Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ጌመርስ››

‹‹ጌመርስ››

ቀን:

ቦሌ በኤድና ሞል መስመር የሚገኘው የሞርኒንግ ስታር ሞል የመጨረሻው ፎቅ በጌመሮች (ጌም ተጫዋቾች) ተሞልቷል፡፡ 50 የሚሆኑ ከፍተኛ የጌም ፍቅር ያላቸው ወጣቶች ከየላፕቶፓቸው ስክሪን ጋር ተፋጠዋል፡፡ ስክሪናቸው ላይ የሚታዩትን የጌም ገፀ ባህሪዎች ለማንቀሳቀስ ደጋግመው ላፕቶፖቻቸውን ይነካካሉ፡፡ ገፀ ባህሪዎቹ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ፣ ወደ ፊት ወይም ወደኋላ ይጓዟሉ፡፡ ይተኩሳሉ፡፡ ከጠላት ይሸሸጋሉ፡፡ ጌመሮቹም የገፀ ባህሪዎቹን እንቅስቃሴ በስሜት ይከታተላሉ፡፡ በጠላት ሲመቱ ይበሳጫሉ፡፡

ጌመሮቹ ከአክሽን ጌሞች አንዱ የሆነው ፈርስት ፐርሰን ሹተር በቡድን ሆነው እየተጫወቱ ነበር፡፡ ከፍተኛ የውድድር መንፈስ ይታይባቸዋል፡፡ አንዱ ቡድን ሌላውን ለማሸነፍ የሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሰዓታት ሊወስድ ይችላል፡፡ ጌመሮቹ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሲሆኑ በየ15 ቀኑ እየተገናኙ ጌም ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታቸው የውድድር መንፈስ ቢኖረውም አሽናፊዎቹ አይሸለሙም፡፡

ዝግጅቱ ጥቂት ጌመሮች ተሰባስበው ከወራት በፊት የጀመሩት ሲሆን፣ ዲ5 ጌም ኮን ይሰኛል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆች አልያም በሥራ ቦታ የኮምፒዩተር ጌሞችን የሚጫወቱ ቢኖሩም ቁጥራቸው ውስን ነው፡፡ ዲ5 ጌም ኮን የጌም ፍቅር ያላቸው ሰዎች በተወሰነ ጊዜና ቦታ እንዲገናኙ ያለመ ነው፡፡

በአገራችን ጌም መጫወት እንደሌሎች አገሮች ጎልቶ የሚታይ ነው ማለት ባይቻልም፣ እንደመዝናኛ በሞባይላቸው ወይም በዴስክቶፕ የሚጫወቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጌምን ከመዝናኛነት ባለፈ በጌመርነት ደረጃ የሚጫወቱ ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በተቀረው ዓለም ጌመርነትን በፕሮፌሽናል ደረጃ ወስደው ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ባይጀመርም ዲ5 ጌም ኮን ለጌመሮች ጥሩ መገናኛ ፈጥሮላቸዋል፡፡

ከመሥራቾቹ አንዱ የማስታወቂያ ባለሙያና ጌመር ስመኝ ታደሰ እንደሚናገረው፣ ቀድሞ በሁለት ወይም በሦስት ወር እሱና ጓደኞቹ እየተገናኙ ጌም ይጫወቱ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የተሳታፊዎች ቁጥር ሲጨምር ሰፊ ቦታ ተከራይተው በቋሚነት ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ኢትዮ ጌመርስ የተባለ የፌስቡክ ገጽና የቫይበር ግሩፕ ስላላቸው ምን ዓይነት ጌም የት እንደሚጫወቱ መረጃ ይለዋወጣሉ፡፡ ሁሉም ተጫዋች ላፕቶፕ ይዞ በየ15 ቀኑ ይገኛል፡፡ ጨዎታዎች የሚጀመሩት ጠዋት ሲሆን፣ እስከ ምሽት ድረስ ግጥሚያዎቹ ይቀጥላሉ፡፡ ስትራቴጂ፣ ፈርስት ፐርሰን ሹተርና ፊፋ የተባሉት ጌሞች ይዘወተራሉ፡፡

ዓለም ላይ እነዚህን ጌሞች የሚጫወቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጌመሮች አሉ፡፡ ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው ውድድር ይካሄዳል፡፡ ብዙ ፕሮፌሽናል ጌመሮች ውድድሮቹን በማሸነፍም ሚሊየነር ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ካርሎስ ሮድሪጌዝ ወይም በቅጽል ስሙ ኤቬሎቴ በጌሚንግ እስከ 950,000 ዶላር ያገኛል፡፡ ጆናታል ዌንዴል (ፋታሊቲ)ና ጆን ሙን ሆ(ሙን) በጌሚንግ ዝናን ያተረፉ ሚሊየነሮች ናቸው፡፡ ወደ አፍሪካ ስንመጣ ደቡብ አፍሪካና በመጠኑ ግብፅ በፕሮፌሽናል ጌሚንግ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡

ስመኝ እንደሚለው፣ ዲ5 ጌም ኮንን የአፍሪካ ጌመሮች እየመጡ የሚጋጠሙበት የማድረግ ህልም አላቸው፡፡ ጌመሮችን በአንድ ቦታ አሰባስቦ ከማጫወት ባሻገር ውድድር የማካሄድና በዩቲዩብ ላይ ቀጥታ የማሰራጨት እቅድ አላቸው፡፡ ‹‹አፍሪካ ወጣቷ አኅጉር የምትባለው ብዙ ወጣቶች ስላሏት ነው፡፡ ጌሚንግ ኢላማ ያደረገው ደግሞ ወጣቱን ነው፡፡ በአገራችን የጌሚንግ ፍላጎቱና ችሎታውም ያሏቸው ጌመሮች አሉ፡፡ መወዳደሪያ ቦታ ከተመቻቸላቸው ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መግባት ይችላሉ፤›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ጌመሮች የሚወዳደሩበት ዝግጅት ማካሄድ አዋጭ እንደመሆኑ ስፖንሰር ማድረግ የሚፈልጉ ድርጅቶች ወደ ጌሚንግ ፊታቸውን ቢያዞሩ መልካም እንደሆነም ይገልጻል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ለጌም የሚሆን ቦታና የስፖንሰር አለመገኘት የኢንተርኔት ኮኔክሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥም ፈተና ሆነውባቸዋል፡፡ ወደ ዲ5 ጌም ኮን ለመግባት ጌመሮች 90 ብር ቢከፍሉም የሚቀርብላቸውን ምግብና መጠጥ ከመሸፈን አያልፍም፡፡ እንደ ስመኝ ያሉ ጌመሮች እነዚህ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ለጌሚንግ ያላቸው ፍቅር ፈተናዎቹን እንዲታገሱ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ የዲ5 ጌምኮንን ተሞክሮ ከግምት በማስገባት ስለ ጌሚኒግ ያለው ግንዛቤ እንደሚያድግና የሚደግፏቸው ተቋሞች እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ጌሚንግን እንደ ሙያ የወሰዱ ተጫዋቾች ከዓመት እስከ ዓመት ውድድር ያካሂዳሉ፡፡ ጌሚንግን ኢስፖርት (ኤሌክትሮኒክ ስፖርት) በሚል ስያሜ ዕውቅናው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ጌመሮችን በቡድን አደራጅተው የሚያሠለጥኑ፣ ስፖንሰር እያደረጉ የሚያወዳድሩ ትልልቅ ድርጅቶችም አሉ፡፡ እንደ ዋርነር ብራዘርስ ያሉ የፊልም ካምፓኒዎች በሱፐር ሒሮ (ልቦለዳዊ ጀግኞች) ፊልሞች በመመርኮዝ በሚያሠሯቸው ጌሞች ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ፕሮግራመሮች፣ ጌም ዲዛይነሮችና ሌሎችም ባለሙያዎች ቁጥርም እየተበራከተ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ተማሪዎችም ጌም ለመሥራት የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የተሳካላቸውም አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ የፕሮግራሚንግ ምሩቁ ጌመር ያፌት ጌታቸው ነው፡፡ ቱዲ (ባለሁለት አውታር) የሞባይል ጌም ሠርቷል፡፡ ያፌት እንደሚለው፣ ብዙ ጌም መሥራት የጀመሩ የአይቲ ባለሙያዎች ቢኖሩም ዘመኑ የደረሰባቸው የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን ለማግኘት ስለሚቸገሩ የሚሳካላቸው ጥቂቶች ናቸው፡፡ ‹‹ጌሞች ለመሠራት ያሉ ፈተናዎች ታልፈው ጌሙ ቢሠራም እንኳን ኢንተርኔት ላይ ለመጫን ፍቃድ ለማውጣት የግድ የክሬዲት ካርድ ክፍያ ሲስተም ያስፈልጋል፡፡ ሲስተሙ እኛ አገር ስለሌለ ጌሞችን ሕጋዊ ለማድረግ ይከብዳል፤›› ይላል፡፡

ያፌት ጌም መጫወት የጀመረው የስድስት ዓመት ልጅ ሳለ ራምቦ ፊልምን ተመርኩዞ በወጣው ራምቦ ጌም ነበር፡፡ ለኮምፒዩተር ፍቅር ያደረበት ኮምፒዩተር ጌሞች ስለሚወድ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የኢትዮጵያ ጌመሮችም ይሁን የጌም ዲዛይነሮች የሚሰባሰቡበት ዝግጅት መኖሩ የጌሚንግ ሒደት እንዲለወጥ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ያምናል፡፡ የጌሚንግ ትርፋማ መሆን የግዙፍ ተቋሞችን ትኩረት መሳቡ ላይ ከስመኝ ጋር ይስማማል፡፡ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የሚያወጣቸው ጌሞችና የሚያዘጋጃቸው የጌም ውድድሮች ያላቸውን ተቀባይነት እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡

በጌሚንግ ከታዩ ትልልቅ ውድድሮች አንዱ የተካሄደው ከሁለት ዓመት በፊት ደቡብ ኮርያ፣ ሴዑል ውስጥ ነበር፡፡ በከተማው ግዙፍ ስቴዲየም የተካሄደውን ውድድር ወደ 40,000 የሚጠጉ ሰዎች የታደሙት ሲሆን፣ ከ27 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ኦን ላየን ተከታትለውታል፡፡  አምስት አምስት ተጫዋቾች ያሏቸው የ‹‹ሳምሰንግ ኃይት››ና ‹‹ስታር ሆርን ሮያል ክለብ›› የተጋጠሙበት የሊግ ኦፍ ሌጀንድስ ወርልድ ሻምፒዮን ሺፕ፣ ለ ‹‹ሳምሰንግ ኃይት›› ተጫዋቾች  የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት ያስገኘ ነበር፡፡

ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ በዓለም ላይ 70 ሚሊዮን የሚደርሱ ጌመሮች ተወዳድረውበት ለማጣሪያ አሥሩ ብቻ የደረሱ ሲሆን፣ ሴዑል የተካሄደው መዝጊያ ውድድር ግዙፍና ዓለምን ያነጋገረ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ውድድሮችን በቅርበት የሚከታተለው ጌመር በእደ አዳም እንደሚለው፣ ፕሮፌሽናል ጌመሮች ለማፍራት የአገር ውስጥ ውድድሮች መበራከት አለባቸው፡፡ እሱ በፕሮግራሚንግ፣ በማስታወቂያ ሥራና በዲዛይን ውስጥ ካሉ ጓደኞቹ ጋር የጌሚንግ ውድድር ለመጀመር ንድፈ ሐሳብ ጨርሰዋል፣ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራምም በቅርቡ ያካሂዳሉ፡፡

የጌም ውድድሮች ሲበራከቱ ጌመሮች ኦሪጂናል ጌሞች ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ጌመሮች ኦሪጅናል ጌሞችን በዶላር የመግዛት አቅሙ መንገዱም ስለሌላቸው አይገዙም፡፡ ‹‹ኦሪጅናል ጌሞች ኦንላይን ከ70 ዶላር ጀምሮ ይሸጣሉ፡፡ ክሬዲት ካርድ ሲስተም ስለሌለ መግዛት አይቻልም፡፡ አንዳንዶች ከውጪ አገር በሰው ያስገዛሉ፡፡ ብዙዎቻችን በሁለተኛ ደረጃ (ፌክ) የጌም ቨርዥኖች እንጠቀማለን፤›› ይላል፡፡

ብዙዎች ጌም የሚያገኙት እንደ በእደ ቢሆንም፣ ጥቂቶች ኦርጂናል ጌም በሰው እያስገዙ ሌላ አገር ከሚኖሩ ጌመሮች ጋር ኦንላየን ይጫወታሉ፡፡ እሱ ስፖርታዊ የኮምፒዩተር ጌሞች ይወዳል፡፡ ፊፋ፣ የኤንቢኤ ባስኬት ቦል፣ ዩኤፍሲ ቦክስና ካር ፕሮጀክትን ያዘወትራል፡፡ የፊፋን ጌም በጣም ስለሚወደው ከውጪ 35 ዶላር ከፍሎ በሰው አስገዝቷል፡፡ በየቀኑ እስከ አንድ  ሰዓት ጌም ይጫወታል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመድረስ ጊዜ ቢወስድም ጥሩ የሚባሉ ጅማሮዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ እንደምሳሌ የሚጠቅሰው አንድ ግለሰብ በግል ተነሳሽነቱ ዶታ2፣ የተባለ ጌም ጌመሮች እንዲጫወቱ መጠየቁ ነው፡፡ ጌሙ የቡድን ሲሆን፣ ግለሰቡ አሸናፊውን 10,000 ብር ለመሸለም ቃል ገብቷል፡፡ በእደና ሌሎችም ጌመሮች ልምምድ እያደረጉ ሲሆን፣ ውድድሩ በቅርቡ ይካሄዳል፡፡

ዶችፑል በሚል የጌመር ስሙ የሚታወቀው በእደ እንደ ያፌት ሁሉ ጌሞች ይሠራል፡፡ አዳዲስ ጌሞች ሲወጡ በፍጥነት ለማግኘት ከሚጣጣሩ ጌመሮችም አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲጠብቀው የነበረ ኖ ማንስ ስካይ የተባለ ጌም እስከሚወጣ በጉጉት እየተጠባበቀ ነው፡፡ ‹‹ጌም መጫወት በጣም ያስደስተኛል፡፡ ከፍተኛ የተወዳዳሪነት መንፈስ ስላለኝ ያለኝን አቅም አሟጥጬ ለማሸነፍ እታገላለሁ፤›› ይላል ጌም ሲጫወት ያለውን ስሜት ሲገልጽ፡፡

በእሱ እምነት፣ ኢትዮጵያውያን ጌመሮች በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዘመኑ የደረሰባቸው የጌሚንግ መገልገያዎች ማግኘት አለባቸው፡፡ ብዙዎች ጌም ለመሥራትም ይሁን ለመጫወት የሚሆኑ ፕሮፌሽናል ኮምፒዩተሮች፣ ጆይስቲክ (መጫወቻ)ና ሔድፎን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ቢሆንም እንደሱ ተነሳሽነቱ ያላቸው ጌመሮች በሚያዘጋጇቸው ውድድሮች ገንዘብ በማግኘት አሸናፊዎቹን ፕሮፌሽናል የጌሚንግ ዕቃዎች መሸለም እንደሚችሉ ከሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ጋር ይስማማበታል፡፡

ካሉት ጥቂት ሴት ጌመሮች አንዷ ረድኤት አባተ (በጌመር ስሟ ፕሮዲዤ) አርክቴክት ናት፡፡ እንደ ዲ5 ጌም ኮን ባሉ ዝግጅቶች ተገኝታ ጌም ትጫወታለች፡፡ እንደ ብዙዎቹ ጌመሮች ጌም መጫወት የጀመረችው በልጅነቷ ነው፡፡ ከማዮታ ዲቪዲ ፕለየር ጋር የሚሸጠውን ጌም ከወንድሟ ጋር በመጫወት ነበር የጀመረችው፡፡ አሁን ስትራቴጂ ጌሞች ላይ የምታተኩር ሲሆን፣ ክላሽ ኦፍ ክላንስ የምትወደው ጌም ነው፡፡ ጌሙ የቡድን ሲሆን፣ እሷ ጥቁር አንበሳ የተባለ ቡድን ውስጥ ትጫወታለች፡፡  ዓደዋ፣ አቢሲኒያንስ፣ ዘ ዋልያስ፣ ኢትዮጵያን ሞብ፣ አክሱምና ፋንተም ግሩፕ የሚባሉ ቡድኖችን ይገጥማሉ፡፡

‹‹ጌም መጫወት የልጆች እንደሆነ ይታሰባል ጌም የሚጫወቱ ወጣቶች ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ተደርገው ይወሰዳሉ፤›› ትላለች ስላለው የተዛባ አመለካከት ስትናገር በእሷ እምነት እውነታው ከዚህ የራቀ ነው፡፡ ጌም መጫወት ከሚጠይቀው የአዕምሮ ብቃት ባሻገር፣ ዛሬ ዛሬ ጌመሮች ዝነኛና ብዙ ተከታይ ያላቸው ሆነዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ስለ ፕሮፌሽናል ጌሚንግ ብዙም ግንዛቤ ባይኖረውም፣ ኢትዮጵያውያን ጌመሮች እርስ በእርስ የሚደጋገፉበት መንገድ እያገኙ ነው ትላለች፡፡ እርስ በእርስ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በጋራ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ችሎታቸውንም ያዳብራሉ፡፡ ወደ 15 ዓመታት ያህል ጌም የተጫወተችው ረድኤት፣ ፕሮፌሽናል ጌመር መሆን የሚፈልጉ ተጫዋቾች መበረታታት እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡ የአገሪቱን ስምም እንደሚያስጠሩ ታምናለች፡፡

በእርግጥ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሳይሆን፣ ዛሬ ጌመሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ ናቸው፡፡ እንደ ሙዚቀኞችና ፊልም ሠሪዎች አድናቂዎቻቸው አብረዋቸው ፎቶ ለመነሳት ይጓጓሉ፡፡ የጌሚኒግ ውድድሮችም የዓለምን ትኩረት ስበዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የጌሚንግ ኢንዱስትሪ ለዓለም 74 ቢሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ ሚሊየነርነት ደረጃ የደረሱ ጌመሮች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ጌም ሕይወታቸውን ያመሰቃቀለባቸውም አሉ፡፡ ረዥም ሰዓት ጌም በመጫወት ሕይወታቸው ያለፈና በጌም ሱስ ተይዘው ሆስፒታል የገቡም ጥቂት አይደሉም፡፡ ጌምን እንደ ሥራ ይዘውና ከማኅበረሰባዊ ሕይወታቸውም ሳይገለሉ እውቅናና ሀብት ያገኙ ደግሞ ሌላውን ገጽታ ያሳያሉ፡፡

ጌሞች በይዘታቸው፣ በአጨዋወታቸውና በሌሎች መስፈርቶችም ይለያያሉ፡፡ ቀላልና ለልጆች የሚሆኑ፣ የፕሮፌሽናል ጌመሮችና፣ ለወታደራዊ ሥልጠና የሚሆኑም ጌሞች አሉ፡፡ ፋይቲንግ ጌም፣ ሹተር ጌም፣ አድቬንቸር ጌም፣ ሲሙሌሽን ጌም፣ ሮል ፕለይ ጌምና ሌሎችም ዓይነት ጌሞች አሉ፡፡ የኮምፒዩተር ጌሞች የሚሰጣቸው ቦታ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ የጌም ሙዚየም ያሠሩ እንደ ጀርመን፣ ሩሲያና አሜሪካ ያሉ አገሮችም አሉ፡፡ በየዓመቱ የሚወጡ ጌሞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን፣ ትርፋማም ናቸው፡፡ ፓርታል፣ ስታር ክራፍት፣ ሀፍ ላይፍና ሲድ ሜይርስ ሲቪላይዜሽን ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ጌሞች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መራቀቅ የጌሞችን አሠራር እያሳደገው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጌሚንግ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም የጌም ፍቅር ያላቸው ጌመሮች ሌሎች አገሮች ከደረሰቡት ለመድረስ ከማለም ወደ ኋላ አላሉም፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...