Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር በአፈር ምርምር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቀድሞው ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታነት ያገለገሉት ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ፣ የአፈር ለምነትን ለማከም ባበረከቱት ምርምርና ባስገኙት የላቀ አስተዋጽኦ እ.ኤ.አ. የ2016 ‹አይኤፍኤ ኖርማን ቦርላውግ አዋርድ› የተሰኘ ዓለም አቀፍ ሽልማት እንዳገኙ ተገለጸ፡፡

የሽልማት ድርጅቱ (ኢንተርናሽናል ፈርቲላይዘር ኢንዱስትሪ አሶሴሽን) ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ ፕሮፌሰር ተካልኝ የዓመቱን ክብር ሊያሸንፉ የቻሉት እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2014 ባሉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ የአፈር ለምነት መሳሳትን ማከም የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና የተፈጥሮ ሀብት መራቆትን መልሶ ማልማት በሚያስችሉ ውጤታማ ሥልቶችን በማበርከት፣ አሥራ አንድ ሚሊዮን አርሶ አደሮች ከድህነት መውጣት እንዲችሉ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ፕሮፌሰሩ በተለይም በመሬት መራቆት፣ በአፈር አሲዳማነትና በንጥረ ነገር እጥረትና መሰል ምክንያቶች በኢትዮጵያ ይከሰት የነበረውን የምርታማነት ማሽቆልቆልን በማሻሻል ለአገሪቱ ‹‹የግብርና ህዳሴ እጅግ የላቀ ሚና›› ተጫውተዋል ብሏል፡፡

በአፈር ምርምርና በማከም ረገድ ባለፉት 14 ዓመታት ባከናወኑዋቸው ተግባራት የአገሪቱ የጥራጥሬ ምርት በሦስት እጥፍ ማደግ የቻለ መሆኑን፣ ድህነትንና ረሃብ ለመቀነስ የተጣለው ግብ እንዲሳካ በማገዝ፣ አገሪቱ በዓለም እጅግ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ከቻሉት አገሮች ስሟ እንዲጠራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን፣ ይኸው የማዳበሪያ አምራች የሆነው የሽልማት ድርጅት ገልጿል፡፡

ምንም እንኳ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኤልኒኖ በተሰኘው የአየር መዛባት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ አገሪቱን እያስመዘገበችው ባለው የዕድገት ስኬት ላይ ተፅዕኖ ቢፈጠርም፣ አርሶ አደሮች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የአየር መዛባትን መቋቋም የሚያስችል ክህሎትና ሥልት ባለቤት እየሆኑ መምጣታቸውንም ድርጅቱ ጠቅሷል፡፡

‹‹ለዚህ ስኬት ዕውን መሆን መመስገንም ሆነ መደነቅ የሚገባቸው ፕሮፌሰር ተካልኝ በሚኒስትር ዴኤታነት ባገለገሉባቸው ዓመታት በግብርናና በተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ በልማት አጋሮችና በአርሶ አደሮች ለአሥርት ዓመታት በጋራ በተከናወኑት ማኅበረሰብ ተኮር የአፈር መልሶ ማልማት ሥራዎች፤›› ነው ሲል የሽልማት ድርጅቱ ባወጣው መገለጫ አስታውቋል፡፡

ተሸላሚው በበኩላቸው በተበረከተላቸው ሽልማት መደሰታቸውን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ የአፈርን ጤናማነት ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች በአፍሪካ ላበረከተችው የመሪነት ሚና ዕውቅና ያስገኘ ሽልማት በመሆኑ ‹‹ኩራት ይሰማኛል›› ማለታቸውን መግለጫው አስፍሯል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን የዕድገት ሽግግር ዕውን ለማድረግ ገና ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ገና ከድህነት ያልወጣ በርከት ያለ ሕዝብ አሁንም አለ፡፡ ይህ ሽልማት የአገሬ ዜጎችንም ሆነ የአፍሪካ ባልደረቦቼን የዚህን ድህነትን የመታገል ጉዞ በይበልጥ እንዲቀጥሉ ትልቅ የመነቃቃት ኃይልና ክብር እንደሚያበረክት እምነቴ ነው፤›› በማለት ፕሮፌሰር ተካልኝ መናገራቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ፕሮፌሰሩ እ.ኤ.አ. ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ በቆየው አገር አቀፍ የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ ማበልፀግና የአፈር ጥበቃ ሥራ ከ15 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የተራቆተ መሬትን እንደገና በማልማት ምርታማነትን እንዲያረጋግጥ ማድረግ መቻላቸው ይነገራል፡፡ በተይም ፕሮፌሰር ተካልኝ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የቀድሞ ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ አዲሱ ለገሰ አማካሪ ሆነው በሠሩበት ወቅት፣ በራሳቸው ሐሳብ አፍላቂነት በመላው አገሪቱ አፈርን መልሶ የማበልፀግ ሥራዎች ማከናወን የቻሉ መሆናቸው፣ በዋነኝነት አሲዳማነትን የላይም (ኖራ) ቴክኖሎጂ በመጠቀም መቀነስ ማስቻላቸውና በአብዛኛው አርሶ አደሮችም ተቀባይነት ማግኘታቸው ይወሳል፡፡

በተጨማሪም በአገሪቱ የአፈር ለምነትን ማጥናት፣ ማወቅና ቆጠራ ማከናወን የሚያስችል የኢትዮጵያ የአፈር መረጃ የተባለ ቴክኖሎጂን ማፍለቅና ማስተዋወቅ መቻላቸው ይነገራል፡፡ ይህ የእሳቸው አስተዋጽኦ ያለበት የቴክኖሎጂ ውጤት ደግሞ በአፍሪካ የአፈር ሀብት ካርታ ለማጥናት የሚያስችልና የላቀ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑም ጭምር ይነገርለታል፡፡

ፕሮፌሰር ተካልኝ በአፈር ኬሚስትሪና አፈር ለምነት ስኮትላንድ ከሚገኘው አበርዲን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፣ በርከት ላሉ ዓመታት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በአመራር የሥራ ዘርፎች አገልግለዋል፡፡ በሥራዎቻቸው የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን፣ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. ‹አፍሪካን ግሪን ሪቮሊዩሽን አዋርድ› ሌላኛው የማዳበሪያ አምራች ከሆነው ያራ አዋርድ፣ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) “Special Global Ambassadorship Role for 2015 International Year of Soils” የተባሉ ሽልማቶች በዋነኘነት ይጠቀሳሉ፡፡

‹አይኤፍኤ ኖርማል ቦርላውግ አዋርድ› በየዓመቱ ከተለያዩ አገሮች በግብርና ዘርፍ፣ በተለይም በሰብልና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች የላቀ የምርምር ውጤት ያበረከቱ ተመራማሪ ግለሰቦችን ዕውቅና የሚሰጥ ሽልማት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ የሽልማት ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ1970 ረሃብን በማጥፋት ባበረከቱት ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ለነበሩት አሜሪካዊው ዶ/ር ኖርማን ቦርላውግ መታሰቢያነት የተቋቋመ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች