Sunday, May 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የዴሞክራሲ ሥርዓት ወሳኝ ማዘዣ ጣቢያዎች ላይ ማሻሻያ ሳይደረግ መልካም አስተዳደር ማስፈን አይቻልም

በመንግሥቱ መስፍን

መልካም አስተዳደርን የማስፈንና ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን›› የማስወገድ ጥረት በተለይ በመንግሥትና በኢሕአዴግ ደጃፍ ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ የሥርዓቱ ትልልቅ ሰዎች እየመጣ ያለው አደጋ ከሕዝብ የሚያጣላ ብቻ ሳይሆን ህልውናንም የሚፈታተን ‹‹ናዳ›› ነው ብለው ካወጁ በኋላ፣ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የስብሰባ አጀንዳ፣ የአደባባይ መነጋገሪያና የየጎዳናውም ሹክሹክታ ሆኗል፡፡ እንዲያውም ከቅርብ ወራት ወዲህ የድርቅና የጎርፍ አደጋዎች ትንሽ አጠሉበት መሰለኝ፡፡

አጀንዳው መነጋገሪያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙዎቹ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ከሥራ ታግደዋል፣ ከሹመት ወርደዋል፣ አንዳንዶቹም ተከሰው ታስረዋል፡፡ በችግሩ ውስጥ የነበሩና የሰጉ እየተሰደዱ እንደሆነም እየተሰማ ነው፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት በኩል የአሠራር ክፍተቶችን በመለየት የማጣራት ዕርምጃና ፈጥኖ የማስተካከያ ሥራ ለመሥራት እየተደረገ ያለ ጥረት አለ፡፡ አንደኛው በአዲስ አበባ የጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ ላይ የተሠራው ሥራ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በሕገወጥ መንገድ መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ማንና እንዴት አስተላለፈው? በሕገወጥ መንገድ አንድ ሰው ሁለትና ከዚያ በላይ የሕዝብ ቤት እንዴት ሊወስድ ቻለ? የሚሉት እያነጋገሩ ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ በጥቃቅንና በአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማቶች ላይም ቆጠራው ቀጥሏል፡፡

ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ጋር በተያያዘም በርካታ የመንግሥት ሕንፃዎችንና መንገዶችን ሲሠሩ የነበሩ ከ60 በላይ ‹‹ተቋራጮች›› ፈቃድ በፎርጅድ የወጣ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ዕውን ይኼ በመሳሳት ነው ወይስ አብሮ ሌብነት ውስጥ በመዳከር የተከሰተ ብሎ መመርመር ያሻል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ እንደ ሱሉልታ ባሉት ከተሞች እስካሁን ማንም ትንፍሽ ሳይል ያውም ሕዝቡ ‹‹ኧረ መሬት ተዘረፈ›› እያለ ከንቲባውን ጨምሮ 14 ባለሙያዎችና አመራሮች ሰባት ሺሕ መሬት ባልታወቀ ምክንያት ሌላ ወገን አስተላልፈዋል (ሸጠዋል) ተብለው ተከሰዋል፡፡ እንግዲህ በዚህ ውስጥ ስንቱ በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ ተሳተፊ የማለውን ፈጣሪ ካልሆነ ሰው የሚደርስባት አይመስልም፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን እስካሁን እየወጡ ያሉ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት ጥሰቶችን፣ እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነትን ማጋለጥ አይደለም፡፡ ይልቁንም አሁን በተጀመረው መንገድ ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም የሚል ክርክር ለመሰንዘር ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን ያለ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማሰብም የእምቧይ ካብ ከመደርደርና ውድቀትን ከማፍጠን ውጪ መላ እንደሌለው መከራከሪያዎችን በመጥቀስ ለውይይት በር መክፈትን እሻለሁ፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ምሁራን ዴሞክራሲን በተመለከተ የሚስማሙበት የጋራ ብያኔ አለ፡፡ ቫኑዋነን ቲ. የተባሉ ጸሐፊ፣  ‹‹ዴሞክራሲ በጊዜ የተወሰነ፣ መሪዎችን ለመለወጥ የሚያስችል ሕጋዊ ዕድል የሚሰጥ የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በወሳኝ ውሳኔዎች አሰጣጥ ላይ በቂ ተፅዕኖ ለማድረግ እንዲችል የሚያደርግ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት ሥርዓት የተላበሰ መንግሥታዊ አስተዳደርን የሚያሰፍን፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ያረጋገጠ፤›› ሲሉ በጥቅል ያስቀምጡታል፡፡

እንግዲህ ሕዝብ በሚፈራቸው ባለሥልጣናት ከመከመተዳደር ወጥቶ ‹‹ሕዝብ በሚፈሩ›› በየደረጃው ያሉ መሪዎች እንዲኖሩት ነው ዴሞክራሲ የሚያዘው፡፡ ይህ ሲሆን ነው የአብርሃም ሊንከን ‹‹የሕዝብ መንግሥት በሕዝብ ለሕዝብ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ዕውን ሆነ የሚባለው፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በተለይ ካለፉት ሥርዓቶች የጭቆና ዘመናት አንፃር በጎ ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ከግል መብት ይልቅ ለቡድን መብቶች ማድላቱ፣ የነፃ ፕሬስ፣ ነፃ ማኅበራትና ነፃ ተቋማትን በገደብ ውስጥ ማድረጉ፣ ገዢው ፓርቲ የጠቅላይነትና የአውራነት ባህሪ በመላበሱ፣ የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅሮች መቀላቀላቸው፣ ብሎም በፖለቲካ ተነፃፃሪነት ፈርጅ የሚሠለፉ ኃይሎችንም በቂ ምኅዳር የሚነፍግ አካሄድን መከተሉ ዋና ዋናዎቹ ድክመቶች መሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህንን ኢሕአዴግን የሚተቹ ሁሉ ከውስጥም ከውጭም የሚያነሱት ነው፡፡

ታዲያ ይኼ የመልካም አስተዳደር መስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመታገልም ሆነ የሕግ የበላይነት በተጨባጭ ከማረጋገጥ ጋር በምን ይገናኛል የሚል አይኖርም፡፡ ካለም አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ይበልጥ ለውይይት በር ይከፈታል፡፡

ምርጫ ነፃና ነፃ ብቻ መሆን አለበት

      በእኛ አገር ወቅቱን የጠበቀ፣ ከፍተኛ ሕዝብ የሚሳተፍበትና ተደራሽነትን የተላበሰ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ የምርጫ ቦርድ መዋቅርና የሚመደብለት በጀትም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በቀዳሚነት የቦርዱና የአስፈጻሚዎች ገለልተኝነት፣ በሁለተኛ ደረጃም የተወዳደሪዎች አለመመጣጠን መኖሩ ይታወቃል፡፡ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት ሀብት፣ የሰው ኃይልና መዋቅርን ጭምር ሲጠቀም ተቃዋሚዎች ግን በአብዛኛው ተበታትነውና ከከተማም ብዙም ሳይወጡ መወዳደራቸውም ይታወቃል፡፡

ይህ አካሄድ የመንግሥትን የተጠያቂነት አካሄድ የማይገድብ ከመሆኑም ባሻገር፣ ፍትሐዊነትንም ያጓድላል፡፡ በመሆኑም በጥብቅ ድርጅታዊ ሚስጥርና ትስስር ገዢው ፓርቲ እንዲያሸንፉ የሠሩ አስፈጻሚዎች፣ ካድሪዎችና ባለሥልጣናትን በተጠያቂነትና በግልጽነት ባህል ለመገንባት አያስችልም፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ህልሞች›› (2008) መጽሐፍ ላይ ‹በምርጫ ወቅት አጭበርብሮ ያሸነፈን ተወዳዳሪ፣ መሬትና የሕዝብ ሀብት ሲያጭበረብር እንዴት ተው ልትለው ትችላለህ?› ማለታቸውን ልብ ይሏል፡፡

ምርጫ ነፃ ይሁን የሚለው ሌላኛው መከራከሪያ ደግሞ ሕዝቡ በሙሉ ፈቃዱና ሳያወላዳ ለመምረጥ ዕድል ስለሚሰጥ ነው፡፡ በዚያው ልክ አይበጀኝም ብሎ ያመነበትንም በድምፁ አለመቀበሉን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ስለሆነም በሕጋዊ መንገድ ተመርጦ ሊያሳይ ይችላል፡፡ ስለሆነም አገር ለመምራት የተዘጋጀ ፓርቲም ይሁን አስፈጻሚው አካል ተጠያቂነትን በተላበሰ መንገድ እንዲሠራ ይገደዳል፡፡ በብዙዎቹ የሠለጠኑ አገሮች እንደምናየው ለሚፈጠር ስህተትና ሕዝባዊ ጥቅምን የሚጎዳ ተግባር ሁሉ ኃላፊነት እየወሰዱ ሥልጣን እስከመልቀቅ የሚደርሱ ሰዎች የሚኖሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ነፃ ምርጫ በተቻለም መጠን በብዙኃኑ ሕዝብ በታመነበትና በገለልተኛ ታዛቢዎች በተመሰከረለት ሁኔታ ሲካሄድ ሌላ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ይኼውም በየደረጃው ባሉ የሕዝብ ምክር ቤቶች የፖሊሲም ሆነ የስትራቴጂ አማራጭ ያላቸው ተቃዋሚዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎች የመቀላቀል ዕድል ያገኛሉ፡፡ ስለሆነም የመንግሥትን አፈጻጸምና ውሳኔ በመተቸት ለመስተካከልና ለማረም የሚችልበት መንገድ ይፈጥራሉ፡፡ ሕዝቡም የዴሞክራሲ ባህልን እየገነባ እንዲሄድ ዕድል መክፈት ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር በምርጫ ወቅት ተነስቶ የሚያስኮርፍና የሚያቃቅር ሒደትን አርሞ ዜጎች በነፃነት ያመኑበትን እንዲመርጡ ነፃ ምርጫን ማስቀደም ይገባል፣ ያስፈልጋል፡፡

ነፃ ፕሬስ ያብብ

የፕሬስ ቅድመ ምርመራም ሆነ ሐሳብን ከመግለጽ መታቀብን የቀበረ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በተለይ በአንቀጽ 29 የዜጎች የማሰብ፣ የመናገርና የመጻፍ መብት ከመረጋገጡም ባሻገር ዜጎችም የትኛውንም መረጃ በግልጽነትና ለተጠያቂነት አግባብ የማግኘት መብታቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህን የሚያግዝ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅም 590/2000 ፀድቆ በሥራ ላይ ውሏል፡፡

እነዚህ ከዓለም አቀፍ የመስኩ ሕግጋት የተቀዱ መርሆዎች በአገሪቱ ሰማይ ሥር ያሉ ቢሆኑም፣ አተገባበር ላይ ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ በአንድ በኩል እንደ ፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ያሉ ተደራቢ አዋጆች ዜጎች በጻፉትና ባራመዱት ሐሳብ ለመወንጀል የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሐሳብ ነፃነትን መሠረት አድርገው በሚንሸራሸሩ የፕሬስ ውጤቶች የሙያውን ሥነ ምግባርና መርሆዎች የሚጥሱ ድርጊቶች ተባብሰው መፈጸም ጀመሩ፡፡ የሚዛናዊነት፣ የገለልተኘነት፣ የማኅበራዊና የአገራዊ ኃላፊነት፣ ብሔራዊ ጥቅምን የማክበር እሳቤዎች በተለይ በአንዳንድ የኅትመት ውጤቶች ተሸራረፉ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ፕሬሱ የፖለቲካ መሣሪያ ወደ መሆንም ወረደ፡፡

እንደ ለጋ ዴሞክራሲ እነዚህን እንከኖች እያረሙ ነፃ ፕሬስ እንዲያብብ ከማድረግ ይልቅ፣ በመንግሥትም ሆነ በመስኩ ሙያተኞች የተከናወኑ ሥራዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ መንግሥት በራሱ ጥላ ሥር ያሉ ሚዲያዎችን በማበረታታት፣ ኮሙዩኒኬሽን (የመንግሥት ቃል አቀባይን) እና ሚዲያዎች ሚና በመቀላቀል ‹‹ልማታዊ›› ወደተባለ አስተሳሰብ ሲነጉድ፣ በነፃ ፕሬስ ጎራ ውስጥ የነበረው አብዛኛው ሙያተኛና የሚዲያ ተቋም ተበታትኗል፡፡ ተሰዷል፡፡ አለፍ ሲልም ታስሯል፡፡ የጋዜጠኛ ማኅበራቱም ተሸመድምዳው በስም ብቻ ቀርተዋል፡፡

ይህ በመሆኑ ያለጥርጥር ጠያቂ ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር ገድቧል፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል ግንባታውን አጓድሏል፡፡ በምርመራ ዘገባ፣ በመልካም አስተዳደር ጥሰትና ሙስናን በማጋለጥ ላይ ሊያተኩሩ የሚገባቸው ፕሬሶች ተዳክመዋል፡፡ ያሉት የግል የፕሬስ ውጤቶችም ያለጥርጥር በተሟላ ድፍርት ውስጥ አይደሉም፡፡ የሕዝብ የሚባለው መገናኛ ብዙኃንም ስኬት ተናጋሪና ድክመትን እየመረጠና እየቆነጠረ የሚሠራ ብቻ ሆኗል፡፡

ከዚህ አንፃር በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የተፈለገው የመልካም አስተዳደር የመስፈን ጉዳይ ፕሬስ ሊጫወተው የሚገባው ሚና ቀጭጯል፡፡ የሕዝብ ሀብት ቀማኞች፣ ፀረ ዴሞክራቶችና ከሕግ በላይ ነን የሚሉ የሕግ ሚዛን ሰባሪዎች እንዳይጋለጡ ሆኗል፡፡ የአሠራር ክፍተትም እየተጋለጠና እየተተቸ ንፋስና ፀሐይ እንዲመታው አልተደረገም፡፡ ይህ ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲ ምሰሶዎችን ጠብቆ መቀጠል ግድ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ገዢው ፓርቲና መንግሥት መለያየት አለባቸው

በዴሞክራሲ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሱ በሚባሉት የምዕራቡ ዓለም አገሮችም ሆነ በአንዳንድ እመርታ ባሳዩ የአፍሪካና የእስያ አገሮች፣ የፓርቲና የመንግሥት መዋቅር የተለያዩ ናቸው፡፡ የመንግሥት መዋቅር በተቻለ መጠን ከፖለቲካ ጫና ነፃ ሆኖ ፖሊሲ እንዲያስፈጽም፣ ሕዝብን በፍትሐዊነትና በቅልጥፍና የሚያገለግል እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ማንም ሄደ ማን መጣ የሕዝብና የአገርን ጥቅም አስቀድሞ በተቀመጠው ሕግ መሠረት ሥራውን ማከናወን ነው ሚናው፡፡ የሚተዳደርበት በጀትም የመንግሥት ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ገዢም ይሁኑ ተቃዋሚዎች መንግሥት ለመሆን በእኩል (ቢያንስ ፍትሐዊ በሆነ አግባብ) የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ የገንዘብ ምንጫቸውም አባላት፣ ደጋፊዎቻቸውና አጋር አካላት እንደሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በምንም መንገድ የመንግሥትን ሀብት፣ የሰው ኃይል፣ አሠራር፣ ወዘተ ፓርቲ ተግባር መጠቀም አይቻልም፡፡

በእኛ አገር ሁኔታ ቀደም ባለው ጊዜ የተሻለ ነገር ቢኖርም በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ ከላይ እስከ ታች ባሉ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የፓርቲ ክንፍና አባላት አሉ፡፡ በመንግሥት ሥራ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሚሆኑት የገዢው ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ የሌላ ተፎካካሪ አባልና ደጋፊ ሆኖ ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ በይፋ መቀጠል ግን በፍፁም የማይቻል ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ወቅት ደግሞ ገዢው ፓርቲ መንግሥታዊ መዋቅሩን የመጠቀም ሰፊ ዕድል አለው፡፡ ሰውነት መልካሙ የተባሉ ጥናት አቅራቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዓመታት በፊት ‹‹ምርጫ ከማንና ከምን?›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት አንድ ጥናት፣ ‹‹የነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መሠረታዊ መለኪያ የተለያየ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ያለ ምንም ፍርሐት እኩል ዕድል ተሰጥቷቸው መደራጀት፣ ሕዝብ መቅረብና ማስረዳት መቻላቸው ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን የምርጫው ዋና ተዋናይ የሆነው ኢሕአዴግ የአገራቱን ገንዘብ፣ መገናኛ ብዙኃንና የፀጥታ ኃይል እንደፈለገው ያዝበታል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ አካሄድ ደግሞ ገዢው ፓርቲና በውስጡ ያሉ ሰዎችን ለመጠየቅ፣ ከችግራችሁ ታረሙ ለማለት የሚቻልበትን ዕድል ይዘጋል፡፡ ተገዳዳሪነት ይዳከማል፡፡ ገዢው ፓርቲ ምንም ያህል በውስጥ ለውጥ ለማምጣት ቢሠራም በተገደበ ወስን ታጥሮ እንጂ፣ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት አልቻለም፡፡ አሁን በተጨባጭ ሁኔታ የሙስናና የኪራይ ሰብሰባነት ትግሉ ሥር የሰደደ አለመሆኑና ወደ ላይኛው አካል ያለማተኮር ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡

ስለሆነም ያለበቂ ተወዳዳሪነት የተፈጠረን አውራነትና ጠቅላይነት ከገዢው ፓርቲ ላይ ቀንሶ ብርቱ ተገዳዳሪዎችን በዴሞክራሲ ምኅዳር ውስጥ መፍጠር ካልተቻለ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውም ሆነ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ቀላል አይሆንምና ይታሰብበት፡፡

የሦስቱ የመንግሥት አንጓዎች ሚና ይለይ

አንዳንድ መንግሥትን የሚተቹ ተቃዋሚዎች ‹‹ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ›› ሲሉ ትርጉሙ ግልጽ ነው፡፡ በማንኛውም ፖለቲካ አቋም ወይም ጉዳይ ላይ አስፈጻሚው አካል ከከሰሰ የዳኝነት አካሉ የሚፈርደውም ከከሳሹ ወገን በመቆም ነው ለማለት ነው፡፡ ለዚህም በሕግ ጥብቅ መረጃና ማስረጃ ባልቀረበባቸው ክሶች ለዓመታት በወህኒ ቆይተውና ፍርድ ቤት ተመላልሰው በመጨረሻ ‹‹በነፃ ተለቀዋል›› የሚባሉ ኢትዮጵያውያንን ሁኔታ ያነሳሉ፡፡

ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ የተባሉት የመንግሥት አንጓዎች የተለያየ ተግባርና ኃላፊነት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን፣ አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት እንደሚገነባ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና በገቢር ይህ ጉዳይ ተጠናክሮ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ መገለጫውም በሕዝብ ምክር ቤቶች፣ በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች፣ በፍትሕና በዳኝነት ሥርዓቱ የገዢው ፓርቲ አባላትና ተሿሚዎች በመኖራቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይህም ቢሆን በንጉሡ፣ በደርግ ጊዜም ሆነ አሁንም ልዩነት አልታየበትም፡፡ ይልቁንም የፓርቲው ክንፍ የ1ለ5 ጥርነፋና የህዋስ አስኳል እያንዳንዷን ጉዳይ አስተሳስሮ በመቀጠሉ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

ይህ በመሆኑም በሙስና የሚከሰስም ሆነ ከኃላፊነት የሚነሳ ተሿሚ ከሕግ ይልቅ የፓርቲውን ውሳኔ መጠበቅ አለበት፡፡ ያለጥርጥርም አንዱ የመንግሥት ክንፍ ሌላውን ለመጠየቅና ለመቆጣጠር አሠራሩን የሚከተል ሳይሆን የፓርቲውን ውሳኔ ያዳምጣል፡፡ ለዚህም ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚውን ሲከታተል ‹‹ይህን አድርግ›› ይል እንደሆነ እንጂ፣ ለዕርምጃና ለውሳኔ የሚያመች ቆፍጣና አቅጣጫ የማያስቀምጠው፡፡ ምክር ቤቱ ባቀረበው በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ የተሻረም ሆነ የተጠየቀ የሥራ ኃላፊ አለመኖሩም አንድ ማሳያ ነው፡፡ ምክር ቤቱም ሆነ ቋሚ ኮሚቴዎች ‹‹ጥርስ የሌላቸው አንበሶች›› ከመባል የመውጣት ምልክት ቢያሳዩም የሚቀረው ሥራ በእጅጉ የበዛ ነው፡፡

በተለይ በክልሎች ደግሞ ራሱ ሕግ አውጪው አካል ከአስፈጻሚው በታች የሚታዘዝ ነው፡፡ አዲስ አበባን እንመልከት፡፡ የከተማው ምክር ቤትም ሆነ አፈ ጉባዔው እንኳንስ ከንቲባውን ጠርቶ ማብራሪያ ሊጠይቅና የቁጥጥር ሥርዓት ሊያደርግ ይቅርና ከአንድ ጽሕፍት ቤት ኃላፊ የዘለለ ሥልጣን የለውም፡፡ የምክር ቤት ስብሰባን በመምራት ብቻም ሕገ መንግሥታዊ ሚናን መውጣት አይቻልም፡፡ ይህ እውነት ደቡብ፣ ኦሮሚያና አማራ ወይም ትግራይ ክልሎች ቢኼድ ያው አንድ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር እውነተኛ መልካም አስተዳደር የማስፈን ጥረት ይጀመር ከተባለ፣ ሦስቱ የመንግሥት ክንፎች ሚና መለያየትና የተጠያቂነት ሥራ መጀመር አለበት፡፡ ምክር ቤቶች ያላቸውን የሥልጣን የበላይነት በገቢር ሊያሳዩ ግድ ይላል፡፡ ካልሆነ ግን አሁንም አስፈጻሚው አካል የፈለገውን እየፈጸመ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ሙስናም እንደሚታሰበው በቀላሉ ሊገታ አይችልም፡፡

በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ወሳኝ ማዘዣ ጣቢያዎች ላይ ማሻሻያ ሳይደረግ የተዋጣለት መልካም አስተዳደር ማስፈን አይቻልም፡፡ የግልጽነት፣ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነትንም ለማረጋገጥ ያዳግታል ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ያለው ወይም ተጨማሪ አቋም የሚያራምድ ቢጽፍ መልካም ይመስለኛል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles