Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየትግራይ ሕዝብ ሚና በለውጡ

የትግራይ ሕዝብ ሚና በለውጡ

ቀን:

በበረራ ቢያ

ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የትግራይ ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት በሰሜን ኢትዮጵያ ወራሪ ኃይሎችን ሲከላከል የቆየ፣ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር የኢጣሊያንን የዓደዋ ጦርነትንና ሌሎችንም የተጋፈጠ አገር ወዳድና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ብዥታ የሌለው ሕዝብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ በአገራችን እየተካሄደ ባለው ለውጥ ይበልጡኑ ከሕወሓት ነባር የተወሰኑ አመራሮች ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ውዥንብር ውስጥ የመግባት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በለውጡ በግንባር ቀደምትነት ሊጫወት የሚገባውን ያህል ሚና እየተጫወተ አይደለም የሚሉ ትችቶች ይደመጣሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ቀጥሎ በሚቀርቡት ሐሳቦች የሚንፀባረቁ አሁን በአገራችን ለተጀመረው ለውጥ ስንቅ የሆኑ መሠረታዊ ሥራዎች፣ ከትግራይ ሕዝብ በወጣው ሕወሓት ግንባር ቀደምት አመራር ሚና በነበረው የገዢ ፓርቲ በሆነው ኢሕአዴግ ተከናውነዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ከዚህ ቀደሙ የአገራችን ፖለቲካ በኢሕአዴግ የተመራው የፖለቲካ ሥርዓት በማርጀቱና ለውጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በሕዝብ ግፊት ለውጥ ሊመጣ ችሏል፡፡

የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) ትግል የኦሮሞን ሕዝብ ድጋፍ በማግኘቱና ተጠናክሮ በመቀጠሉ፣ በኦሕዴድ የአመራር ለውጥ ማስከተሉም ዕውን ነው፡፡ ይህ ለውጥ እነ ክቡር አቶ ለማ መገርሳን ወደ ኦሕዴድ ሊቀመንበርነት በማምጣቱ ለለማ ቡድን (ቲም ለማ) መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም ቡድን ከተለመደው የኢሕአዴግ አሠራር ወጣ በማለት የሕዝቡ ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ሕዝብ በመውረዱ በኦሮሞ ሕዝብ ተቀባይነት እያገኘ ሄዷል፡፡ ይህ በኦሕዴድ ሲራመድ የነበረው አቋም ከሕወሓት አካሄድ ጋር ባለመጣጣሙ፣ የትግራይን ሕዝብ ለማጥቃት እንደሚደረግ ትግል በወቅቱ ተወስዶ ነበር፡፡ በየካቲት ወር ለሥራ ጉዳይ መቀሌ ነበርኩና ከአንዳንድ በምሁራን ደረጃ ከሚገኙ ሰዎች ጭምር ጋር ስንነጋገር የሚሰማው ስሜት፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ለሚካሄደው እንቅስቃሴና በተለይም በእነ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ላይ የነበረው ዕይታ በጥላቻና በሥጋት ላይ የተመሠረተ እንደ ነበር ነው፡፡ ይህ እንዲሆን በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚሠራጩ መረጃዎች እንደነበሩ ነው መረዳት የቻልኩት፡፡

በኦሮሚያ ውስጥ በሚኖሩ የትግርኛ ተናጋሪዎች ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ነበር፡፡ በዚያ ኅብረተሰብ ውስጥ የነበረው ስሜት እውነታው ግን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግርኛ ተናጋሪ ሰዎች በኦሮሚያ ውስጥ በሰላም እየሠሩ ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው፣ ግን በኦሮሚያ ክልል ከሚኖሩት የሶማሌ ክልል ኅብረተሰብ ጋርም በሰላም ሲኖሩ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ አመፅና ተቃውሞ እየተነሳ አንዳንድ ግለሰቦች ከፈጠሩዋቸው በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ክስተቶች በስተቀር፣ የሁሉም ክልል ተወላጆች በኦሮሚያ ውስጥ በሰላም ኖረዋል፡፡ አሁንም እየኖሩ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው የኦሮሞ ሕዝብ በጣም አስተዋይና ታጋሽ፣ የሌሎችን ክልሎች ሕዝቦች አቅፎ በሰላም መኖር የሚችል ትልቅ ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሕዝብም ሆነ ከዚሁ ሕዝብ የወጣው የኦሕዴድ አመራር ለትግራይ ሕዝብ ሥጋት የሚሆንበት ሁኔታ በፍጹም አይታይም፡፡

የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ የክልሉ አመራር ጥያቄ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የመልካም አስተዳደርና የመሳሰሉት  የዴሞክራሲ መብት ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ መብቶች ሕወሓት ጉልህ ሚና በነበረው በኢሕአዴግ አመራር በኢትዮጵያ ያልተከበሩና የተጣሱ መሆኑን በማመን፣ ኢሕአዴግም ሆነ ሕወሓት ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ለመታደስም ብዙ ጥረቶችን ለማድረግ ተሞክሮ የተደረገውም ተሃድሶ ሕዝቡን ባለማርካቱ፣ የሁሉም ክልል ሕዝቦች ማለት ይቻላል የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቀጥሎ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዴሞክራሲ ሥርዓት መሻሻል ይረዳል በሚል በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መገደዳቸው የችግሩን ግዝፈት ያሳያል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ግን፣ በአገሪቱ አንዣቦ የነበረው ሥጋትና የፖለቲካ ቀውስ በሕዝባዊ አመፅ ተገፎ ማለት ይቻላል የሰላም አየር በመንፈሱ፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ከከፍተኛ ሥጋት ታድጓል፡፡ ምንም እንኳ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ጊዜያዊ ሰው ሠራሽ ችግሮችና የሚያሳስብ የፀጥታ መታወክ ቢኖርም መፍትሔ እየተገኘ ነው፡፡ ይኼንን ለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብዛኛው በውጭ ከሚኖሩ በተቃውሞ በተሠለፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጭምር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትና ድጋፍ አግኝቶ ሕዝቡ እፎይ ማለቱ የሚታይ ነው፡፡

ክቡር አቶ ለማና ዶ/ር ዓብይ ከሌሎች ቡድናቸው ጋር ወደ ሥልጣን ያመጣቸውም የሕዝብ በተለይም የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ የለውጥ ፈላጊነት ትግል ውጤት ነው፡፡ እነርሱም ለዚህ ውጤት የሠሩትን የሕዝቡን ፍላጎት በተለይ የወጣቱን ጥያቄዎች ግፊቶችን ተከትለው መጓዛቸውና የሕዝቡን ጥያቄ በብልኃት በመምራታቸው ነው ሰላማዊ ሽግግሩ እንዲካሄድ የተደረገው፡፡ በፅሞና መታየት ያለበት ትግሉ ሰላማዊ እንዲሆን ወደ የኢሕአዴግ የጠረጴዛ ክርክር በመውሰድ አሥራ ሰባትና በተጨማሪ ዘጠኝ ቀናት በመውሰድ ያለ ምንም ደም መፋሰስ ለውጡ እንዲካሄድ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ ማድረጋቸውም ነው፡፡ ኢሕአዴግም እንደ ድርጅት ይኼንን ሐሳባቸውን ተቀብሎ ውሳኔ ላይ በመድረሱ ሊመሠገን ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን የሕዝብ መሪ ሆኖ ተወዳጅነትን ማትረፍ መቻል ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በእነዚህ መሪዎቻችን ለአገራችን የዚህ ዓይነት ሁኔታ በመፈጠሩ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው፡፡ ለውጡን የበለጠ ከግብ ለማድረስም የኦሮሞን ሕዝብ ከአማራው ሕዝብ ጋር ለማቀራረብ ለተደረገው ሥራ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያዊነት ላይ የነበረው የላላ አቋም ተጠናክሮ የአገር አንድነትን ለማጠናከር የተራመዱት አቋሞች ሁሉ በተለይ በሁለቱ የአገሪቱ ሕዝቦች ትልቅ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡

ይህ በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ቀንድና ለመላው አፍሪካ ብሎም ለዓለም ጠቀሜታ ያላቸው ዕድሎች ያስገኛል፡፡ ለዚህም ነው ኤርትራውያን እናቶች ዶ/ር ዓብይን ‹‹ነብይ›› ያሉት፡፡ የጎረቤት አገሮች የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ የኬንያና፣ የደቡብ ሱዳን ዜጎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥና ዶ/ር ዓብይ የሚያራምዱዋቸውን ለየት ያሉ ሐሳቦች በአገሮቻቸው ጭምር በጎ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብለው በተስፋ፣ በጉጉትና በስስት እየጠበቁ መሆናቸው ከዓለም አቀፍ የተለያዩ ምንጮች ሳይቀር እየተደመጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ታሪክ እንደ አሁኑ መሪ በተማሩ ዜጎች (ልሒቃን)፣ በወጣቶች፣ በተቃዋሚዎች ወይም በተፎካካሪዎች የተወደደና ተቀባይነት ያተረፈ መሪ አልተገኘም፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች እኚህ ሰው ኢትዮጵያን ለማዳን ከእግዜር የተላከ መልዓክ ናቸው እስከ ማለት የደረሱት፡፡ አሁን የደረስንበት ሁኔታ አገሪቷን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስድ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ለአገራችን አንድነት፣ ሰላምና ብልፅግና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ፣ በዕድሉ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ይህ ዕድል ከማናችንም ሊያመልጥ አይገባም፡፡ አጠቃላይ ሁኔታው ይኼንን ከመሰለ በኢሕአዴግ ውስጥ ለውጡን ያልተቀበሉ ወይም የሚጠራጠሩ ጥቂት ኃይሎች አሉ ለሚባለው ለምን ኖሩ ማለት አይቻልም፡፡ በለውጥ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች መኖራቸው የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሕዝቡን ፍላጐት በማክበር ልዩነቶች ጠበው ወደ ተመሳሳይ አቋም መምጣትና የሥልጣን ሽግግሩን የተሟላ አድርጎ ወደ ልማት በፍጥነት በመግባት፣ የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ደረጃ በደረጃ መመለስ የመጀመር አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

በለውጡ የትግራይ ሕዝብ ተጎጂ ይሆናል?

በሕወሓት የተመራው የትግራይ ሕዝብ ትግል የደርግን ሥርዓት በማስወገድና ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ፣ በተለይ ቁሳዊ ከፍተኛ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ረድቷል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍም በትምህርትም ሆነ በጤና ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በተለይ በትምህርቱ በጥራት ላይ ያለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ብዙ ሰው የመማር ዕድል በማግኘቱ ለውጥ ፈላጊና ጠያቂ የኅብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በሁለተኛነት እስካሁን ኢሕአዴግ ሲያከናውናቸው የነበሩትን ተግባራት ለመማርም ዕድል ሰጥቷል፡፡ እንቅስቃሴዎቹ ባይካሄዱ ማለት ባይሠሩ ስህተቶች አይፈጠሩም፡፡ ከተፈጠሩት ስህተቶችም መማር አይቻልም፡፡ ስለዚህ የተሠሩት ሥራዎችና ያጋጠሙት ችግሮች ለአሁኑ በመማርያነት አገልግለዋል፡፡ በሦስተኛነት ለውጡን የመሩት የለማ ቡድን የሚባሉት እንደ ክቡር አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ዓብይ አህመድ የኢሕአዴግ ውጤቶች ናቸው፡፡ በኢሕአዴግ በተፈጠሩላቸው ዕድሎች ነው ተኮትኩተው ያደጉትና የሥራ ልምድ ገብይተው ለዚህ ኃላፊነት የደረሱት፡፡ ስለሆነም እነዚህን ኃይሎች ኢሕአዴግ በማፍራቱ ሊኮራበትና ሊረካበት ይገባል፡፡ ሕወሓት ደግሞ የኢሕአዴግ አደራጅና ምሰሶ ስለነበር ትግሉን ከዚህ ደረጃ በማድረሱ የበለጠ ሊኮራበትና ሊደሰትበት ይገባው ነበር፡፡

በአራተኛነት የሥልጣን ሽግግር በሌሎች አገሮች ብዙ ደም አፍሶና ጉዳት አድርሶ ሲሆን፣ በአገራችን በዚህ ዓይነት ሽግግር ሰላማዊ በሆነ መንገድ መካሄዱና  ለኢሕአዴግም ሆነ ለቀደመው ለውጥ ግንባር ቀደም ሚና ለነበረው የትግራይ ሕዝብ ትልቅ ኩራትና ድል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ከ60 ሺሕ በላይ ልጆቹን ለዚህ መስዋዕት አደረገ የሚባለው የትግራይ ሕዝብ፣ መስዋዕትነቱ ይህችን አገር ወደ ተሻለ ሁኔታ ሽግግር ያስኬደ በመሆኑ ሊደሰትና ሊረካ ይገባዋል እንጂ ሊቆጭና ሊሠጋ ፈጽሞ አይገባውም፡፡ በዚህ ረገድ የአመለካከት ማስተካከያ ያሻል፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተደጋጋሚ ስለይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር የሚያወሱት፡፡ ባለፈው በመቀሌ ባደረጉት ጉብኝታቸው የትግራይ ሕዝብንም ሲያሞካሹና ሲያወድሱ የነበረው፡፡ በአገራችን በተፈጠረው በፍትሕ መጓደል፣ በሰብዓዊ መብት መጣስ፣ በእኩልነት አለመኖር፣ ፍትሐዊ ባልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ በሙስናና በአጠቃላይ በደረሰው የመልካም አስተዳደር ችግር ለውጥ ማስፈለጉ ግዴታ ነበር፡፡ የዛሬ አራት ወር አካባቢ በአንድ ግብዣ ላይ ያገኘሁት የቻይና ዲፕሎማት በወቅቱ የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የነበረበት ጊዜ ነበርና ስለአገራችን ሁኔታ ስንነጋገር፣ የዚህ ዓይነት ሁኔታ በዕድገት ሒደት ውስጥ የሚያጋጥም ነው ብሎኝ ነበር፡፡ ‹በእኛም ማለት በቻይናም ይኼንን ሒደት አልፈን ነው አሁን የምንገኝበት ደረጃ ላይ የደረስነው፡፡ ይህ የሚጠበቅና መሆን የሚችል በመሆኑ የኢሕአዴግ ስብሰባም ለውጥን በመቀበል በሰላም እንደሚጠናቀቅ እምነት አለኝ› በማለት መልካም ምኞቱን ገለጸልኝ፡፡

ደቡብ ኮሪያን ከድህነት በማውጣት ወደ ከፍተኛ የብልፅግና ጎራ ያስገቡት ጄነራል ፓርክ አገዛዝ ላይ የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ መጀመርያ ለበለጠ ዴሞክራሲ መብቶች ያደረገው ትግል፣ ብዙ መስዋዕትነትን አስከፍሎ ነው አገሪቱ አሁን ላለችበት የብልፅግናና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበቃችው፡፡ እንዲህ ዓይነት የሽግግር ትግሎች በቅርቡ በታይላንድ፣ በብራዚልና በደቡብ አፍሪካም ተካሂደዋል፡፡ የቀድሞዎቹን መሪዎች ያስለወጠ በመሆኑና ይህ በኢትዮጵያም መካሄዱ ዕድገቱ ያመጣውና መምጣት የሚኖርበት ለውጥ ነው፡፡ ስለሆነም ለውጡን ሁሉም በበጎ ጎኑ ሊያየውና ከጎኑ በመቆም የራሱን ድርሻ ሊጫወት ይገባል፡፡ እውነታው ይኼን ከመሰለ በቅርቡ ይኼንን የመንግሥታችንን ለውጥ በሚመለከት የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ውስጥ ቅሬታ መፈጠሩን፣ ሕገ መንግሥቱ አልተከበረም፣ የኢሕአዴግ መርሕ ተጥሷል፣ በሌሎች ክልሎች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ደርሷል ወይም ይደርሳል የሚሉ መረጃዎች ይሰራጫሉ፣ ወይም ይደመጣሉ፡፡ ለዚህ መረጃ ምንም እንኳ ዝርዝሩ ባይኖረኝም ጠቅለል ባለ ሁኔታ ሲታይ፣ የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ጥርጣሬና ሥጋት የሚፈጥር ነው፡፡ በእውነት ይህ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድጋፍ ያገኘ ለውጥ የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሊጎዳ አይችልም፡፡ በኢሕአዴግ ሃያ ሰባት ዓመታት የትግራይ ሕዝብ የተለየ የተጠቀመው ነገር የለም፡፡ በዚህ ለውጥ የሚቀርበትና የሚያደርስበትስ ጉዳት ምንድነው? የትግራይ ሕዝብ የለውጡ ተፃራሪ ሊሆንስ ይችላል? እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሴ በፊት ወደ ኋላ መለስ በማለት ለተፈጠሩት ሁኔታዎች የዳረጉትን ክስተቶችን ማየቱ ጠቀሜታ አለው፡፡

ሕወሓት የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና በነበረው በኢሕአዴግ ብዙ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሥራዎች የተሠሩትን ያህል፣ በዚያው መጠን የተፈጸሙ ስህተቶች በርካታዎች እንደ ነበሩ የታወቀ ነው፡፡ ታሪክ ለመማርያነት ለመጠቀም ማለት ወደፊትም ተመሳሳይ ስህተቶችን ላለመፈጸም ስለሚረዳ፣ የስህተቶቹን ምንጮች የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በተረዳው መሠረት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡ የችግሮቹ መንስዔዎች ከመጀመርያው ጀምሮ ተያያዥነት ያላቸውና እየተደማመሩ የመጡ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመመሥረት በነፃ አውጭነት በጦርነት የሚመጡትን ሁሉ ፈታኝ ያደረጉ ጉዳዮች ናቸው ኢሕአዴግንም ያጋጠሙት ማለት ይቻላል፡፡ በጦርነት የሚመጣ ኃይል ነባሩን ኃይል አሸንፎ የሚመጣ እንደ መሆኑና ሰጥቶ የመቀበል ዕድል ስለሌለው፣ ተሸናፊውን የሚያገልና የሚጨቁን ስለሚሆን የሚመጣው መንግሥት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ይቸገራል፡፡ እንዲያውም ከሌሎች የጎረቤት ተመሳሳይ ነፃ አውጭ መንግሥታት ጋር ሲመዘን፣ ዴሞክራሲያዊ ሒደቱን በማስኬድ በኩል ኢሕአዴግ የተሻለ ተጉዟል ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ መሠረተ ሐሳብ ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን ገርስሶ ሥልጣን ሲይዝ፣ በደርግ ሥርዓቱ ብቸኛ ገዢ ፓርቲ የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) አባላትና በቀድሞ መንግሥት የኢትዮጵያ የጦር ኃይል አባላትን በጦርነት ካሸነፈ በኋላ፣ እነዚህን ኃይሎች ከመንግሥታዊ ሥልጣን ማግለሉ ይታወሳል፡፡ በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ውስጥም ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸው አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ እንደ ኢሕአፓና መኢሶን የመሳሰሉት አልተሳተፉም ነበር፡፡ ሌሎችም በርካታ በተለይ የአማርኛ ተናጋሪ ልሂቃን ኢሕአዴግ የተከተለውን በብሔርና ብሔረሰብ ላይ የተመሠረተውን የፌዴራል ሥርዓት ሲቃወሙ ስለነበር፣  እንዲሁም በመጀመርያ የኦሮሞ ልሂቃን ቢሆኑ በኦነግና በሌሎች አራት ድርጅቶች የተሳተፉት፣ ኢሕአዴግን በጥርጣሬ የሚከታተሉና የሚገዳደሩ ነበሩ፡፡ በጦርነት ጭምር የተደገፈ ፍትጊያ ስለነበር ኢሕአዴግ ከተለያዩ ኃይሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ነበር የገጠመው፡፡ የተማረውን የሰው ኃይል በሚፈለገው መጠን አሳምኖ ለአገር ግንባታ ወይም ለልማት በመጠቀሙ በኩል ኢሕአዴግ ከመጀመርያው ጊዜ ጀምሮ ክፍተት ነበረበት፡፡

እንደሚመስለኝ የዚህ ምክንያት ከመነሻው የኢሠፓ አባላትንና የተበተነውን የጦር ኃይል በሙሉ ከፖለቲካው ማግለሉ፣ ከፖለቲካው የተገለሉት እነዚህ ኃይሎች በአንፃራዊነት ከኅብረተሰቡ የነቁና ከግል ጋዜጦች አዘጋጅነት ጀምሮ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ ያደጉ ነበር፡፡ በኅብረተሰቡም ውስጥ ፀረ ኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳን በማሠራጨት የተገለሉትን ያህል ኢሕአዴግም እንዲገለል አድርገዋል፡፡ በአብዛኛው በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተማረውን የሰው ኃይል ተቃዋሚ እንዲሆን መደረጉ፣ ኢሕአዴግን ከተማሩት አብዛኞቹ የሕዝብ ኃይሎችና ከሌላው ኅብረተሰብ ያቃቃረ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ምክንያት በአብዛኛው በትምህርታቸው ያልገፉና ከኢሕአዴግ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት የፈለጉ ዜጎች ነበሩ ወደ ኢሕአዴግ የተጠጉት፡፡ ይህ ሁኔታ ለአሁኑ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ጉድለትም የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል የሚል ግምት አለ፡፡ በሌላ በኩል የኦነግ ከሽግግሩ መንግሥት መውጣትና ሌሎችም የሽግግሩን መንግሥት መልቀቅ ተጨማሪ ጫና በፖለቲካ ሥርዓቱ በመፍጠር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መቀጨጭና ለሰብዓዊ መብት አጠባበቅ መዛነፍ፣ ብሎም ለመልካም አስተዳደር ጉድለቶችና ውስብስብ ጉዳዮች አገሪቷን ዳርጓል፡፡

ይህ ሁኔታ የዴሞክራሲው መገለጫ በሆነው የነፃ ምርጫ መብት በሕገ መንግሥቱ የሰፈረውን ተግባራዊ ለማድረግ አላስቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት የግልጽነትንና የሐሳብ ነፃነትን በመገደብ፣ የሚቀርቡ ሐሳቦችንና ጥያቄዎችን በሐሳብ ትግል ለማሸነፍ አቅም በማጠሩ ለአሉባልታዎች መስፋፋት ዕድል ሰጠ፡፡ ይህም ለነውጠኛ አመለካከት መስፋፋት በር ከፈተ፡፡ ሥልጣን በገዢው ፓርቲ በሚመራው መንግሥት እጅ ተከማቸ፡፡ የቁጥጥር ሥርዓት ጠፋ፡፡ ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ እንደሚሉት ሕግ አውጪው በሕግ አስፈጻሚው ቁጥጥር ሥር ገባ፡፡ ሕግ ተርጓሚውም በማናለብኝነት ፍትሕን አዛባ፣ ሕዝቡን የፍትሕ እኩልነትንም ነፈገ፡፡ የእኩል ተጠቃሚነት መብቶች ተጣሱ፡፡ ውጤቱ ማኅበራዊ ፍትሕን ገደበ፡፡ ለሕዝብ መሠረተ ሰፊ ቅሬታና ተቃውሞ ሥርዓቱን አጋለጠ፡፡ ይህ ጉዳይ ለሕገ መንግሥቱ ወደ ተግባር መተርጎም ዋነኛው ተግዳሮት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ራሳችንን እንደ ኢሕአዴግና ገለልተኛ አገር ወዳድ ዜጋ ሆነን ስናስብ፣ ጉዳዩ የኢሕአዴግ ታጋዮችና መሪዎች ለብዙ ዓመታት የታገሉለትን ሕልም ዕውን ለማድረግ የመቸገር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓትን በታዳጊ አገሮች ለመተግበር ያለውን አስቸጋሪነት በግልጽ የሚያሳይ ፈታኝ ሁኔታ እንደሆነ ይህ ክስተት ያሳያል፡፡ ከላይ ከተገለጹት ምክንያቶች በተጨማሪ ዛሬ አገራችንም ሆነ ዓለም ያለበት ተጨባጭ ሁኔታ ከዛሬ 25 እና 27 ዓመት የተለየ የሚያደርጋቸው በርካታ ተለዋዋጭ ዕድገቶችና ሒደቶች በመኖራቸው፣ በጊዜ መለያየት የሚፈጠሩ ክስተቶች ይኖራሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ሊታሰቡ የማይችሉ በዛሬው ዕይታ ግን መሆን ነበረባቸው የሚባሉ ጉዳዮች በርካታዎች ናቸው፡፡ በወቅቱ የነበረው የሕወሓት አመራር ልምድም ከትኩረት ውስጥ ሊገባ የሚገባ ነው፡፡ ወጣት ታጋዮች ከትምህርት ቤት ወደ ጫካ በመግባት ለ17 ዓመታት ጫካ ቆይተው የነበረውን ሥርዓት አፍርሰው አዲስ ሥርዓት በመገንባት፣ የኢትዮጵያን የተወሳሰበ የፖለቲካ ፍላጎትን መምራት ቀላል አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል የፖለቲካ ባህሉ ከኢኮኖሚና ከማኅበራዊ ለውጦች ጋር የመለወጥ ዕድል ያለው በመሆኑ፣ ኢሕአዴግ ከጀመረበት ጊዜ ከነበረው አካሄድ አሁን የተደረሰበት ሁኔታ ተመሳሳይነት አይኖረውም፡፡ ይህን ለማብራራት ያህል በዚያን ወቅት ሥልጣን መያዝና ማስከበር የሚቻለው በኃይልና የሚያስቸግርን በማግለል እንጂ፣ አሁን እየተራመደ ያለው በፍቅር፣ በይቅር ባይነትና በመደመር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ አልነበረም፡፡ ከ1960ዎቹ የመገዳደርና የኃይል ፖለቲካ (Emotional Politics) ይህ የተቀደሰ የአሁኑ ዓይነት ሐሳብ ሊታይ የሚችልበት ዕድል የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር ዓብይና ክቡር አቶ ለማም ቀደም ብለው በዚያን ጊዜ ተወልደው ደርሰው ቢሆን፣ ይኼንን አሁን ያሰቡትንና የሚያቀነቅኑትን አዲስ አስተሳሰብ ይኖራቸዋል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ‹‹ጊዜ ሰዎችን ይፈጥራል›› ጊዜ የለማ ቡድንን (ቲም ለማን) ፈጥሯል፡፡ አሁን ጊዜው አዲስ ነው፡፡ የቀደመው አርጅቶ ለአዲስ ቦታ መልቀቅ በማርክሲስቶች ቋንቋ የዲያሌክቲክስ ሕግ ነው፡፡ ይህ በጊዜ ሒደት ከሚታዩት አገራዊ ተጨባጭ  ሁኔታዎችና ከተፈጠሩ ችግሮች አኳያ ከሕዝቡ ፍላጐት ጋር የሚራመድ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማሰላሰል የተደረሰበት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ይህ ለውጥ በጊዜ ሒደት ከታዩትና ከተፈጠሩት ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት፣ የሕዝቡን ፍላጐት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና በማሰላሰል የተደረሰበት የመፍትሔ ሐሳብ በመሆኑ በሕዝቡና ዳያስፖራን ጨምሮ በሁሉም ለማለት የሚያስደፍር ተቀባይነት ማግኘቱ በግልጽ ይታያል፡፡

ይሁን እንጂ ለውጡ ፈጣንና ይዘቱ ከተለመደው ወጣ ያለና አዲስ በመሆኑ፣ ሁሉም በተለይ ልዩነቱ ጎልቶ በሚታይ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለነበራቸው ወዲያው ለመቀበል ሊያስቸግራቸው ይችላል፡፡ ስለሆነም ጊዜ ተወስዶ ራሱን ማሳመንም ያሻል፡፡ መሠረታዊ ጭብጡ ይህ ከሆነ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ለውጥ የትግራይን ሕዝብ እንዴት ሊጎዳ ይችላል? የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ተባብሮ የትግራይን ሕዝብ ለምን ያጠቃል? የትግራይ ሕዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታታሪ፣ መከባበርን የሚያዘወትር፣ ሌብነትና ማጭበርበርን የማይወድ ሰላማዊ ሕዝብ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በእኔ አረዳድ ኑሮውን ለማሸነፍ ተግቶ የሚሠራ ሥራ ወዳድ፣ የሌሎች ክልሎች ሕዝቦች ወደ ትግራይ ክልል ሲሄዱ በማክበርና በእንግዳ ተቀባይነቱ የኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የሚባለውን በይበልጥ የሚያረጋግጥ ሕዝብ ነው፡፡ በሥራ ኑሮዋቸውን የበለጠ ለማሻሻል በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከትግራይ ሕዝብ የወጡ ዜጎች ተበትነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ምናልባት ከእነዚህ ጥቂቶች ከአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥረው በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት በመሰማራት የሌሎችን ሕዝቦችንና የአገር ጥቅም የሚጐዳ ተግባር ላይ ሊሳተፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ የትግራይ ሕዝብ እንዲህ ዓይነት ጥቂት ሰዎች በሚፈጽሙት ተግባር ዓይን ፈጽሞ መታየት የለበትም፡፡ እነዚህ ከቶውኑ የትግራይን ሕዝብ ሊወክሉ አይችሉም የሚል እምነት አለኝ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡

አሁንም ይህ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሰላምና ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በአገራችን ለሚያጋጥሙ የፖለቲካ ቀውሶች ተጠያቂው የትግራይ ሕዝብ አይደለም፡፡ በተወሰኑ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ምክንያት በተቀረው ሕዝብ ላይ ጣት መቀሰር የለበትም፡፡ ለአገሪቷ ሕዝቦች ብልፅግና፣ ሰብዓዊ መብት ጥበቃና ፍትሕ መረጋገጥ የልጆቹን ደም የገበረ ይኼ ሕዝብ በተቃራኒው የመታየት አዝማሚያ ሊሆን የማይገባው ነበር፡፡ ስለሆነም የሌሎች ክልል ሕዝቦችም ይኼንኑ ተገንዝበው፣ ለአገራችን ሰላምና  ልማት የትግራይን ሕዝብ አጋር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በትግራይ እንደ ባህል የሚታይ መሸነፍን እንደ ውርደት መውሰድ አለ፡፡ ወጣቶች ‹‹መሸነፍን አባቶቻችን አላስተማሩንም›› የሚሉት አለ፡፡ ይህ ጀግንነትን የሚገልጽ፣ በጦርነት በአገርን ከጠላት ለመከላከል ተቀባይነት ያለው እሴት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይኼንን በሐሳብ ከመሸነፍ ጋር የማያያዝ ሁኔታ የሚታይ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ በሐሳብ በመሟገት ማሸነፍ ወይም መሸነፍ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛው መለያ ነው፡፡ መሸናነፍ ሲያቅት በድምፅ ብልጫ ይወሰናል እንጂ፣ በጠመንጃ ልዩነቶችን ለመፍታት ማሰብ ጊዜ ያለፈበት ያረጀ ሥልት ነው፡፡ ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅም የተሻለ ሐሳብ ያቀረበ ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ ከሆነ ያሸንፋል፡፡ ስለሆነም አጥንቶና አመዛዝኖ የተሻለውን መምረጥ ካልተቻለ በራስም ሆነ በአገር ላይ ለውጥና ዕድገትን ማምጣት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ መረጃ በተለምዶ ከሚታወቁት መሬት፣ የሰው ኃይልና ካፒታል በተጨማሪ እንደ አገር ሀብት የሚቆጠር ነው፡፡ መረጃ ማለት በሌላ በኩል የተሻለ ሐሳብ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የተለየ ሐሳብ ከመጣ መቀበልና ስህተትን በማመን ተሳስቻለሁ ይቅርታ ማለትን እንደ ውርደት የምንወስድ ከሆነ ለዳግመኛ ስህተት መዳረግ ነው፡፡ ስህተትን ማረም የተሻለ ሐሳብን መቀበል እንደ መሸነፍ የሚታይ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ የሐሳብ መሸናነፍ ጉዳይ ብዙዎችን በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲያስቸግር የቆየ ባህሪ ስለነበር፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በሁላችንም ሊሰፍን ይገባል፡፡ ተሳስቻለሁ ይቅርታ ማለት እንደ ትሁት፣ አክባሪነትና የሠለጠነ አካሄድ ሊወሰድ ይገባል፡፡

በአገራችን እየታየ ያለው ለውጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚገነባ፣ የሕግ የበላይነት የሚያስከብር፣ ነፃነትንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የሚያስገኝ፣ ሙስናን የሚከላከል፣ በአጠቃላይ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ላይ የተመረኮዘ ከሆነ የትግራይ ሕዝብም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች ከለውጡ ተጠቃሚ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡  የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ የኢሕአዴግ አባል በሆኑት ድርጅቶቻቸው አማካይነት የሁለቱን ሕዝቦች ማቀራረብና አብሮ መሥራት፣ ኢትዮጵያ የመበታተን አደጋ ባንዣበበባትና ቀውስ ውስጥ እየገባች ባለችለበት ጊዜ ከዚህ አደጋ ለመታደግ መሥራታቸው ጥሩ መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ የትግራይም ሕዝብ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ ሊሆን አይችልም፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንዱ ሌላውን ሊያጠቃ የሚያስችል ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሕዝቦችን በእኩልነት በመከባበር የሚያኖር ሥርዓት ነው የሚፈጠረው፡፡ ይህ የማይሳካ ከሆነ ነው የበለጠ አደጋ የሚፈጠረው፡፡ በመርህና በሕጋዊነት ላይ የተመሠረተ ሁሉም የየድርሻውን ኬክ ከቆረሰ፣ የሚያሳስብ ሁኔታ ሊከሰት አይገባም፡፡ በእርግጥ ሁሉም በሕጋዊነት ማግኘት የሚገባውን ድርሻ  ብቻ ነው መውሰድ የሚኖርበት፡፡ በዚህ የጨዋታ ሕግ ስምምነት ከተፈጠረ፣ ሁሉም በሰላም በመከባበር አብሮ መኖር ይችላል፡፡ ጊዜው የእውነትና የግልጽነት  ነው፡፡

አዋጭ መፍትሔ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ የጭቆናን ሥርዓትን በማስወገድ ፍትሕ የሰፈነበት፣ ሰብዓዊ መብት የተከበረበት፣ ለሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት ሊያመጣ የሚያስችል ሥርዓት ለመገንባት የልጆቹን ደም የገበረበትን ዓላማውን ለማሳካት በሚያስችል ደረጃ ትግሉን ከግብ ማድረስ ነው፡፡ ይህ ነው ለእኩልነትና ተከባብሮ አብሮ በሰላም ለመኖርና ለጋራ ብልፅግና ዘለቄታ ዋስትና የሚሆነው፡፡ መሠረታዊው መርህ ይህ ሆኖ ሳለ ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል፣ የኢሕአዴግ መርህም ተዛንፏል፣ የትግራይ ሕዝብ ክብር ተነክቷል፣ ክብርን ከማስነካት መሞት ይሻላል፣ ወዘተ በማለት የሚደመጡ ሐሳቦች ተገቢ አይሆኑም፡፡ የሕገ መንግሥት መጣስና የኢሕአዴግ መርህ መዛነፍን በተመለከተ በቂ መረጃ ስለሌለኝ ብዙ የምለው የለኝም፡፡ ግን በሰላማዊ ሠልፍ ላይ ሕዝቡ የኮከብ ምልክት የሌለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ መገኘት አልነበረበትም የሚሉ ሐሳቦች  ይንፀባረቃሉ፡፡ ይኼንን ሕዝቡ በራሱ የወሰደው አቋም በመሆኑ ሕዝብ ያልተቀበለውን ደግሞ በጉልበትና በኃይል እንዲቀበል መገፋፋት በአሁኑ ጊዜ እየተራመደ ካለው የለውጥ ዓላማ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ኃላፊዎች በሚሳተፉባቸው ስብሰባዎች የሚታየው ሰንደቅ ዓላማ ኮከብ ያለው በመሆኑ፣ መሪዎቹ ይኼንን አለመጣሳቸውን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ሕገ መንግሥቱ ከሕዝቡ በላይ ባለመሆኑና ሕዝብ ሊያሻሽለውና ሊለውጠው የሚችል በመሆኑ፣ ለወደፊቱ ሕዝቡ ተወያይቶ ሊወስንበት የሚችል ጉዳይ በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ እንደ ትልቅ ችግር ቀርቦ ውዝግብ ውስጥ ሊያስገባ አይገባም፡፡

በእርግጥ ሌሎች ጉዳዮች ከመርህ መጣስ ጋር በተገናኘ በግልጽ ቀርቦ መነጋገር ያሻል፡፡ የብዙኃን መገናኛ አውታሮችም ጉዳዮቹን በመርማሪ ጋዜጠኝነት ሊያግባባና ሊያስማማ በሚችል መንገድ በማቅረብ ግልጽ እንዲደረግ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጣት መቀሳሰርና መኮራረፍ ሳይሆን፣ ቅሬታዎችን በግልጽ መወያየትና በመተራረም መፍትሔ እየሰጡ መሄድ ነው ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመው፡፡ የትግራይ ሕዝብን በተመለከተ ክብሩን የሚነካና የሚያዋርድ ምንም የተሠራ ነገር አይታይም፡፡ ሕዝቡ በአገሪቱ በሁሉም ክልሎች እንደ ማንኛቸውም ሌሎች ሕዝቦች በሰላም እየኖረ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ነው፡፡ በእርግጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከሰቱት አመፆች በሌሎች ክልሎች በተለይ ሕዝባዊ አመፁ በበረታባቸው በኦሮሚያና በአማራ ክልል ሥጋት ውስጥ የጣሉ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዚህ መንግሥት የሕወሓት የበላይነት ሰፍኗል፣ ስለሆነም የመንግሥት ለውጥ ሊደረግ ይገባል የሚል ከትግራይ ሕዝብ የወጣውን ሕወሓትን ዒላማ ያደረገ ትግል ስለነበር ነው፡፡ የሕወሓት ደጋፊ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩት ላይ ጉዳት የመድረስ ሁኔታዎችም ተከስተዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሕዝባዊ እንቅስቃሴን መቆጣጠር በሚያስቸግርበት ሁኔታ፣ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ በዚህ  ወገኖች መጎዳታቸው ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊወገዙና እንዳይደገሙ ሁሉም ዜጋ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያዊነት የጨዋነት ባህልና የዳበረ እሴት በመኖሩ እንጂ፣ በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ከዚህም የከፋ አደጋ ሊደርስ የመቻል ዕድል ነበር፡፡ ባለመድረሱም ሕዝቦች ያስመሠግናል፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች በግንፍልተኝነት የሚፈጽሙትን ጥፋቶች  በማጋነንም ማቅረብ ተገቢ አይሆንም፡፡

ይህ ክስተት የተፈጸመው በትግራይ ተወላጆች ብቻ ላይ ሳይሆን በሌሎችም ብሔሮች ላይ ነው፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎች የሞቱትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል፣ በጌዲኦ፣ በጉጂ፣ በቤንሻንጉል፣ በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች ሞትና መፈናቀል በሰሞኑ በጅግጅጋና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች፣ ወዘተ ችግሮችን ማን እንደሚያቀጣጥልና እሳቱም እንዳይጠፋ የሚሠራ ባልታወቀበት የብዙ ወገኖች ሕይወት ተቀጥፏል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሕወሓት ጥቂት ነባር አመራሮች፣ እንዲሁም የሌሎች የአማራ፣ የኦሮሞና የሌሎችንም ይመለከታል፡፡ እነዚህንም የሚያስተባብሩት የሕወሓት የቀድሞ መሪዎተ ናቸው የሚለው መረጃ በሕዝቡ ውስጥ የተሠራጨ በመሆኑ ለሚፈጠሩት ጥፋቶች ሌሎችም ቢያጠፉ የትግራይ ተወላጅን በጥርጣሬ የማየት ሁኔታ አሁንም ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ከለውጡ ሒደት በከፊል ራስን ማግለልና ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ የሚጥሉ ክስተቶች መኖራቸው አግባብ አይሆንም፡፡ እውነታውን በግልጽ መመርመርና መረዳት ያሻል፡፡ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት በዚህ ላይ የሕወሓት የቀድሞ መሪዎችም ሆኑ የአሁኖቹም ሁኔታዎችን ከንዴትና ከአልሸነፍነት በፀዳ መንገድ በመረጋጋት ተጨባጭ ሁኔታዎችን ገምግመው፣ የራሳቸውን ፍላጐት ወደ ጐን በመተው የትግራይን ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅምን ማዕከል አድርገው አቋማቸውን እንደገና ፈትሸው ሰላም ቢያሰፍኑ ችግሩ ይቀረፋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት መሪዎችም በፍቅርና ይቅርባይነት መርህ በመቅረብ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በገቡት መሠረት ሕዝቡ ሊታዘብና ሊከታተል በሚችልባቸው መድረኮች፣ ውይይቶች እንዲካሄዱና መግባባት እንዲደረስ ቢሠራ መልካም ነው፡፡ አግባብ ባልሆነ መንገድ ማንም ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ ሊያልፍ አይገባም፡፡ ጥፋት የፈጸሙ ካሉ ማንም ጥፋት ሊፈጽም ይችላል፡፡ ግን በመፀፀት ጥፋትን አምኖ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ እንጂ፣ ገድሎ ለመሞት ማሰብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለመግደል ሲታሰብ መሞትም ስላለ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ላይም የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ሕዝባዊ ድጋፍ ያለውን ለውጥ ለማሸነፍም አይቻልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚያሸንፉት ሐሳቦች ናቸው፡፡ ዶ/ር ዓብይ በኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሁሉም  ኅብረተሰብ ማለት ይቻላል ተቀባይነትና ተወዳጅነትን ለማትረፍ የቻሉት አዲስ ሐሳብ ስለሚያራምዱ ብቻ ነው፡፡ አሮጌው ለአዲሱ ቦታ መልቀቅ ግዴታ ስለሆነ ይኼ ሐሳብ አሸናፊ ነው፡፡ የአንድ ድርጅት ፖለቲካ ከሞተ ወይም በሐሳብ ከተሸነፈ በወታደራዊ ኃይል ማዳን አይቻልም፡፡፡ ይኼንን ለመግታት መጣር ትርፉ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከፍሎ መውደቅ እንጂ አሸናፊ አያደርግም፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክም የታየ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከ1966 ዓ.ም. አብዮት በኋላ በጦር ኃይል የተሻለ ተደራጅቶ የነበረው ኢዲዩ በሕወሓት መሸነፍ፣ ያን ያህል የጦር ኃይልና መሣሪያ የያዘው ደርግ በኢሕአዴግና በኢትዮጵያ ሕዝብ መሸነፍ፣ በፖለቲካ ከተሸነፉ በጦር ኃይል ማሸነፍ የማይቻል መሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለዚህ ማሸነፍ የማይቻለውን ገድሎ ለመሞት በራስ ላይ መወሰንን ምን አመጣው?

የትግራይ ሕዝብ ለውጡን በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ እንጂ፣ በምንም ዓይነት በኃይል ወደ መፍታት ማሰብ የለበትም፡፡ ጥፋት ፈጽመዋል የሚባሉ ሰዎች የፍትሕ የበላይነትን ለማስከበር ለፍርድ ይቀርቡ ይሆናል፡፡ ግን ጥፋተኝነታቸውን አምነው የሕዝብን ገንዘብ ያላግባብ ወስደው ከሆነ፣ ገንዘቡን መልሰው ይቅርታ ቢጠይቁ ሕዝቡና መንግሥት ይቅርታ ያደርጉላቸው ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓይነት በደቡብ አፍሪካ እንደተደረገው በዕርቅና በምሕረት የዚህ አገር ቂም በቀልና ጥላቻ ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ሆኖ በፍቅር ቢጠናቀቅ ተመራጭ ነው፡፡ ከዚህ ለውጥ የትግራይ ሕዝብ ራሱን ማግለልና ወደ ኋላ መቅረቱ ለራሱም ሆነ ለአገራችን ጉዳት ነው፡፡ ስለሆነም የትግራይ ተወላጆች ልሒቃን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የተቀረው ሕዝብ ተንቀሳቅሰው የሕወሓትን ከፍተኛ አመራሮች መክረውና አስመክረው ወደ ሰላም የማምጣትን ሚና በጉልህ ሊጫወቱ ይገባል፡፡ በሕወሓት አመራር ላይ ግፊት በመፍጠር ለውጡን የሚያራምድ ተራማጅ ኃይል ከውስጡ ወጥቶ ከሌሎቹ ጋር በቅርበት እንዲሠራ ማድረግ አለባቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ለሰላም የራሳቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰላም ለሁላችንም ምትክ የሌላት ፀጋ ናትና፡፡ መልካሙን እመኛለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...