Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ማስፈጸሚያ መመርያን  አፀደቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መመርያው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሥራ ላይ ውሏል

በብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የሚገዙበት ዝርዝር መመርያ በብሔራዊ ባንክ ፀድቆ ሥራ ላይ ዋለ፡፡

ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማስፈጸም ከተቋቋመውና በቅርቡ ወደ ሥራ ከገባው ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር አገልግሎት ጋር ተያይዞ በብሔራዊ ክፍያ ሥርዓቱ ውስጥ የሚሳተፉ ባንኮችና ሌሎች ተዋንያኖች የሚገዙበት ይህ መመርያ፣ በብሔራዊ ባንክ ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ነው፡፡

በብሔራዊ ክፍያ ሥርዓቱ ውስጥ በዋና ተዋናይነት የሚጠቀሱት ባንኮችና ወደፊትም በኢትስዊች አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ የሚካተቱ ተቋማት ሊተገበሩ ይገባቸዋል የተባሉ የክፍያ ማስፈጸሚያ ስልቶችና አስገዳጅ ድንጋጌዎችን የያዘው መመርያ፣ በተለይ የኢትስዊች ባለአክሲዮኖች የሆኑ ባንኮች ተፈጻሚ እንዲያደርጉት የመመርያው ቅጅ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

ይህ መመርያ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓትን ለመተግበር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 718/2002 መሠረት አድርጐ የተዘጋጀና ‹‹ብሔራዊ የክፍያ ስዊች ሲስተም ደንብ›› የሚል መጠሪያ ያለው መመርያ ስለመሆኑ፣ ከኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱን ለማስተግበር ዝርዝር መመርያዎች እንደሚወጡ በአዋጁ የተገለጸ በመሆኑ፣ ለብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱ ማስፈጸሚያ ከሚያስፈልጉ መመርያዎች ውስጥ አንዱ ይኸው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው መመርያ ነው ተብሏል፡፡ ኢትስዊች በቅርቡ ያስጀመረው አገልግሎት ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ኤቲኤሞች ላይ የየትኛውንም ባንክ ደንበኛ እንዲጠቀም የሚያስችል መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚሁ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ እያንዳንዱ ባንክ ያለበትን ኃላፊነትና ግዴታ በዝርዝር የያዘው አዲሱ መመርያ፣ በአገልግሎቱ ዙሪያ ሁሉም ባንኮች አንድ ስታንዳርድ የሆነ ካርድ እንዲኖራቸው የሚያስችል ድንጋጌ የያዘ ጭምር ነው፡፡ አሁን እየተጠቀሙበት ካለው የኤቲኤም ካርድ ጐን ለጐን፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ካርድ እንዲሆን በተዘጋጀው ኢትዮ ፔይ ካርድ ስታንዳርድ መሠረት ካርዶች እንዲዘጋጁ ያደርጋል፡፡ የኤቲኤም ማሽኖችም የሚገዙት በወጣላቸው ስታንዳርድ መሠረት ይሆናል፡፡

የኢትስዊች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት አዋጁ መሠረት የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓት የአገልግሎት አሰጣጥን የተመለከተ ደንቦችና መመርያዎች አዘጋጅተው በብሔራዊ ባንክ አፀድቀው ሥራ ላይ ያውላሉ የሚል ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ረቂቁ በኢትስዊችና የኢትስዊች ባለአክሲዮኖች በሆኑት ባንኮች ተዘጋጅቶ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ ሊፀድቅ ችሏል፡፡

በዚሁ መሠረት ብሔራዊ ባንክም የቀረበለትን ረቂቅ መመርያ ተመልክቶ ማስተካከያዎችን በማድረግ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ተብሏል፡፡ የመመርያውን የተለየ ያደርገዋል የተባለውም ረቂቁ በክፍያ ሥርዓቱ ተዋንያኖች የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡

ብሔራዊ ክፍያ ሥርዓቱን ለማስፈጸም እያንዳንዱ ተዋንያን ምን መፈጸም ይኖርባቸዋል የሚለውን ኃላፊነትና ግዴታዎቻቸውን የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ፣ መመርያውን መተላለፍና ሊያስወስድ የሚችለውን ዕርምጃ የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡

እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ መመርያውን ማተላለፍ ሊያስወስድ የሚችለው ዕርምጃዎች በተለያየ ደረጃ የሚወሰኑ ናቸው፡፡ መመርያ ለማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው ኢትስዊች አክሲዮን ኩባንያ ቢሆንም መመርያውን መተላለፍ የሚያስከትሉትን ዕርምጃዎች የሚወሰዱት በኢትስዊች ማኔጅመንት፣ በኢትስዊች ቦርድና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡

በኢትስዊች አስተዳደራዊ ማኔጅመንት ሊወሰኑ የሚችሉትን ደንብ መተላለፎች የትኞቹ እንደሆኑ የሚያሳይ ሲሆን፣ ከኢትስዊች ማኔጅመንትና ቦርድ በላይ የሆኑ ጉዳዮች ግን ውሳኔ የሚሰጠው በብሔራዊ ባንክ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 817/2002ን መሠረት በማድረግ የወጣ በመሆኑም መመርያው ከአዋጁ ጋር ተሳስሮ የሚሠራበት ሲሆን፣ በዚህ የክፍያ ሥርዓት ተሳታፊ የሆኑ ባንኮችና ወደፊት ኢትስዊችን ይቀላቀላሉ ተብለው የሚጠበቁት እንደ የፖስታ አገልግሎት ድርጅትና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ተዋንያኖችን የሚመለከት ጭምር ይሆናል፡፡ እነዚህ ተዋንያኖች በአዋጁና በመመርያው የተቀመጡትን ደንቦች ከተላለፉ የሚተላለፍባቸውን ቅጣት ተቀምጧል፡፡

በአዋጁ ሕግን ስለመጣስና አስተዳደራዊ ዕርምጃ ስለመወሰድ በሚያመለክተው አንቀጽ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ኦፕሬተር፣ ተሳታፊ ወይም የክፍያ ሰነድ አውጪ የዚህን አዋጅ ወይም በዚህ አዋጅ የወጣን ደንብ፣ መመርያ፣ ትዕዛዝ ወይም የአሠራር ሥርዓት መጣሱን ካረጋገጠ እንደየአግባቡ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡››

ከተጠቀሱት ዕርምጃዎች ውስጥ ጥፋተኛው ላይ ገደብ መጣል ወይም ጥሰቱ ለቀጠለበት ለእያንዳንዱ ቀን እስከ 20 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣትን ያካተተ ነው፡፡

በዚህ አዋጅ የተቀመጡ ደንቦችን መተላለፍ እስከ 100 ሺሕ ብርና እስከ አምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን የሚያመለክቱ አንቀጾች አሉት፡፡ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱን ለማስተግበር ከዚህ መመርያ ውጭ የተለያዩ ተጨማሪ መመርያዎች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአንድ ካርድ በሁሉም ባንኮች ኤቲኤሞች መጠቀም የሚያስችለው አገልግሎት የተጀመረው ከሁለት ሳምንታት በፊት ቢሆንም፣ ባለፈው ሐሙስ አገልግሎቱ በይፋ ተመርቋል፡፡ እንደ ኤቲኤሙ ሁሉ በፓዝ ማሽኖችም ተመሳሳይ አገልግሎት ይጀመራል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች