Tuesday, July 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

እንስሳትን የማላመድ ሳይንሳዊ ትንታኔ

በሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር)

በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፎች ሳይንስንና ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ሕዝባዊ ለማደረግ እየተሞከረ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ልዩ ትኩረት እየተሰጠ ነው፡፡ ሌሎችም የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (በተለይም የሙያ ማኅበራት) በፊት ከነበረው በላቀ ደረጃ ለሳይንስ  ትኩረት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ አንዱ ዋና ዓላማው ሳይንስንና ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ሕዝባዊ ማድረግ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳካት ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸው ጽሑፎች ለሕዝብ በሚዳረሱበት መልኩ አዘጋጅቶ አሠራጭቷል፣ ወደፊትም በዚሁ ተግባር ይቀጥላል፡፡ በተጨማሪ ለዚሁ ዓላማ መተግበሪያ ወርኃዊ የውይይት መድረክም በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህችም ስለእንስሳት ማላመድ ያዘጋጀኋት ጸሑፍ ከዚሁ አንፃር (ሳይንስንና ሳይንሳዊ አስተሳሰብን/ዘዴ ማኸዘብ) ትታይልኝ፡፡

የዕውቀት ማጠናከሪያ ዘዴ

የእንስሳት ማላመድ ተግባርን ሳይንሳዊ ይዘት ባለው መንገድ ከመተንተኔ በፊት አንድ የዕውቀት ማጠናከሪያ፣ ማዳበሪያ ዘዴ (ሳይንሳዊ ዘዴ) ላውሳ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የዚህች ጽሑፍ ዓላማ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ሕዝባዊ ማደረግ ስለሆነ፣ የዕውቀት ማዳበሪያ ዘዴውም የጽሑፏ አካል ተደርጎ መወሰድ ይገባዋል እላለሁ፡፡ አዲስ ዕውቀትን ለማስተላለፍ ቀደም ተብሎ በሚታወቅ ጉዳይ/ተግበር ላይ መገንባት ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ስለሆነም አዲስ ዕውቀት ለማስተላለፍ ‹‹የቤት አንስሳትን ማላመድ››፣  እንዲሁም ለዕውቀት ማጠናከሪያ ዘዴን (ሥልት) ለማመላከት ‹‹ማጭድን›› እንደ ምሳሌነት መምረጤ ያለምክንያት አይደለም፡፡

ዕውቀት በሚዳብርበት ጊዜ (ሳይንሳዊ ዕውቀትንም ያካትታል) ጥያቄው ግልጽ ካልሆነ ትክክለኛ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡ ጉዳዩን በጥልቅ ያሰቡበት ግለሰቦች ስለአንድ ነገር/ጉዳይ መጠየቅ ያለባቸውን ጥያቄዎች አጠር ባለ መልክ አበርክተውልናል፡፡ እነዚህም ጥያቄዎች ምን? ለምን? ማን? የት? መቼና እንዴት? ናቸው፡፡ ይህ ግልጽ እንዲሆንልን ምሳሌ ወስደን ጥያቄዎች ተግባር ላይ እናውላቸው፣ ምሳሌያችንም ‹‹ማጭድ›› ይሁን፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ስድስት ጥያቄዎችን (ምን? ለምን? ማን? የት? መቼና እንዴት?) በመሰንዘር ስለ ‹‹ማጭድ›› ዘርዘር ያለ መረጃ ማካበት ይቻላል፡፡

ምን ለሚለው መልስ የእጅ መሣሪያ የሆነው ማጭድ ነው፡፡  ማጭድ ለምን ያገለግላል? ማጭድ በመሠረቱ ሳር መሰል ሰብሎችንና ለሳር ማጨጃነት ነው የሚያገለግለው፡፡ ከግብርና ጋር ቅርብ ቁርኝት አለው፡፡ ሰብል ከማሳ በማጭድ ተከልቶ ከዚያ በኋላ ነው ፍሬው ከገለባው አውድማ ላይ በማበራየት የሚለያይ፡፡ መቼ? የትና ማን? ለሚለው መልሱ እነሆ፡፡ በቅርብ ምሥራቅ የማጭድ ቅሪት ከ18,000 እስከ 8,000 ዓመታት ባስቆጠሩ የቅሪት አካባቢዎች ተገኝቷል፡፡ ያም የድንጋይ ዘመን (ከሁለት ሚሊዮን እስከ 3,300 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት) የሚባለው ዘመን ነው፡፡ እንዴት? ለሚለው በዚያን ዘመን ማጭድ ከባልጩት (Flint) ይሠራ አንደነበረ ከተገኙት የማጭድ ቅሪቶች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማጭድ ከሌሎችም ቁሳቁስ ይበጅ እንደነበረም ማስረጃ ተገኝቷል፡፡ ለምሳሌ ከመጋፊያ/የትከሻ አጥንት፣ ከቀንድ፣ ወዘተ፡፡ በብረት ዘመን በብዙ አካባቢዎች ማጭድ ከብረት ይሠራ ነበር፡፡ መደበኛ ቅርፁም የክብ ግማሽ፣ ማለት ደጋን መሰልና እጀታ ያለው ሲሆን፣ የተለያዩ ቅርፆች ያሏቸው የማጭድ ዓይነቶች በተለያዩ አካባቢዎች ለዘመናት ሲበጁ (ሲሠሩ) ነበር፡፡ እኔ ባደግኩበት አካባቢ ለሁለት የሚመደቡ የማጭድ ዓይነቶች አሉ፣ አንዱ ዓይነት ጥርስ አልባ የሆነ (መጋዝ የሌለው) ልሙጥ ሲሆን፣ ያን ዓይነቱ ገለዶ ማጭድ ይባላል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚሠራው በአካባቢ ከሚገኝ የብረት ማዕድን ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ጥርስ (መጋዝ) መሰል  ያለው ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ አለቤን/አረቤ ማጭድ ይባላል፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ማጭድ በገጠር አይሠራም፡፡ እንደሌሎች መደበኛ የግብርና መሣሪያዎች ሁሉ፣ ማጭድም ከመደበኛ አገልግሎቱ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች (ጃፓን፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ፣ ፊሊፒንስና ማዕከላዊ አፍሪካ) የጦር መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ እዚህ ላይ የበውቀቱ ሥዩምን አንድ ግጥም መጥቀስ ይበጅ ይሆናል፡፡

ማጭድ ይሆነን ዘንድ፣ ምኒሽር ቀለጠ

ዳሩ ብረት እንጂ፣ ልብ አልተለወጠ

ለሳር ያልነው ስለት፣ እልፍ አንገት ቆረጠ፡፡ 

ይህንን የዕወቅት ማዳበሪ ሥልት/ዘዴ ከዳሰስኩ በኋላ የዱር እንስሳት እንዴት ወደ ቤት እንስሳትነት እንደተቀየሩ (እንደተላመዱ) የሚከተለውን ሳይንሳዊ አስተሳሰብ አቀርባለሁ፡፡

እንስሳትን ማላመድ

በመጀመርያ እንስሳትን ማላመድ ለምን አስፈለገ? ዋና ዋና ምክንያቶች እነሆ፡፡ ምግብ በቀላሉና ብዙ ሳይለፉ ለማግኘት (ምሳሌ ከከብት ሥጋና ወተት) አንዲቻል እንስሳቱ በጉልበት ሥራ እንዲሰማሩ ብሎም ሰውን እንዲረዱ (ማረሻ ጎታች በሬና ፈረስ ለጭነት ወዘተ) እና አጫዋች ጓደኛ ለማፍራት (ምሳሌ ውሻ) ናቸው፡፡

እንስሳትን በጊዜያዊ መልክ ማላመድ እንስሳቱን የቤት እንስሳ አያደርጋቸውም፡፡ እንስሳት በቁጥጥር ሥር ውለው ሰውን ሊየገለግሉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ዝሆን ለትራንስፖርት፣ እንዲሁም ለጦርነት ዘመቻ በብዙ አካባቢ አገልግሏል፣ እያገለገለም ነው፡፡ ግን ይህ አገልግሎት መስጠት ዝሆንን በቤት እንስሳነት መመደብ አያስችልም፡፡ የቤት እንስሳት ለመባል እንስሳቱ በሰው ቁጥጥር ውለው መራባት መቻል አለባቸው፡፡ የሰው ልጅ ያላመዳቸው እንስሳት፣ ለመልመድ የሚችሉት ብቻ ናቸው ይባላል፡፡ ይህም ማለት ለመላመድ የሚያበቃቸው የሚያመቻቻቸው ቅድመ ሁኔታ የበራሂ (የህያው የዘር ማስተላለፊያ)  መሠረት አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ ያም ከሥረ መሠረቱ ተፈጥሮ ለማዳ እንዲሆኑ የሚያስችሉ በራሂዎችን አበርክታላቸዋለች እንደ ማለት ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ማስረጃ ውሻ ነው፡፡ ውሻ ምንም ግንኙነት ባልነበራቸው ቦታዎች (በተለየዩ የዓለም ክፍሎች) ለማላመድ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በእስያና ሌሎች አካባቢዎች፡፡ ይህም ውሻ የመልመድ ቅድመ ሁኔታን በተፈጥሮ ተጎናጽፎ እንደነበረ ያመለክታል፡፡  ያ ባይሆን ኖሮ አለበለዚያ ሁሉም ቦታ የመላመድ ዕድሉ የመነመነ ይሆን እነደነበረ መገመት አያዳግትም፡፡

የሰው ልጅ የሚያላምዳቸውን እንስሳት ሲመረጥ፣ የተለያዩ የእንስሳት ባህሪያትን አጢኖ ፈትሾ ነው ለማላመድ የሚሞክረው፡፡ መሥፈርቶቹም ብዙ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹን እነሆ፡፡ አንደኛ እንስሳው በአጭር ዘመን (አንፃራዊ ከሰው ዕድሜ አንፃር ታይቶ) መራባት መቻል፣ እንዲሁም በቶሎ ለማደግ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ጎሪላ ሙሉ አቅመ መጠን ለመድረስና ሙሉ አካል ተቀናጅቶ ለመራባት የሚበቃ፣ ረዥም ጊዜ ይወስድበታል፡፡ 15 ዓመት ሲሞላው ነው፡፡ ዝሆንም ለመውለድ ተመሳሳይ ዕድሜ ያሻዋል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ጎሪላም ሆነ ዝሆን ዘር ለመተካት (ለማራባት) ብዙ ዘመን ስለሚፈጅባቸው፣ እነሱን ማላመድ ትርጉም የለሽ ይሆናል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ እነኝህን ሁለት የእንስሳ ዝርያ ማላመድ ይቻል ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ቅጠል በል ናቸው (ከሰው ልጅ ጋር ምግብ አይሻሙም)፡፡ በተጨማሪ ከታች እንደሚብራራው ሌሎች ለቤት እንስሳነት የሚያበቁ ባህሪያት አሏቸው ሁለቱም በመንጋ ነው የሚሰማሩ፣ ሁለቱም አውራና ተራ (ጭፍራ)፣ አለቃና ምንዝር አላቸው ወዘተ.፡፡ አንዷ ባህሪ (የዕድግት ዘመን) ስላልተሟላች ብቻ ሁለቱም ከማላመድ ምርጫ ተገለሉ፡፡

ሁለተኛ እንስሳው በውስን አካባቢ መራባት መቻል አለበት፡፡ ለመራባት ሰፊ ቦታ የሚሻ እንስሳን (ምሳሌ ፓንዳና አቦ ሸማኔ) የቤት እንስሳ ማድረግ ያዳግታል፡፡ ለምሳሌ አቦ ሸማኔን (የድመት አስተኔ) ብንወስድ ይህን እንስሳ ለማራባት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም አቅመ መጠን የደረሱ ሴትና ወንድ አቦ ሸማኔዎች ወሲባዊ ግንኙነት ሲያደርጉ በይፋ አይደለም፣ ሰወር ያለ ቦታ ሆነው ነው፡፡ ይህን ዓይነት ሥፍራ ሰው በሚኖርበት አካባቢ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ በተጨማሪ ኦቦ ሸማኔ ወስባዊ ግንኙነቱ ውስብስብ የሆነ የመዳራት ሥርዓት አለው፡፡ ሴቷ ኦቦ ሸማኔ ለመዳራት በጎረምሶች (አቦ ሸማኔዎች) ለቀናት መባረር አለባት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የምትዳራና ከፈቀደችው አባራሪ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት የምታደርገው፣ ግንኙነቱም የሚደረገው ሰወር ያለ ቦታ አካባቢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን መሰል ሥርዓት በሠፈር በለማዳነት ለማስተናገድ ያዳግታል፡፡

 ሦስተኛ እንስሳቱ በመንጋነት (አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው) መሰማራት የሚችሉ መሆን አለባቸው (ያንን ዓይነት ባህሪ እንዲኖራቸው ያሻል)፡፡ መንጋው በአንድ አካባቢ ቢሰማራም፣ ያንን አካባቢ ከሌሎች የእንስሳ መንጋዎች ጋር ለመጋራት የሚችል (መጋራቱ በጊዜ ሊለያይ ይችላል) መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለት መንጋው የእኛ መሰማሪያ ብቻ የሚለው አካባቢ የለውም፡፡ የመሰማሪያ ቦታዎችን ሌሎች መንጋዎች ሊሰማሩባቸው ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የእንስሳቱ መንጋዎች ምግብ የማግኛ ቦታዎችን፣ ከሌሎች መንጋዎች ጋር መጋራት የሚያስችል ባህሪ እንዲኖራቸው ያሻል፡፡  

አራተኛ  የእንስሳት ኅብረት (ግንኙነት) በሥርዓት የተደነገገ (አውራና ተራ፣ አለቃና ምንዝር፣ ወዘተ.) ያለው እንዲሆን ይመረጣል፡፡ ይህን ዓይነት ሥርዓት በፈረስ መንጋ፣ በቀንድ ከብት መንጋ፣ እንዲሁም በሌሎች ለማዳ እንስሳዎች ላይ የሚታይ ባህሪ ነው፡፡ አምስተኛ  እንስሳው የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ቢበላ እንዲሁም ምግቡን ከሰው ጋር ባይጋራ ይመረጣል (ሰው የማይበላውን ምሳሌ ሳር በል ቢሆን)፡፡ ምግብ ከሰው ጋር የሚጋሩ እንስሳትን ለምሳሌ ሥጋ በሎችን ማላመድ ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡ ለዚህ ጉዳይ በምሳሌነት እንዲያገለግሉ በግንና አንበሳን እንውሰድ፡፡ በግ ከሚበላው ምግብ (ምሳሌ በቆሎ) አሥር በመቶ ገደማ ብቻ ነው የበግ አካል ለመሆን የሚችለው፡፡ ወይም ወደ በግ ሥጋነት የሚቀየረው፡፡

ስለሆነም እያንዳንዳቸው አምሳ ኪሎ የሚመዝኑ አሥር በጎች፣ በድምሩ (አሥሩም) 500 ኪሎ የበግ ሥጋ ለማግኘት፣ በጎች 5,000 ኪሎ በቆሎ መመገብ አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ እያንዳንዳቸው 250 ኪሎ ከሚመዝኑ ሁለት አንበሶች በድምሩ 500 ኪሎ የአንበሳ ሥጋ ለማግኘት፣ 5,000 ኪሎ የበግ ሥጋ መብላት አለባቸው፡፡ ይህም ወደ በቆሎነት ሲመነዘር 50,000 ኪሎ በቆሎ ይሆናል፡፡ ስለሆነም አንበሳን ለሥጋ ምርት ለምግብነት ማላመድ ብሎም ማራባት ኪሳራን ያስከትላል፡፡ ስድስተኛ ለማላመድ የሚመረጠው እንስሳ ፀባይ መልካም፣ ገራም (የተረጋጋ) በቀላሉ ሰው ሊቆጣጠረው የሚችል መሆን አለበት፡፡ እንስሳው ጀርጃራ ቀዥቃዣ ከሆነ ያንን ዓይነት እንስሳ በውስን ቦታ ማላመድ ያዳግታል፡፡ ለምሳሌ ዜብራ (Zebra) አንድ መጠፎ ፀባይ አለው፡፡ ሰው ሲጠጋው የሰውዬውን ገላ አመቺ ቦታ ላይ ነክሶ አልለቅም ይላል፣ አንዳንዴም ይራገጣል፡፡ ይህን ዓይነት እንስሳ ማላመድ ያዳግታል፡፡

እንስሳት እንዴት ተላመዱ?

የእንስሳት ማላመድ ሒደት በእርግጠኝነት መተንተን አይቻልም፡፡ ከታች የሚሰጠውም አስተያየት ግምታዊ ነው፡፡ ለምሳሌ የበጎችን አዳኝነት የሰው ልጅ በሞኖፖል ለመቆጣጠር  (በግ የሚበሉ ከሰው ሌላ እንስሳት አሉ፣ ነብር፣ ቀበሮ፣ ወዘተ.) ብሎም ለጥበቃም እንደሚያመች፣ ታዳኞችን (በጎችን) እያባረሩ ወደ አንድ ሸለቆ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፣ አካባቢውን የሰው ልጅ ይቆጣጠር እንደነበረም መገመት ይቻላል፡፡ ከበጎች መንጋ መካከልም፣ ሰዎች ዘገምና ቀናዎችን እየመረጡ በማላመድ ሥርዓት ተሰማርተው እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡ በዚህም ሒደት አስቸጋሪ፣ በጥባጭ፣ ተዋጊና ፀብ ጫሪ የነበሩትን የበግ አውራዎች እንዲሁም ጀርጃራ፣ ከውካዋና መንቃራ የነበሩ እናት በጎች (ሴት) ለስለት መዳረግ አንዱ የማላመድ ምርጫ ተግባር ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡  በዚህ ሥልት ቀናዎች፣ የተረጋጉት፣ ደልዳሎች ሰውነተ ሙሉ ሴቶችና አውራዎች እየተመረጡ ማላመድ፣ ብሎም  የበግ መንጋ መመሥረት እንደተቻለ ይገመታል፡፡ በዚህ ሒደት ከትውልድ ወደ ትውልድ ረጋ ያሉ ወፍራም በቀላሉ የሚሳቡ በጎች ተራቡ፡፡ ከሌላ አንፃር ታይቶ ሰዎች በጎችን በነጠላ አድነው በአካባቢያቸው አቆይተው አስብተው ይበሉ ነበር ብሎ መገመትም ይቻላል፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ የሚንከባከቧቸው በጎች ቁጥር እየጨመረ ሄደ ብሎም መገመትም ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ከታገዱት በጎች፣ ጥቂቶች መክበድ፣ መውለድና መዋለድ ጀመሩ፡፡ ረጋ ያሉት (በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያመቹት) ተትተው አስቸጋሪዎች ታርደው ተበሉ፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ አመለ መልካሞች፣ ለስላሳዎች እንዲራቡ ተደረጉ፡፡ አመለ ቢሶች ተበሉ ብሎ መገመትም ይቻላል፡፡

እንግዲህ በዚህ መንገድ የሥጋ (የቀንድ) ከብቶችም ሆኑ የጋማ ከብቶች ቀስ በቀስ መላመድ ጀመሩ ተብሎ ይገመታል፡፡ ለማዳ የተደረጉት (የተላመዱት) እንስሶች ጥቂቶቹ የምግብ (ሥጋ፣ ወተትና እንቁላል) ምንጭ ሆኑ፡፡ እንዲሁም ሌሎች በጉልበት ሥራ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ (ፈረስ ግመል)፡፡ እንዲሁም ለእርሻ ሥራ ወዘተ. በአንደ ቦታ የተላመዱ እንስሳት ወደ ሌሎች ቦታዎች ተሠራጭተዋል፡፡ የቀንድ ከብት ለመጀመርያ ጊዜ ከእስያ ወደ አፍሪካ የገባው ከክርስቶስ ልደት በፊት 5,000 ዓመት ገደማ ነው ይባላል፡፡ የከብቱም ዘር ሻኛ የሌለው ባለረዥም ቀንድ ነበር፡፡ ከዚያ ሻኛ የሌለው ባለ አጭር ቀንድ የከብት ዘር በክርስቶስ ልደት በፊት በ2,500 ዓመት ገደማ፣ ባለሻኛ የቀንድ  ከብት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1,500 ዓመት ገደማ ወደ አፍሪካ ገቡ ይባላል፡፡ ባለሻኛ ቀንድ የከብት ዘር ወደ አፍሪካ አኅጉር የገባው በግብፅ በኩል እንደነበር ይገመታል፡፡ ከዚያም የዓባይን ወንዝ ተከትሎ ወደ ሌሎች አፍሪካ አገሮች ተሠራጨ፡፡ ይህ ዜቡ የሚባለው የከብት ዘር በብዛት በቀይ ባህር አካባቢ አገሮች ከዚያም በኋላ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ  አገሮች (ኢትዮጵያ ጭምር) በብዛት ተሠራጨ፡፡ ሰዎች ከአጥናፍ አጥናፍ ሲሠራጩ ያላመዷቸው እንስሳትም አብረዋቸው ዘመቱ፡፡ ከአሥር ሺሕ ዓመት በፊት ዓለማችን ጥቂት ሚሊዮኖች የእንስሳት ስብስብ (ላም፣ በሬ፣ በግ፣ ፍየልና ዶሮ ወዘተ.) ብቻ ነበሩ የሚኖሩባት፡፡ በዘመናችን እያንዳንዱ ዓይነት እንስሳ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ (በግ፣ አሳማ፣ ላም፣ በሬና 25 ቢሊዮን በላይ ወፎዎች በብዛት ዶሮዎች) ሰፍረውበታል፡፡ ዋና ዋናዎች የቤት እንስሳት መቼና የት አንደተላመዱ በሰንጠረዥ መልክ ማቅረቡ ይቀል ይሆናል፡፡

ዋናዎች የተላመዱ የእንስሳት መቼና የት አካባቢ እንደተላመዱ አመልካች ሰንጠረዥ

 

ምን?

መቼ ? (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ዓመት

 

የት?

 

ምን?

መቼ?

(ከክርስቶስ ልደት በፊት) ዓመት

 

የት?

 

 

ውሻ

 

 

30,000

አውሮፓ፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት አንደተላመደ ይገመታል

 

 

የውኃ ጎሽ

 

 

 

4,000

 

 

ህንድ፣ ቻይናና ፊሊፒንስ

ፍየል

10,000

ፐርሽያ (ኢራን)

ንብ

4,000

በብዙ አካባቢ (አውሮፓ፣ አፍሪካና እስያ)

አሳማ

9,000

ቻይና

ግመል

4,000

ዓረብ አገር

በግ

9,000-8,000

ቅርብ ምሥራቅ

ፈረስ

3,500

ካዛኪስታን

በሬና ላም (ከብት) የቅርብ ምሥራቅ ዝርያ

 

 

8,000

 

 

ቅርብ ምሥራቅ

 

 

የሐር ትል

 

 

3,000

 

 

ቻይና

በሬና ላም (ከብት) የህንድ ዝርያ

8,000

ህንድ

እርግብ

3,000

በሜዲትራንያን ባህር ዙሪያ ባሉ አገሮች

ድመት

8,000-7,000

ምዕራብ እስያ

ላማ

2,400

ፔሩ/ ቦሊቪያ

ዶሮ

 

6,000

 

ህንድ/ ሩቅ ምሥራቅ

 

ጊኒ ፋውል

 

 

2,400

 

አፍሪካ

አህያ

5,000

ግብፅ

ጥንቸል

600

አውሮፓ

ዳክዬ

4,000

ቻይና

ተርኪ

180

ሜክሲኮ

 

የተላመዱ እንስሳትን ማዳቀል

እንስሳት ለማዳ ከተደረጉ በኋላ በሰው ፍላጎት ላይ ተመርኩዞ የሚፈለገውን ለማግኘት ሲባል (ቅርፅ፣ ፀባይና የአካል መጠን) ተዳቅለዋል፡፡ ከላይ አንደተጠቀሰው ለማዳ እንስሳት ሲዳቀሉም የሰውን ፍላጎት እሳቤ አደርጎ ነው፡፡ ለምሳሌ ፈረሶች፣ ለፈረስ እሽቅድምድም፣ ወይም ሰረገላ/ጋሪ ለመጎተት፣ ወይም ለልጆች ግልቢያ መለማመጃ እንዲሆኑ መጠነ ውስን አንዲሆኑ ታስቦ ይዳቀላሉ፡፡

ከሁሉ በፊት ለማዳ የተደረገው ውሻ ነው፡፡ ያም የሰው ልጅ በግብርና ላይ ከመሰማራቱ በፊት ነበር፡፡ ዘመኑም በጣም የተራራቁ ግምቶች ተሰጥቶታል፡፡ ከ30 ሺሕ ዓመት እስከ ዘጠኝ ሺሕ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት፡፡ የውሻ ዝርያ ማዳቀል ከሁሉም እንስሳት በጎላ ሁኔታ ይታያል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ውሾችም ሲዳቀሉ የሰውን ለጅ ፍላጎት እንያሟሉ ተደርገው ነው፡፡ ምንም እንኳ የውሻ የዘር ሐረግ አንድ ቢሆንም (የቤት እንስሳ የተደረገ የተኩላ ዘር) የሰው ልጅ ውሻን እንደፈለገው አዳቅሎ፣ የተለያዩ ቅርፆች ያሏቸው የውሻ ዲቃላዎች ለማግኘት ችሏል፡፡ ውሻ በመሠረቱ ተኩላ (Wolf) ነው፡፡ የዘመናችን  የውሻ ዓይነቶችን ስናስተውል፣ አንዳንዶቹ ምንም የተኩላ ደም ያለባቸው አይመስሉም፡፡ የተኩላ ዘር የሚያስመስላቸው ቅርፅም ሆነ ሌላ ይዘት የላቸውም፡፡ አንዳንዶች በመጠን ከተኩላ ይልቃሉ፣ ለዚህም ማረጋገጫ ‹‹ግሬት ዴንስ›› የሚባለውን የውሻ ውልድ መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡ እንዳንዶች የድመት መጠን ያላቸውና ከተኩላ ጋር የማይመሳሰሉ ናቸው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ እንድትሆን የቻይናዋን ውሻ ውልድ ‹‹ፒኪንጊስ›› በመባል የምትታወቀዋን  መመልከት ያሻል፡፡ አንዳንዶች ‹‹ውልዶች›› ለሩጫ ተወዳዳሪነት የተዳቀሉ ናቸው (ምሳሌ ግሬይ ሃውንድ)፡፡ እነሱም  ረዥም  እግርና ቀጭን ወገብ፣ ወዘተ. ተቀዳጅተዋል፡፡

በእንስሳት ማላመድ ሒደት ያልታለሙ (ተጓዳኝ) ክስተቶች

የእንስሳት እርባታን ብሎም እንስሳትን ለምግብ ግብዓት እንዲሆኑ የተደረገውም እንቅስቃሴ፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢንዱስትሪ መሰል የኢንዱስትሪ አካል ነው፡፡ በጥንት ዘመን እንስሳት አቀፍ እምነት ንስሳት ልክ እንደ ሰው ሁሉ ነፍስ አላቸው የሚለው ግንዛቤ (እምነት) ተረስቶ (ወደ ጎን ተትቶ) እንስሳትን እንደ ዕቃና እንደ ግዑዝ አካል ማየት ተጀመረ፡፡ የእንስሳት ቁመናቸውና ቅርፃቸው፣ ወዘተ. በቴክኖሎጂ እገዛ እየተወሰነ መጣ፡፡ ያም እንስሳትን የፋብሪካ ዕቃ መሰል አድርጓቸዋል፡፡

በእንስሳት ማላመድ ተከትሎ (መንስዔ) ብዙ እንስሳት ለዘለዓለም ለስቃይ ተዳርገዋል፣ ለምሳሌ በግ፣ ፍየል፣ አሳማና ዶሮ፡፡ በቅድመ ግብርና አብዮት ሰዎች ሥጋ የሚያገኙ ከሚታደኑ የዱር እንስሳት ነበር፡፡ ለምሳሌ ያልተላመዱ በጎች፣ ወዘተ፡፡ በግን እንደ ምሳሌነት ብንወስድ በዚያን ወቅት በአደን የበጎች ቁጥር እንዳይመነምን ግለሰቦች የሚያድኑት አቅመ አካል የደረሱ ወንዶችና ሌሎች በበሽታ የተጠቁ ኮሳሳ በጎችን እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡ እናቶች፣ ወላጆችና ወጣቶች (ቄቦችና ወጠጤዎች) ከታደኑ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚታደኑት በጎች ቁጥር ስለሚያሽቆለቁል፣ እነሱ አይታደኑም ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ በተጨማሪ በጎች በሌሎች አዳኞች (ሰውም ሆነ አውሬ) እንዳይበሉ መከላከል (መጠበቅ) ያስፈልግ እንደነበር መጠርጠር ይቻላል፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ያን መሰል ተግባር ይከናወን የነበረው የሰው ልጅ የሚታደኑ እንስሳትን በሞኖፖል ለመቆጣጠር እንዲያመቸው እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡

ሌላ ጉዳይ እንፈትሽ፡፡ ላም በፍጥረት ዝግመተ ለውጥ ለማዳ ከመደረጓ በፊት፣ ለመተካካትም ሆነ ህያው ሆኖ ለመቆየት የተጎናፀፈቻቸው ባህሪያት አሏት፡፡ ከባህሪያቱም ጥቂቶቹ ከሌሎች ከብቶች ጋር አብሮ የመሰማራት ፍላጎት ነው፡፡ ከሌሎች ከብቶች ጋር አብራ ካልዋለች፣ ከወይፈን ጋር ለመገናኘት ስለማትችል የዘር መተካት አጋጣሚ አይኖርም፡፡ የእንስሳትን አብሮ መሰማራት ሁኔታ ከሌላ አንፃር እንመልከት፡፡ ጥጃዎች (እምቦሳዎች) ከሌሎች እምቦሳዎች ጋር አብረው ሲፈነጥዙ ሲቦርቁ ለመዋል ካልቻሉ፣ አብሮ ከመኖር የሚገኙ የሰላማዊ ኑሮ  ባህሪያትን አያዳብሩም፡፡ ይህ የጋራ ሥምሪት የሚያገለግለው፣ በእንስሳት መካከል ያለ ተፈጥሯዊ ባህሪ ኮትኩቶ ለማዳበር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ እምቦሳዎች የእናት ፍቅር እንዲያድርባቸው ያመቻቻል፡፡ እንዲሁም እናቶች የልጆች (እምቦሳዎች) ፍቅር እንዳይላላ በዝግመተ ለውጥ የተገኙ ባህሪያት (በበራሂ የሚገዙና የሚስተናገዱ) እንዳይመነምኑ ማድረግ ያስችላል፡፡ ይህንን ጠለቅ ባለ ሁኔታ በጥሞና የተገነዘቡ ግለሰቦች እምቦሳዋን (ልጇን) ያለፍላጎቷ የምትነጠቅ ላም (እናት)፣ እንዲሁም ከእናቶቻቸው (ላሞች) እንዲገለሉ የሚደረጉ እምቦሳዎችን (ልጆችን) ሁኔታ አጢነው አድራጊውን ይኮንናሉ፡፡ የድርጊቱ ኮናኞች የእንስሳትን ተፈጥሯዊ ባህሪን መግታትና መከልከል እንደ ከፍተኛ በደልና ቅጣት መታየት አለበት፣ ይህን አድራጊዎችም እንደ ከፍተኛ ወንጀለኞች መታየት አለባቻው ብለው ያምናሉ፡፡ ዶሮን ስንመለከት ደግሞ እንቁላል የሚጥሉ (እንቁላል በማምረት ሒደት) እናት ዶሮዎች ክንፍ ማራገብ በማይችሉበት ሁኔታ በትንሽ ወህኒ ቤት መሰል አካባቢ ታጉረው፣ እንቁላል ለማምረት የሚያስችል ጥሬ ዕቃ (ምግብ) ተሰጥተው፣ የሰው ምግብ የሚሆን ውጤት (እንቁላል) በፋብሪካ ይዘት ያበረክቱ ጀመር፡፡ በዘመናችን ዶሮ በበራሂ አማካይነት ከትውልድ ትውልድ ይተላለፍ የነበረን ተግባር ልታስተናግድ አትችልም፡፡ ለምሳሌ ክንፍ ማራገብና ዞር ዞር ብሎ ጥራጥሬ መለቃቀም በአጠቃላይ ዶሮ ተፈጥሮ የለገሳትን ፀጋና ነፃነት ተገፋለች፡፡

የእንቁላል ፋብሪካው ውጤታማነቱ ዝቅ ሲል (እንቁላል መጣል ሲቀንስ) በመቶዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎች  ያበረከተች እናት ዶሮ እንደ አልባሌ  አንገቷ ተጠምዞ፣ ለሕልፈት ተዳርጋ ሙቅ ውኃ ውስጥ ትጨመራለች፡፡ ከዚያም ሌላ ዓይነት የፋብሪካ ውጤት መሰል ሆና ፀድታ (ላባ አልባ ሆና) ለምግብነት ተዘጋጅታ ለገበያ ትቀርባለች፡፡ በዶሮና በአጠቃላይ በእንስሳት ላይ ለሚደርሰው ግፍ ለማን አቤት ይባላል?

የዶሮን ቋሚ ዕድሜ (የሕይወት ዘመን) ብንወስድ ከሰባት እስከ 12 ዓመታት ነው፡፡ እንዲሁም የላምንና የበሬን ዕድሜ ብንወስድ ከ20 እስከ 25 ዓመታት ነው የሚኖሩት፡፡ ዶሮዎችም ሆኑ ከብቶች (በሬና ላም) ከላይ ለተጠቀሱት ዘመናት ህያው ሆነው ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢታወቅም፣ እነዚህ እንስሳት ገና ለማዳ ሳይደረጉ  (የዱር እንስሳት እንደነበሩ)፣ ብዙዎች የዕድሜ ዳርቻዎቻቸውን ሳይቀናጁ፣ ሕይወታቸው ያልፍ እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡ ሆኖም መጨረሻው የዕድሜ ክልል ውስጥ የመድረስም ዕድል ነበራቸው፡፡ በተቃራኒው በአሁን ዘመን በሠለጠኑ አገሮች የሚኖሩ አሳማዎች፣ ዶሮዎችም ሆኑ ከብቶች (ላምና በሬ)፣ ሕይወታቸው በአጭር ነው የሚቀጨው፡፡  ዶሮዎች ጥቂት ሳምንታት እንዲሁም ከብቶች ጥቂት ዓመታት ብቻ ነው ህያው ሆነው እንዲቆዩ የሚፈቀድላቸው፡፡

በዚያ ዘመን ክልል ውስጥ ነው (በሳምንታት/በወራት) ለሕልፈት የሚዳረጉት (የሚታረዱት/የሚገደሉት)፡፡ የተወሰነ የአካል መጠን ከተቀዳጁ በኋላ ለማዳ እንስሳቱን መቀለብም ሆነ መንከባከብ ትርፍ የለውም፡፡ አንድ ዶሮ በአማካይ በ12 ሳምንት የመጨረሻ ክብደት ከተቀዳጀ ለምን ሦስት ተጨማሪ ዓመታት መቀለብ ያስፈልጋል? ትርፍ አልባ ነው፣ ወጪ ብቻ ነው የሚያስከትለው፡፡ እንቁላል የሚጥሉ እናት ዶሮዎችና የሚታለቡ ከብቶች (ከሌሎች ለሥጋ ውጤት ከሚራቡ ጋር ሲነፃፀር) ለብዙ ዘመን መኖር ይፈቀድላቸዋል፡፡ ያ ሲደረግም በተወሰነ ቦታ ተኮልኩለው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንም ዓይነት የአካል እንቅስቃሴ (ከቦታ ወደ ቦታ) ማድረግ ሳየፈቀድላቸው ወራት ያልፋሉ፡፡ ንግዲህ ኮርማዎችን (ከብት)፣ ፈረሶችን፣ አህያዎችን እንዲሁም ግመሎች ወደ ገራም እንስሳነት (ቅንንት) ለመቀየር (ለማላመድ)፣ ቀደም ብሎ ነፃ በነበሩ ጊዜ ገና ሳይላመዱ የነበሯቸውን አንዳንድ ባህሪዎቻቸውን እንዲቀይሩ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ ያልተገደቡ እንቅስቃሴዎቻቸውንና የዝሙት ተግባራቸውን (የተደጋጋመ ዝሙታዊ ግንኙነታቸውን)፣ ፀብ ጫሪነታቸውን (ፀበኛ) ወዘተ. ማብረድና ማክሰም፡፡ ፀባይ ለማሰቀየርም ገበሬዎች ከተሰማሩባቸው ተግባራት ጥቂቶቹ፣ ኮርማዎችን፣ ፈረሶችን፣ ወዘተ. ማኮላሸት፣ በበረት (በጋጥ) ተከትረው እንቅስቃሴያቸው እንዲወሰን ማድረግ፣ በመግራት በሒደቱም በመግረፍ የሚፈለጉ ባህሪዎችን እንዲቀዳጁ ተደርጎ እንስሳቱ ወደው ሳይሆን በግድ (ሕይወት ከዳረገቻቸው ባህሪ ውጪ ሆነው) የሰው አገልጋይ ይደረጋሉ፡፡

ለምሳሌ ‹‹የአዲሲቷ ጊኒ›› ገበሬዎች የአሳማዎችን አፍንጫ ይጎርዳሉ፡፡ ይህ የሚደረገው አሳማዎች ማሽተት እንዲሳናቸው ነው (የተጎረዱት ማሽተት አይችሉም)፡፡ ለማሽተት ሲሞክሩ አየር በቆሰሉ አፍንጮቻቸው ስለሚያልፍና ስለሚሰቃዩ ለማሽተት አይሞክሩም፡፡ ካላሸተቱ ደግሞ ምግብ ያለበትን ቦታ ማግኘት ይሳናቸዋል፣ እንዲሁም ተግባር ተኮር በሆነ እንቅስቃሴ (አቅጣጫ የሚያገኙ በማሽተት ነው) አቅጣጫ ማግኘት አይችሉም፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች አሳማዎች ሙሉ በሙሉ የገበሬዎች ጥገኞች ይሆናሉ (ሆነዋል)፡፡ ለመመገብ የሚችሉት ምግብ ሲሰጣቸው ብቻ ይሆናል፡፡ ባደጉ አገሮች የአሳማ እርባታ (ማስባት) ፋብሪካ መሰል ነው፡፡ ከላሞች ወተት ማግኛ ዘዴዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከዘዴዎችም ጥቂቶችን እናውሳ፡፡ በመሠረቱ ላም ካልወለደችና የሚጠባ ጥጃ ከሌላት ወተት አትለግስም፡፡ ስለሆነም ላም እንደ ወለደች የሰው ልጅ ወተቷን ከእምቦሳዋ ጋር ይጋራል፣ ወይም በብቸኝነት (በሞኖፖል) በወተቱ ይጠቀማል፡፡ አንዱ መንገድ ላም ጥጃዋን ጥቂት ካጠባች በኋላ ልጇን አሰወግዶ ላሟን በማለብ ነው፡፡

አለዚያም እምቦሳው ወንድ ከሆነ ወደ ሉካንዳ ይላካል፡፡ ሴት ከሆነች ከእናቷ ትለይና ወተቱን ሰው ብቻ ይጠቀምበታል፡፡ ሆኖም በዚህ መንገድ ላም ወተት ለረዥም ጊዜ ለመለገስ ስለማትችል ቶሎ ቶሎ ላሟ እንድታረግዝ ይደረጋል፡፡ በዚህ መንገድ የሚወለዱት ጥጆች ከእናቶቻቸው ይነጠሉና እናቶች (ላሞች) ከ60 እስከ120 ቀናት ውስጥ ተጠቅተው እንደገና እንዲከብዱና ከዘጠኝ ወራት በኋላ አንዲወልዱ ይደረጋል፡፡ ብሎም ወተት ያበረክታሉ፡፡ በዚህ መንገድ አምስት ዓመት ያህል ለሰው ልጅ ወተት ሲለግሱ ቆይተው ከዚያ ወደ ቄራ ይላካሉ፡፡ አንዳንድ ከብት አርቢ ነጋዴዎች ጥጃውን አርደው ከበሉ በኋላ ጥጃ መሰል አሻንጉሊት (ምሥል) ሠርትው እናቲቱ  ሕይወት አልባውን የጥጃ ምሥል እንድታይ እየተደረገች (ላሚቱም የጥጀውን ምስል ሕይወት እንዳለው ሁሉ  እየላሰች) ተታልላ ለጥቂት ጊዜ ወተት ታበረክታለች፡፡ የግብርና አብዮት ለብዙ የቤት እንስሳት መከራ ነው የጣለባቸው፡፡ የእነሱ በቁጥር ልቆ መገኘት (መብዛታቸው) ለእያንዳንዱ እንስሳ ምንም አልጠቀመም፣ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የግብርናው አብዮት እንስሳትን በትንንሽ ሳጥን መሰል ማጎሪያዎች ተገርግሮ መኖር፣ ከምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ተቆጥበው መብላትና መጠጣት ከዚያም መሰዋት ነው፡፡ በተለይ በአደጉ አገሮች አካባቢ የሥጋ ከብት ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ህያው ሆኖ ታስሮ፣ ከእንቅስቃሴ ተገትቶ፣ ከሜዳ ተሰውሮ ሰንብቶ ለሞት ነው የሚዳረገው፡፡ የግብርና አብዮት ለእንስሳት የለገሰው የእንስሳት የህያው ዘመን አጭር ኑሯቸው እስር ቤት መሰል ሆኖ፣ የአማሟታቸው መንገድ አሰቃቂ መሆንን  ነው፡፡

ዕውን ፍርድ አሰጣቱ ፍትሐዊ ነውን? የዓለማችንን ሁኔታ ያገናዘበ ነውን? ከላይ የሰፈረውን ዕይታ በጥሞና ለመገንዘብ እንድንችል የዓለምን የምግብ ሰንሰለት ይዘት መፈተሽ ይኖርብን ይሆናል፡፡ አንድን ጉዳይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መመልከትም ሳይንሳዊ ሒደት ነው፡፡ በምድራችን ያለው የምግብ መረብ ውስብስብ ነው፡፡ ለምሳሌ አይጥ ፍራፍሪ፣ ቅጠላ ቅጠል፣ እህልና ሥጋ ትመገባለች፡፡ ድመት አይጥን ትበላለች፡፡ የድመትን ግልገሎች ጆፌ አሞራ ይበላል፡፡ የተለያዩ ሦስት አጽቄዎች ከላይ የተጠቀሱትን እንስሳት ደም ይመጣሉ፡፡ ስለሆነም የምግብ መረቡ ውስብስብ ነው፡፡ ምድራችንም በህላዊነት ግዳጅ መንስዔ የመበላላት መድረክ ናት፡፡  ስለሆነም የዓለምን የምግብ መረብ ይዘት በአጠቃላይ ስንቃኝ የእንስሳት በዳይነት ጫናው ይቀልልን ይሆናል፡፡ ለዚህ ዕይታ ይረዳን ዘንድ ስለቢምቢ የተገጠመ እነሆ (ሴት ቢምቢ ደም ውስጥ ያለ ኬሚካዊ ውሁድ ካልተመገበች ማህፀኗ ወስጥ ያሉ እንቁላሎች ለዘር መተካት አይበቁም፣ ይጨነገፋሉ)፡፡ ስለሆነም ዘር ለመተካት ሴት ቢምቢ የግድ ደም መማግ አለባት፡፡

ህላዌ አስገድዷት ዘር እተካ ብላ ትንሽ ደም በማገች፣

ሞት አቀባባይ ናት በሚል ተፈረጀች፤

በይና ተበይ በሞላበት ዓለም፣

ወንጀል ወይ ኩነኔ ብሎ ነገር የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ አመራር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኤሚረተስ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ኢንቫይሮመንት ኔትወርክ አመራርና የኢትዮጵያ ሳይንስ ሶሳይቲ ሽልማቶች ተሸላሚ፣ እንዲሁም በርካታ ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles