Tuesday, July 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ የሚሻው የስታፋ ብረት የታሪፍ ከለላ ጥያቄ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጥያቄው ተደጋግሞ ሲነሳ ከሁለት ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ መንግሥት አምኜበታለሁ ለአገር ውስጥ የጥሬ ዕቃ አምራች የታሪፍ ከለላ እሰጣለሁ ቢልም፣ ሚስማር አምራቾች ግን እስካሁን ቅሬታችን ምላሽ ይሰጠው በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለስታፋ ብረት የተሰጠው የታሪፍ ከለላ ይነሳ ሲሉም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት ካሉ ከስድስት ወራት በላይ እንዳለፋቸው ከጻፉት ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የቅሬታቸው መነሻ አገር በቀሉ ስቲሊ አርኤምአይ የተባለ የብረታ ብረት ውጤቶች አምራች ኩባንያ ለሚስማርና ለሌሎች መገልገያዎች በጥሬ ዕቃነት የሚያገለግለውን ስታፋ ብረት በአገር ውስጥ ማምረት በመጀመሩ፣ ከውጭ ከሚመጣው አኳያ የታሪፍ ከለላ እንዲሰጠው መጠየቁና መንግሥትም ጥያቄውን በመቀበል ከለላ መስጠቱ ጉዳት አለው ማለታቸው ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የታሪፍ ከለላ ጥያቄውን በመቀበል ከዚህ ቀደም ስታፋ ብረት ከውጭ ሲመጣ ይከፈልበት የነበረውን የአምስት ከመቶ ታሪፍ ወደ 20 ከመቶ በመሳደግ ምላሽ ሰጥቷል፤ ከዚህም ባሻገር የሱር ታክስ ይከፈልበታል የሚለው ስሞታ ቀድሞ የቀረበለት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ የራሱን ቡድን አዋቅሮ የሚስማር አምራቾችን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ለወቅቱ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጥያቄም አስተያየትም አቅርቦ ነበር፡፡

ከታሪፍ ከለላው በተጓዳኝ ጎልቶ በደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የቀረበው ሌላው ጥያቄ፣ ከለላው የተሰጠው ስቲሊ አርኤምአይ ኩባንያ፣ የሚስማር ገበያውን 65 ከመቶ የገበያ ድርሻ የያዘ፣ አስሚን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተባለ እህት ድርጅት አለው የሚል ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ‹‹ዘርፉን በሚገባ ሳያጤን ኢኮኖሚያዊና ፍትሐዊ ውድድርን የማያሰፍን መመርያ አውጥቷል፤›› በማለት በተለይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ባለሙያዎች ሆን ብለው መንግሥትን አሳስተዋል ሲሉ ሚስማር አምራቾች በጻፉት ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት የተጻፉት ደብዳቤዎች ከ20 በላይ የሚስማር ፋብሪካዎችን ህልውና አደጋ ላይ የጣለና ከ‹‹40 ሺሕ በላይ›› ሠራተኞቻቸውን አደጋ ላይ የጣለው የመንግሥት ታሪፍ ከለላ ዕርምጃ እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡

የመንግሥት ምላሽ

ከመነሻው ጥያቄውን ደጋግመን መርምረናል ያለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ መንግሥት አንድም ይሁን በርካታ አምራች ጥሬ ዕቃ በአገር ውስጥ እስካመረተ ድረስ የታሪፍ ከለላ እንደሚሰጥ ከሪፖርተር ስለጉዳዩ ተጠይቀው የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ናቸው፡፡ ሚስማር አምራቾች ይጎዳናል በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ኮሚቴ በማደራጀት መመርመሩንና ጥናት መካሄዱን ሚኒስትር አህመድ አብራርተው፣ የተጣለው ታሪፍ ሚስማር አምራቾችን እንደማይጎዳ በመታመኑ ውሳኔው እንዲፀና መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ሚስማር አምራቾች ከታሪፍ ከለላ ውሳኔው በፊት ለባንክ ያስገቡትን የሌተር ኦፍ ክሬዲት ጥያቄም አካቶ ስለነበር ይህንን ነፃ እንዲያደርግ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ አስመን 65 ከመቶ የሚስማር ገበያውን በመያዝ ገበያን በሞኖፖል እንዲይዝ፣ ዋጋ በመወሰን ነፃ የገበያ ውድድር መርህን በመጉዳት እያደረሰ ነው በማለት ላነሱት ጥያቄም አቶ አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት በሁለቱ እህት ኩባንያዎች አማካይነት የዋጋና የምርት አቅርቦት መዛባት ይከሰታል የሚለውን ሥጋት ቁጥጥር በማድረግ እንደሚወጣው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ሚስማር አምራቾች ጥያቄውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መውሰዳውቸውን በማስመልከት ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ አህመድ፣ ‹‹እንግዲህ ምላሻችን አላረካቸውም ማለት ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ 

የብረታ ብርት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምላሽ

አገሪቱን የብረታ ብረት አምራቾች በቅርበት እያገዘ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪውን እንዲያድግ የመደገፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ስለ ታሪፍ ከለላውም ሆነ መንግሥት ሆነ ብሎ ለአንድ ኩባንያ ያደላ የሞኖፖል አሠራር አስፍሯል ለሚለው አቤቱታ ምላሽ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፊጤ ከበደ ናቸው፡፡

አቶ ፊጤ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ሚስማር አምራቾች ያነሱትን ጥያቄ በማስመልከት ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ለሚስማር ብቻም ሳይሆን ለአጥር ሽቦና ለሌሎች አገልግሎቶች በጥሬ ዕቃነት የሚውለውን የስታፋ ብረት በአገር ውስጥ  መመረቱን የሚደገፍ በመሆኑ የታሪፍ ከለላ መስጠቱን ገልጸው፣ በምርት ረገድም ቢሆን ከለላው የተሰጠው ስቲሊ ኩባንያ በዓመት አገሪቱ ከሚያስፈልጋት እጥፍ በላይ የሚያመርት መሆኑ በመረጋገጡ የምርት አቅርቦት ችግር እንደማይኖር መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡ ስቲሊ አርኤምአይ በዓመት 120 ሺሕ ቶን ስታፋ ብረት የሚያመርት ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ፍጆታው መጠን ግን ከ50 እስከ 60 ሺሕ ቶን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሞኖፖል ገበያውን እንዲቆጣጠሩ ተደርጓል ለሚለው ቅሬታ በሰጡት ምላሽም፣ መንግሥት በሁለቱ እህት ኩባንያዎች በኩል የሚደረጉ ግዥና ሽያጮችን እንደሚከታተል፣ ሌሎች ከሚሸጡበት ዋጋ አሳንሶ ለእህት ኩባንያው አስሚን ቢያቀርብ፣ ስቲሊ በሕግ እንደሚጠየቅ ያብራሩት አቶ ፊጤ፣ ገበያው በሞኖፖል ተይዟል የሚለው ሥጋት ከዚህ በበለጠ ምላሽ የሚያገኝበት ጊዜ መቃረቡን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ፊጤ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት አራት ኩባንያዎች በመ<span style=”font-size:12.0pt;line-height:200%;font-family: &quot;Ge” ez-1=”” numbers”,”sans-serif”‘=””>Gለ፣ በአዳማና በቢሾፍቱ የስታፋ ብረት ለማምረት የሚያስችላቸውን የፋብሪካ ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሲ ኤንድ ኢ ብራዘርስ የተባለው ኩባንያ፣ የግንባታ ሥራውን በማጠናቀቁ በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት እንደሚገባ አቶ ፊጤ ገልጸዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጥሬ ዕቃ አምራቾች እንዲገቡና ለስቲሊ አርኤምአይ የተሰጠውን ማበረታቻ ጨምሮ ሌሎችም ድጋፎችን ከመንግሥት እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል፡፡

ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥበት የተጠየቀው ሌላኛውና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ሪፖርተር የሚስማር አምራቾችን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ፣ በአጭሩ የሰጡት ምላሽ ሚስማር አምራቾች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን የወሰዱ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ምንም ዓይነት ምላሽ ለመስጠት እንደማይችል የሚገልጽ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለቀረበለት አቤቱታ የሰጠው ምላሽ ስለመኖሩ ለማጣራት ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሚስማር አምራቾች በጽሑፍ ስላቀረቧቸው ጥያቄዎች ለሪፖርተር ማብሪሪያ እንዲሰጡ ለማድረግ የተደረገው ሙከራም እንዲሁ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ሆኖም ከሚስማር አምራቾች ወገን ሪፖርተር በጽሑፍ ለመንግሥት ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን የያዙ ደብዳቤዎች እንዲደርሰው ተደርጓል፡፡

የስቲሊ ምላሽ

ስቲሊ አርኤምአይ የቀረበበትን ወቀሳ ያስተባበለው በሚስማር አምራቾች ላይ ያደረሰው ምንም ዓይነት ጫናም ሆነ የፈጠረው የሞኖፖል ተፅዕኖ እንደሌለ በመግለጽ ነው፡፡ የስቲሊ ኩባንያ የፖሊሲና ኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ለማ እንደገለጹት፣ ኩባንያው በአገር ውስጥ ለሚያመርተው ጥሬ ዕቃ የታሪፍ ከለላ ማግኘቱ በመንግሥት ፖሊሲ መሠረት የተሰጠው መሆኑን፣ የታሪፍ ከለላም ቢሆን ለኩባንያው ብቻ ተብሎ ሳይሆን ጥሬ ዕቃ ለሚያመርቱ ሁሉ የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ስቲሊ ኩባንያ 65 ከመቶ በላይ የገበያ ድርሻ ላለው እህት ኩባንያው ያደላ የምርትና የዋጋ ቅድሚያ ይሰጣል የሚለውን ስሞታውም እያንዳንዱ ሚስማር አምራች የሚገዛበትን ዋጋ ለአስመን ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር ማነፃፀር የሚፈልግ ማንኛውም አካል ምርመራ ማድረግ እንደሚችል፣ የኩባንያው አሠራር ለሁሉም ግልጽ መሆኑንና በየትኛውም መጠን ለሚገዛ ድርጅት በእኩል ዋጋ እንደሚሸጥ ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡

ስቲሊ ያለአግባብ ዘመቻ እንደተከፈተበት የሚገልጹት የኩባንያው ኃላፊዎች ይህ ሁሉ እየደረሰበት ያለው በአጋጣሚ ብቸኛ የስታፋ ብረት አምራች ሆኖ በመገኘቱ እንጂ ወደፊት የሚመጡት ሌሎች አምራቾች የገበያው ተጋሪዎች ቀደም ብለው ጀምረው ቢሆን ኑሮ እንዲህ ያለው ቅሬታ ከሚስማር አምራቾች ዘንድ ሊነሳ ባልቻለ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን ከስምንት እስከ 24 ሚሊ ሜትር የሆኑ ብረቶች ከውጭ በብዛት እንደሚገቡና የታሪፍ ከለላ እንደተጣለባቸው ሲገለጽ፣ ከ5.5. እስከ 6 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለውና በብዛት ለሚስማርም ሆነ ለአጥር ሽቦ መሥሪያነት የሚውለው ስታፋ ብረት ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገር ውስጥ ሳይመረት በመቆየቱ ከውጭ ሲገባ ከቀረጥ ነፃ ይገባ እንደነበር ይገለጻል፡፡ ይሁንና ስቲሊ ጥሬ ዕቃውን ወደ ማምረት በመግባቱ ሳቢያ መንግሥት ከቀረጥ ነፃ ይገባ በነበረው ስታፋ ብረት ላይ የ20 ከመቶ ታሪፍ መጣሉን ይፋ ካደረገ ሁለተኛ ዓመቱ ተቆጥሯል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች