Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየገቢ ግብር ስወራ ወንጀልን የሚያስረዱ የኦዲት ግኝቶች

የገቢ ግብር ስወራ ወንጀልን የሚያስረዱ የኦዲት ግኝቶች

ቀን:

በተካ መሓሪ ሓጎስ

   የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ግብር በአግባቡ ተከፍሏል ወይስ አልተከፈለም የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት በዋናነት አራት የግብር ኦዲት ስልቶች ይጠቀማል፡፡ እነዚህም ልዩ ምርመራ ኦዲት (Investigation audit)፣ አጠቃላይ ምርመራ (Comprehensive audit)፣ ዴስክ ኦዲት (Desk audit) እና ውሱን ምርመራ (Spot audit) በመባል ይታወቃሉ፡፡ በየትኛውም የግብር ኦዲት ስልት በመጠቀም ኦዲት በተደረገው የግብር ዓይነት በልዩነት የተገኘ ያልተከፈለ ወይም መከፈል የሚገባው የግብር መጠን ተስተካክሎ እንዲከፈል የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ፣ ሥራውን የሠራው የግብር ሰባሳቢው መሥሪያ ቤት ኦዲተር ሙያዊ ግዴታ ነው፡፡ ኦዲተሩ በሠራው ኦዲት ላይ ልዩነት ካገኘ በኋላ ስለተገኘው የኦዲት ግኝትና በዚሁ መሠረት የተደረገ ማስተካከያ ለኦዲት ተደራጊው መግለጽ ይኖርበታል፡፡ ኦዲት ተደራጊው ደግሞ በተሠራው ኦዲት ላይ ስህተት ካለ ወይም ሊታይለት የሚገባ ነገር ግን በታክስ ኦዲተሩ ያልታየ ፍሬ ነገር ካለ ይህንኑ ኦዲቱን ለሠራው ባለሙያ ለማስረዳት የሚያስችል ዕድል ሊመቻችለት ይገባል፡፡ የኦዲት ተደራጊው ሐሳብና አስተያየት ለማድመጥ ዕድል የማይሰጥ የታክስ ኦዲት ሥራ የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ የኦዲት ተደራጊውን ሐሳብና አስተያየት ታሳቢ መደረግ አለበት ሲባል ደግሞ ለይስሙላ ተብሎ ብቻ የሚደረግ ከሆነም ውጤቱ ያው ነው፡፡ ስለዚህ የታክስ ኦዲት ሥራው የኦዲት ተደራጊውን ሐሳብና አስተያየት ታሳቢ አድርጓል ለማለት፣ በመጀመሪያ ስለ ኦዲት ግኝቶቹ ዝርዝር ይዘት ኦዲት ተደራጊው እንዲያውቀውና እንዲረዳው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሁለተኛነት ግኝቶቹን ለማስተባበል የሚያስችል ማስረጃ ካለው እንዲያቀርብ ዕድል መስጠት እንዲሁም በሦስተኛነት ኦዲት ተደራጊው በተሠራው ኦዲት ላይ በአግባቡ ለማስረዳት እንዲችል የባለሙያ ድጋፍ የሚያስፈልግው ከሆነ ይዞ እንዲቀርብ ሊፈቀድለት ይገባል፡፡

በታክስ ኦዲት ሥራ አማካኝነት የሚገኙ የኦዲት ግኝቶች (Audit findings) ኦዲት ተደራጊው የፈጸማቸውን ስህተቶች ወይም ጥፋቶች በመለየትና በኦዲት ተደራጊው ላይ ሊመጣ ስለሚችለው ኃላፊነት በማሳየት በኩል የጐላ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚጠቀምባቸውን የኦዲት ስልቶች በተመለከተ የተደረገው ክፍፍል በተግባር ላይ የፈጠራቸውን የአፈጻጸም ድክመቶች እግረ መንገዱ ጠቅሶ ማለፋ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሱ የግብር ኦዲት ስልቶችን ጥቅም ላይ ያውላል፡፡ በአጠቃቀም ጊዜ ግን በግብር መሰወር ወንጀል የጠረጠራቸው ግብር ከፋዮች ላይ የልዩ ምርመራ ኦዲት (Investigation audit) የሚጠቀም ሲሆን፣ ቀሪዎቹን በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ይጠቀማል፡፡ ይህ አካሔድ በመሠረቱ ስህተት አለው የሚባል ባይሆንም፣ በተግባር እየተሠራበት ያለው አካሔድ ሲታይ ከልዩ ምርመራ ኦዲት ውጪ ባሉ የኦዲት ስልቶች በተሠሩ የግብር ኦዲቶች ላይ በግብር ስወራ ወንጀል የሚያስጠይቁ ግኝቶች ተገኝተው እያለ፣ ኦዲቱ ከልዩ ምርመራ ውጪ በመደረጉ ብቻ በአጥፊዎች ላይ ሊቀርብ የሚገባ የወንጀል ክስ የማይቀርብበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ጉዳዩ ከሕጉ አንፃር ከታየ ግን በአንድ ግብር ከፋይ ላይ በግብር ስወራ የወንጀል ክስ ለማቅረብ መሠረቱ በኦዲቱ የተገኙ ግኝቶች እንጂ፣ ለኦዲት ሥራው ጥቅም ላይ የዋለው የግብር ኦዲት ስልት ዓይነት መሆን የለበትም፡፡

ከዚህ በመቀጠል የገቢ ግብር ስወራ መኖሩን ለማስረዳት የሚቀርቡ የታክስ ኦዲት ግኝቶች ምን ዓይነት ይዘት ሊኖራቸው እንደሚገባ ከገቢ ግብር ሕጉ አንፃር የሚከተሉትን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

  1. ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የሽያጭ መደበቅ

ይህንኑ የንግድ ትርፍ ግብር ስወራ የሚመለከት ሲሆን፣ በዚሁ መደብ የገቢ ግብሩ መሠረት በዋናነት ሽያጭ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ግብር የሚከፈልበት የንግድ ሥራ ገቢ የሚወሰነው ተቀባይነት ያለው የሒሳብ አያያዝ መርህ (GAAS) በመከተል የሚዘጋጅ የትርፍና የኪሳራ ሒሳብ ወይም የገቢ መግለጫ ተከትሎ መሆን እንዳለበት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 18 ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ አንድ ነጋዴ ከሰረ ወይም አተረፈ የሚለው ጉዳይ ወይም ደግሞ የገቢውን መጠን ለማወቅ አስቀድሞ የሽያጩ መጠን ማወቅ የግድ ይላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነጋዴዎች ለንግድ ሥራቸው ደረሰኝ የመጠቀም ግዴታ ያለባቸው ሆነው እያለ  ለግብይቱ ደረሰኝ ቆርጦ  ባለመስጠት፣ ደረሰኝ የመጠቀም ግዴታ የሌላቸው  ደግሞ የፈጸሙት የሽያጭ መጠን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመደበቅ ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ሽያጭ ከተደበቀ ወይም ከተቀነሰ ደግሞ በተቀነሰው ወይም ባልተገለጸው  ሽያጭ ላይ የተገኘ ገቢ ላይ ለመንግሥት ሊከፈል የሚገባ የንግድ ትርፍ ግብር እንዲሰወር ያደርጋል፡፡

  1. የመሸጫ ዋጋ እንዲያንስ ማድረግ (Under invoicing)

በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተገለጸው ድርጊት የሚያመለክተው ሽያጭ መደበቅ ወይም የሽያጭ መጠኑ መቀነስ ድርጊት ሲሆን፣ በሁለተኛው ድርጊት ደግሞ ነጋዴው የሽያጩ መጠን ሳይደብቅ ወይም ሳይቀንስ የዕቃው የመሸጫ ዋጋ የሚያሳንስበት ሁኔታ ይመለከታል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ይህንኑ ሕገወጥ ድርጊታቸው የሚፈጽሙት ለገዢ ከፍ ባለ ዋጋ የሸጡት ዕቃ በሽያጭ ደረሰኝ ላይ ዋጋውን ዝቅ አድርጐ በመመዝገብ ቀጥተኛ ባልሆኑ ታክሶች (ለምሳሌ ቫት) ላይ ከሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ በተጨማሪ ሊከፈል የሚገባ  የንግድ ትርፍ ግብር መጠን እንዲያንስ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶቹም ቀን ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ ውለው ደረሰኝ ለምን አልተቆረጠም የሚል ጥያቄ እንዳይነሳባቸው ማታ ላይ ዕቃው ከተሸጠበት ዋጋ በታች በመሰላቸው ዋጋ ደረሰኝ የመቁረጥ ይባስ ብሎ አንዳንዶቹ ለወር ያህል ጊዜ ያለደረሰኝ ሽያጭ ያከናወኑባቸው ግብይቶች በወር መጨረሻ ደረሰኝ ቆርጠው የሒሳብ መዝገባቸው በአነስተኛ የሽያጭ ዋጋ የሚመዘግቡበት ሁኔታ እንዳለም በፍርድ ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት ሲቀርቡ ከነበሩ የወንጀል ክሶች መረዳት ይቻላል፡፡

  1. ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የትርፍ ህዳግ ማጥበብ

ይህ ድርጊት ሕገወጥና በወንጀል የሚያስጠይቅ የሚያደርገው ነጋዴው በፈጸማቸው ሽያጮች ከፍ ያለ ትርፍ አግኝቶ እያለ የሚከፍለው የንግድ ትርፍ ግብር መጠን እንዲያንስ ሆነ ብሎ የትርፍ መጠኑ ዝቅ አድርጎ የሚይዝበት ሁኔታ ካለ ነው፡፡ ነገር ግን ነጋዴው በትክክለኛ መንገድ የንግድ ዕቃው ያወጣኛል በሚለው አነስተኛ የትርፍ መጠን ሽያጭ ስላከናወነ በአነስተኛ ትርፍ ለምን ሽያጭ አከናወንክ የሚል ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታክስ ኦዲተሮች አማካኝነት ተሠርተው በሚቀርቡ አንዳንድ የታክስ ኦዲቶች ላይ በደፈናው ነጋዴው የትርፍ ህዳጉ (Profit margin) አሳንሷል በሚል የሚቀርብ ክርክር ከሕጉ አንፃር ሲታይ ትክክለኛ አይደለም፡፡ ነጋዴው የትርፍ ህዳጉ በማሳነሱ በወንጀል ሊያስጠይቀው የሚችለው ከፍ ያለ ትርፍ አግኝቶ እያለ ባገኘው የትርፍ መጠን ለመንግሥት ሊከፈል የሚገባ የንግድ ትርፍ ግብር ላለመክፈል ሆነ ብሎ ያገኘው ትርፍ አንሶ እንዲመዘገብ በማድረግ፣  መክፈል ከሚገባው የንግድ ትርፍ ግብር በታች ከፍሎ የተገኘ መሆኑ በቂና አሳማኝ በሆነ ማስረጃ  ሲረጋገጥ ነው፡፡

  1. በመጋዘን ያለ የንግድ ዕቃ መጠን ማነስ (shortage of stock)

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ካሉባቸው ግዴታዎች ውስጥ ከንግድ ሥራው ጋር በተያያዘ የተገዙና የተሸጡ ዕቃዎችንና አገልግሎቶች እንዲሁም በመጋዘን የተከማቹ የንግድ ዕቃዎችን ዓይነት ብዛትና ለዕቃዎቹ የተደረገውን ወጪና ዕቃዎቹ የተገመቱበትን ዘዴ ጨምሮ በሒሳብ ዘመኑ መጨረሻ በእጅ ያሉትን ዕቃዎች የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸው የገቢ ግብር ሕጉ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነጋዴው በእጁ ያልተሸጠ ዕቃ አለኝ ብሎ ካሳወቀ በኋላ በመጋዘኑ ፍተሻ (ቆጠራ) ሲደረግ አሉ የተባሉ የንግድ ዕቃዎች የማይገኙበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አለ የተባለው የንግድ ዕቃ ቆጠራ በሚደረግበት ጊዜ ካልተገኘ ተሽጦ ከሽያጩም ላይ ገቢ ተገኝቶበት እያለ ሳይገለጽ የቀረበት ወይም የተደበቀበት ሁኔታ መኖሩ ሊያሳይ ይችላል፡፡ ሁኔታው የተፈጠረው ጥፋት በሌለበት ስህተት ምክንያት መሆኑ የሚያሳይ ነገር ካልተገኘ የንግድ ዕቃ እጥረት (shortage of stock) የንግድ ትርፍ ግብር መሰወር ስለመፈጸሙ በማስረጃነት ሊወሰድ የሚችል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

  1. ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የንግድ ሥራ ወጪ ማጋነን (over statement of expenses)    

በአገራችን የገቢ ግብር ሕግ መሠረት ሊከፈል የሚገባ የንግድ ትርፍ መጠን ለመወሰን በመጀመሪያ ከተገኘ ያልተጣራ ትርፍ (Gross income) ላይ  ተቀናሽ ሊደረጉ የሚገቡ የንግድ ሥራ ወጪዎች እንዲሁም በልዩ ሁኔታ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 21(2) ላይ እና በገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 78/1995 አንቀጽ 8(6 ) ሥር የተገለጹት የንግድ ሥራ ወጪ ያልሆነ ወጪዎች ከተቀነሱ በኋላ በሚገኘው የተጣራ ትርፍ ላይ በሕጉ የተቀመጠው የግብር ምጣኔ በመጠቀም ከተሰላ በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ የተጣራ ትርፍ ለማግኘት ካልተጣራ የንግድ ትርፍ ላይ በዋናነት የንግድ ሥራ ወጪዎች መቀነስ አለባቸው፡፡ ተቀናሽ መደረግ ያለባቸው የንግድ ሥራ ወጪዎች መሠረታዊ ይዘት በተመለከተ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 20 ላይ ለንግድ ሥራው ገቢ ለማግኘት፤ ለንግድ ሥራው ዋስትና ለመስጠትና እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል የወጡ ወጪዎች ናቸው በማለት ይተረጉማቸዋል፡፡ እነዚህ ወጪዎችም መደበኛ ወጪዎች (ordinary expenses) እና ካፒታል ወጪዎች (capital expenses) በማለት በሁለት ይከፈላሉ፡፡ መደበኛ ወጪዎች በእያንዳንዱ የግብር ዘመን ተቀናሽ የሚደረጉ ሲሆን፣ ካፒታል ወጪዎች ደግሞ በረጅም ጊዜ የእርጅና ቅናሽ ሥርዓት መሠረት የሚቀነሱ ናቸው፡፡ የሁለቱን የንግድ ሥራ ወጪዎች የማጋነን ድርጊት ካለ ግን ሊከፈል የሚገባ የንግድ ትርፍ ግብር መጠን ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ የካፒታል ወጪዎች ከተጋነነ የሚፈጥረው ተፅዕኖ በእርጅና ቅናሽ ሥርዓት ላይ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ በሌላ የጽሑፍ ርዕስ የሚገለጽ ስለሆነ፣ በዚሁ ርዕስ የመደበኛ ወጪዎች ዋጋ ማጋነን ካለ በግብር ሥርዓቱ የሚኖረው ተፅዕኖ እንመልከት፡፡ በዚሁ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው የንግድ ትርፍ ግብር የሚከፈለው ተቀናሽ መደረግ ያለባቸው ወጪዎች ከተቀነሱ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ተቀናሽ ወጪ ከፍ ካለ ሊከፈል የሚገባ የንግድ ትርፍ መጠን እንዲያንስ ያደርጋል፡፡ ተቀናሽ ወጪዎቹ ከፍ ያሉት በትክክለኛና ሕጋዊ በሆነ አካሔድ ከሆነ የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ ነገር ግን ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ተቀናሽ ወጪዎች የማጋነን ድርጊት ካለ ወይም የወጣ የንግድ ሥራ ወጪ ሳይኖር አላግባብ በንግድ ሥራ ወጪ የመያዝ ድርጊት ካለ ግን በገቢ ግብር ስወራ ወንጀል ያስጠይቃል፡፡

  1. የንግድ ትርፍ ግብር እንዲያንስ ለማድረግ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የካፒታል ዕቃዎች ዋጋ ማጋነን

በተራ ቁጥር 5 ላይ እንደተገለጸው ለንግድ ሥራ ዓላማ የወጣ የካፒታል ወጪ ተቀናሽ የሚደረገው ወጪው በወጣበት የግብር ዘመን ላይ ሳይሆን በረጅም ጊዜ የእርጅና ቅናሽ ሥርዓት መሠረት ነው፡፡ በገቢ ግብር ሕጉ ላይ ግብር የሚከፈለበትን የንግድ ሥራ ገቢ ለመወሰን የንግድ ሥራው ሀብት ባለቤት ለንግድ ሥራው ሀብቶች ላይ በተናጠል ቀጥተኛ የእርጅና አቀናነስ ዘዴ (straight line basis) እና ሁለት ዓይነት በጥቅል የእርጅና አቀናነስ ሥርዓት (pooling system 1 and 2) ይፈቅዳል፡፡ ከመጀመርያውኑ የካፒታል ዕቃው ዋጋ ከፍ ከተደረገ የንግድ ዕቃው የእርጅና ቅናሽ መሠረቱ (base of depreciation) ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡ የዕቃው የእርጅና ቅናሽ መሠረቱ ከፍ ካለ ደግሞ የንግድ ዕቃው የእርጅና ቅናሽ ጊዜው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከፍ ያለ የእርጅና ተቀናሽ እንዲኖር በማድረግ በየዓመቱ ሊካፈል የሚገባ የንግድ ትርፍ መጠን አላግባብ  እንዲቀነስ ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያለው አሠራር ሲታይ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ የማሳነስ (under invoicing) ድርጊት እንዳይኖር የሚያደርገው ክትትል ያህል የንግድ ዕቃዎች መግዣ ዋጋ ከፍ ስለማድረግ (over invoicing) ላይ አስፈላጊ ቁጥጥር ሲያደርግ አይታይም፡፡ ነገር ግን የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ከፍ የማድረግ ድርጊት ካለ የእርጅና ቅናሽ መሠረቱ በማብዛት የሚከፈለው የግብር መጠን እንዲያንስ በማድረግ በግብር ሥርዓቱ ላይ የማፈጥረው ተፅዕኖ ከበድ ያለ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

  1. የግብር እፎይታ መብት አለአግባብ መጠቀም (abuse of tax holiday right)

መንግሥት በአንዳንድ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሚኖር ኢንቨስትመንት ለማበረታታት በእነዚህ ዘርፎች የሚሳተፋ ኢንቨስተሮች ለተወሰነ ጊዜ ገቢ ግብር ከመክፈል ነፃ የሚያደርበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ግብር የሚከፈልበትና የግብር እፎይታ ጊዜ የተሰጠው የንግድ ሥራ አቀላቅለው በሚሠሩበት ጊዜ ግብር በሚከፈልበት የንግድ ዘርፍ ያገኙት ገቢ ላለመክፈል የግብር እፎይታ ባለው የንግድ ዘርፍ ውስጥ በማካተት ሊከፍል የሚገባ የንግድ ትርፍ መጠን የሚደበቁበት ሕገወጥ ድርጊት አለ፡፡

  1. ያገኘውን ገቢ አለመግለጽ

ማንኛውም ሰው በገቢ ግብር አዋጁ የሚሸፈን ገቢ ከቅጥር፣ ከቤት ኪራይ፣ ከንግድ ሥራ ወይም ከሌሎች ሥራዎች ገቢ አግኝቶ እያለ ሆነ ብሎ ሳያሳውቅ በመቅረት በዚሁ ላይ ሊከፈል የሚገባ የገቢ ገብር እንዲቀር የማድረግ ድርጊት ካለ የግብር መሰወር ድርጊት ያቋቁማል፡፡

  1. ሳይከስሩ ሆነ ብሎ ኪሳራ ማሳወቅ

አንድ ነጋዴ በንግድ ሥራው ኪሳራ ገጠመው የሚባለው በግብር ዘመኑ ያወጣው ወጪ ካገኘው ገቢ በልጦ ሲገኝ ነው፡፡ በአንድ የግብር ዘመን አንድ ነጋዴ ኪሳራ ካጋጠመው ደግሞ ይህንኑ ኪሳራ በሚቀጥሉት ሦስት የግብር ዘመናት ከተገኘው ግብር የሚከፍልበት ገቢ ላይ እንደሚካካስለት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28 ላይና በገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 78/1995 አንቀጽ 12 ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ በሕገወጥ መንገድ የመበልፀግ ፍላጐት ያላቸው ግብር ከፋዮች አላግባብ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው አድርገው የሒሳብ መዝገባቸው በማደራጀት ሊከፍሉት የሚገባ የገቢ ግብር የማስቀረትና ይህንኑ ኪሳራ ደግሞ በቀጣይ የግብር ዘመናት ከሚያገኙት ገቢ አላግባብ እንዲቀናነስላቸው በማድረግ የሚፈጽሙት የገቢ ግብር ስወራ ወንጀል በእኛ አገርም የተለመደና በብዛት የሚታይ በመሆኑ፣ ድርጊቱ ለመከላከል በግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ሊሠሩ የሚገቡ የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች መጠናከር ይገባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ የገቢ ግብር መሠረቱ ግብር ከፋዩ የሚያገኘው ገቢ ስለሆነ አንድ ሰው የገቢ ግብር መሰወር ወንጀል ፈጽሟል በማለት ተሠርተው በማስረጃነት በሚቀርቡ የታክስ ኦዲቶች ላይ ግብር ከፋዩ ያገኘው ገቢ ሆነ ብሎ ሳይገለጽ በመቅረት ወይም ለገቢው መገኘት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ሽያጮች ወይም ግብይቶች ሆነ ብሎ በመደበቅ ሊከፍለው የሚገባ የገቢ ግብር መጠን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲቀር (እንዲደበቅ) ስለማድረጉ ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡

ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሌላ ማንሳት አለብኝ ብዬ ያሰብኩት በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዘንድ ግለሰብ ነጋዴዎች የገቢ ግብር መሰወር ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ሲያቀርባቸው በነበሩ የወንጀል ክሶች ላይ እንደ ታክስ ኦዲት ግኝት ተደርጎ በብዛት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው፣ በግለሰብ ነጋዴዎች የባንክ ሒሳብ ላይ የሚገባ ገንዘብ (Bank deposit) በተመለከተ ያለው አሠራር ነው፡፡ ይህ የኦዲት ግኝት አጠቃቀም አስመልክቶ በግብር ከፋዮችና በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ብዙ ጭቅጭቅ ሲነሳበት የነበረ ሲሆን፣ በፍርድ ቤቶች በዚሁ ጉዳይ እስካሁን ድረስ የጠራ አሠራር አይታይበትም፡፡ የግብር ከፋይ የባንክ ሒሳብ ገቢ የሚሆን ገንዘብ በተመለከተ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታክስ ኦዲተሮች ዘንድም የተዘበራረቀ አካሔድ ይታይበታል፡፡ አንዳንድ የታክስ ኦዲተሮች ወደ ግለሰብ ነጋዴ የባንክ ሒሳብ የሚገባ ገንዘብ በሙሉ ሽያጭ ነው ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ገቢ ነው ይላሉ፤ ይባስ ብሎ አንዳንዶቹ ደግሞ የተጣራ ትርፍ ነው የሚል አመለካከት ያላቸው ነበሩ፡፡ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ይህንኑ ግኝት አስመልክቶ ያለው አሠራር ሲታይ ወጥነትና ተመሳሳይነት የሌለው  በተለያዩ ችሎቶች የተለያዩ ውሳኔዎች የሚሰጥበት ከዚህም አልፎ አንዳንድ ዳኞች በግለሰብ ነጋዴዎች የባንክ ሒሳብ ላይ ገቢ የሚደረግ ገንዘብ  ለፍትሐ ብሔራዊ ኃላፊነት ለመወሰን ብቻ እንጂ ለወንጀል ክስ መጠቀም የለብንም የሚሉ አንዳንዶቹም ደግሞ ለሁለቱን መጠቀም እንችላለን የሚሉ ውሳኔዎች ሲሰጡበት ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በግለሰብ ነጋዴዎች የባንክ ሒሳብ ገቢ የሚደረግ ገንዘብ ለገቢ ግብር አወሳሰን እንደ ግኝት በጀመረበት ወቅት በባንኮች የሚቀመጥ ገንዘብ እጥረት ፈጥሮ እንደነበረ በወሬ ደረጃ እሰማ ነበረ፡፡ ምክንያቱም  በግብር ከፋዩ ዘንድ ወደ ባንክ ሒሳባችን የሚገባ ገንዘብ በሙሉ እንደ ሽያጭ ወይም እንደ ገቢ የሚወሰድብን ከሆነ ወደ ባንክ ሒሳባችን ገንዘብ ገቢ ማድረግ የለብንም ከሚል  ሥጋት በመነሳት የግል ካዝና በመግዛት ገንዘብ ከባንክ ውጪ በግለሰቦች እጅ እንዲቀመጥ ዕድል ፈጥሮ ነበር፡፡

በዚህ ጉዳይ በሌሎች አገሮችም ወጥነት ያለው አሠራር የማይታይ ሲሆን፣ በአንዳንድ አገሮች ያለው ተሞክሮ ሲታይ በባንክ ገቢ የሚደረግ ገንዘብ ለሌሎች ግኝቶች ማጠናከሪያ ተደርጐ ለፍትሐ ብሔራዊ ኃላፊነት ብቻ አልፎ አልፎ ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ መኖሩ ለወንጀል ክስ በማስረጃነት መጠቀሙ ግን በወንጀል ክስ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ምክንያታዊ የሆነ እርግጠኝነት ሊፈጥር በሚችል መልኩ ማስረዳት አለባቸው በሚል በሕግ ከተቀመጠው ግደታ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገለጻል፡፡ በእኔ ዕይታም ግለሰብ ነጋዴዎች ለንግድ ሥራቸውና ለግል ጥቅማቸው በአንድ ላይ የባንክ ሒሳብ የሚጠቀሙበት ሁኔታ በመኖሩ፣ ግል ጥቅምና ለንግድ ሥራ ተብሎ ለየብቻ የባንክ ሒሳብ መክፈት አለብህ የሚል በግለሰብ  ነጋዴዎች ላይ በሕግ የተጣለ ግዴታ የሌለ ከመሆኑ አንፃር፣ የግል ገንዘብና የንግድ ሥራ ገንዘብ ተብሎ ሳይለይ  በቀላሉ ወደ ግለሰብ ነጋዴው የባንክ ሒሳብ የሚገባበት አሠራር ያለ በመሆኑ፤ የንግድ ሥራው የሽያጭ ገንዘብና የብድር ገንዘብ፣ የቤተሰብና የጓደኛ ገንዘብ በቀላሉ ተቀላቅሎ ሊቀመጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ሲታይ፤ በሌላ በኩል ወደ ግለሰብ ነጋዴ የባንክ ሒሳብ ገቢ የሚደረገው ገንዘብ ሽያጭ ነው ወይስ ገቢ ነው የሚለው ጉዳይም በቀላሉ በማይለይበት ሁኔታ በግለሰብ ነጋዴ የባንክ ሒሳብ  ላይ የገባ ገንዘብ ሁሉ ለገቢ ግብር መሰወር ወንጀል ይቅርና ለፍትሐ ብሔራዊ ኃላፊነት አወሳሰን በማስረጃነት ከመውሰድ ጋር ተያይዞ  በሌላ ማስረጃ ካልተደገፈ በቀር የማስረጃነት ብቃቱ በጣም ደካማ ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...