Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበ300 ሚሊዮን ብር የተሠራው የግል ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

በ300 ሚሊዮን ብር የተሠራው የግል ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ቀን:

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ጎተራ ኮንዶሚኒየም አካባቢ በ300 ሚሊዮን ብር የተገነባው ባለስምንት ፎቅ ዘመናዊ የግል አጠቃላይ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ‹‹ሃሌ ሉያ›› በሚል ስያሜ የሚጠራውን ሆስፒታል መርቀው የከፈቱት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንዳሉት፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ዘመን ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት፣ የዘርፉን የጥራት ደረጃ ማሻሻልና ከፍ ማድረግ ነው፡፡

ሃሌ ሉያ አጠቃላይ ሆስፒታልም የአገሪቱን የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ እንደታመነበት፣  በተለይም ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ አገር እንዳይሄዱ በማድረግ፣ የጎረቤት አገሮች ታካሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምና እንዲያገኙና የሕክምና ቱሪዝምንም በማበልፀግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ በበኩላቸው፣ የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ በሽታን መከላከልን መሠረት ያደረገ መሆኑንና መንግሥትም ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በሽታን መከላከልና መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ማዳረስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና ዕውቀት በሚጠይቁ የጤና አገልግሎቶች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን አስቀምጦ መንቀሳቀሱን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ፕሮፌሰር ጌታቸውና ባለቤታቸው ወ/ሮ የትናየት እሸቱ፣ መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትለውና ሆስፒታል ገንብተው ለአገልግሎት በማብቃታቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች የእናቶችንና ሕፃናትን ሞት መቀነስ፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቆጣጠር እንደሚገኙበት፣ የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የጤና ተቋማት መንግሥት ያወጣቸውንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያስቀመጧቸውን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎች ማሟላት፣ የጥራት ዕቅድ መንደፍና ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ፓኬጆችን መተግበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ በመዲናይቱ ውስጥ  ባለሀብቶች ከ30 በላይ የግል ሆስፒታሎችንና በርካታ ክሊኒኮች በመገንባትና አገልግሎት በመስጠት አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በከተማዋ በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ዕውቀትና ሀብታቸውን በማቀናጀት የከተማዋን የጤና ሽፋን ለማሳደግና ጥራቱን ለማሻሻል እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጠውም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

የሃሌ ሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ኤክስኪዩቲቭ ሜዲካል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ በበኩላቸው፣ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የቱሪስትና የኢንቨስትመንት ፍላጎት በማገናዘብ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች መፍጠር የቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ፍላጎት በመሆኑ መንግሥት ለግሉ የጤና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬና ባለቤታቸው ወ/ሮ የትናየት እሸቱ ያሠሩት ሆስፒታል፣ የድንገተኛ አደጋ፣ የውስጥ ደዌ፣ የነርቭ፣ የማንኮራፋትና የእንቅልፍ ችግር፣ የጽኑ ሕመምና የሕፃናት ሕክምናዎችን ያደርጋል፡፡ የኩላሊት ማጣራት ቅድመ  ምርመራ፣ የልብና የደም ሥሮች ሕክምና፣ የላቦራቶሪ አገልግሎቶች የጥርስና  የአንገት በላይ፣ የዓይንና የሕዋሳት ምርመራና ተጓዳኝ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ የሳምባና የትንፋሽ ሥርዓት መፈተሻ ማዕከልም አለው፡፡

ሚያዝያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመረቀው ሆስፒታሉ የስብሰባ አዳራሽና ቤተ መጻሕፍት፣ የፋርማሲ፣ የአምቡላንስና የአስከሬን መጠበቂያ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ 228 አልጋዎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...