Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

77 ቢሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሰው ስኳር ኮርፖሬሽን የገጠመው ፈተና

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለስኳር ኮርፖሬሽን መውደቅ ሜቴክ ትልቅ ድርሻ አለው››

‹‹የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ አመራሮች መጠየቅ አለባቸው›› የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች

በ2003 ዓ.ም. በተካሄደው የመጀመርያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት አንደኛው ነው፡፡ አገሪቱ ለስኳር ልማት ያላትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አሥር ግዙፍና አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት በዓመት 4.07 ሚሊዮን በላይ ስኳር በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ዕቅድ በጣም የተለጠጠ መሆኑ በስተመጨረሻ ሲታወቅ፣ ሰባት ፋብሪካዎችን በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠናቀቅ ተብሎ እንዲከለስ ተደርጓል፡፡

እነዚህ አዳዲስና ግዙፍ ፕሮጀክቶች በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገነቡት ኩራዝ አንድ፣ ኩራዝ ሁለት፣ ኩራዝ ሦስት፣ በለስ አንድ፣ በለስ ሁለት፣ ከሰም፣ ወልቃይት፣ አርጆ፣ ደዴሳና ተንዳሆ ናቸው፡፡

መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጠናቆ ስኳር ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ዕዳ መክፈል እንደሚችል በማሳመን ለስኳር ፋብሪካዎቹ መገንቢያ ከተለያዩ አበዳሪዎች ሁለት ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል፡፡ ከአገር ውስጥ ባንኮችም ከፍተኛ ብድር አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የስኳር ልማቱን የሚመራው የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር በላይ እያንቀሳቀሰ የሚገኝ ቢሆንም፣ አንድም ፋብሪካ እስካሁን ተጠናቆ ወደ ሥራ አልገባም፡፡ በሌሎች አገሮች አንድ ስኳር ፋብሪካን ለማጠናቀቅ ግፋ ቢል አንድ ዓመት የሚፈጅ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ግን አንድ ዓመት ከስድስት ወራት (18 ወራት) አንድ ስኳር  ፋብሪካን ለማጠናቀቅ አቅዶ የውል ስምምነቶችን ቢያደርግም፣ አንድ ፋብሪካ ሥራ ሳይጀምር ስድስተኛ ዓመት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በ2008 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለማቅረብ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ተገኝተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ከተሾሙ የወራት ዕድሜን ያስቆጠሩት አቶ እንዳወቅ አብቴና ሌሎች ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች ያቀረቡት ሪፖርት ‹‹ተስፋ በመቁረጥና እያመመን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከሰባት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ስኳር ማምረት ቢጀምርም ጥራቱ የተጓደለ የእንፋሎት አቅርቦት፣ የፋብሪካውን ፊልተር በቆሻሻ በመዝጋቱና በተርባይን ላይ ጉዳት በማድረሱ እንዲቆም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ጥገና ከተደረገ በኋላ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ለፋብሪካውና ለመስኖ የሚሆን የውኃ አቅርቦት ችግር ወደ ምርት እንዳይገባ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡

የተንዳሆ ቁጥር ሁለት ፋብሪካ ግንባታም ገና 27 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ኩራዝ አንድ የተባለው ፋብሪካ ኮንትራት ውል የተገባው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ የውል ማሻሻያ ሰኔ 2004 ዓ.ም. ላይ እንደተደረገ አቶ እንዳወቅ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ግንባታውን የሚያከናውነው አገር በቀሉ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ፕሮጀክቱን በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም. አጠናቆ ማስረከብ ይጠበቅበት ነበር፡፡

ፕሮጀክቱ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ላይ የደረሰበት ደረጃ 83 በመቶ ሲሆን፣ ሜቴክ ግን 97 በመቶ ክፍያ እንደተፈጸመለት አቶ እንዳወቅ ተናግረዋል፡፡ ኩራዝ ሁለት የተባለውን ፋብሪካ ለማስገንበት ውል የተፈረመው እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር 2014 ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 58 በመቶ መድረሱን ይጠቅሳሉ፡፡ በውሉ መሠረት በመጪው ሐምሌ ወር ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም መዘግየቱን አስታውቀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ጊዜ እንዲራዘምለት ጠይቆ እስከ መጪው ኅዳር ወር እንዲያጠናቅቅ መመርያ እንደተሰጠው አብራርተዋል፡፡

ኩራዝ ሦስት ግንባታው የተጀመረው እ.ኤ.አ. በፌብሯሪ 2015 ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 25 በመቶ ደርሷል፡፡ ይህም ቢሆን መሆን ከነበረበት ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካን ለማስጀመር ከቻይና ኩባንያ ጋር ውል የተፈጸመ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ለመግባት ኩባንያው ዝግጅት ላይ መሆኑን አቶ እንዳወቅ ይገልጻሉ፡፡ በለስ አንድ ስኳር ፕሮጀክት ወደ ሥራ የገባው በየካቲት 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. የውል ማሻሻያ መደረጉንና በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም. ኮንትራክተሩ ሜቴክ አጠናቆ ማስረከብ የነበረበት ቢሆንም፣ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት ገና 60 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ኮንትራክተሩ ግን 94 በመቶ የሚሆነውን ክፍያ መቀበሉን ገልጸዋል፡፡

በለስ ሦስት ፋብሪካን ለመገንባት ውል የተፈጸመው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ መጠናቀቅ የሚገባው በ2005 መጋቢት ላይ እንደነበረ ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ገና 23 በመቶ ሲሆን፣ ኮንትራክተሩ ሜቴክ ግን 94 በመቶ ክፍያ እንደተከፈለው ያስረዳሉ፡፡

የከሰም ስኳር ፋብሪካ አፈጻጸም 96 በመቶ መድረሱን ነገር ግን ገና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንዳልገባ አክለዋል፡፡ ወልቃይት ስኳር ፋብሪካም ግንባታው እንዳልተጀመረና በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን ገንብቶና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ ዕዳውን የመክፈል ኃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም፣ ኤክስፖርት ማድረግ ይቅርና የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ግንባታዎቹን ለማከናወን 77 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር የተበደረ በመሆኑ፣ አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ባልገባበት በአሁኑ ወቅት 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመክፈል ኃላፊነት ከፊቱ ተጋርጧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ይገዙና የኮሚቴው አባላት የኮርፖሬሽኑ ችግር ምን እንደሆነ፣ ሥራው ባልተሠራበት ሁኔታ ከ90 በመቶ በላይ ገንዘብ ለምን እንደተከፈለ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንትና ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ በሰጡት አስተያየት፣ የአሥሩም አዳዲስ ፋብሪካዎች ኮንትራት የተሰጠው ለአገር በቀሉ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) መሆኑን አስታውሰው፣ ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን መገንባት እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህ ቢሆንም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አመራሮች ከሜቴክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በቢዝነስ ኮንትራት ሕግ የማይመራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹አሥሩም ፋብሪካዎች በዚህ ኮንትራክተር እንዲሠሩ ነበር የተወሰነው፡፡ በኋላ ላይ የመፈጸም አቅሙ እየታየ ፕሮጀክቶቹ እየተነጠቁ አሁን እጁ ላይ ሦስት ፋብሪካዎች ናቸው የቀሩት፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ኮንትራክተር (ሜቴክ) ተነጥቀው ፋይናንስ ተገኝቶላቸው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ከሰም ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ እስከ ኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ይደርሳሉ ብለዋል፡፡ በሜቴክ እጅ የሚገኙት ግን መቼ እንደሚጠናቀቁ እንኳን ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና ከድርጅቱ ጋር ልቅ የሆነው ግንኙነት በውል ያልታሰረ በመሆኑ ዕርምጃ እንኳን ለመውሰድ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ሜቴክ በእጁ የሚገኙትን ሦስት ፋብሪካዎች በተለይም ኩራዝ አንድ ፋብሪካን በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ገልጾ፣ በልዩ ሁኔታ ስኳር ኮርፖሬሽን የአገር ውስጥ ብድር እንዲያገኝ ተደርጎ ሊከፈለው መቻሉን አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ ይህ ፋብሪካ እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡ እኛ ግን ዕዳ የመክፈል አደጋ ከፊታችን ተጋርጧል፤›› ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ባለመድረሳቸው ምክንያት አጠቃላይ የስኳር ኮርፖሬሽን ወጪ እየናረ መሆኑን የሚገልጹት የሥራ ኃላፊው፣ የሸንኮራ አገዳው ቢደርስም አገዳውን ከማስወገድ ሌላ አማራጭ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኩራዝ ላይ 870 ሔክታር አገዳ ለማስወገድ ተቃርበናል፡፡ 300 ሺሕ ሔክታር የሸንኮራ አገዳ በለስ ላይ አስወግደናል፡፡ ይህንን ለማስወገድ በሔክታር 50 ሺሕ ብር እያወጣን ነው፤›› በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህ ኮንትራክተር ላይ እንደ ማንኛውም ኩባንያ ቅጣት መጣል እንደማንችል ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ የሚያስጠይቅ ነገር ካለ ባለቤቱ ተለይቶ መጠየቅ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው የኮርፖሬሽኑ አመራርም የሜቴክ ችግር በመገንባት ላይ ባሉት ፋብሪካዎች ላይ ብቻ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በማምረት ላይ ለሚገኙ ፋብሪካዎች መለዋወጫ የሚያቀርበው ሜቴክ መሆኑን በመጥቀስ፣ መለዋወጫ ባለማቅረቡ ምክንያት ፋብሪካዎች ለበርካታ ቀናት ምርት እንደማያመርቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹የማይችሉትን ሁሉ እንችላለን እያሉ አገርን ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ነባሮቹ ፋብሪካዎች ያለ ችግር ቢሠሩ ቢያንስ በውጭ ምንዛሪ ስኳር አናስገባም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ መለዋወጫ ከሜቴክ የመግዛት ግዴታ ለአገሪቱ አዋጭ አለመሆኑን፣ ምክንያቱ ደግሞ ሜቴክ ራሱ ከውጭ ከሚገባው በላይ እየሸጠ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ሮለር ከውጭ ስንገዛ ከ200 ሺሕ ብር አይበልጥም፡፡ ሜቴክ ግን 600 ሺሕ ብር ነው የሚሸጥልን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንቢ ብለን እንኳን እንዳንታገል አመራሮች ያሸማቅቁናል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ከሌሎች አካላት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለብቻ በሌላ መድረክ እንደሚያይ አስታውቆ አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በኮርፖሬሽኑ ውስጥ መኖሩን በመጥቀስ ፋብሪካዎች ኦዲት እንዲደረጉ አዟል፡፡

    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች