Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ችግራችን መቶ መፍትሔያችን አሥር!

‹‹ይኼኛው ተራራ ያን እየጋረደው፣ የት ይታይ አካልህ ርቆ የሄደው?›› ትላለች ዘፋኟ ለዛ ባለው ድምጿ። ከሜክሲኮ ወደ ቄራ ልንጓዝ እየተሣፈርን ነው። ትዝታ የታክሲዋን የውስጥ ድባብ ለስለስ አድርጎታል። እንደ ነጠላ ገላ የምትለሰልሰው የማለዳ ፀሐይ ሙቀት በመስኮቱ እየሰረገ የሚያገኘንን ብቻ ይዳስሳል። ቀትር ከመሆኑ በፊት የጠዋት ፀሐይን ማንም ይጓጓታል። ‹‹ልጅነትና ይህች የክረምት ፀሐይ ይመሳሰሉብኛል፤›› ይላል አንድ ከኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹እውነት ነው ልጅነት ካለፈ አይገኝም፤›› እያለ ይጨማምራል። ‹‹አሁንማ አንዴ ካለፈ ተመልሶ የሚገኝ ምን ነገር አለ? ሁሉ እያለፈን ሁሉን ስናባርር አይደል እንዴ ቀኑ መሽቶ የሚነጋው? ዕድሜስ በዛው ልክ የሚሸመጥጠው?›› ይለዋል አዲስ የገባው ተሳፋሪ። ‹‹እውነት ነው! እውነት ነው!›› ይላል መልሶ የቀደመው።

አብዛኞቻችንን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በብዙ ጉዳዮች ስለሚያስተሳስረን ሕይወታችን እንጫወታለን። እየተጨዋወትን እንጓዛለን። መራራውን ስንጋፈጥ፣ ጣፋጩን ስናጣጥም ብዙ ድካምና ብዙ ዕድሜ እየከፈልን ወደፊት መጓዝ አይሰለቸንም። ‹‹ቆይ፣ ቆይ ቢሰለቸንስ? በምን ጉልበታችን ተፈጥሮ ላይ እናምፃለን?›› ይላል በውስጡ የሚያስበውን ከወዳጁ ጋር የሚጨዋወት ተሳፋሪ። ‹‹ታዲያስ! እንኳን ተፈጥሮ ላይ እርስ በእርሳችንም መብታችንን አስከብረን ግዴታችንን መወጣት አልቻልንም፤›› ይለዋል። ረጅሙ የትዝታ ሙዚቃ እስኪገባደድ ተሳፋሪዎች ታክሲውን እየሞሉ በጠዋቱ የሐሳብ እሳት ላይ ተጥደዋል። አዳሜ እንዳሰበው ለመዋል እየታገለ እንዳላሰበው የኖረውን ያውጠነጥናል! አሁንማ የምንጣድበት የሐሳብ ምድጃ ግለቱ የሚቻል አልሆነም፡፡ አንዳንዶች የዘመኑን ኑሮ ከእሳት ጋር ሲያወዳድሩት ኧረ የባሰ ነው የሚሉት ደግሞ ገሐነም ነው ይሉታል፡፡ መጥኔ!

ወያላው በጮርናቄ ቀኝ ጉንጩን ወጥሮ ባልተወጠረው በኩል ሽርፍራፊ ቃላት ቀምሮ ይጣራል። ደግሞ ትንሽ ተወት አድርጎ ከሻዩ ፉት ይላል። ‹‹ፋታ የሌላት ሕይወት፤›› ይላል ይህን የሚያስተውል ጎልማሳ ተሳፋሪ። ‹‹እንዲህ ይኖርና ደግሞ ይሞታል፤›› ይላል ሌላው። አጠገቤ ከትንሽ ደቂቃ በፊት ገብቶ የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹እንዴ! ዛሬ ሰው ‘ሰላም አውለኝ ቀኝ አውለኝ’ ብሎ አልወጣም መሰለኝ?›› ብሎ ጠየቀኝ። የጨለምተኝነት አመለካከት የሰፈነ ስለመሰለው። ‹‹ደግ ደጉን እንይ . . . ደግ ደጉን እናውራ . . .›› የሚል ጥቅስ አይቼ ቀና አልኩ። ‹‹ለነገሩ መርጦ መኖር እንደማይቻለው ሁሉ እየመረጡ ማውራትም ይከብዳል፤›› አለኝ መልሶ አውጥቶና አውርዶ ሲያበቃ። በሕይወት ጉዞ ላይ ሐሳብ ሐሳብን እየሻረ የሰው ልጆች ምልከታና ፍልስፍና ታክሲያችን ውስጥ እየተነሳ ይጣላል። አቤት ስንቱ በየመንገዱ ላይ ተነስቶ ሲጣል ያለ ፋይዳ ቀረ? ስንቱ በሰምቶ እንዳልሰማ ባህል ታልፎ ዋጋ ሲያስከፍለን ኖረ? ኧረ ስንቱ!? ስንቱ!? ስንቱ!?

አድማጩ ዝም ሲል ተናጋሪው ይተርካል። ሁሉም ግን እንደ መልኩ የሕይወትን መራራና ጣፋጭ እውነት ከአቦል እስከ በረካዋ እኩል ይጨልጣል። ‹‹ኧረ እንሂድ ሞልቷል!›› አለ አንዱ ከኋላ። ሾፌሩ በኋላ በመመልከቻው መስታወት ቃኘት አድርጎን፣ ‹‹ዓለም እኮ ሞልታ አታውቅም፤›› አለን ኮስተር ባለ የድብርት ድምፅ። ‹‹መቼም ሰው የማይሆነው የለም። ምስኪን በጠዋቱ ምን ለክፎት ይሆን?›› በማለት ከፊታችን የተቀመጡ ሴቶች ተነጋገሩ፡፡ ‹‹ማን ስለዓለም ዘጠኝነት አወራ?›› ቢለው አንድ ወጣት ሾፌሩም ለመመለስ ቸኮለ። ‹‹ስንቱ ክፋት ታቅፎ ደግነት አላውቅ ብሎ አገር ሲያጠፋ ዝም እያላችሁ፣ እኛን ስታጣድፉና ስታሳጡ ምንም አይመስላችሁ፤›› ሲለን ነገሩ ገባንና ዝም አልነው። ‹‹ለዚያ ይሆን ‘ስንት ጉልበተኛና ጨካኝ በሞላባት አገር ሾፌርና ወያላ ላይ ብቻ ጡንቻዎትን አያሳዩ!’ የሚል ጥቅስ የተለጠፈው?›› ብለን ተንሾካሾክን! የሹክሹክታ ዘመን! ቀና ብዬ ወደ አንደኛው ጥግ በኩል ስመለከት የተሰቀለው ጥቅስ ፈገግ አሰኘኝ፡፡ ‹‹መብታችሁ ትዝ የሚላችሁ ታክሲ ውስጥ ነው ወይ?›› ይላል፡፡

ወያላው የጮርናቄውን ዘይት በእጁ እየጠራረገ መጣና ‹‹ሳበው›› አለው ሾፌሩን። ምንም እንኳ ሾፌሩ የወያላውን ቁርስ በልቶ መጨረስ እየጠበቀ እንደነበር ቢገባንም፣ የመለሰልን መልስ ብዙዎቻችን እንዳብሰለሰለን ተቀምጠናል። ‹‹ኤድያ! ፌስቡክ እያለ በየት በኩል ሥራ ይሠራል?›› አለ አንድ ጎልማሳ የእጅ ስልኩን እየወዘወዘ። መልኩ ሰሞነኛ ጭንቀትና ሐሳብ እንዳለበት ያሳብቃል። ‹‹ከምን ተነስተህ ነው ወዳጄ?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ሰው ሥራ ፈታ ብዬ ነዋ! እርግፍ አድርጎ ሰው ሥራ መሥራት ትቷል እኮ ነው የምልህ? ጭንቅላታችን አለቅጥ ፈዞ እውነትን ማየት አቃተው። ‘አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል’ የሚባለው አባባል አሁን ‘ፌስቡክ ሲከፈት ገመና ይገለጣል’ ተብሎ ቢቀየር የለውጥ ጉዟችን በትክክል ወዴት እንደሚያመራ ባሳየ ነበር። ሌላው ቀርቶ ሾፌሩ እንዳለው ስንቱን ጥጋበኛ ፌስቡክ ላይ ልንጠቋቆመው ሲገባ . . .›› ብሎ ራሱን አወዛወዘና ‹‹ . . .ኧረ ተወኝ ወንድሜ፣ ማን እንደ ሞዴል እየተቀናጣን የምንነሳውን ፎቶ ይጠቋቆምልን?›› ብሎት በረጅሙ ተነፈሰ። ወያላው ‹‹ሾፌር›› መባሉን ስለሰማ ስለምን እንደሚወራ ለመስማትና ራሱን ከተሳፋሪዎች ‹‹ሙድ›› ጋር ለማጣመር ትኩረቱን ይሰበስባል። የፌስቡክ አፍቃሪያን ደግሞ፣ ‹‹ታዲያ በምን እንደበር? ምድረ ወሬኛና አሉባልተኛ በእኛ ሲደበር እኛ በፌስቡክ ካልተደበርን በምን ልንደበር ነው?›› ይባባላሉ። ዘመናዊነትና ቴክኖሎጂን ማን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንዳደረጋቸው መርምረን መድረስ ከብዶናል! ወያላው ወሬው ከአቅሙ በላይ ስለመሰለው ወደ ደጅ አንጋጦ ወሬ ማየት ይዟል። ‹‹ጣልቃ ገቦች በበዙበት ዓለም ዝምተኞች የምሽት ከዋክብት ናቸው›› ያለው ማን ነበር?

ታክሲው መንገዱን ይዞ ፍጥነቱን ሲያበረታ ወያላው ወደ ሥራው ተሰማራ። ‹‹እሺ ሳንቲም ያላችሁ እባካችሁ እየተባበራችሁኝ፤›› አለ ድምፁን ከፍ አድርጎ። ‹‹እንዴ አላበዛችሁትም ግን እናንተ? የእናንተን ሥራ እኛ መሥራት አለብን?›› አሉት አንዲት ወይዘሮ። ‹‹እንደሱ አይደለም፡፡ አሥር ብር የምንዘረዝረው በርካታ ሳንቲሞችን ገብረን ስለሆነ ነው። እንዴት ያዋጣናል እንዲህ እየዘረዘርን ታዲያ?›› አለ ረጋ ብሎ። ‹‹አንተ እሱን ትላለህ ዶላር እንደገና ለመጨመር እየተጣደፈ አይደል እንዴ?›› አለው ከኋላ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹ታዲያ እንዴት ነው የምናከብረው?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ ድንገት። ‹‹ምኑን?›› አለው ጎልማሳው ግራ ተጋብቶ። ‹‹ማለቴ አንድ ዶላር በ30 ብር መዘርዘር ሲጀምር መቼም የሆነ ነገር አዘጋጅተን እንኳን ደስ አለህ ማለት ያለብን ይመስለኛል። ከዚህ ወዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?›› ሲል የንዴት ፈገግታ ጥርሳችንን አስገለፈጠው፡፡

መንገድ ላይ ሁለት ቆነጃጅት ጉሮሯቸው እስኪደርቅ ተጣርተው አስቆሙንና ተሳፈሩ። ‹‹አንተ ጆሮህን ተኝተህበታል እንዴ?›› አለችው አንደኛዋ ወያላውን እየገላመጠች። ወያላው ፈገግ ብሎ እየተቅለሰለሰ ዝም አለ። ዝምታው ያበሸቃት ጠያቂ ደጅ ጀምራው የነበረውን ወሬ ለመቀጠል ተጣደፈች። ‹‹ . . . እና ይገርምሻል እንደዚያ ምላ ተገዝታ የወሰደችውን ልብስና ጫማዬን ሳትመልስ፣ ደውላ እንኳ ‘በይ መሄዴ ነው’ ሳትል ቀረች፤›› እያለች አንድ ጓደኛዋን ማማት ጀመረች። ‹‹‘ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ’ አለ የአገሬ ሰው፤›› አለ ከኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ በሽሙጥ። ቆነጃጅቱ የሰሙት አይመስሉም። ቤት ውስጥ ለብቻ የሚወራውን በአደባባይ ከሚወራው ሳይለዩ ብዙ ይባባላሉ። ቀሪዎቹ የታክሲ ተሳፋሪዎች የሚሰሙት ነገር አሳዝኖዋቸው ይመስላል በኃፍረት አንገታቸውን ደፍተዋል። የወጣቶቹ ቁንጅና ከሰብዕናቸው የበለጠበት አንዱ ደግሞ፣ ‹‹ይገርማል ኑሮ እንዲህ ተወዶም የእህቶቻችን ውበት በየቀኑ አብሮ እየናረ ነው። ጎበዝ! ውበታቸው በስንት መቶኛ እያደገ ይሆን?!›› ሲለን ተሳሳቅን። ‹‹ምን ዋጋ አለው?›› አለ አንዱ ደግሞ ተበሳጭቶ። ‹‹ምነው?›› ሲሉት ፈጠን ብሎ ‹‹ሚስት ጠፋ። እኛም በየካፌውና በየሲኒማ ቤቱ እየዞርን መፈለጉ ደከመን፤›› ከማለቱ፣ ‹‹አይ አንተ ፌስቡክ እያለ ምን ነዳጅ አስጨረሰህ?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠ። አንገብጋቢው ነገር ሲመናመን ቀስ ብሎ የሚደርሰው ይበረክታል። ጨዋታን ሐሜት ሲያደፈርሰው ጆሮ ድፈኑኝ፣ ድፈኑኝ ይላል። ሕይወት በተቃርኖ ውስጥ ስትጓዝ፣ የሚጓዙበትን ለመወሰን ይጨንቃል!

መዳረሻችን እየተቃረበ ነው። ሾፌሩ የሬዲዮውን ጣቢያ ከትዝታ ወደ ስፖርት ዘገባና ትንታኔ መልሶታል። ‹‹ምናለበት ኢኮኖሚያችን፣ ፖለቲካችን፣ ኑሯችን እንዲህ ቢተነተንልን? ቀላል ቀላሉዋን ስንመርጥ እስከ መቼ ልንኖር ነው?›› ብለው አንድ አዛውንት ጠየቁ። ወያላው፣ ‹‹ምን አሁንማ ኳሱም ፖለቲካ አልሆነም ብለው ነው?›› አላቸው። ‹‹እንዴት?›› አሉት ግር ብሏቸው። እኛም ግር ብሎን ለማዳመጥ አሰፈሰፍን። ‹‹ኳስ በደህናው ቀን መዝናኛችን ነበር። አሁን ግን ቬንገር የሚባሉ ሰውዬ ሄደውም በአዲሱ ሰውዬም ጨጓራችንን በሽተኛ እየሆነ ኳሱ ፖለቲካ ሆነብን፤›› ሲል የአርሰናል ደጋፊ መሆኑ ገብቶን ሳቅን። አዛውንቱም፣ ‹‹ምን ይሻላችሁ ይሆን?›› አሉት እየሳቁ። ‹‹እንደገና ሌላ አሠልጣኝ ካልመጣ ለውጥ የለም፤›› አለ ወያላው ፈርጠም ብሎ። አዛውንቱ ድምፃቸውን ጠራርገው፣ ‹‹አሄሄ ተው እባክህ! ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም፡፡ ሰው ቢቀያየር አሠራር ካልተቀየረ ምን መፍትሔ ይመጣ ብለህ ነው ልጄ? ተሿሚው ቢቀያየር አብረን ካልሠራንና ውጤት ካልታየ ምን ዋጋ አለው?›› አሉና ትንሽ ትንፋሻቸውን ሰብስበው፣ ‹‹ሰሞኑን በአገራችንም አዲስ የሥልጣን ሽግግር ተደርጓል። ሥልጣኑ ዋጋ የሚኖረው የአሠራር ለውጥ እንዲኖር እኛም ስናግዝ ጭምር ነው፡፡ አሠልጣኝ በመቀያየር ብቻ ለውጥና ውጤት ናፋቂዎች ከመሆን እኛም የድርሻችንን እንወጣ፡፡ ዳር ሆኖ ለውጥ መጠበቅ ሞኝነት ነው!›› ሲሉ ወያላው የገባው መስሎ አንገቱን ነቀነቀ።

‹‹የአሠልጣኝ ለውጥ ወይም የፖለቲካ ሹመትና ሽግሽግ አባታችን እንዳሉት ከኋላቀርና ከጭካኔ ድርጊቶች ለውጥ ጋር ካልተቀናጀ እርባና ቢስ ነው፤›› አለ አንዱ፡፡ ሌላኛው ከአፉ ላይ ለቀም አድርጎ፣ ‹‹እኛ የሰው አገር ኳስና አሠልጣኝ ጉዳይ ስናማስል የራሳችን እያረረብን ነው፤›› አለ፡፡ የባሰ አታምጣ በአንድ ጊዜ ምን ውስጥ ገባን ይሆን? አዛውንቱ ሳቅ እያሉ፣ ‹‹የእኛን ኳስ ነገርማ እያየኸው አይደል? ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የማይፎካከርና አንዳች የሚረባ ነገር የማይሠራ ቁመና ይዘን ቀኑ ነጎደ እኮ፤›› ሲሉ፣ ሌላው ተቀበላቸው፡፡ ‹‹አይ አባባ ይኼው ዘመናዊ ስታዲዮም እየገነባን ማን እንደሚጫወትበት እንጃ፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ ግን ለዚህ ሲባል የሚጠፋው ገንዘብና ጊዜ ነው፤›› አለ፡፡ አዛውንቱ ኮስተር ብለው፣ በአገራችን አንድ ታዋቂ አባባል አለ፡፡ ‘ዘጠኝ ድስት ጥዳ አንዱንም ሳታማስል ቀረች’ ይባላል፡፡ ዘጠኝ ድስት ከመጣድ ይሰውራችሁ . . . ›› እያሉ ሳለ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ አወጀ፡፡ በኳስ ሰበብ የጊዜውን ጉድ በአሽሙር እየሰማንና በነገር እየተብሰለሰልን ወደ ጉዳያችን አመራን፡፡ ችግራችን መቶ መፍትሔያችን አሥር ሆነ እኮ ነገሩ፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት