የወሳኝ ኩነቶች (የሞት፣ የልደት፣ የጋብቻና የፍቺ) ምዝገባን በመላ አገሪቱ በመጪው ሐምሌ ወር ለመጀመር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ቢሆንም፣ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንትን ማግኘትም ሆነ በክልሉ የምዝገባ ዝግጅቶችን ለማከናወን ፈቃድ ባለመስጠታቸው፣ ምዝገባውን በክልሉ በሐምሌ ወር ለመጀመር እንደተቸገረ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የምዝገባ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንና የየክልሎቹ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አደረጃጀቶችና የሥራ ኃላፊዎች የተመደቡ ቢሆንም፣ በሶማሊ ክልል ግን ምዝገባውን ለመጀመር ቀርቶ ዝግጅት ለማድረግ አለመቻሉንና ያለ ክልሉ ፕሬዚዳንት ዕውቅናና ፈቃድ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የማይቻል መሆኑን ለፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የገለጸው ኤጀንሲው፣ የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ ቋሚ ኮሚቴው ጣልቃ ገብቶ እንዲያግዘው ጠይቋል፡፡ ኤጀንሲው ይህንን የገለጸው ባለፈው ዓርብ ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡ በሶማሊ ክልል ምዝገባውን ለመጀመር ፕሬዚዳንቱ አልተገኙም ተብሎ የቀረበው ምክንያት ግራ ያጋባቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሶማሊ ክልል ችግር ያለበት አካባቢ ቢሆንም፣ ምዝገባውን በወቅቱ ለማስጀመር የክልሉ ፕሬዚዳንትን ማግኘት አልተቻለም ተብሎ የቀረበው ምክንያት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንን አስመልክቶ አንድ የኮሚቴው አባል፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ዓመቱን ሙሉ አይገኙም የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሮች ያሉበት አካባቢ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ ክልሉን መርዳት እንጂ ፕሬዚዳንቱ አይገኙም የሚል ምላሽ በቂ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባል ላቀረቡት ትችት አዘል ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኤጀንሲው ቦርድ አባልና የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋለም ይህደጐ፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ጭራሽ አይገኙም ሳይሆን አጋጣሚ ሆኖ የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር በክልሉ ተገኝተው ሊያገኟቸው አልቻሉም ለማለት ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ርዕሰ መስተዳድሩ ችግር የለባቸውም፤›› ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገንባቶ ከሶማሊ ክልል ጋር በተገናኘ እውነቱን መነጋገር እንደሚጠቅም ጠቁመው፣ በክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን በሐምሌ ወር መጀመር ይቻላል ብሎ የማይቻለውን ለቋሚ ኮሚቴው መናገር እንደሚከብድ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኔ ራሴ በክልሉ በአካል ተገኝቼ የምዝገባ መዋቅር ሠርቼ ነው የተመለስኩት፡፡ ነገር ግን ይህንን መዋቅር ተግባራዊ ለማድረግ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ዘንድ ለመግባት ግን እንደዚህ እንደምታስቡት ቀላል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ አጋር ከሆነው ከክልሉ ፓርቲ ሊቀመንበር ጋር በመሆን ፕሬዚዳንቱን ለማግኘትና መዋቅሩን ለማፀደቅ ቢጥሩም፣ ፕሬዚዳንቱን ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ያልወሰኑበትን ማንኛውም ጉዳይ ሶማሊ ክልል ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ለክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥራ አስኪያጅ ለመቅጠር የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ወረቀት አቅርቦላቸው እስካሁን አልተፈረመበትም፤›› ብለዋል፡፡ ሥራ አስኪያጅ ሳይቀጠር የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መዋቅርን እስከ ታችኛው የክልሉ አደረጀጀት ድረስ መተግበር የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን ለፍትሕ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን የገለጹት አቶ ታምሩ፣ ሚኒስቴሩም በሶማሊ ክልል የገጠመውን ችግር ለመፍታት ቁርጠኝነቱን በማሳወቅ፣ ከዚህ በኋላ ነገሮች ሊስተካከሉ ይችላል የሚል ዕምነታቸውን ገልጸው ቋሚ ኮሚቴውም በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ገና በተሠራው መዋቅር ላይ ተነጋግሮ ማፅደቅ፣ መዋቅሩን መዘርጋት፣ የሠራተኞች ቅጥርና ሥልጠና እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ስለምዝገባው ማስገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ምዝገባውን ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች እኩል በሐምሌ ወር መጀመር እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ የቀረበውን ችግር ፍትሕ ሚኒስቴር በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩልም ሆነ በሌላ መንገድ መፍታት ሲችል፣ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ድረስ መምጣቱ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ተችተዋል፡፡ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን በሐምሌ ወር በመላ አገሪቱ ለማስጀመር 368 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 101 ሚሊዮን ብር ለሰነዶች ኅትመት ወጪ ተደርጓል፡፡ ምዝገባው በመላ አገሪቱ እንዲጀመር ቢደረግም የምዝገባው ተደራሽነት በአንድ ጊዜ መቶ በመቶ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ሥራው እጅግ ውስብስብ በመሆኑ፣ ምዝገባውን 30 በመቶ ተደራሽ ለማድረግ ኤጀንሲው ማቀዱን አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ ወሳኝ ኩነቶች የሚባሉትን ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺን የማስመዝገብ ኃላፊነት የኩነቱ ባለቤት ግለሰብ ላይ የወደቀ መሆኑን ያለማስመዝገብ የሚያስቀጣ እንደሆነ በአዋጁ ላይ መቀመጡን አቶ ታምሩ አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ግንዛቤ የመፍጠር በተለይም በአገሪቱ ገጠሮችና ኋላቀር አካባቢዎች የማኅበረሰቡን ባህል ሰብሮ መግባት አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሞተ ሰው እስከ ስድስት ወራት እንደማይቀበር፣ የሟች ቤተሰቦችም ከአስከሬን ጋር ስድስት ወራት የሚኖሩት ሞቱን ካለመቀበል ባህላዊ ልማድ በመሆኑ፣ እንዲህና መሰል ልማድ ባለባቸው አካባቢዎች ሥራው ውስብስብ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ምዝገባውን በአጭር ጊዜ መቶ በመቶ ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻልና ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡