Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ስለጫት የሚንፀባረቁ ጽንፎች ንግግር የሚጋብዙ አይደሉም››

ዶ/ር ዘሪሁን መሐመድ፣

የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ አጥኚ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የጫትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎችን (አዎንታዊም አሉታዊም) የሚዳስስ የውይይት መድረክ በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍኤስኤስ) ተካሂዶ ነበር፡፡ በውይይት መድረኩ 15 ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች፣ የሥነ ልቦናና የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ምሕረት አስቻለው የመድረኩ አዘጋጅ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ማኅበራዊ ጥናት መድረክ) አጥኚዎች ከሆኑትና የመድረኩ አስተባባሪዎች ከነበሩት ዶ/ር አስናቀ ከፍአለና ዶ/ር ዘሪሁን መሐመድ ጋር በጫት ላይ ስለተሠሩት 15 ጥናቶች እንዲሁም ኤፍኤስኤስ በቀጣይ በጫት ላይ ሊሠራ ስላሰባቸው ሥራዎች ቆይታ አድርጋለች፡፡ ዶ/ር አስናቀ ከፍአለ በአዲስ አበባ የዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ተባባሪ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ጫት ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሠራቸውን ሥራዎች ሲያስተባብሩ ቆይተዋልም፡፡ ዶ/ር ዘሪሁን መሐመድ አንትሮፖሎጂስት ሲሆኑ በድርጅቱ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተመራማሪ ናቸው፡፡ ጫት ላይ የተለያዩ ጥናቶችንም ሠርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ጫት ላይ የሠራችሁት ሥራ ነበር?

ዶ/ር አስናቀ፡- ‹‹ወጣትና ልማት›› በሚል ርዕስ ተከታታይ የውይይት መድረኮች አዘጋጅተን ነበር፡፡ እዚያ ላይ ጫት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡ ጫት ላይ የቀረበው አንድ ጥናት ሲሆን አጠቃላይ የውይይቱ ዓላማ ወጣቶች በልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የልማት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው? ተግዳሮቶቹስ? የሚል ነበር፡፡ ጥናቱ የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡ በጥናቱ ጫት ጐልቶ ሲወጣ በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውም ታወቀ፡፡ ያኔ ይህ ጥናት በቀረበበት ሕዝባዊ ውይይት ላይ ብዙዎች የጫትን አሉታዊ ተጽእኖ በማስመልከት አስተያየት ሲሰጡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ያነሱም ነበሩ፡፡ ለበርካታ የኅብረተሰብ ክፍል ቋሚ የገቢ ምንጭ የኑሮ መሠረትም መሆኑ ከዚያ በድጋሚ የውይይት መድረክ ተዘጋጀ፡፡ በዚያ ያለው የፖሊሲ ክፍተት በጉልህ በመታየቱ ኤፍኤስኤስ ፕሮጀክት ቀርጾ ለመሥራት ተገደደ፡፡ በሌላ በኩል መሬት ላይ የምናየው ነገር አሳሳቢ መሆንም ሌላው ምክንያት ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሲቪል ሶሳይቲ ግራት መገኘት ደግሞ ነገሮች እንዲሳኩ አደረገ፡፡ በመጨረሻ ኤፍኤስኤስ የራሱን ጥናት ከማድረግ በተጨማሪ ጫት ላይ የተሠሩ የተለያዩ ጥናቶች፣ እውቀቶች፣ የተለያዩ አቋሞች እንዲሰባሰቡና በአንድ መድረክ እንዲቀርቡ አደረገ፡፡ በዚህ መልኩ ጫትን በሚመለከት ስንነጋገር ወደ አራት ዓመት ቆይተናል፡፡ አሁን ስለዚህ ስለጫት መነጋገር ማነጋገርም ላይ ነን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጫት ላይ በምትሠሩት ሥራ እነማን አጋሮቻችሁ ናቸው?

ዶ/ር ዘሪሁን፡- ድርጅቱ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ የአካዳሚክ ፀባይ አለው፡፡ ስለዚህም ጥናቶችን ከማንም ይቀበላል፡፡ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችም ይሠራሉ፡፡ መሥራት የምንፈልገውም ከሁሉም ከሚመለከተው ጋር ነው፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የምርምር ተቋማት፣ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ካሉ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህም ነው ስንጀምር ለእነዚህ አካላት ሁሉ ጥሪ ያደረግነው፡፡ ባዘጋጀነው መድረክ ላይ ከቀረቡት አሥራ አምስት ጥናቶች ከመንግሥት ተቋማት፣ ከማኅበራት፣ ከሙያ ማኅበራት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችም ብዙ ቀርበዋል፡፡ ከእኛም እንደዚሁ፡፡ ፖሊሲን በሚያክል ትልቅ ነገር ስንወያይ የተወሰኑ ክፍሎች ብቻ የሚገኙበት ሳይሆን ሁሉም የሚሳተፉበት መሆን አለበት፡፡ ምንም እንኳ እስካሁን ባለው ተሞክሮአችን ለሚመለከተው ሁሉ ያደረግነው ጥሪ ተሳክቷል ባንልም ግን ያገባኛል የሚለውን ሁሉ እየጋበዝን ስለሆነ ውይይቱ በሁሉም በኩል ይቀጥላል ብለን እናምናለን፡፡

ዶ/ር አስናቀ፡- ከመንግሥት ተቋማት ማኅበራዊ ጉዳይ ነበር፡፡ የአእምሮ ሕክምና ላይ ያሉ ባለሙያዎችም እንዲሁ፡፡ ወጣት ምሁራንም ነበሩ፡፡ በዚህ ፕሮጀክት በዋነኝነት ከእኛ ጋር የተሳተፉት የኢትዮጵያ ወጣት ማኅበራት ኔትወርክ የሐረሪ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ልማት ማኅበሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በጫት ሱስ ለተጐዱ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ ሌሎችንም ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ስለጫት ግንዛቤ እንዲፈጠርም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንደታየው ስለጫት ሁለት ጽንፍ የወጡ አመለካከቶች አሉ፡፡ ጫት ከባህል፣ ከኢኮኖሚና ከሃይማኖት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ መንካት አያስፈልግምና ጫት አደገኛ በመሆኑ መንግሥት ሊያስቆመው ይገባል የሚሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጫት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፣ የኢኮኖሚ ጠቀሜታውም ቀላል የማይባል በመሆኑ (የተለያዩ ግምቶች እንደሚያስቀምጡት አገሪቱ በዓመት ከጫት ከ200 እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች) እንዲሁ እንደ ቀላል የሚቆም አይደለም፡፡ በመጨረሻ ጉባዔው የደረሰው በሁለቱ ጽንፎች መካከል መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ምክንያቱም የዛሬው የጫት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናልና፡፡ ቡና ተነቅሎ ጫት እየተተከለ ጫት እንደ ዋና ወደ ውጭ የሚላክ ምርት እየታየ ነው፡፡ በሌላ በኩል አገሮች ጫትን እየከለከሉ ነው፡፡ ስለዚህም መፍትሔ የሚሆነው ጫት የት ይሸጥ? በማንና እንዴት ባለ ሁኔታ? የሚለውን መወሰን ማስፈለጉ ላይ ከሞላ ጐደል በጉባዔው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- የጉባዔው ዋና ዓላማ ምንድን ነበር?

ዶ/ር ዘሪሁን፡- ስለጫት ንግግር መፍጠር ነው፡፡ ስለጫት ሁሌም የሚንፀባረቁት ጽንፎች ንግግርን የሚጋብዙ አይደሉም፡፡ ከእነዚህ ወጥተን ምን እናድርግ? የሚለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ የቀረቡት ጥናቶች ይህንን ጥያቄ በሚመለከት አንዳንድ ነገሮችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ከአቅርቦት እንዲሁም ከፍላጐት አንፃር ጫት ላይ ሊሠራ ይገባል የሚል አስተያየት ቀርቧል፡፡ አቅርቦትን በመቆጣጠርና በመወሰን ጫት ላይ ለመሥራት የሞከሩ አገሮች አሉ፡፡ በእኛ አገር ብዙዎች ጫትን የገቢ ምንጭና የኑሮ መሠረት ባደረጉበት እውነታ አቅርቦትን መገደብ አዋጭ ላይሆን ይችላል፡፡ ይልቁንም በማስተማር ፍላጐት ላይ መሥራት ውጤት ይኖረዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ መኖር ግን ወሳኝ ነው፡፡ ትምህርት ቤት፣ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ጫት ሊሸጥ አይገባም፡፡ ከሕግ ባሻገር ግን ስለጫት አሉታዊ ተፅዕኖ ማስተማርና ማስረጽ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባካሄዳችሁት የውይይት መድረክ ላይ ጫትን በሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የኤፍኤስኤስ ቀጣይ እርምጃ ምንድን ነው?

ዶ/ር ዘሪሁን፡- ከሁሉም በፊት ራዕያችን ከሱስ የፀዳ አምራች ኅብረተሰብ ማየት ነው፡፡ አሁን የምናደርገው ሕዝባዊ ውይይት ዳብሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ የምንፈልገው ደረጃ ላይ መድረስን ነው፡፡ ውይይቱ ወደ ላይ እንዲወጣና ስለጫት አሉታዊ ጐን ጥናት ሠርታችሁ አሳዩ ያሉ የመንግሥት አካላትም የጥናቱ አካል ሆነው ማየትም እንፈልጋለን፡፡

ዶ/ር አስናቀ፡- የሕግ ማዕቀፉ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይም መሥራት መወያየት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ አሁንም የተደረገውን ውይይት ጭብጥ አሳትመን እናሰራጫለን፡፡

ሪፖርተር፡- ጫት ላይ ስትሠሩ ያጋጠሟችሁ ተግዳሮቶች?

ዶ/ር አስናቀ፡- ጫት ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ እሴት እንደመሆኑ ስለጫት ሲወራ ተቃውሞው ቀላል አይሆንም፡፡ ነገር ግን ስለጫት ውይይት መጀመሩ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ ማሰብ ማመዛዘንም የሚጠይቅ በመሆኑ መንግሥትም በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድ አይጠበቅም፡፡ የሒደቱ መጀመር ራሱ እንኳ እንደ ስኬት ሊታይ ይችላል፡፡    

         

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች