣ በሚያሳዝን ሁኔታ የሁለትና የሦስት ዓመታት ወደ ኋላ ሄደን ያሉ መረጃዎችን ለማግኘት ያልቻልንበትና የተገረምንበት ሁኔታ ገጥሞናል፡፡ በነገራችን ላይ በዘርፉ ውስጥ መረጃን በአግባቡ ለረጅም ጊዜ ማስቀመጥ ያለመቻል ትልቅ ክፍተት መሆኑን በተለያየ አጋጣሚ ለመመልከት ችያለሁ፡፡

ለማንኛውም አብዛኞቹ ኮንትራክተሮቻችን ከውጭ እንደምንመለከታቸው ሳይሆን፣ በብዙ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች በሚያገኟቸው የባንክ ብድርም ሆነ የአራጣ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው፡፡ ማረጋገጫ ባይኖረኝም በቅርቡ ከአንድ ወዳጄ እንደሰማሁት፣ የማንጠብቀው ኮንትራክተር በቢሊዮን የሚቆጠር የባንክ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ወጣም ወረደም ግን ብዙ ሥራዎች ተሸክመው የነበሩ ትልልቅ ኮንትራክተሮች ዓይተን ሳንጠግባቸው መክሰማቸውን እያየን ከርመናል፡፡ አማካሪ ድርጅቶችን በተመለከተም ከዲዛይን ሥራ ጀምሮ እስከ ፕሮጀክት ክትትል ድረስ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ቢሆንም፣ በአደረጃጀትም ሆነ በገንዘብ አቅም አብዛኞቹ ትንንሽ የሚባሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ለዲዛይን ዝግጅትም ሆነ ለፕሮጀክት ክትትል የሚከፈላቸው ክፍያ ዝቅተኛ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በድርጅታቸው ውስጥ ለማቆየት የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ይነገራል፡፡ ለዲዛይን ዝግጅትም ሆነ ለሌሎች ተግባራቶቻቸው ያላቸው አቅም በጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሆነበትም ምክንያት ተፈጥሯል፡፡

ለፕሮጀክቶች የሚልኳቸው ተቆጣጣሪ መሐንዲሶች በኮንትራክተሩ አቅም በመረታት ከሁለት ኪስ ደመወዝ እንደሚበሉና እንደሚመሳጠሩ የጠራራ ፀሐይ ሀቅ ነው፡፡ በተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ አማካሪ ድርጅቶች ኮንትራክተሮችም ‹‹ጉልበተኞች ናቸው›› የሚል ተቃውሞ አዘል ነቀፌታ ቢያቀርቡም፣ ኮንትራክተሮቹም ቢሆኑ ‹‹ንጉሦቻችን እነሱ ናቸው፣ ካለ እጅ መንሻ ለጥያቄዎቻችን መልስ አይሰጡንም›› የሚል ወቀሳ ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ግን ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት ተመሳጥረው ያልተገባ ጥቅምን ማካበትም በአማካሪ ድርጅቶች ላይ ጎልቶ የሚታይ ባህሪ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ግን እንደ ኮንትራክተሮቹ ሁሉ የተወሰኑ አማካሪ ድርጅቶች ብቻቸውን ተደራራቢ ሥራዎች በተለያየ መንገድ የሚያገኙበት እውነታ አለ፡፡ ይኼም ብዙ አማካሪ ድርጅቶች እንዲቀጭጩ፣ ሠራተኛ እንዲቀንሱና የአንድ ሰው ድርጅት ወደ መሆን እንዲሻገሩ ሲልም እንዲጠፉ እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡ ይኼንንም በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ አማካሪ ድርጅቶችን ቢሮዎች ለመርገጥና ከባለቤቶች ጋር ለመወያየት ዕድል በማግኘቴ፣ በቢሮዎቹ ውስጥ ባስተዋልኩት ሁኔታ ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡

በአጠቃላይ ግን ዘርፉ በእኔ አቅምና ግምገማ ተገምግሞ የሚያልቅ ባይሆንም፣ ከላይ ከጠቀስኳቸው ችግሮች ባሻገር የፕሮጀክቶች ከዕቅዳቸው ውጪ ከፍተኛ ጊዜያትን መውሰድ፣ ከመንግሥት ዕቅድ በላይ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መጨረስ፣ ከፍተኛ የሆነ ከውጭ የሚገቡ ቁሶችን የሚጠይቅ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ብክነት፣ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ሙስና የተንሰራፋበት በመሆኑ በፖለቲካ፣ በዘርና በመሳሰሉት ሰንሰለቶች በመጠቀም ሁሉን አሳታፊ ያልሆነና ግልጽነት ያልሰፈነበት፣ የተወሰኑ ቡድኖች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት የሚያካብቱበት ከፍተኛ አቅም ያለው ዘርፍ በመሆኑ፣ ሌሎች ባለሙያዎች የበለጠ ቢሄዱበት እመክራለሁ፡፡ በዘርፉ ላይ የሚያተኩሩ ዓውደ ጥናቶችና የውይይት መድረኮች በብዛት የሚካሄዱ ቢሆንም፣ ታች ወርዶ ሲሠራበት አይታይም፡፡ የሚመለከታቸው አካላት ማለትም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፣ በቅርቡ ለብቻው ተገንጥሎ ጐጆ የወጣው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ መመሥረቱ ከተሰማ በኋላ ድምፁን ያላሰማው የኮንስትራክሽን ምክር ቤትና የመሳሰሉት አካላት ዘርፉን የማስተካከል ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡

 በዘርፉ ውስጥ ምንም ጥሩ ነገር የለም፣ ባለድርሻ አካላት ምንም እየሠሩ አይደለም የሚሉና ከላይ የጠቀስኳቸውን ህፀፆች ስትመለከቱ እንደ ጨለምተኛ እንዳትቆጥሩኝም ሠጋሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቴ ግን ዘርፉ በጣም ሰፊ፣ ከፍተኛ በጀት የሚበላ፣ ለሙስና በእጅጉ የተመቻቹ ክፍተቶች ስላሉትና በአገራችን ይኼንን ዘርፍ በአግባቡና ግልጽነት በሠፈነበት፣ ወጪ ቆጣቢ በሆነና በጥራት ማከናወን ካልቻልን ያሰብናቸውን ግቦች መምታታችን ጥያቄ ውስጥ መግባቱ የግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አሁን በተከሰተው አዲስ መንገድ በአግባቡ ሊፈተሹ ከሚገባቸው ዘርፎች፣ አንደኛውና ሁነኛው ዘርፍ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እስቲ ዘርፉ ይመለከተኛል የምትሉ ባለሙያዎች ሌሎችንም ሐሳቦች አክሉበት፡፡ ግልጽነት የሠፈነበት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለመፍጠር በጋራ እንታገል!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...