ይሄ እንደቀይ ምንጣፍ ጎዳናው ላይ የተበተነው ቀይ ፅጌረዳ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከደቂቃ በፊት የኮካ ኮላ ሳጥን የጫነ ባለ ተሳቢ ተሽከርካሪ ኮልፌ አበራ ሆቴል አካባቢ ተገልብጦ የመንገዱን አጥር ከመሰባበር አልፎ ጠርሙሶቹን በታትኖና ከጥቅም ውጪ አድርጓቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ እዚሁ ቦታ ከ15 ቀናት በፊት ባለ ተሳቢ ተሽከርካሪ ተገልብጦ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በፌስቡክ ገጹ ላይ በግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ካሰፈረው
********
ፊደል ሲሸሽ
ሆሄ ብዙ ቃላት …
ለማጠር አስበው
አደባባይ ወጡ …
ፊደል አንጠባጥበው፡፡
‘ፍ’ን ተወና ፍቅር …
ታየ ሰው ብሎት ‘ቅር’፤
‘ጋ’ ን ትቶ ለጋሱ …
ሆኖ ቀረ ‘ለሱ’፤
‘ብ’ ን ወርውሮ ንብረት …
ሸሸ ጥሎ ‘ንረት’፤
ዝ‘ ን ክዶ ዝነጣ …
ባዶ ቀርቶ ‘ነጣ’፤
‘ው’ ን ጥሎ መውደዴ …
ሆነብኝ ‘መደዴ’፡፡
- ዶ/ር ኤልያስ ሳሙኤል ‹‹ከርከሬሻ›› (2008)
********
በበረዶ ገና ጨዋታ ላይ የወደቁት ፑቲን ዋንጫ አነሱ
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድርሚር ፑቲን ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባላቸው ፍቅር ይታወቃሉ፡፡ ፈረስ ግልቢያ፣ ዋናና አይስ ሆኪ ወይም የበረዶ ገና ጨዋታ ከሚያዘወትሯቸው ስፖርቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ፕሬዚዳንቱ የሳይቤሪያን በረዷማ ውኃ በዋና ማቋረጣቸው የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ነጋዴዎችን የያዘ የአይስ ሆኪ ቡድን ይዘው ወደ ውድድር አምርተዋል፡፡ በበረዶው ላይ ወዲያ ወዲህ በመንሸራተት ለተጋጣሚ ቡድኑ ችሎታቸውን እያሳዩ በነበረበት ወቅት ግን ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ፕሬዚዳንቱ ሲጫወቱ በረዶው አንሸራቷቸው ወድቀዋል፡፡ በሩሲያ፣ ሶቺ በተካሄደው አይስ ሆኪ ላይ ቀይ በሰማያዊ ማልያ ለብሰው ቡድናቸውን ይመሩ የነበሩት ፑቲን፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ቢወድቁም፣ ጨዋታውን ከማጠናቀቅ አላገዳቸውም፡፡ ጨዋታውንም በድል ፈጽመዋል፡፡ የቀድሞው የሶቭየት ኅብረት አይስ ሆኪ ተጨዋች አሌክሳንደር ያኩሼፍም ዋንጫ አበርክቶላቸዋል፡፡
*******
በታይላንድ በተራቀቀ የኩረጃ ቴክኖሎጂ የታጀበው ፈተና ተሰረዘ
በታይላንድ ሦስት ተማሪዎች የሕክምና ትምህርት መግቢያ ፈተና ላይ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው መኮራረጃቸውን ተከትሎ ፈተናው ሙሉ ለሙሉ ተሰረዘ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ተማሪዎቹ የተጠቀሙት በእጅ ሰዓታቸው ላይ የተገጠመና በስለላ ወቅት አካባቢን መቃኘት የሚችል የተራቀቀ መሣሪያ ነው፡፡
ሰዓታቸው ላይ የተገጠመው ቴክኖሎጂ ‹‹ሚሽን ኢምፖሲብል›› በተሰኘውና እ.ኤ.አ. በ1996 በተለቀቀው የስለላ ፊልም ላይ ይታይ የነበረ ዓይነት ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የታይላንዱ ቻናል ሦስት እንደሚለው፣ የተማሪዎቹ ማንነት ለጊዜው ባይገለጽም፣ በጥቁር መዝገብ ውስጥ ሰፍረዋል፡፡
ሦስቱ ተማሪዎች ገመድ አልባ ካሜራ ከእጅ ሰዓታቸው ላይ በመግጠም፣ የፈተናውን ጥያቄና መልስ ፎቶ በማንሳትና ቁጥራቸው በግልጽ ላልታወቁ ተማሪዎች በማስተላለፍ ነው ኩረጃውን በተራቀቀ ዘዴ የመሩት፡፡
የራንግሲት ዩኒቨርሲቲ አስተዳዳሪ እንደሚሉት፣ በሚያዝያ 29 እና 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው የሕክምና ትምህርት መግቢያ ፈተና ተሰርዞ ግንቦት 2008 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
********
ጥቁሩ አሜሪካዊ ማርቲን በነጭ ፖሊስ የተገደለበት መሣሪያ ለጨረታ ቀረበ
የፍሎሪዳ ነዋሪ የሆነው የ17 ዓመቱ ትራይቮን ማርቲን እ.ኤ.አ. በ2012 ጆርጅ ዚመርማን በተባለው ፖሊስ የተገደለበት ሽጉጥ ለጨረታ ቀረበ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ መሣሪያውን ለጨረታ ያቀረበው፣ ማርቲንን ራስን በመከላከል ምክንያት ተኩሶ የገደለው ዚመርማን የተባለው ፖሊስ ነው፡፡
ዚመርማን መሣሪያውን ለጨረታ ያቀረበበት ምክንያትም፣ በ2016 ማብቂያ አሜሪካ ለምታካሂደው ምርጫ ዕጩ የሆኑት ሒላሪ ክሊንተን ያቀረቡትን ‹‹መሣሪያዎች ላይ ገደብ የመጣል ዕቅድ›› ለማክሸፍ ነው፡፡
ክሊንተን፣ በአሜሪካ የጦር መሣሪያ ያለገደብ ለግለሰቦች መሸጡን፣ ንፁኃንም በግለሰቦች የጦር መሣሪያ እየተገደሉ መሆናቸውን በመቃወም፣ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቢያሸንፉ፣ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ላይ ገደብ እንደሚጥሉ አሳውቀው ነበር፡፡
ወጣቱና ጥቁሩ ማርቲን በነጩ ፖሊስ ዚመርማን በመሣሪያ መገደሉ በፍሎሪዳ ብጥብጥ አስነስቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጉዳዩም የዘር ሆኖ ነበር፡፡ ዚመርማን መሣሪያ ያልታጠቀውን ማርቲን ተኩሶ ቢገድልም፣ ‹‹ራሱን ለመከላከል ነው›› በሚል በነፃ መለቀቁም ይታወሳል፡፡