Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‘አርባ ቢወለድ አርባ ነው ጉዱ…’

እነሆ መንገድ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ሾፌራችን በወያላው ቅዝዝ ፍዝዝ ማለት የሚያደርገው ጠፍቶታል። ‹‹ምን ዝም ትላለህ? ወይ አንተን አባርሬ ቻይና ልቅጠር መሰል፤›› ይላል። ‹‹እንዴት እንዴት በአገርህ ስንት ሥራ አጥ ወገን እያለ ቻይና?›› ይሉታል አጠገቡ የተሰየሙ ባርኔጣ የደፉ አዛውንት። ‹‹ምን አባቴ ላድርግ? እንዲሁ በቆምኩበት ነዳጅ እየጨረስኩ ተቸገርኩ እኮ አባት?›› አላቸው። ‹‹እሱስ አንተ ብቻ አይደለህም አይዞህ። እኛም በቆምንበት ነው ዕድሜያችን ያለቀው፤›› አሉት። ‹‹የባሰ አታምጣ። ያውም የማይሞላውን ነዋ የጨረሱት?›› ብላ የደስ ደስ ያላት ወጣት የጋቢናውን በር ከፍታ እየዘጋች ተናገረች። ‹‹ዲስኮ ሰዓት መሰለሽ ታዲያ ዕድሜ?›› አባታዊ የፍቅር አስተያየታቸውን ገጿ ላይ እያረበቡ አናገሩዋት። ‹‹ምን የዘንድሮ ሰዓት እኮ ብንሞላውም ባንሞላውም አንድ ነው፤›› አለቻቸው። ‹‹ቢሳሳትም በቀን ሁለቴ  ልክ መሆኑ አይቀርም እያልሽኝ ነው?›› አሉዋት።

‹‹እሱ እንዳለ ሆኖ የመሙላትና የመጉደሉን ሒሳብ ገንዘብ ተክቶታል ለማለት ፈልጌ ነው፤›› ስትላቸው፣ ‹‹ጊዜና ገንዘብ አንድ መስለውኝ?›› ብለው ግራ በተጋባ መንፈስ አስተዋሏት። ‹‹እሱማ እኛም መስሎን ነበር። ግን ጎዳናውን ስናየው ጊዜና ገንዘብ፣ ዕድሜና ሥፍራ ገጥመው አይገኙም። አይደለም እንዴ?›› ብላ ተራዋን ቀና ብላ እያየቻቸው ቦርሳዋን መጎርጎር ጀመረች። አዛውንቱ ሲያወጡ ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ፣ ‹‹እሱማ እንኳን ጊዜና ሁኔታ ገንዘብና ዕድሜ ሊገጥሙ፣ ግጥሙ ራሱ አልገጥም ብሎን ተቸግረናል። ይኸው በ-ታታታ፣ በ-ላላላ፣ በ-ሃሃሃሃ እያሉ አብደው ሲያሳብዱን ዝም ያልነው ለምን ሆነና? ተስፋ ብንቆርጥ አይደለም እንዴ?›› ብለው በሬዲዮ የሚንቆረቆረውን ዘመነኛ የችክችክታ ዘፈን ጠቆሙ። ቢገጥም ባይገጥም እኛ ምን አገባን? አገር ባይኖረንም አገራችን ያግባን ሆኗል እኮ ነገሩ። ይኼን ያህል በጊዜና ገንዘብ አገጣጠም ተስፋ ቆርጠን መድረሻ ቢስ ሆነናል ማለት ነው? ይገርማል!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረች። ብዙም የማይናገረው ወያላ ንዴትና ቁጣ የተቀላቀለበትን የሾፌሩን ተግሳፅ እያዳመጠ የሚያዳምጥ አይመስልም። ‹‹ስማ … እኔ ለራስህ ብዬ ነው … መጀመሪያ ከሰው ጋር የሚያኗኗር ፀባይ ይኑርህ … ሲቀጥል ሰው የሚነግርህን አዳምጥ። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ … እንቢ ካልክ…›› ብሎ ሳይጨርስ፣›› አሄሄሄ! ልፋ ቢልህ ነው ልጄ፡፡ ደግሞ ዘንድሮ ከሰው ጋር የሚያኗኑር ፀባይ ሊያስጨንቀን ቀርቶ መቼ ከራሳችን ጋር የሚያስታርቅ አመል ይወድልን ብለህ ነው?›› አለች ከጀርባው የተሰየመች ወይዘሮ። ከፋይ ሻርፕዋን በተደጋጋሚ ከትከሻዋ አውርዳ መልሳ አጣፍታ እየለበሰች በመልኩና በልዩነቱ ከተሳፋሪው ነጥሎ በፈጠረላት መስህብ የተመሰጠች ትመስላለች። ‹‹ምን እናድርግ ታዲያ? ልማቱንና ፈጣኑን የአኮኖሚ ዕድገት እስካልተገዳደረብን ድረስ ይኼ ይኼ አያሳስበንማ፤›› አላት አጠገቧ የተሰየመ ወጣት።

‹‹እኔ ምለው? ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገብን እንደሆነ ስንቶቻችን እናውቃለን፤›› ብሎ መሀል ረድፍ ላይ የተሰየመ ተሳፋሪ ጣልቃ ሲገባ፣ ‹‹ይቅርታ ጥያቄው ይስተካከል፤›› አለች ሦስተኛው ረድፍ ላይ ተብቃቅታ በምቾት የተንሰራፋች ዘመናይ። ‘ቀጥይ’ ሲላት ተሳፋሪው በዓይኑ፣ ‹‹ኢኮኖሚ ሲባል ትርጉሙንና ሥሌቱን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?›› አለች ጮክ ብላ። ‹‹አቦ ደህና ተገላገልን ስንል ሌላ ኮርስ ታስጀምሩናላችሁ እንዴ? አይደብራችሁም?›› አሉ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ሁለት ወጣቶች እየተቀባበሉ። ‹‹ምኑን ነው የተገላገላችሁት?›› አላቸው ጥጉን ይዞ መስኮት በመክፈትና በመዝጋት የታክሲያችንን የአየር ሁኔታ የሚቆጣጠር ጎልማሳ ተሳፋሪ። ‹‹የኢኮኖሚክስ ተማሪዎች ነን…›› ከማለቱ አንደኛው ያኛው ተቀብሎት ‹‹እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ…›› ብሎ ዘፈነ። መከራና ትምህርት መዝሙራቸው አንድ በሆነበት ጎዳና ሰው ከሰው ጋር ቀርቶ ከራሱም የሚያኗኑር አመል ቢያጣ ታዲያ ይገርማል? ማነው ማንን ማዳመጥ ያለበት? ዕዳ ከሜዳ አለ ሰውዬው!

ጉዟችን ቀጥሏል። በየመሀሉ ታክሲያችን ቆም ብላ ቦታ እያሸጋሸገች፣ እያጠጋጋች፣ እያራገፈች ደግሞ ትሄዳለች። ደግሞ ቆም፣ ደግሞ ሄድ። ‹‹መቼ ይሆን ይኼ ሄድ እያሉ የመቆም ዘመን የሚያከትመው?›› አለች ወይዘሮዋ በለሆሳስ። ‹‹ዘመነኛ እንጂ ዘመን ያከትማል እንዴ? ባይሆን ያልፋል፤›› አላት ወጣቱ። ወጣቱ ላይ ተደርቦ የተሰየመ አዲስ ተሳፋሪ፣ ‹‹ጥቅሱን አላያችሁትም መሰል?›› ብሎ ወደ ጣራው ጠቆመን። ‘አሠላለፉ ካልጣመህ ወርደህ ባቡር ያዝ’ ይላል። ወይዘሮዋ ፈገግ ብላ፣ ‹‹አንተ ነህ የጻፍከው?›› አለችው ወያላውን እያየች። አልመለሰላትም። ሾፌሩ በግንባር መስተዋቱ አሻግሮ የወያላውን ሁኔታ እያየ፣ ‹‹ደንበኛ ክቡር ነው አላልኩህም?›› አለው ተለሳልሶ። ‹‹ለአጫዋችነት አልተቀጠርኩም፤›› አለው ወያላው ኮስተር ብሎ።

ይኼም አለ ለካ አለ ዘፋኙ። ‹‹ኧረ እኛ አጫዋችም ተጫዋችም አልፈለግንም። ሜዳውን ካገኘን በቂ ነው፤›› ብሎ ወጣቱ ሲያሸሙር፣ ‹‹ሜዳውንስ በዬት በኩል አገኘነው? አታዩትም እንዴ ዙሪያውን አጥረውት ብሎ ጎልማሳው ተናገረ። ‹‹ታዲያ ለውጤትም ለጤናም ለሚጫወተው ሁሉ ሜዳው ከተከፈተማ ሣሩ አይሰነብትም፤›› ብላ ደግሞ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ዘበናያችን መልስ ሰጠች። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ የሕዝብ ነው አላሉም እንዴ?›› አሉ ከፊት ለፊት አዛውንቱ ዘወር ብለው እየቃኙን። ‹‹ምኑ?›› ሲላቸው መላው ተሳፋሪ በኅብረት ሜዳው?! አሉ። ‹‹ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በተኮነንን ጋሼ። እኛ እኮ በዘመናት አንዴ ዋንጫ ካነሳን በቂያችን ነበር፤›› ስትል ወይዘሮዋ፣ ‹‹እኮ እንደ ሌስተር ሲቲ?›› አለች የጋቢናዋ። ግን ዋንጫው ነው ሜዳው የሚቀድመው?

ወያላው ሒሳብ ተቀብሎ መልስ ይመልሳል። ‹‹አንተ በቃ ያ ልጅ እዚያው ገብቶ ቀረ?›› ይላል መጨረሻ ከተቀመጡት ጓደኛማቾች አንደኛው። ‹‹የት ይሆን የገባው?›› ብሎ አጠገቤ የተሰየመው ለወሬ ለቀማ ተመቻቸ። ‹‹ምን እባክህ ከአንዱም ሳይሆን ቀረ እኮ?›› አለው። ‹‹ቆይ ምንድነው የተፈጠረው? እኔ እኮ የሚነግረኝ ሰው አጣሁ። እኛ እንደሆንን አገር ስንለቅና ስንሞሸር ካልሆነ አናወራም፤›› አለ አጥብቆ የሦስተኛ ወዳጃቸውን ፍዳ ለመስማት የጓጓው። ‹‹ያው ያኔ እህቱ አልሞተችም? ደብረ ዘይት ሁለት ሱቆች ነበሯት። ተናዛለት ነው የሞተችው አሉ። አንድ ፍሬ ናት እኮ ብታያት፡፡ ምስኪን…። አላገባች አልወለደች። ፎቅ የላት ልጅ የላት። ሱቅ ብቻ። ኋላ እሱም በቃ አዲስ አበባ ያለውን ነገር ጣጥሎ እዚያው ገባ። ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ሱቆች ያሉበት ይዞታ ለልማት ስለታሰበ ፈራሽ ነው ብለው አፈረሱበታ። ግራ ገብቶታል ብታየው…›› አለው።

‹‹ምነው የእህቱን ቀን በሰጠው፤›› አለ ጨዋታውን የጀመረው ወጣት እያዘነ። ምነው አንተ፡፡ ምነው ምን አደረገህ? አለች ወይዘሮዋ ወደኋላ ዞራ። ‹‹ያዝ እንግዲህ…››› ይላል ከጎኔ የተቀመጠው አስተኳሽ። ‹‹እኔንማ ማን ይነካኛል መሬት የለኝ ንብረት የለኝ፤›› ሲል ጎልማሳው ቀበል ድአርጎ ‹‹አይዞህ ትንሽ ቀን ነው። ቦታና መሬት ለምቶ ሲያልቅ ሰው ፈርሶ መሠራት ይጀመርልሃል፤›› ሲለው መሠራቱን በለን እንጂ ከፈረስንማ ቆይተናል…›› ብሎ ተመራቂው ኢኮኖሚስት መለሰ። ይኼኔ ጋቢና ከአዛውንቱ ጋር የተሰየመችው ወጣት ‹‹ውይ ውይ ውይ…›› ብላ ጮኸች። ‹‹ምነው አይጥ አይታ ነው?›› ብሎ በወይዘሮዋና በተደራቢው መሀል የተሰየመው ወጣት ከመጠየቁ፣ ኧረ አይጥስ ጥርስ አለው። አሁን በአሁን ሃምሳ ብር ሞልቼ ሃምሳ ሳንቲም ቀረሽ የሚለኝ ቴሌ ነው የሚያስጮኸኝ እባክህ፤›› አለችው። ‹‹እም! ጥርስ የሌለው ሕፃን አትይም ታዲያ? ምን ቴሌ ትያለሽ…›› ባዩ መላው ተሳፋሪ ነው።

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጎልማሳው ተራውን ስልኩን ሲጎረጉር ቆየና ደውሎ ማውራት ጀመረ። ‹‹እሺ… እሺ… አዎ… አዎ…፤›› ሲል ቆይቶ፣ ‹‹ያው ዘመኑ አስገደደን እንጂ ቃታ ይዞ መጠባበቅ አልሰለቸንም ብለህ ነው?›› ሲል ተሳፋሪዎች ክው ብለው መተያየት ጀመሩ። አጠገቤ የተሰየመው ወጣት እየተቁነጠነጠ፣ ‹‹ማን ነው? ምንድነው? ወይኔ እናቴ ኮንዶሚኒየም ሳይደርሰኝ መንገድ ልቀር ይሆን?›› እያለ ተሸበረ። ሁሉም እርስ በእርሱ እየተንሾካሾከ ግን ማንም ደፍሮ ‘የምን ቃታ ነው?’ የሚለው ጠፋ። ጎልማሳው ስልኩን ዘግቶ የታክሲውን ድባብ ሲቃኝ ነገሩ ገባው መሰል አጠገቤ ለተሰየሙት ወጣቶች፣ ‹‹ይገርማችኋል አንድ ሌት ተቀን ደም ተፍቶ የሚሠራ ወዳጅ አለኝ። እና እያደር ኑሮው ሲሻሻል ሲበረታ እያዩ የገዛ ጓደኞቹ ቤቱ በር ላይ ጠብቀው አይመቱት መሰላችሁ?›› አለ። ይኼኔ ክፍተቱን ሲያገኝ ሁሉም ጥያቄ ይዞ ተንጋጋ።

‹‹በምን?›› ከማለቷ አንዷ ‹‹በጥይት›› ሲል ወይዘሮዋ ‹‹እግዚኦ›› አለች፡፡ ‹‹አልቋል እኮ ዘመኑ…›› እያለች ታዳምቃለች። ‹‹እና ሞተ?›› ትላለች ከሦስተኛው ረድፍ ልጅቱ። ‹‹ፊኛውን በጥይት በመመታቱ ይኼው ሆስፒታል ተኝቷል። አሁን እኮ የማወራው እንዴት በሕጋዊ መንገድ ራሱን የሚጠብቅበት መሣሪያ መያዝ እንደሚችል ኢንፎርሜሽን ለመጠየቅ ነው፤›› ሲል ገሚሱ በዕፎይታ ገሚሱ ግራ በመጋባት ተያየ። ‹‹እኔ ምለው ሕግ ባለበት አገር ራስን መጠበቂያ ብሎ ነገር ምንድነው?›› ሲል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ተወን አቦ። እኛ ሳንኖር ሕጉ ቢኖር ምን ዋጋ አለው?›› አለው። ‹‹እንዴት?›› ሲባል፣ ‹‹አንዱ በጉልበቱ፣ አንዱ በገንዘቡ፣ አንዱ በእምነቱ፣ አንዱ በፀባዩ፣ አንዱ በትህትናው እየታመነ ነው ችግር ያለው፡፡ ሕግ ባለበት አገር ከሜትር ከሃምሳ በላይ አጥር ገንብቶ፣ ግንቡ ላይ አደገኛ ውሻ አለ ብሎ ፅፎ ለጥፎ፣ ወይም የጠርሙስ ስባሪ ከስክሶ ሰክቶ በሚኖርበት አገር ሕግ ስም እንጂ ምን አተረፈ?›› ብሎ ደመደመው። ‹‹ታዲያ ከስም በላይ ለማትረፍ በጨዋታው ሕግ መሠረት መጫወት አይቻልም? አርባ ቢወለድ አርባ ነው ጉዱ…›› ብለው አዛውንቱ ቀድመው ወረዱ። ወይ ጉድ ከማለት ውጪ ምን ይባላል? ወዲያው ‘መጨረሻ’ ብሎ ወያላው ሸኘን። መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት