Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትራንስፖርትን ለገጠር እግረኞች የማድረስ ተልዕኮ

ትራንስፖርትን ለገጠር እግረኞች የማድረስ ተልዕኮ

ቀን:

ሐኒ ሰመረ ለንደን በሚገኘው ሆልት ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ስኩል የቢዝነስና ኢንተርፕሩነርሽፕ ፕሮግራም ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ ትውልድና ዕድገቷ እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን፣ የአሥረኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ነበር ወደ ዱባይ ያቀናችው፡፡ የተሳካላቸው ነጋዴ ከሆኑ ወላጆቿ የተገኘችው ሐኒ፣ ንግድን ከሳይንስ ጋር አጣምራ የመሥራት ፍላጎት ያደረባት ገና ልጅ ሳለች ነበር፡፡

‹‹ቢሔቪየራል ኢኮኖሚክስ በጣም ይስበኝ ነበር፤›› የምትለው ሐኒ፣ ወደ ዱባይ ያቀናችው ፍላጎቷ የነበረውን ትምህርት ማጥናት እንድትችል ነበር፡፡ በዱባይ ኢንተርናሽናል ባችለሬት በተባለው ፕሮግራም ሥር የሚሰጠውን ትምህርት ለሁለት ዓመታት ያህል ተከታትላለች፡፡ ዱባይ በቆየችባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም ዘርፍ ከሚሰጠው በተለየ ኢኮኖሚክስንና ቢሔቪየራል ሳይኮሎጂን በአንድነት መውሰድ ችላለች፡፡

‹‹ሰዎች አንድን ነገር ለመግዛት እንዴት ነው የሚወስኑት የሚለው ነገር ደስ ይለኛል፡፡ ውሳኔያቸው በኢኮኖሚያቸውም ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ነው ሁለቱን በአንድ አጣምሬ ማጥናት የፈለኩት፤›› ትላለች፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ በነበራት የዕረፍት ጊዜ የምትሞካክራቸው አንዳንድ ነገሮች ቀጣይ የትምህርት ጉዞዋ ወደ ለንደን እንዲሆን ዕድሉን እንደሰጣት ትናገራለች፡፡

በትርፍ ጊዜዋ ግጥም የምትጽፈው ወጣቷ፣ ‹‹ሰላም እኔ ሴት ነኝ›› የሚል አብዛኛውን በእንግሊዝኛ ቋንቋና በመሀል ጣል በምታደርጋቸው የተለያዩ አገሮች ቋንቋ የጻፈችው ግጥም ነበር የበርካቶችን ትኩረት የሳበላት፡፡ ሁለት ደቂቃ አካባቢ በቃሏ የምታነበንበውን ግጥም ከመኖሪያ ቤቷ በስተጀርባ ነበር በስልኳ ካሜራ የቀረፀችው፡፡

በፌስቡክ ገጿ በለቀቀች በቀናት ውስጥ 160 ሺሕ ተመልካች እንዳገኘች ትናገራለች፡፡ ‹‹ያልጠበቅኩት ነገር ነበር፤›› የምትለው ሐኒ፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተፅዕኖ መፍጠር በመቻሏ ሆልት ቢዝነስ ስኩል ባዘገጀው የስኮላርሺፕ ዕድል ተጠቃሚ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ የምትማረው የቢዝነስና ኢንተርፕሩነርሺፕ ትምህርት የአራት ዓመት ፕሮግራም የነበረ ቢሆንም፣ ቀድሞ ዱባይ የወሰደቻቸው ኮርሶች እንዲታሰቡላትና አንድ ዓመት እንዲቀነስላት ማድረጓን ትገልጻለች፡፡  

‹‹ፈጥኜ እዚህ ተመልሼ ብዙ መሥራት የምፈልገው ነገር አለ፤›› ትላለች፡፡ ልትሠራበት የምትፈልገው የቢዝነስ ዘርፍ የንግድና የበጎ አድራጎት ሥራ መሥራት የሚያስችላትን ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ላይ ነው፡፡

ሶሻል ኢንተርፕራይዞች ያለምንም ድጋፍ ራሳቸውን ችለው መቆም የሚችሉና ቀጣይነት ያለው ማኅበራዊ አገልግሎት እንደአስፈላጊነቱ እያስከፈሉና ትርፍ እያገኙ፣ አቅሙ የሌላቸውን በዕርዳታ መልክ የማስተናገድ ተግባር የሚሠሩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ አንዳንድ ድርጅቶች ብቅ ብቅ እያሉ ሲሆን፣ ስለጉዳዩ ግን እምብዛም ግንዛቤ ባለመኖሩ የሚመዘገቡትም በንግድ ስም ነው፡፡

‹‹ብዙም ስለማይታወቁ ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን እዛ ተቀጥሬ ብሠራ ምንም አይደለም፡፡ ብዙ ነገር ማድረግ የሚቻለው ግን እዚህ ነው፡፡ እዚህ ብዙ ያልተጠቀምንባቸው ዕድሎች አሉ፤›› ስትል ፈጥና ወደ እዚህ መመለስ የፈለገችው የተሻለ ነገር እዚህ መሥራት እንደሚቻል በማመኗ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

እዚህ መጥታ ለመሥራት ያሰበችው፣ ትራንስፖርት እንደ ልብ በማይገኝባቸው የአገሪቱ የተወሰኑ ክፍሎች የትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማስፋት ነው፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ሆልት ፕራይዝ በየዓመቱ በሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኮሌጅ ተማሪዎች ውድድር ላይ ለመሳተፍ ስታስብ ነው፡፡ ሆልት ፕራይዝ የሚሰጠው የሚሊዮኖችን ሕይወት መቀየር የሚችልና ተግባራዊ መሆን የሚችል ፕሮጀክት ለቀረፀ አንድ ቡድን ይሆናል፡፡ በዚህኛው ዓመት ውድድር የእነሐኒ ቡድንን ጨምሮ 100,000 የሚሆኑ ከተለያዩ የዓለም ጥግ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቡድን በቡድን እየሆኑ ተሳትፈውበታል፡፡

በውድድሩ ሐኒና ሌሎች የቡድኑ አባላት በእሷ ግፊት ኢትዮጵያ ላይ ለመሥራት ተስማምተው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ በመጀመርያ ትክክለኛ የማኅበረሰቡን ችግር ማግኘት ላይ አተኩረው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ መተዳደሪያ የሆነውን ግብርና ዙሪያ ለመሥራትም ተስማሙ፡፡ ቀጥሎ ቢያሸንፉ የሚያገኙት አንድ ሚሊዮን ዶላር ሊፈቱት የሚችሉትን የገጠሩን ማኅበረሰብ ችግር ለመለየት በየገጠሩ መንቀሳቀስና ማኅበረሰቡን ማነጋገር ያዙ፡፡

በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎችም የትራንስፖርት አገልግሎት ባልተደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ሸጠው ለማደር እንደሚቸገሩ አስተውለዋል፡፡ ያለሙትን በገንዘብ ለመለወጥ በማዳበሪያ ቋጥረው ጋራ ሸንተረሩን አቋርጠው መኪና ይገኝበታል ብለው ተስፋ ከሚያደርጉበት የጠጠር መንገድ ላይ ወጥተው ብዙዎች ለሰዓታት ቆመው መኪና ይጠብቃሉ፡፡ ተሳክቶላቸው ቢያገኙም ገበያ የሚደርሱት ከረፈደ ስለሚሆን ተሸክመው የመጡትን ተሸክመው የሚመለሱ፣ አሊያም ድካሙ አሰልችቷቸው የያዙትን ያገኙበት ጣጥለው ወደ ቤታቸው ባዶ እጃቸውን የሚመለሱ መኖራቸውን አይተዋል፡፡

የሶሻል ኢንተርፕራይዝ ባህሪ ያለውና ይህንን የትራንስፖርት ችግር መቅረፍ የሚችል ድርጅት ለመመሥረት ይስማማሉ፡፡ ድርጅቱ የትራንስፖርት አገልግሎት በበቂ ተደራሽ በማይሆንባቸው የገጠር መንገዶች የሚመደቡ ተሽከርካሪዎችንና መንገደኞችን በስልክ መልዕክት ማገናኘት የሚችል አሠራር ነው፡፡ ይህ የስልክ መልዕክት የኢንተርኔት መረብ ኖረም አልኖረ መሥራት የሚችል ሲሆን፣ ነዋሪዎች መኪና በመጠበቅ የሚያጠፉትን ጊዜ መቀነስ የሚችል ነው፡፡

መንገደኞች የት አካባቢ እንደሚገኙ በስልክ መልዕክት ማስተላለፍ ከቻሉ፣ አሽከርካሪዎች በስንት ደቂቃ እንደሚደርሱ አሊያም የማይችሉ እንደሆነ ከቤታቸው ሳይወጡ መነጋገር የሚያስችላቸው ነው፡፡ ‹‹ውድድሩን ባናሸንፍ የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ ሌላ ኢንቨስተር እንፈልጋለን፤›› የምትለው ሐኒ፣ ውድድሩን ቢያሸንፉ የሚያገኙ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደመነሻ ካፒታል ቀላል የማይባል ቢሆንም፣ ባያሸንፉ በሌላ መንገድ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ ትናገራለች፡፡

እስካሁን በተደረገ የማጣሪያ ውድድሮች ከ100 ሺሕ ተማሪዎች መካከል ከምርጥ 40 ቡድኖች ውስጥ መግባታቸውን፣ ከዚህ በኋላ የሚቀራቸው ምርጥ አምስት ውስጥ መግባትና አንደኛ ለመውጣት ትግል ማድረግ እንደሆነ ትናገራለች፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...