Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የተፈራው ሲደርስ

በሁለት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ርዕሰ ከተሞች ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት ተመሳሳይ የሕንፃ መደርመስ አደጋዎች ተከስተው ነበር፡፡ የናይሮቢና የአዲስ አበባው የሕንፃ መደርመስ አደጋዎች በቀናት ልዩነት የተከሰቱ ናቸው፡፡

በናይሮቢው አደጋ ሕይወት አልፏል፡፡ ከቀናት በኋላ ከፍርስራሽ በሕይወት የተገኙም ነበሩና አደጋው የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት እንዲስብ አድርጐት ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ በሚገኘውና በግንባታ ላይ በነበረው ሕንፃ መደርመስ አደጋ ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ የጠፋ ሕይወት የለም፡፡ ወሬም እዚሁ አገር ውስጥ ተወርቶ የቀረ ነው፡፡ አደጋው የደሰው ሌሊት ላይ በመሆኑ የሰው ሕይወት ሊጠፋ አልቻለም፡፡ ተመስገን! አደጋው ቀን ላይ የተከሰተ ቢሆን ግን ሊጠፋ የሚችለውን ሕይወት መገመት አያቅትም፡፡

በሁለቱ ከተሞች የተከሰተው አደጋ መንስዔ ግን ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ይገመታል ወይም ይታመናል፡፡ በአጭሩ ጥራቱን ካልጠበቀ አገነባብ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ምንም ተባለ ምን የችግሩ መንስዔ ግንባታን በጥራት ካለማካሄድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከናይሮቢ የተናፈሱ ዜናዎች እንደዘገቡት፣ ለአደጋው መንስዔ ናቸው የተባሉ ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በአዲስ አበባም ለተከሰተው አደጋ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ጉዳይ በሕግ መያዙ ተሰምቷል፡፡

እንዲህ ዓይነት ያልታሰበ የሕንፃዎች መደርመስና መገንደስ እንዳይከሰት ግንባታዎች በጥራትና በጥንቃቄ መገንባት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ይህንን ለማስፈጸምም ገዥ የሆነ ሕግ አለ፡፡  

ሕንፃዎቹ በትክክልም እየተገነቡ ስለመሆናቸው ክትትል ማድረግ ቢቻል እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ባልተከሰተ ነበር፡፡ ግን ሆነ!! በታደሉ አገሮች ሕንፃ ሲገነባ ይህንን ያህል መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት እንኳ ንቅንቅ የማይሉ መሆናቸው ተረጋግጦ የሚገነቡ ናቸው፡፡ እንደ ናይሮቢና አዲስ አበባው ሕንፃው ፈንግል እንደያዘው ዶሮ አይፈነገሉም፡፡

ከዚህ አንፃር በርካታ ግንባታዎች ከጥራት ጋር በተያያዘ ወይም በተቀመጡላቸው ዲዛይንና የግንባታ ደረጃ እየተገነቡ ያለመሆናቸው ሲታሰብ፣ ሕንፃዎቻችን ቢያስፈሩን አይገርምም፡፡ በዘፈቀደ ከሙያና ከሥነ ምግባር ውጭ የምናቆማቸው ሕንፃዎች አንድ ቀን ዋጋ ያስከፍሉናል የሚለው ሮሮ መደመጥ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የአዲስ አበባ ሕንፃዎች አገነባብ ሲታይ ባለሙያ መሆን ሳያስፈልግ ከደረጃ ውጭ መሆናቸውን መመስከር ያስችላል፡፡ ለሕንፃው ማቆሚያ ተብለው የተገነቡ አርማታዎች በጠንካራ ቡጢ ግንድስ የሚሉ ይመስላል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ካሉት ግንባታዎች አንፃር ጉዳዩ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚያሻው ስለመሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ይህም ታምኖበት አገሪቱ የሕንፃዎች አገነባብ ሥርዓት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያስገድድ የሕንፃ አዋጅ አውጥታለች፡፡ ይህ አዋጅ ከፀደቀና ሥራ ላይ ከዋለ ከሰባት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ አዋጁን በዝርዝር የተመለከተ በአገሪቱ የሚካሄዱ ግንባታዎች ሥጋት የመሆናቸው ጉዳይ ታሪክ መሆኑን ሊገነዘብ ይችላል፡፡ ሕንፃዎች ግንባታ እንዴት መካሄድ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የሕንፃ ግንባታ ግብዓቶች ደረጃ ማረጋገጫ ካልተሰጠባቸው ሥራ ላይ ማዋል የሚከለክል አዋጅ ነው፡፡

አሳዛኙ ነገር ግን በአዋጁ ውስጥ የተካተቱ የሕንፃ ግንባታ ሒደትና በተለያዩ ጊዜያት የወጡትን መመርያዎች በተግባር ላይ መዋል ባለመቻሉ፣ በዜጐች ሕይወት ብሎም በአገሪቱ ሀብት ላይ ከፍተኛ ሥጋት እየተንዣበበ ይገኛል፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው መሥሪያ ቤት አዋጁ እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ሊባል ይችላል፡፡ አዋጁን ለማፀደቅም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ምን ያህል እንደመከሩበት እናስታውሳለን፡፡

የሕንፃ ግንባታዎች እንደእንጉዳይ እዚህም እዚያም የሚበቅልባቸው የአገራችን ከተሞች እንዲህ ባለው ሕግ ቁጥጥር ካልተደረገባቸው፣ ወደፊት አደጋ መሆናቸው የማይቀር በመሆኑ የሰሞኑ ገጠመኝ በሚገባ አሳይቶናል፡፡ ስለዚህ የአዋጁ መውጣት በእርግጥም አስፈላጊ ነበር፡፡

ነገር ግን አዋጁ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ለመተግበር ያለመቻሉ የአስፈጻሚውን ደካማነት ከማሳየቱም በላይ፣ የሕንፃ ሕግ አውጥተናል ብሎ ወረቀቱን ታቅፎ ከመቀመጥ ውጭ የከወነው ነገር አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡

የሕጉን አስፈላጊነት በማመን ይህ ይቀነስ ይህ ይጨመር በማለት ሕጉን ያፀደቁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሕጉ ያለመተግበሩ ለምን? ብለው ያለመጠየቃቸውም አዋጁ ያለ ግን የሌለ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

በሕንፃው መደርመስ ዕድለኛ ተሁኖ የሰው ሕይወት አልጠፋም እንጂ ቢጠፋ ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው? አስገንቢው? ኮንትራክተሩ? የሕንፃ ሕጉ እንዲተገበር ኃላፊነት የተሰጠው መሥሪያ ቤት? ወይስ ሕንፃው ሳያልቅ የተከራዩት ድርጅቶች?

ሁሉም የየራሱ ተጠያቂነት ሊኖርበት ይችላል፡፡ ለእኔ ግን እንደ አስፈጻሚው አካል ቀዳሚ ተጠያቂ የለም፡፡ የሲኤምሲው ሕንፃ መደርመስን ሳስብ ከደረጃ በታች በሆነ የአገነባብ ስልት የተገነቡ ሌሎች ሕንፃዎችም ዛሬ ሳይሆን ነገ ሊደረመሱ ይችሉ ይሆናል የሚለውን ሥጋት ያሳድርብኛል፡፡

አንዳንዴ አንዳንድ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ አገነባብ በተቀመጠው ዲዛይንና የግንባታ ግብዓት ያልተገነቡ ናቸው የሚለው ሹክሹክታ ሲታወሰኝ ደግሞ፣ ስቱዲዮ መኖሪያ ቤቴ የሚገኝበትን ኮንዶሚኒየም ሕንፃን እንድፈራ ያደርገኛል፡፡ አያድርገውና ከወራት በፊት በሐዋሳ እንደተከሰተው ዓይነት የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት፣ አራትና አምስት ሜትር ወደታች መሠረት ይቆፈርላቸው ተብሎ ሁለት ሜትር ብቻ በተቆፈረ መሠረት ላይ ተገንብተዋል የተባሉት ኮንዶሚኒየም ሕንፃዎችና ሌሎች ሕንፃዎች ይዘውን ዘጭ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ባለው አሠራር የበርካታ ሕንፃዎች ግንባታ አገነባብ በሚመለከተው አካል ከልብ ቁጥጥር አይደረግበትም፡፡  

ስለዚህ የፈራነው ደርሷልና ሌላም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይኖር የሕንፃ አዋጁና አዋጁን ተንተርሰው የወጡ መመርያዎች ይተግበሩ፡፡ ተጠያቂነትም ይኑር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት