- እነ ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁ በእስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጠ
ከተከሰሱበት የሽብር ተግባር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በነፃ ቢያሰናብታቸውም፣ ችሎት በመድፈር ወንጀል ተወስኖባቸው የነበረውን የ14 ወራት ለማጠናቀቅ ላለፉት ስምንት ወራት በእስር የቆዩት የሰማያዊና የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራሮች ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ከእስር ተለቀቁ፡፡
የቀድሞ አንድነት አመራር የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራትን በእስር አሳልፈው ከእስር የተለቀቁት፣ ዓቃቤ ሕግ የሥር ፍርድ ቤቶችን ‹‹መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ›› ውሳኔን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ያስቀርባል ሲባል የታገደ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብለው እንዲለቀቁ በተሰጠ ብይን ነው፡፡
በውጭ ሆነው በዓቃቤ ሕግ ይግባኝ አቤቱታ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እያየው የሚገኘውን ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ሀብታሙ አያሌውን ጨምሮ፣ ‹‹የሥር ፍርድ ቤት በነፃ አሰናብቶን መብታችን ተገድቦ በእስር እንድንቆይ መደረጉ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው፤›› በማለት ለሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱና ሰበር ችሎቱ፣ ‹‹በሌላ ወንጀል ካልተቀጡ ይለቀቁ፤›› በማለቱ አቶ ሀብታሙ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ዳንኤልና አቶ የሺዋስም ችሎት በመድፈር ወንጀል የተወሰነባቸውን የ14 ወራት እስራት ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው በሰበር ችሎቱ ብይን መሠረት ተፈትተዋል፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎቹ በሥር ፍርድ ቤት (ከፍተኛው ፍርድ ቤት) በአግባቡ ሳይመዘኑ በመቅረታቸው፣ ተከሳሾቹ በነፃ መሰናበታቸው አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ ለይግባኝ ሰሚው ችሎት አቅርቧል፡፡ በተለይ የመንግሥት ተቋም ከሆነው ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት አገልግሎት የተገኘ ማስረጃ እንደታለፈበት በመግለጽ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ለብይን ተቀጥሯል፡፡
ከእነ ዳንኤልና የሺዋስ ጋር በተጣለባቸው የችሎት መድፈር ወንጀል ቅጣት በእስር ላይ የሚገኙት የአረና ትግራይ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ ሁለት ወራት ስለሚቀራቸው (16 ወራት ስለተፈረደባቸው) በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በተመሠረተባቸው ክስ ሲከራከሩ ከርመው ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁ፣ አቶ ሰለሞን ግርማና አቶ ተስፋዬ ተፈሪ ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ውሳኔ አቶ ዘለዓለም በአምስት ዓመታት ከአራት ወራት ጽኑ እስራት፣ አቶ ሰለሞን ግርማ በሦስት ዓመታት ከሰባት ወራት ጽኑ እስራትና አቶ ተስፋዬ ተፈሪ በሦስት ዓመታት ከ11 ወራት ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡