ከጂቡቲ በመመለስ ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሕክምና የሚሰጡ አራት የድንገተኛ ሕክምና ጣቢያዎች በድሬዳዋና አካባቢው መቋቋማቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፣ ከተመላሽ ኢትዮጵያዊያን መካከልም 74 የድንገተኛ ሕሙማን ታክመው 24ቱ ሲያገግሙ፣ የተቀሩት ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
በምሥራቅ ሐረርጌ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተጎዱ ወገኖች የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ በሦስት ሆስፒታሎች አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ሲሆን፣ የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ተጨማሪ ዕገዛና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል::
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ወደ ጅግጅጋ የተሰማራው የባለሙያዎች ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው 128 ሰዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት ችሏል፡፡
ከተጎጅዎቹ መካከልም ግማሽ ያህሎቹ የጭንቅላት፣ የደረት፣ የሆድና የደረት ቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረገላቸው መሆናኑን የሕክምና ቡድኑ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል፡፡ የሕክምና ቡድኑ ወደ ጅግጂጋ ከማቅናቱ በፊትም በድሬዳዋ ከተማ በተፈጠረው ግርግር ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጅዎችም የሕክምና ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ገለጻ፣ የሕክምና ቡድኑ ወደ ጅግጅጋ ማቅናቱ ለተጎጅዎች የሕክምና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በማኅበረሰቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲፈጠርና የአካባቢው ጤና ባለሙያዎችም ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው የሕክምና አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈ መልኩ እንዲሰጡ ዕድል እንዲፈጠር አድርጓልም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በተፈጠረው ችግር ምክንያት መድኃኒታቸውን ያቋረጡ ሕሙማን ወደ ቀድሞ ክትትላቸው እንዲገቡም ተደርጓል፡፡
አሥር የቀዶ ጥገና ሐኪሞች፣ ሦስት አንስቴዮሎጂስቶች፣ ስድስት አንስቴቲስቶችና አራት የኦፕሬሽን ክፍል ነርሶች፣ በአጠቃላይ 23 የጤና ባለሙያዎች በሕክምና ድጋፉ ተሳትፈዋል፡፡ ቡድኑ ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከየካቲት 12 እና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተወጣጡ 24 የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ ነው፡፡