Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአዲስ አበባና ሞስኮ ምንና ምን ናቸው?

አዲስ አበባና ሞስኮ ምንና ምን ናቸው?

ቀን:

መሰንበቻውን በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓ-እስያ ከተከናወኑት ዐበይት ሁነቶች መካከል፣ ኢትዮጵያ ከ75 ዓመታት በፊት በፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት ላይ የተቀዳጀችውን ድል፣ እንዲሁም ሩሲያ የናዚ ጀርመን ሠራዊትን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ድል የመታችበትን 71ኛ ዓመት ማክበራቸው ይጠቀሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ያከበረችው አልማዛዊ የድል ኢዮቤልዩ መንሥኤ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በመስከረም 1928 ዓ.ም. በወልወል በኩል የጀመረችው ወረራ አጠናክራ ለአምስት ዓመታት አገሪቱ በወረራ ከያዘችበት በኢትዮጵያውያን ተጋድሎና እርመኛነት በድል የተጠናቀቀበት መሆኑ ነበር፡፡ የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት (1923-1967) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደትና በዲፕሎማሲያዊ ትግል ከቆዩበት የእንግሊዟ ባዝ ከተማ በሱዳን በኩል በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሜድላ ላይ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበለቡበት ከወራት ቆይታ በኋላም ከአርበኞች ጋር የዘለቁበትና በዕለተ ቀኑ ሚያዝያ 27 አዲስ አበባ የደረሱበት ነበር፡፡

የፋሺስቶች ወረራና ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያን መያዛቸው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው በአውሮፓ ውስጥ ነው ከሚለው አተያይ በተቃራኒው፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በተፈጸመው ወረራ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሩን የሚሞግቱ ምሁራን (ዶ/ር ንጉሤ አየለ፣ ዶ/ር ዓለሜ እሸቴ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት) አሉ፡፡ እንዲያውም የአፍሪካ ቀንድ ለአሠርት (1928 እስከ 1933 ዓ.ም.) የዘለቀ የጦርነት ጎራ ሆኖ መዝለቁም ታውቆለታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አፍሪካዊ አውሮፓዊን ድል ለማድረግ የቻለበት ከዓድዋው ድል ቀጥሎ ሁለተኛው የድል ቀን ሚያዝያ 27 መሆኑ በአፍሪካውያንም ሆነ በሌላው ዓለም እንደሚታወቅ ይወሳል፡፡

ከግማሽ ምእት ዓመት በፊት፣ የኅትመት ብርሃን ባየ አንድ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የታሪክ ድርሳን ላይ እንደተመለከተው፣ በነገሥታቱ መሪነት ኢትዮጵያን የድል አክሊል እንደተቀዳጀች እንድትኖር ያደረጓት ሕይወታቸውን ስለ ሠዉላትና የማትናድ ሕንፃና የማትፈርስ ግንብ አድርገው ስለ ገነቧት ነው፡፡

‹‹ትንሣኤና ሕይወት ሚያዝያ ፳፯ት›› የተሰኘው የ1956 ዓ.ም. ድርሳን እንደሚያወሳው፡- የታሪክ ሥፍራዎችና ሜዳዎች፣ የነፃነት ቀኖችና ወሮች ከነዘመናቸው የማይረሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዓድዋና የካቲት ሐያ ሦስት ቀን በመቼውም ዘመን በማናቸውም ወርና ቀን ቢሆን ሲታወሱ ትዝ የሚለው፣ በ1888 ዓ.ም. ከኢጣሊያኖች ጋር ተደርጎ በነበረው ጦርነት የተገኘው ድልና በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ ጮራውን የፈነጠቀው የኢትዮጵያ የመታወቅ ዝና ነው፡፡ ድሉም ሲታሰብ አብረው ከሚታሰቡት ከንጉሠ ነገሥቱ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ ከሠራዊት እስከ መኳንንት የነበሩት የጦር ጀግኖች ናቸው፡፡

‹‹ለአፄ ምኒልክና ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ካሉዋቸው የድል ቀኖች ዋናዎቹ የካቲት 23 ቀን (1888 ዓ.ም.) እና ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ናቸው፡፡ ከዚህም አስቀድሞ ለነበሩት ለአፄ ቴዎድሮስና ለአፄ ዮሐንስ የድል ቀኖችና ሜዳዎች ነበሯቸው፤ እነ ጉንደት፣ እነጉራዕ፣ እነ ሰሐጢና እነዶግዓሊ የየራሳቸው የድል ቀኖች አሏቸው፡፡

ከሰባ አምስት ዓመት በፊት የተገኘው የሚያዝያ 27ቱ ድል ለመላው ለአፍሪካ አህጉር ነፃ አወጣጥ መንገድ ጠራጊ መሆኑንም ያመሠጥራሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በሰጠችው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከቅኝ ግዛቶቿ የአፍሪካ አገሮች የተመለሱት አፍሪካውያን ወታደሮች ኅሊና ውስጥ ‹‹እኛም ነፃ መውጣት አለብን!›› የሚለው መነሣሣት የታየው በሚያዝያው ድልና  ስኬት መሆኑም ተመልክቷል፡፡

እንደ ታሪካዊው ድርሳን አዘጋገብ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም. ከሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በፋሺስት ኢጣሊያ የተያዘችበት) እስከ 1933 ሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በድል የተያዘችበት) ድረስ የጠላት ኰቴ በመስኮቿ ላይ ቢዘዋወርም ገዢነቱን አላወቀችለትም፡፡ ጫካው ሁሉ የጃርት ወስፌ ስለሆነበትና ሜዳውም ቢሆን አቃቅማ ብቻ ሆኖ ስላስቸገረው ምን ያህል ጭንቀት እንዳደረበት አምስት ዓመት ያልሞላው የሥቃዩ ዘመን ምስክር ነው፡፡››

ሰባ አምስተኛው የአልማዝ ኢዮቤልዩ እንዴት ተከበረ?

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1934 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የድሉ በዓል ይከበር የነበረው ሚያዝያ 27 ቀን ሲሆን፣ ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ በዓሉን ወደ ‹‹መጋቢት 28›› ለውጦት ከወደቀም በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በወጣ በአምስተኛ ዓመቱ በነባር አርበኞቹና በኅብረተሰቡ ጥያቄ፣ በታሪክ ምሁራንም አረጋጋጭነት በዓሉ በ1988 ዓ.ም. ወደ መሠረታዊ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን ተመልሶ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን በያዘበት ሚያዝያ 27 ቀን (1928 ዓ.ም.) በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያን የድል ቀን ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ተበሰረ፡፡ 75ኛ ዓመቱንም ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ተዘከረ፡፡

ኢትዮጵያ ከ75 ዓመት በፊት ፋሺስት ኢጣሊያ ድል የመታችበት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት  ተከብሯል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የክብር እንግዳ በሆኑበት ክብረ በዓል ላይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት፣ ጥቂት ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና ወታደራዊ አታሼዎቻቸው ከነሙሉ ክብራቸው ተገኝተዋል፡፡

በዓሉ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር ቢጠበቅም፣ ከአዘቦቱ የተለየው የባህልና የታሪክ ሲምፖዚየሞች መካሄዳቸው ብቻ ነበር ልዩው ነገር፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ዝግጅቱን ለውጭ ተቋም ሰጥቶ ያሳተመው ‹‹እኔ ለአገሬ  ፲፱፻፳፰ – ፲፱፻፴፫›› መጽሔት፣ የአልማዝ ኢዮቤልዩን በሚመጥንና ብዙነት ባለው መልኩ ለመቅረብ አልታደለም፡፡

ታሪካዊ ነገሮችን ከማድመቅ የማይቦዝነው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ያሳተማቸውና ለሕዝብ የሚሠራጩ የመታሰቢያ ቴምብሮች በቅርቡ እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡

አራት ኪሎ በሚገኘው ሚያዝያ 27 አደባባይ በተከበረውና በአገሪቱ ርእሰ ብሔር ጉንጉን አበባ በድል ሐውልት ሥር ሲቀመጥ ለክብረ በዓሉ የተገኘው የከተማው ነዋሪ ከአንድ ሺሕ በታች ነበረ (በአንዳንዶች ግምት ከ600 እስከ 800 ይሆናል)፡፡

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር ኃይል ጥንስስ የሆነው የቅድመ ፋሺስት ወረራ ዘመን የአገሪቱ ጦር፣ ለአሁኑ የመከላከያ ኃይል መሠረት ቢሆንም እንደሁሌው በየበዓሉ ያልተገኙት የምድርና የአየር ኃይል፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላትና አዛዦች ዘንድሮ የአልማዝ ኢዮቤልዩውን አስታከው በሰልፍ ትርዒት ጭምር ያደምቁታል ተብሎ ቢጠበቅም አልሆነም፡፡ ከተማሪ እስካውትና ከአባትና እናት አርበኞች ሰልፈኞች በስተቀር የታየ አልነበረም፡፡ ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ማርሽ ባንዶች በቀርም፡፡

‹‹ሚያዝያ 27 ቀን አደባባይ››፣ በዋዜማው (ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም.) ስምንት ሰዓትም አልፎ አካባቢው የበዓል ድባብ አልነበረውም፡፡ ከስድስት ኪሎ (የካቲት 12 ሰማዕታት ሐውልት) እስከ ታላቁ ቤተ መንግሥት (ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት) ፊት በር ድረስ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በግራና በቀኝ ማድረጉ ቀርቶ በአራት ኪሎ ሚያዝያ 27 አደባባይ ዙሪያ አንዳችም ምልክት አልነበረበትም፡፡

ታሪካዊ ውርሱን አመላካቹ ኢዮቤልዩ ለማክበር፣ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን አጅበው የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማና የቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአሁኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሐሙዳ አህመድ ገአስ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ተለያዩ የአፍሪካና ሌሎች አገሮች ሚሊተሪ አታሼዎች በከፍተኛ ወታደራዊ መኰንን ልብስ ያሸበረቁ የኢትዮጵያ ከፍተኛ መኰንኖችም ፈጽሞ አልታዩም፡፡ የመከላከያ እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮችም አልተከሰቱም፡፡

‹‹ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ!››

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረችው በጀግኖች ልጆቿ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአምስቱ የመከራ ዘመን (1928 እስከ 1933 ዓ.ም.) በአርበኝነት፣ በውስጥ አርበኝነት፣ በስደተኝነት፣ ባላገሩም ጭምር የአገሪቱን የነፃነት ቀንዲል ለመለኮስ ሲንቀሳቀሱ ኖረዋል፡፡

በዓሉ ብሔራዊ በዓል ሆኖ በዝግ የሚከበር ቢሆንም፣ ስለ በዓሉ ምንነትና ታሪክ ያለው ዕውቀት ጥላ እያጠላበት መሆኑ ይታያል፡፡ ‹‹ሐሙስ በዓል ነው፤ የድል በዓል ሥራ የለም፤›› የተባለ የአንድ መሥሪያ ቤት ባልደረባ፣ ‹‹የምን በዓል? መሥሪያ ቤት ይዘጋል እንዴ? ባለፈው የካቲት 23 አክብረን የለም እንዴ?›› ማለቱ እንዴት ነው ነገሩ ያሰኛል፡፡ ‹‹የሠራተኞች ቀን ነው?›› ብሎ የጠየቀም አለ፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ  ነዋሪዎች – የድል በዓልን፣ እንደ ርሱ አጠራር ‹‹የአርበኞች በዓልን›› ምን ያህል ያውቁታል? ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡ በድረ ገጹ ካሰፈረው ውስጥ አርሶ አደርና ዓይነ ሥውር ተማሪን ጨምሮ የሁለት ተማሪዎች ምላሽ ይገኝበታል፡፡ እንዲህ አሉት ለአብመድ፡-

አርሶ አደሩ አቶ ቁሜ ሙጨ

‹‹በባሕር ዳር ዙሪያ ላት-አምባ ቀበሌ ነው የምኖረው፡፡ የአባት አርበኞች ቀን ሲባል እሰማለሁ፤ የት እንደዘመቱ፣ ማንን እንዳሸነፉ፣ ለምን ጉዳይ እንደሚከበር ግን አላውቅም፡፡ በቀበሌያችን በሚደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ እገኛለሁ፡፡ የተለያዩ በዓላት የኤድስ ቀን፣ የሴቶች ቀን፣ የግንቦት 20 በዓል ሲከበር የበዓላቱ አስፈላጊነት ትምህርት ይሰጠናል፡፡ የአባት አርበኞች ቀን ግን የሚከበርበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ተማሪ ልጆችም አሉኝ፤ በተለይ ትልቁ ልጄ አምስተኛ ክፍል ነው፤ እሱም ነግሮኝ አያውቅም፡፡ ራዲዮም አደምጣለሁ፤ ስለዚህ በዓል ታሪክ ግን በደንብ አልሰማሁም፡፡››

አሥረ ክፍል ተማሪው አስፋው ደረጀ

‹‹እኔ የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ስለሆንኩና በታሪክ ትምህርታችንም የተካተተ ስለሆነ፣ በየዓመቱ የሚከበረውን ሚያዝያ 27 ቀን ዘንድሮ በመጠኑ አውቄዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት በዓሉ መከበሩን እንጅ ምክንያቱን አላውቀውም ነበር፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በየዓመቱ በዓሉ ሲከበር ለምን እንደሚከበር በቂ ትምህርት ስለማይሰጠን ይመስለኛል፡፡ እኔ ዓይነ ስውር በመሆኔ የምከታተለው ሚዲያ ራዲዮ ነው፤ በራዲዮም በዓሉ ተከበረ ከሚል ዘገባና የባለሥልጣናት ንግግር ውጭ፣ የበዓሉን ሙሉ ታሪክ መስማቴን አላስታውስም፡፡ ሌላው ለእንደኔ ዓይነት ዓይነ ስውራን ታሪኩን በሚገባ ላለማወቃችን አንዱ ምክንያት፣ የታሪክ መጻሕፍት በብሬል አለመዘጋጀታቸው ነው፡፡ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶች በሚገባ በብሬል ተዘጋጅተው ቀርበውልናል፤ ታሪክ ግን የለም፡፡››

ዘጠነ ክፍል ተማሪ ፍሬሕይወት ዓለሙ

‹‹የአርበኞች በዓል በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን እንደሚከበርና ጀግኖች አርበኞች ጠላትን ያሸነፉበት ቀን መሆኑን እሰማለሁ፡፡ መቼ፣ የት፣ ማንን አሸነፉ የሚለውን ግን በደንብ አላውቀውም፡፡ አሥረኛ ክፍል የታሪክ መጽሐፍ ላይ ሙሉ ታሪኩ እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ግን አላነበብኩትም፡፡ ብቻ ትልልቅ ሰዎች የድሮ የጦር ሜዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ ወደ አደባባይ ሲወጡ አልፎ አልፎ በሚዲያ አያለሁ፡፡ ከዚያ ያለፈ ዕውቀት የለኝም፤ ወላጆቼም ስለዚህ በዓል የነገሩኝ ቁም ነገር ስለመኖሩ አላስታውስም፡፡››

ቀደምቱ እርመኛ አርበኞች ‹‹በሰሜን ቢመጡብን በሰሜን ሄድንባቸው፤ በደቡብም ቢዘምቱብን በዚሁ ክፍል ዘምተንባቸዋል፡፡ ወደ ማህል አገርም ገብተው ቢያጠቁን በየሸለቆዎቻችን ሁነን አጥቅተናቸዋል፡፡ የእኛ ደም በእነሱ ጥይት ብቻ ፈስሶ አልቀረም፡፡ የነሱም ደም በእኛ ጥይት ፈስሷል፤›› ያሉት እንዴት ይረሳል? እልፍ አዕላፋት የተሰዉለት የአርበኝነት ታሪክስ እንዴት ይረሳል? ለዛሬ ማንነት መነሻው የቀደምቱ አሻራ መሆኑ ላፍታም ቸል መባል የለበትም ያሉት አንድ አባት አርበኛ፣ ተረትና ምሳሌውን ‹‹ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅን›› አንርሳው ብለዋል፡፡

ታዋቂዋ አሜሪካዊት ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ሜሪ ፒፈር፣ ‹‹ታሪክህን ካላወቅህ፣ የራስህን ቤተሰብ ካላወቅህ አንተ ማነህ?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የጁራሲክ ፓርክ ፊልም ደራሲው ሚሸል ክርሽቶንም ‹‹ታሪክህን ካላወቅህ፣ ምንም ነገር አታውቅም፡፡ አንተ የግንዱ አካል መሆንህን የማታውቅ ቅጠል ነህና፤›› ያለውም ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡  

የድል ቀን በሞስኮ

ሩሲያ ከሰባ አንድ ዓመት በፊት፣ የሶቪየት ኅብረት ቀይ ጦር በአዶልፍ ሒትለር የሚመራው ናዚ ጀርመንን ድል የመታበትን ቀን፣ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሞስኮ ቀይ አደባባይ በታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ አክብራዋለች፡፡ ሩሲያና የቀድሞዎቹ የሶቪየት ሪፐብሊኮች ‹‹ታላቁ የአርበኝነት ጦርነት›› እያሉ በሚጠሩትና ከ1934 እስከ 1937 ዓ.ም. በቆየው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንፀባራቂ ድል የተገኘበትን ክብረ በዓል ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ ቀይ አደባባይ በተገኙበት ተከብሯል፡፡

ታላቁ የአርበኝነት ጦርነት 71ኛ ክብረ በዓል በሞስኮ ቀይ አደባባይ ሲከበር የሩሲያ ፕሬዚዳንትና የሩሲያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ቭላድሚር ፑቲን በጦርነቱ የተሳተፉትን የአባታቸውን ፎቶ ይዘው ከሰልፈኞቹ ጋር አብረው ተጉዘዋል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ በመሩት አጠቃላይ የሰልፍ ሥነ ሥርዓት ከ10 ሺሕ የሚበልጡ እግረኛ ወታደሮች፣ ዘመናዊ ታንኮች፣ ኒውኩሌር ማስወንጨፍ የሚችሉ ሚሳይሎችም ታይተዋል፡፡ ‹‹ሱ 35›› (SU35) የተሰኘውን ዘመናዊ ተዋጊ ጄትን ጨምሮ የተለያዩ ተዋጊ አውሮፕላኖች የአየር ላይ ልዩ ትርኢት አሳይተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን በመሩት የኅሊና ጸሎት ተጋዳይ አርበኞች ታስበዋል፤ ሐያ አንድ ጊዜም መድፍ ተተኩሷል፡፡  

‹‹አንጋፋ አርበኞቻችን ዛሬ በልጅ ልጆቻቸውና በልጅ-ልጅ ልጆቻቸው እንደሚኮሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም አልጣሉዋቸውምና፤ ሁሌም ታላቁን ድል፣ የገናናው ትውልድ በድል የታጀበ የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ያስታውሳሉና፤›› በማለት የተናገሩት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...