Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስዊዘርላንዱ ኔስሌ ከአቢሲንያ ማዕድን ውኃ ጋር ተጣመረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም የተለያዩ የምግብና መጠጥ ሸቀጦችን በማምረትና በማከፋፈል ለሚታወቀው የኔስሌ ግሩፕ አካል የሆነው ኔስሌ ዋተርስ ከአቢሲንያ የማዕድን ውኃ ጋር በእሽሙር የጋራ የታሸገ ውኃ አምራች ኩባንያ በመመሥረት ለመሥራት ተስማሙ፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ያደረገው ኔስሌ፣ ከአቢሲኒያ ጋር በሚመሠርተው ኩባንያው ውስጥ ከፍተኛውን የባለቤት ድርሻ እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡

በአገሪቱ ያለው የውኃ ሀብት ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ተመሳሳይ መጠን ያለው መሆኑ ለኔስሌ መምጣት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በታሸገ ውኃ ኢንዱስትሪው ውስጥ አብረው ለመሥራት የሽርክና ውል ግንቦት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባደረጉት የእሽሙር ስምምነት መሠረት፣ የታሸገ ውኃ ፋብሪካ በመገንባት ወደ መስኩ ይገባሉ፡፡

 “ይህ ስምምነት ኔስሌ ከረጅም ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ ለማምረት የሚያስችለው ሲሆን፣ በአገራችን ኢኮኖሚ የወደፊት ዕድገት ላይ ያላቸውን መተማመን ያሳያል፤” ሲሉ የአቢሲኒያ ማዕድን ውኃ ባለቤቶች አቶ ጎበዝአየሁ ዘሪሁን፣ አቶ ዳዊት ዘሪሁንና አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡

በባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የመጠጥ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ እንዲሁም ጥራት ላለው የታሸገ ውኃ በኢትዮጵያ ያለው ፍላጎት በሁለት አኃዝ ማደጉ ሲገለጽ፣ በውኃ አቅርቦት መስክ በኢትዮጵያ ዘላቂ የውኃ አቅርቦት ያለው አካባቢ የሚገኝ የአቢሲኒያ ውኃ ፋብሪካ የሚገኘው በዓመት በአማካኝ 1250 ሚሊ ሜትር ዝናብ በሚያገኘው ከሱሉልታ ከተማ ነው፡፡ ይህ የዝናብ መጠን በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ አገሮች ከሚያገኙት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዘላቂ የውኃ አቅርቦት ምንጭ መሆኑ ለዚህ ውል መፈረም ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡

ሁለቱም ተዋዋዮች ለአካባቢው ኅብረተሰብ የጋራ የሆኑ እሴቶችን የመፍጠር እሳቤዎችን ይጋራሉ፡፡ ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች በአካባቢው ያለውን የውኃ አቅርቦት ምንጭ ዘላቂነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን ለማከናወን እንዲሁም የኔስሌ ግሩፕ ዓለም አቀፍ መርህ ሆነውን ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ መጠቀምን ዓላማ በመከተል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት በመተባበር ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

ሌሎች አገሮች ያሉት የታሸገ ውኃ ማምረቻ ፋብሪካዎች ውስጥ እንደሚያደርገው ሁሉ ኔስሌ ዋተርስ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ በማተኮር በኃላፊነት ሥራውን ይወጣል፡፡ ፋብሪካ ከማቋቋም ጀምሮ እስከ ሥራ ማካሄዱ ላይ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት በማድረግ ሥራው የሁለትዮሽ ጥቅም እንዲኖረው ያረጋግጣል፡፡ ከዚህም አንዱ የሚሆነው አካባቢው የንፁህ ውኃ አቅርቦት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም ለአካባቢው ኅብረተሰብ የገቢ ምንጭ የሚያስገኝ የውኃ አጠባበቅ ፕሮግራም ይኖራል፡፡ ይህም የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ ፈጣሪነትን የማበረታታት ልምምድን ያካትታል፡፡

“ይህ ኢንቨስትመንት ኔስሌ ግሩፕ ለአፍሪካ ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ትኩረታችንም የአካባቢው የንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ ዘላቂ የጋራ የውኃ ምንጭ አጠቃቀምና ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሆናል፤” ሲሉ የኔስሌ ዋተርስ ሪጅናል ማናጀር ጋይ ባኒ ተናግረዋል፡፡

የዚህ ውል ዝርዝሮች ይፋ አልሆኑም፡፡ ስለ አቢሲኒያ ውኃ ባለቤቶች አቶ ጎበዝአየሁ ዘሪሁን፣ አቶ ዳዊት ዘሪሁንና አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን የአቢሲኒያ ስፕሪንግስ የታሸገ ውኃ ድርጅት ባለቤቶች ናቸው፡፡ የታሸገ ውኃ ድርጅታቸውን እ.ኤ.አ. 2004 አሁን የገበያውን አሥር በመቶ መያዙ የሚነገርለትን የአቢሲኒያ ስፕሪንግስ ብራንድ አስተዋውቀዋል፡፡ እንዲሁም በጭማቂና በለስላሳ መጠጥ፣ በተፈጨ ቡና፣ በታሸገ ሻይ፣ በኅትመትና በሪል ስቴት በመሳሰሉ የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ይሠራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በሚከፈቱ ሁለት የቤስት ዌስተርን ሆቴሎችና በሱፐር ስቴክ ራንች የቼን ሬስቶራንት በመስተንግዶ ዘርፍ ውስጥ ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች በሽርክና ውሉ ውስጥ አልተካተቱም፡፡

ኔስሌ ዋተርስ በኔስሌ ግሩፕ ውስጥ የተዋቀረ የታሸገ ውኃ ክፍል ሲሆን፣ በሥሩ 52 የታሸጉ የውኃ ብራንዶች ያለው ቀዳሚ ዓለም አቀፍ የታሸገ ውኃ አምራች ድርጅት ነው፡፡ በ36 አምራች አገሮች ከ33 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ የኔስሌ ብራንዶች በኢትዮጵያ በደንብ ታዋቂና ለብዙ ዓመታት የቆዩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኒዶ፣ ማጂ መረቅ፣ ኪትካት፣ ኮፊሜት፣ ኒስካፌ፣ ናንና ኤስ – 26 ብራንዶች ኔስሌ ወደ ኢትዮጵያ ከሚያስገባቸው ሌሎች ብራንዶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ኔስሌ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው አንደኛ ደረጃ ልዩ ቡና ገዝቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ ለሆኑት ኔስፕሬሶና ዶልቼ ጉስቶ ብራንዶቹ ይጠቀማል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች