Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየትዝታው ንጉሥ

የትዝታው ንጉሥ

ቀን:

መሐሙድ አህመድ ከአምስት አሠርታት በላይ በሙዚቃው እንደተወደደ የኖረ ድምፃዊ ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ የቀደመውንና የአሁኑን ትውልድ በልዩ ስሜት ያስተሳስራሉ፡፡ የትዝታው ንጉሥ መሐሙድ 75 ዓመት ቢሞላውም ዛሬም ወኔው አልቀዘቀዘም፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ከሮሃ ባንድ ጋር ዳግም ተጣምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ያቀረበው ድንቅ ትርኢት ለዚህ ምስክር ይሆናል፡፡

መሐሙድ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ያበረከተውን ታላቅ አስተዋጽኦ ለመዘከር ልደቱ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ የመሐሙድ 75ኛ ዓመት ልደት ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በተካሄደ የሙዚቃ ኮንሰርት ተከብሯል፡፡  ከኮንሰርቱ በተጨማሪ ለአንድ ሳምንት የቆየ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይም ተካሂዷል፡፡

በማሪዮት ሆቴል የተዘጋጀው የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ፣ መሐሙድ በተለያዩ አገሮችና መድረኮች ያቀረባቸውን ኮንሰርቶች አካቷል፡፡ ከአንጋፋና ወጣት ሙዚቀኞች ጋር የተነሳቸው ፎቶዎች፣ እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች የተበረከቱለት ስጦታዎችና ሽልማቶችም ለእይታ በቅተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከፎቶግራፍ ስብስቦቹ መካከል መሐሙድ በተለያየ ወቅት አብረውት ከዘፈኑት ሙዚቀኞች ጋር የተነሳቸው ይገኙበታል፡፡ የክብር ዘበኛና የሕዝብ ለሕዝብ አባሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

መሐሙድ የተወለደው አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ክብር ዘበኛ ባንድ አባላት ከሥራ በኋላ የሚዝናኑበት አሪዞና ክለብ ውስጥ  ከመቀጠሩ በፊት ሊስትሮ ነበር፡፡ አንድ ምሽት የባንዱ ዘፋኝ ጥላሁን ገሠሠ ሳይገኝ ይቀራል፡፡ መሐሙድም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለመዝፈን ይጠይቃል፡፡ ከዛ በኋላ የባንዱ አባላት በመረዋ ድምፁ ተስበው አብሯቸው ለዓመታት ዘለቀ፡፡

ድምፃዊው በሸክላ የሠራቸው በርካታ ሙዚቃዎች ያሉ ሲሆን፣ ወደ ካሴት ከተሸጋገረ በኋላ የሠራቸው ተወዳጅ ዘፈኖችም ብዙ ናቸው፡፡ የእነዚህ አልበሞች ሽፋኖች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ ከሌሎች ድምፃውያን ጋር የተነሳው ፎቶዎችም ተካተዋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ዓለማየሁ እሸቴና ምኒልክ ወስናቸው ይገኙበታል፡፡ በተለያየ ሙያ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች ጋር የተነሳቸው ፎቶዎችም ትውስታን የሚያጭሩ ናቸው፡፡ ከደበበ እሸቱ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ አፈወርቅ ተክሌና ካትሪን ሐምሊን ጋር የተነሳቸው ይጠቀሳሉ፡፡

መሐሙድ ከበርካታ ባንዶች ጋር የሠራ ሲሆን፣ በተለይ በክራር፣ ጊታርና ማንዶሊን ታጅቦ የሠራቸው ሙዚቃዎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪም ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈ ድምፃዊ ነው፡፡ ዐውደ ርዕዩ በተለያዩ ኮንሰርቶችና ፌስቲቫሎች ላይ ሲያቀነቅን የተነሳቸውን ፎቶዎች አካቷል፡፡ ኒውዝላንድ፣ አሜሪካና ፈረንሳይን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዝነኛው የሕዝብ ለሕዝብ ጉዞ ወቅት የነበረውን ቆይታ የሚያንፀባርቅ ፎቶም ይገኛል፡፡

መሐሙድ እ.ኤ.አ. በ2007 የቢቢሲ ወርልድ ሚውዚክ አዋርድ ተሸላሚ ነበረ፡፡ በዐውደ ርዕዩ ከዚህ ሽልማት በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜዎች ያገኛቸው ሽልማቶችም ቀርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር፣ ሚሌንየም ባንድ፣ ሎስአንጀለስ ከተማ፣ በዴንቨር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ጄሚኒ ኸልዝ ግሩፕና አትላንታ ከተማ ከሸላሚዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡

‹‹ኧረ መላ መላ››፣ ‹‹ተው ልመድ ገላዬ፣ ‹‹የሺ ሐረጊቱ››፣ ‹‹ትዝታ››፣ ‹‹በምን ሰበብ ልጥላሽ›› እና ‹‹አታውሩልኝ ሌላ›› ከዘፈኖቹ ጥቂቱ ሲሆኑ፣ መድረክ ላይ ሲያቀነቅን ጾታና ዕድሜ ሳይለይ ታዳሚዎች ሁሉ በስሜት ሲያዜሙ ይስተዋላል፡፡

‹‹ኧረ በከተማው ጭራሽ በሀገሩ

ከኔና አንቺ በቀር እነማን ነበሩ

ዛፍ ጥላ ሥር ሆነን ስንነጋገር

ከቶ እነማን ሰሙ ሰንመካከር…›› ከብዙዎች ህሊና በማይጠፉ ተወዳጅ ዘፈኖቹ አንዱ ነው፡፡ የድምፃዊው ትውልድ ተሻጋሪ አልበሞች ሳይለቀቁ በፊት መነሻው የነበረውን ጫማ መጥረግም አልዘነጋም፡፡ በዐውደ ርዕዩ የሙዚቃ ስኬቱን ከሚያሳዩ ፎቶዎች ጎን ለጎን ጫማ ሲጠርግና የሊስትሮ ዕቃ ይዞ የሚያሳዩ ተካተዋል፡፡ ፎቶዎቹን የተነሳቸው በዕድሜ ከገፋ በኋላ ቢሆንም የቀድሞው ማስታወሻ ይሆናሉ፡፡

ከአዘጋጆቹ አንዱ ዘሩባቤል ብርሃኑ፣ የመሐሙድ ሥራዎች እንዲታወሱና ለአስተዋፅኦውም እውቅና እንዲሰጥ አሻራ ፊልምስ መርሐ ግብሩን እንዳዘጋጀ ተናግሯል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በተዘጋጀው ኮንስርት፣ በስሙ ዛፍ መተከሉ መልካም ማስታወሻ እንደሆነና ዐውደ ርዕዩ የሙዚቃ ጉዞውን እንደሚያስቃኝ ገልጿል፡፡

ድምፃዊው በሙዚቃው ያሳለፋቸውን ጊዜዎች ሕዝቡ ሲመለከት በትዝታ ወደኋላ ከመመለሱ በላይ ጠቃሚ መረጃ እንዳገኘም ይናገራል፡፡ ‹‹ዐውደ ርዕዩ ከመሐሙድ ሥራዎች ውስኑን ቢያሳይም ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ አሁን ያለውን መሐሙድና ሥራዎቹን በመጠኑ አስቃኝቷል፡፡ መሐሙድ ተመልካቹም ይህን ታሪክ በማየቱ ደስተኛ ሆኗል፤›› ይላል፡፡ በሙዚቃው ወይም በሌሎች የጥበብ ዘርፎች ገናና የሆኑ ባለሙያዎች ሥራዎች የሚታዩባቸውና ለአስተዋፅኦዋቸው የሚመሰገኑባቸው ዝግጅቶች መብዛት እንዳለባቸው ዘሩባቤል ይናገራል፡፡

ለአንጋፋ ባለሙያዎች ክብር ሲሰጥ ከሚፈጥርባቸው ደስታ በተጨማሪ ወጣቶችን ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳም ያምናል፡፡ እንደ ፎቶ ያሉ ታሪክን የሚያሳዩ መረጃዎች መሰብሰብና ለሕዝብ ማሳየት መለመድ እንዳለበትና ባለሙያዎቹ በሕይወት ሳሉ ማድረጉ የተሻለ እንደሆነም አክሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...