Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ የተጠረጠሩ በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

በአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ የተጠረጠሩ በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

ቀን:

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ስድስት የአዲስ አበባና አራት የአማራ ክልል ነዋሪዎች የሽብር ተግባር ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥረው ተከሰሱ፡፡

በሽብር ድርጅት ውስጥ በድረ ገጽና በፌስቡክ ገጻቸው በመሳተፍ የተጠረጠሩት ትንሳዔ በሪሶ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ግሩም አስናቀው፣ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ፍሬው ተክሌና ኤርሚያስ ፀጋዬ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡ አሰጋ አሰፋ ከምሥራቅ ጎጃም፣ ጌታቸው ይርጋና ኃይሌ ማሞ ከሰሜን ጎንደር ሲሆኑ፣ ሽቴ ሙሉ ከምዕራብ ጎጃም መሆናቸውን የከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ ከድርጅቱ አመራሮች የሚሰጣቸውን ዓላማ ለመፈጸም ጽዮን ሆቴል በመገናኘት መመካከራቸውን፣ ጎንደር ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ጥቃት ፈጽመው ገንዘብ ለመዝረፍ ባደረጉት ምክክር የባንኩ ጥበቃ የተጠናከረ መሆኑን ሲያውቁ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርጉት በመመካከር መተዋቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ የነዳጅ ማደያ ላይ ጥቃት በመፈጸም በመንግሥት ላይ ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ በማድረስ ከአገር ለመውጣት የተወሰኑት ተከሳሾች መረጃ በመለዋወጥ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ በተንቀሳቃሽ ስልክ፣ በድረ ገጽና በፌስቡክ ገጻቸው በተለይ ከሽብር ቡድኑ አመራር ከሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ ጋር ግንኙነት በማድረግ፣ ኢሳት ቻናልን፣ ኤልኤንቢ እና የመሳሰሉ ቻናሎች እንዲጠቀሙ በማድረግ፣ ሌሎች በመንግሥት ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡ ‹‹አለ ነገር ሸገር ላይ አለ ነገር፣ የሚታይ እንጂ የማይነገር፤ ቀድሞ ነበር እንጂ ወጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፤›› የሚሉ ቀስቃሽና ለአመፅ የሚያነሳሱ መፈክሮችን በማስተጋባት ሌሎችም ወደ ሽብር ድርጅት እንዲገቡ ሲቀሰቅሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም አካባቢ በሚገኘው አርዲ ካፌ ውስጥ በመገናኘት፣ ‹‹ወደ ኤርትራ በመሄድ አርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅትን መቀላቀል አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያዋጣው ሰላማዊ ትግል ሳይሆን የትጥቅ ትግል ነው፤›› በማለት ከድርጅቱ አመራር ዶ/ር ታደሰ ብሩ ጋር በስልክ በመገናኘት፣ እንዴት እንደሚጓዙ መመርያ መቀበል እንዳለባቸው ሲመካከሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀን) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ሥር የተደነገገውን መተላለፋቸውን የገለጸው ዓቃቤ ሕግ፣ በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ በማናቸውም ሁኔታ መሳተፍ የወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱ ለተከሳሾቹ ከደረሳቸው በኋላ፣ አቅም ለሌላቸው የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመድብላቸው ትዕዛዝ በመስጠት፣ ክሱን ለመስማት ለግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...