Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየማይዘጋው በር

የማይዘጋው በር

ቀን:

ከተለያዩ አካባቢዎች በእግራቸው አልያም በታክሲ መጥተው ወደ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚወስደውን አቅጣጫ የሚጠይቁ ሴቶች ካዛንችስ ላይ በተደጋጋሚ ያጋጥማሉ፡፡ በተለይም ጠዋት ላይ ካዛንችስን ለሚያዘወትሩና በካዛንችስ ለሚያልፉ ወደ ‘ዓረብ አገር’ ለመሄድ እንደሆነና ለዚህም ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መድረስ እንደሚፈልጉ የሚናገሩ ሴቶችን ማግኘት የሚደጋገም አጋጣሚ ነው፡፡

የቤተሰብ ሀብትና ጥሪት ተሸጦ ብድርም ተገብቶ ወደ ተለያዩ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ጉዳትና እንግልት በመመልከት መንግሥት ጉዞውን ካገደ የቆየ ቢሆንም ተፈቅዶ እንደገና ጉዞው ተጀምሯል በሚል ብዙዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሁም ኢሚግሬሽን ለመሄድ ሲማስኑ ይገኛሉ፡፡

በሕጋዊ መንገድ መሄድ ተጀምሯል ብለው ለመሄድ የሚያስችላቸውን ሒደት ለመጀመር ከሚንከራተቱት በተለየ መልኩ ደግሞ በተለያዩ ሕገወጥ መንገዶች ያሰቡትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ በሱዳን፣ በኬንያ በሕገወጥ ደላሎች ድጋፍ ለመሄድ ይሞከራል፡፡ በዚህም ተሳክቶላቸው ካሰቡት የደረሱ እንዳሉም ይነገራል፡፡ በቱሪስት ቪዛ ሄዶ በደረሱበት በሕገወጥ ደላሎችና ኤጀንሲዎች ሥራና የሥራ ፈቃድ አግኝቶ ለመቅረት መሞከርም ጥቂት የማይባሉ እየወሰዱት ያለ ሌላው አማራጭ ነው፡፡

- Advertisement -

ከጥቂት ቀናት በፊት በፍላይ ዱባይ አንድ በረራ የሄዱና በተጠቀሰው መንገድ ዱባይ ለመቅረት የሞከሩ 30 ኢትዮጵያውያን በኤርፖርቱ ኢሚግሬሽን ተይዘው መመለሳቸው ምንም እንኳ መንግሥት ጉዞውን ካገደ ረዥም ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም ዛሬም ብዙዎች በራሳቸው መንገድ እየሄዱ የመሆናቸው ግልጽ ማሳያ ነው፡፡

ከተለያዩ ዓረብ አገሮች አካላዊና አእምሮአዊ ጉዳት ደርሶባቸው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን የሚቀበለውና መልሶ ማቋቋም ላይ የሚሠራው ጉድ ሳማሪታን ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጥሩብርሃን ጌትነትም መንግሥት በቤት ሠራተኝነት ወደ ዓረብ አገሮች ጉዞ ከከለከለ በኋላ በተለያየ መንገድ ሄደው የተመለሱትን እየተቀበሉ እንደሆነ ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊትም አሥራ አንድ ልጆች የመንን አልፈው ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት ሲሉ ተይዘው የተመለሱ ልጆችን እንደተቀበሉም ይናገራሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው በማንኛውም ውስጥ ሕይወትን ሊቀጥፍ በሚችል በየመን ያለው ጦርነት ዓይነት ሁኔታ እንኳ ቢሆን ኢትዮጵያውያን በስደት ወደ ተለያዩ የዓረብ አገሮች እየሄዱ መሆኑን ነው፡፡

ከአራት ወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው አዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ 923/2008 ዜጐች ደህንነታቸውና መብታቸው ተጠብቆና ተረጋግጦ በውጭ አገር በሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መመቻቸትን በሚመለከት ዝርዝር ሁኔታዎችን ያስቀምጣል፡፡

ቀደም ሲል ወደ ዓረብ አገሮች በሚልኩ ኤጀንሲዎች፣ የምርምራ አገልግሎት በሚሰጡ የሕክምና ተቋማትና በሌሎችም አካላት በሚፈጠሩ ክፍተቶች የደረሱ ችግሮችንም ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው ሕገወጥ ሥራ ይሠሩ የነበሩ ኤጀንሲዎች እንዲሁም የሕክምና ተቋማት በብዙዎች ስቃይ ገንዘብ ማትረፋቸውም የሚረሳ አይሆንም፡፡

አዋጁ ማን መሄድ ይችላል? ምን ዓይነት ሥልጠናና መሥፈርቶችን አሟልቶ? የኤጀንሲዎችና የአሠሪዎች ግዴታና ኃላፊነትስ ምን መምሰል አለበት? የሚሉ ጉዳዮችን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም የአዋጁ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ከሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

አዋጁ ከሚያስቀምጣቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ኤጀንሲዎች ወደ ሥራ ለመግባት በግል ከሆነ የአንድ ሚሊዮን ብር፣ በቡድን ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲኖራቸው በተጨማሪም መቶ ሺሕ ዶላርም ተቀማጭ እንዲያደርጉ የሚለው ይገኝበታል፡፡ በተመሳሳይ መድህን እንደሚቋቋምና ኤጀንሲዎችም በሚልኩት ሰው ብዛት መሠረት እንዲያዋጡ የሚለውም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

የዜጐች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት መስመር እንዲይዝና ዜጐችም ከጉዳት፣ አገርም ከኪሳራ እንዲጠበቁ የአዋጁ መውጣትና መፅደቅ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም ተፈጻሚነቱ መዘግየቱ ደግሞ ከየአቅጣጫው ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ ጉዳዩ ብዙዎችን የሚመለከትና የተለያዩ ፍላጐቶችም ያለበት በመሆኑ ወደ ተግባር መሸጋገሩ ቀላል እንደማይሆን ቢታወቅም መዘግየቱም የዚያኑ ያህል ከባድ ተጽእኖዎችን እንደሚያስከትል አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡

ወደ ዓረብ አገሮች ይደረግ የነበረው ጉዞ ከታገደ በርካታ ወራት በመቆጠራቸው ያ እርምጃ ከተወሰደበት ጊዜ ጀምሮ ቀጣዩ ሥራ መጀመር ነበረበት የሚል አቋም ያላቸው ደግሞ ለአዋጁ ተግባራዊነት መዘግየት የሚቀመጥ ምክንያት እምብዛም አሳማኝ አይደለም የሚል ሐሳብ ያንፀባርቃሉ፡፡

የአዋጁ ተፈጻሚነት መዘግየት ምክንያትን በሚመለከት ያለው ክርክር እንዳለ ሆኖ አዋጁ በሚያስቀምጠው መሠረት ጉዞ የሚጀመረው መቼ ነው? ነገሮችስ ምን ላይ ናቸው የሚለው ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡

ጉዳዩ በቀዳሚነት የሚመለከተውና ዛሬም መረጃ የሌላቸውና ወደ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት ለመሄድ የሚሹ ኢትዮጵያውያት ደጅ የሚጠኑት ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አዋጁን ማስፈጸም የሚያስችለው ደንብና መመርያ ላይ እየሠራ እንደሆነ ከሚኒስቴሩ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግርማ ሸለመ ለመረዳት ችለናል፡፡

የጉዞው መጀመር ዘግይቷል የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው እሳቸውም ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን መዘግየቱ ሥራው ሰፊ በመሆኑ፤ የተለያዩ አደረጃጀቶችን የሰው ኃይልም የሚጠይቅ በመሆኑ እንደሆነ በመጥቀስ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ አጠቃላይ ነገሩ ከአገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚመለከት መሆኑ፣ እንደቀድሞ ሳይሆን ተጓዦች በመንግሥት የቴክኒክና የሙያ ትምህርት ተቋማት የሦስት ወር ሥልጠና የሚወስዱበት ሌሎችም ትልልቅ ሥራዎች ያሉበት በመሆኑ አሁንም በዚህ ጊዜ ወደ ሥራ ይገባል ማለት የሚያስደፍር ነገር የለም ይላሉ አቶ ግርማ፡፡

በሌላ በኩል ወደ ዓረብ አገሮች ለሚሄዱ ተጓዦች የሕክምና ምርመራ ማድረግ የሕክምና ተቋማት ወሳኝ ቢዝነስ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ግን ትርፋማ ቢዝነስ የነበረው ለሁሉም ተቋማት ሳይሆን የባህረሰላጤው አገሮች የተመረጡ የሕክምና ማዕከላት ማኅበር Gulf Approved Medical Association (GAMCA) መርጠዋቸው ለነበሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ የግል ሕክምና ተቋማት ብቻ ነበር፡፡ ይህና የሕክምና ተቋማቱ የተለያዩ አሠራሮች በጊዜው ብዙ ተቃውሞዎችን አስነስተው እንደነበርም ይታወሳል፡፡ አሁንስ በአዲሱ አሠራር የትኞቹ የሕክምና ተቋማት ምርመራውን ይሰጣሉ?

ቀደም ሲል ከዚህ በተደረገላቸው ምርመራ ጤንነታቸው ተረጋግጦ የተጓዙ ኢትዮጵያውያን ለምሳሌ እንደ ሳንባ ምች ያሉ በሽታዎች እንዳሉባቸው ተገልጾ ይመለሱ ነበር፡፡ ይህ ብዙ ገንዘብ አፍስሰው፣ ረዥም ጊዜ ጠብቀውና ሠርቶ መለወጥን ተስፋ ሰንቀው የሄዱ ብዙዎችን ለኪሳራና ለሥነ ልቦና ጉዳት ዳርጓል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ጀነራል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ዳንኤል ገብረ ሚካኤል እንደሚሉት በአዲሱ አሠራር ጉዞው ሲጀመር ምርመራውን ሁሉም የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች እንዲሁም በውስጥ ደዌ ስፔሻላይዝ ያደረጉ (በቀድሞ አደረጃጀት ከፍተኛ ክሊኒክ የሚባሉት) እንዲሰጡ ታስቧል፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ጉዳዩ ለሚመለከተው ለባህረሰላጤው የተመረጡ የሕክምና ማዕከላት ማኅበር ጋምካ ከስድስት ወር በፊት በሚኒስቴሩ ደብዳቤ የተጻፈ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አልተገኘም፡፡ ስለዚህም ባለፈው ሳምንት ሁለተኛ ደብዳቤ መጻፉን ዶ/ር ዳንኤል ይናገራሉ፡፡

ከዚህ አስፈላጊውን ምርመራ አድርገው ጉዞውን ለማድረግ ብቁ ናቸው ተብሎ ሄደው በሚመለሱ ምክንያት የሚደርሰው ኪሳራ የሚወድቀው ማን ላይ ነው? የሚል ጥያቄ ለዶ/ር ዳንኤል አቅርበን ነበር፡፡ ‹‹በዓረብ አገራቱ ዓለም አቀፍ ብሔራዊ ስታንዳርድም ከሚያስቀምጠው ውጪ ይኼ ችግር ተገኝቶባቸዋል ብለው የመመለስ ነገር አለ፤›› በማለት በዚህ ረገድ ግልጽ ንግግር እንደሚያስፈልግ ይናራሉ፡፡

የአዋጁ መዘግየት በብዙ መልኩ ያደረሰባቸው ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አሠሪ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ ደግሞ ባንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የጤና ችግር አለባቸው ተብሎ በሚመለሱ የሚደርስ ኪሳራ ሙሉ በሙሉ ምርመራውን ያደረገው ተቋም መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ዶ/ር ዳንኤል ነገሩ ከጋምካ፣ ከኤጀንሲዎችና ምርመራውን ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ቀጣይ ንግግር ማድረግና ማጥራትን የሚጠይቅ ነው ቢሉም የምርመራ ላይ ችግር መኖሩ ከተረጋገጠ ምርመራውን የሰጡት ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ይናገራሉ፡፡

የአዋጁ መዘግየት በብዙ መልኩ ጫና አሳድሮብናል የሚሉት አቶ መዝገቡ መንግሥት ወደ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሚደረግ ጉዞን አግዶ እያለ በተለያየ መንገድ ብዙዎች መሄዳቸውና እየሄዱ መሆኑም ከባድ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በቱሪስት ቪዛና በተለያየ መንገድ ብዙዎች ዱባይ ላይ ተከማችተዋል፡፡ አሁንም እየሄዱ ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ አፍስሰን የምንገባበት ሥራ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ትርፋማ ሊሆን ይችላል፤›› በማለት በቀላሉ መሄድ የሚቻልበት መንገድ (አደገኛም ቢሆን) እስካለ ድረስ ማን ሥልጠና ወስዶ፣ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጐና ሌሎችንም መሥፈርት አሟልቶ በኤጀንሲዎች በኩል ይሄዳል? ሲሉ አቶ መዝገቡ ይጠይቃሉ፡፡     

አጠቃላይ ሁኔታውን በመመልከት ወደ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሚደረገው ጉዞ እገዳ ተነስቶ አዲሱ አሠራር እስካልተጀመረ ድረስ መዘግየቱ ሕገወጡ አካሄድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በር መክፈት እንደሆነ በመግለጽ የሚያሳስቡ ብዙዎች ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...