ሰላም! ሰላም! “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት፤” ሲባልም ሰማን። ምን እኛ የሕግና ሥርዓት ባላንጦቹ የሰው ልጆች፣ እነሆ እዚህ ትዕዛዝ ላይ ተጋን። ተግተንም ተዋለድን። ይኼው እንደምታዩት እኛም ችግራችንም እኩል ተባዛን። አንድ ጎጆ እሞላ ብሎ መከራውን ያየ አዳም ዛሬ ዓለም ሞልታብን ቢያይ ምን የሚል ይመስላችኋል? ሳስበው ሳስበው ‘እውነትም እንቁላል በእግሩ ሲሄድ ቀስ በቀስ ነው’ ብሎ የሚተርት ይመስለኛል። ኧረ ተረት የእኛ ብቻ ነው ሲባልም ይገርመኛል። የእኛ ነው ማለት ስንወድ እኮ! በነገራችን ላይ ስንባዛ አንድም ለመገራረም ነው። አይደለም? ነው? እግዜሩም ብዙ ጊዜ ተገርሞ፣ ተገርሞ፣ ተገርሞ፣ መገረም ሲያቅተው ፀፀተው። እዚህ ጋ ነው እንግዲህ ቁልፉ። ፍቅር በሌለበት የመባዛት ሒሳብ ሁሌም ፀፀት ይኖራል።
ትንሽ ከታገሳችሁኝ እንደ ሙሴው ዘፍጥረት ብዙ ጥያቄ የማታነሱበትን ይህን የደላላው አንበርበብር ምንተስኖት ዘፍጥረት መልክ ይዞ ታዩታላችሁ። ታዲያ እንዳልኳችሁ እንደ ዘመኑ ሰው መልኩ የፍቅር ግብሩ የፀፀት አይሆንባችሁም። ነገራችን ሁሉ እንዲያ ሆኗል ብዬ እኮ ነው። ጀምሮ አለመጨረስ አማሮ ሳይጨርሰን መልካም መስሎ ገደል የሚከተንን ተግባር እያደር ሙጥኝ ብለናል። በአስቀመጡት ሥፍራ በብዙ ተባዙ የፍቅር ሕግ መመራቱን ትታችሁት ቁም ነገረኛ ብላችሁ ያከበራችሁት ሰው፣ አየር ወለድ በሚያስንቅ ፍጥነት ተከርብቶ እንደ ሊጥ ቦክቶ ያቦካችኋል። ምን ትሉታላችሁ? ከስንቱ ሳንነካካ ከስንቱ ርቀን ከስንቱን የእንጀራና የወዳጅነት ገመድ ተባጥሰን እንችላለን? ‹‹መደብ ነው ብለን ስንደላደል . . .›› አሉ ባሻዬ በቀደም “ . . . ያነዱብናል ባሩድና ደን፤” የባሻዬ ባልሆን ይቆጨኝ ነበር!
ጨዋታዬ ‹አብስትራክት› ከሆነባችሁ ከመቻል ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም። እንኳን ይኼን ይኼን ስንቱ አስብቶ አራጅ አልቻልነውም እንዴ? መቻቻል ብቻ አይምሰላችሁ ሐበሻን ሐበሻ ያስባለው። እውነቴን ነው። መቻልም ጭምር ነው። አንዱ በቀደም እንዲህ ስለው፣ “መቻቻልና መቻል ምን ለየው?” አለኝ። “እንዴት አይለያይም? እኩል መሸከምና አሸክሞ መንዳት አንድ ነው ወይ?” አልኩት። “ይልቅ እሱን ተወው። አንድ ነገር ልመክርህ ነው አመጣጤ . . .” ብሎ ተገላምጦ አጠገቡ ሰው እንደሌለ አጠና። ከዚያ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “ጊዜው እየከፋ ነው። ሰው ትዕግሥቱ እዚህች አፍጫው ላይ ሆናለች። በቀደም አንዱ ምን እንዳደረገ አልሰማህም? . .. . ” ሕፃን ልጅን በሚያባብል አኳኋን መልስ ሲጠብቅ፣ “አልሰማሁም፤” አልኩት። “ከፊቱ ያለ አሽከርካሪ መንገድ ይዘጋበታል። እሱም ባለመኪና ነው። አሳልፈኝ ብሎ ‘ክላክስ’ ይነፋል። ጆሮ ዳባ ልበስ ይለዋል። እንደ ምንም ታኮ ለማለፍ እየሞከረ በመስኮት ‘ምነው ብታሳልፈኝ?’ ሲለው አጅሬ ምራቁን ተፋበት። መሣሪያውን አውጥቶ ግንባሩን ብሎ ገደለው! ገደለው! . . .፤”
ገደለውን መሄጃ እንዳጣ ሰጋር ፈረስ በመቁነጥነጥ ደጋገመው። አሁን እዚህ ላይ ድንገት ከተከታዩ ሙዚቃ በኋላ ተመልሰን እንገናኛለን ብዬ ጣቢያውን ሁሉ በሞኖፖል እንደያዙት ዋዘኞች፣ የአስቴር አወቀን ‘ፍቅር ገደለ አሉ የወደደውን፣ እሱን ማን አስታሞ ይቀብረው ይሆንን ብጋብዛችሁ አትናደዱም? ታዲያ ምነው እኔ ላይ ብቻ? ኦኦ ለካ ወዳጄ የሰው ትዕግሥት አፍጫው ላይ ናት ብሎኛል። ግን የሚገርመኝ አፍንጫ በመጥፎ ጠረን ተመታ፣ በየሄድንበት የዓይነ ምድርና የሽንት ጠረን ተደፍና ስታበቃ ትዕግሥት ማንጠልጠያ ሆና ቀረች ማለት ነው? እውነትም ዕቃ መጣል አንወድም እናንተ? ምናልባት ለዚያ ይሆን ውስጣችንና ጓዳችን በትርኪ ምርኪ ሐሳብና መጣል ባለባቸው አሮጌ ዕቃዎች ተጣቦ ቢያጣብበን፣ በየመንገዱና በየሰው ላይ መውደቅ ያበዛነው? ምናልባት ነው!
ሎቤድ ላሻሽጥ ሁለት ደንበኞች ቀጥሬ ስለነበር ወዳጄ የሚለውን ብሎ እንዲለቀኝ፣ “ለምን ወደገደለው አትገባም?” አልኩት። “አንበርብር ዘንድሮ ሳስበው ብዙ ጠላት ያለህ ነው የሚመስለኝ። ስለ አንተ ብዙ እሰማለሁ። እንደሌለው መኖር የሚያዘወትረው ዕድሜውን ሙሉ በድለላ ስም ያጭበረበረውና ያምታታው ገንዘብ ቀልብ ስለነሳው ነው ይሉሃል፤” ሲለኝ አቋርጬው፣ “ሰውዬ የተከበረ የሥራ ሰዓቴ ላይ ከምትቀልድ የምትለውን አትልም?” አልኩት። አያናድድም? እርር ቅጥል ብዬ የመጨረሻ ቃሉን ስጠባበቅ፣ “ልልህ የፈለግኩት መሣሪያ ግዛ ነው፤” አለ። እኔ ደግሞ አንዳንዴ ነገር ይዞርብኝ አደል? እሱ እንዳለው ወይ ሲሉ እንደሰማው ቀልብ በነሳኝ በቀበርኩት ገንዝብ አንድ ማሽን ገዝቼ ፋብሪካ ከፍቼ ገንዘቤን እንድሠራበት የመከረኝ መስሎኝ ነበር። ለነገሩ በዚህ ጊዜ መልዓክ ካልሆነ ስለፋብሪካና ስለማሽን መትከል የሚያዋይ የሚመክር ወዳጅ ይኖራል ብዬ ማሰብም አልነበረብኝም።
ግን አስቀድሜ እንዳልኳችሁ በፍቅርና በመተሳሰብ ላይ በተዘረጋው የብዙ ተባዙ ትዕዛዝ ልጅነቴ ስለተቃኘ፣ ሸብቼም ይኼው ጡት እንዳልጣለ ሕፃን በተላላ ጎኔ እገኛለሁ። እናማ፣ “ይሁን ጥሩ ብለሃል፤ ግን እስኪ መጀመርያ የታማሁትን ዓይነት ሀብታም ልሁንና አስብበታለሁ፤” ስለው፣ “ኧረ በቀላል ገንዘብ እኔ ራሴ አስመጣልሃለሁ፤” ሲለኝ ግራ ገባኝና፤ “እኮ ምኑን?” ብለው፣ “ሽጉጡ!” አለኝና አረፈው። “እኔ የምሸጎጥበትም የምሸጉጥለትም የሚሸጉጥብኝም ጠላት የለኝም፤” ብዬው አፈፍ ብዬ ስነሳ፣ “ተው ግዴለህም መጪው ጊዜ አያስተማምንም እየተባለ ነው፤” ብሎ ትዕግሥቴን ጨረሰው። አላወቅኩትም እንጂ ለካ የእኔም ትዕግሥት አፍጫዬ ላይ ደርሳለች። “ስማ ልንገርህ አገሬ ገና ታብባለች፣ ትበለፅጋለች። ሰላም ይትረፈረፋል፣ ሕዝቦቿም ገና ስለፍቅር ብዙ ይገለጽላቸዋል። ይኼ አንተ የምትለውን ሄደህ ለመሣሪያ ሻጮችና ለአሸባሪዎች ንገራቸው፤” ብዬ ጢሙን አበረርኩለት። ሆ! ምነው ግን ሰው እንዲህ ጭር ሲል አልወድም ሆነ?!
ያልኳችሁን ሎቤድ ገዥንም ሻጭንም አገናኝቼ ለማስፈተሽ ላይ ታች እያልኩ ሳለ ማንጠግቦሽ ደወለች። ሳነሳው “ኧረ ቶሎ ድረስ አንበርብር!” እያለች ሀቲቴን በላችው። የትንፋሽዋ ቶሎ ቶሎ መቆራረጥ የኃይል መቆራረጥ ችግራችንን አስታወሰኝና ተመስገን አልኩ። እንኳንም በኤልፓ እጅ አንተነፍስ ብዬ ነዋ። በዚያው በተቆረጥንበት ነበራ የምንቀረው። ለነገሩ የማይቆራረጥ ነገር ምን አለና? አንዱን ተችተን አንዱን እንተዋለን? ዋሸሁ? ‹‹ረጋ በይና የሆንሽውን ንገሪኝ?›› ስላት ባሻዬ መውደቃቸውን ነገረችኝ። ነፍሴን አላውቅም። ደንበኞቼ እየተስማሙልኝ ስለነበር የሆንኩትን ነግሬያቸው ጥያቸው ጠፋሁ። ሠፈር ስደርስ ‘ኡኡኡ’ ይባላል። ስደርስ ባሻዬ እግራቸው ተሰብሮ ኖሮ በጄሶ ታሾጎ ቀኝ እግራቸው ወደ ላይ ተንጠልጥሏል። ልጃቸው ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል። “ምን ሆነው ነው? ሰው ነው እንዲህ ያረጋቸው እንዴ?” ስል፣ “አዎ!” ተባልኩ። ከዚያማ እኔ ባስኩ።
“ቆይ ተረጋጋ አሁን ብትሄድም አታገኘውም፤” ተባልኩ። “ከስንቱ ተጣልተህ ትችለዋለህ ተረጋጋ፤” የሚለኝ በዛ። ‘ጭራሽ ብዙ ናቸው? እንዴት ቢያስቡ ነው እኚህን የሚያክሉ አዛውንት እግር የሚሰብሩት?” ስል ማንጠግቦሽ፣ “መቼ በእጃቸው ሰበሯቸው አንበርብሬ? በተዘዋዋሪ ነው እንጂ ያገኙዋቸው፤” አለችኝ። እንቆቅልሹ ሲበዛብኝ እግዜር ይስጠው አንድ ጨዋ ነገር የማይወድ ጎረቤት አለኝ፣ “በቅጡ ያልተከደነ ቱቦ ውስጥ ገብተው ነው፤” ብሎ ገላገለኝ። የቱቦውን ሳስብ መቼ ዕለት እንድ አንዳች የሚያህል ውሻ መተላለፊያ መንገድ ላይ እንደ ሞተ የሚያነሳው ጠፍቶ ሽታው በአጠገቡ አልፈውት የሚጓዙትን የአስም በሽተኛ ለዓመታት የታገሰ አስም ቀስቅሶባቸው ሳይታለም ሳይታሰብ ልባቸው ቀጥ ማለቷን የሰማሁት ትዝ አለኝ። እኔ ምለው? እንዳሻን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ያልተገደበ ነፃነት ሕገ መንግሥቱ ሲያረጋግጥልን ጉድጓድ የሚምሰው ላይ ግዴታ አላስቀመጠም እንዴ? “መንገድስ ነበረ ሰባሪው በዛ እንጂ. . .” ያለው ያ ጎረቤቴ ነው!
በሉ እስኪ እንሰነባበት። ባሻዬ እየተጠገኑ ነው። ‘ባሻዬን ያየ ገደል አይያችሁ፤’ የመንደሬ ነዋሪ ምርቃት ሆኗል። እኔና የባሻዬ ልጅ ያልተከደኑ የፍሳሽ ቱቦ አናቶችን ለማስደፈን ያደረግነው ሙከራም አልተሳካልንም። ምክንያቱ ደግሞ ብዛቱ ነው። እንዲያው በአጠቃላይ መሬት ቆንጣጭ መሆናችን እንጂ አንድ ቀን እኛም መንኮራኩር ያመጠቅን ቀን፣ ከህዋ ቁልቁል ወደ አዲስ አበባ አጮልቆ የሚያይ ካሜራ የሚቀርፀው ትልቅ ገደል መሆን አለበት። “ምን አለ በለኝ፤” ብለው የባሻዬን ልጅ፣ “መቼም መንኮራኩር አናመጥቅም ብለህ ነዋ፤” እያለ ሳቀ። ሲስቅ ምን አስታወሰኝ ከቅርብ ዓመታት በፊት እንጦጦ ላይ ተቋቋመ የተባለው የኢትዮጵያ ስፔስ ኤጀንሲ (ስያሜውን ካልተሳሳትኩ) ትዝ አለኝ። ሳተላይት የማምጠቅ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመራቀቅ ህልማችንን ብደግፍም በበኩሌ የምድሩን ሳንጨርስ ብንንጠራራ ምን ዋጋ አለው ብዬ ራሴን እጠይቀዋለሁ። ሌላውማ ራሱን ቢጠይቅ ስብራታችንም በዳነ፣ አስማችንም ባልተቀሰቀሰ ነበር።
“መንገድ ለመንገድ መፀዳዳት ነውር ነው፤” እየተባለ እንደ ጨቅላ በሚነገረው ኅብረተሰብ ብቻ እየፈረዱ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ችላ ብሎ ለስፔስ ምርምር፣ ለሳተላይት ማምጠቅ ፕሮጀክት በጀት መመደብን ሳስብ ግርም ይለኛል፡፡ ኧረ አላየው ብለን እንጂ ግራ የሚያጋባን የልማት ዘርፍ የለም ጎበዝ። መንገድ ገንብተንና መርቀን፣ ለመንገዱ ማስፋፊያ ጭቃ ቤቶችን አፍርሰን ስናበቃ፣ ከመንገዱ ባሻገር ‘ታላቅ የስፖርት ማዕከል ለምርታማና ጠንካራ ዜጎች ማፍለቂያ’ ለማስገባት ኮንትራት ለቻይና ስንሰጥ፣ በስንት መከራ በብድር ያለቀውን መንገድ ጭምር ለመልሶ ማልማት አብረን የሰጠነው ይመስል አፈር ተሸካሚ ከባድ መኪኖች ጭቃ በጭቃ ያደርጉልኛል። ጭቃ ቤት አፋርሰን መንገድ አስፋፍተን አስፋልት ጭቃ በመለቅለቅ ተግባር ተጠምደን ዕቃ ዕቃ ጨዋታ ያለፈብን ሙሉ ሰዎች ነን እንላለን። ድህነትና አፈር አብረው የተቦኩ ይመስል ጭቃ ቤት ላይ አምፀን፣ አፍስሶ በመልቀም የሞኝ ጨዋታ ስንሰማራ ለልማት ያለንን ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነትና ርብርብ የሚያሳይ ነው ይባላል። ባሻዬ ያሉኝ ነው . . .፤ “ተሻለዎ?” ስላቸው “የት ይቀራል አንበርብሬ። ድጋሚ ወድቄ፣ ድጋሚ ልሰበር፣ ድጋሚ ልጠገን መሻሉ የት ይቀራል?” ነበር ያሉኝ። ‘ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር . . .’ የሚለው አባባል ትዝ እያለኝ ስለሆነ ሰላም ሁኑ! መልካም ሰንበት!