Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየታገዱ ቡና ነጋዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቀረቡ

የታገዱ ቡና ነጋዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

ንግድ ሚኒስቴር ከ19,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ሰውረዋል በማለት እንዲታገዱ ያደረጋቸው 24 ነጋዴዎች፣ ዕግዱን በመቃወም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ነጋዴዎቹ ግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡት አቤቱታ የንግድ ሚኔስቴር ዕገዳ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ መከራከርያቸውን አቅርበዋል፡፡

የታገዱ ነጋዴዎች አቤቱታ ማጠንጠኛ በመጀመርያ ደረጃ ንግድ ሚኒስቴር የማገድ ሥልጣን የለውም፣ የማገድ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ነው፣ ባለሥልጣኑም ቢሆን ዕግድ ከማውጣቱ በፊት ማሳወቅ ይኖርበታል የሚል ነው፡፡

ነጋዴዎቹ የተጠረጠሩበት ሕገወጥ የተባለ ተግባር ካለ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ዕድል ወይም በአዋጁ የተሰጣቸው የመስማት መብት ሊከበር እየተገባ፣ ሳይከበር ቀርቶ ዕግድ መጣሉ አግባብ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የታገዱት ነጋዴዎች ቡና ሰብስበው ለምርት ገበያ የማያቀርቡ መሆናቸውን፣ በምርት ገበያ በኩል ያቀረቡት ቡናም ለ54 ቡና ላኪዎች በመሸጡ እነሱን እንደማይመለከታቸው ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹ቡናው በምርት ገበያ በኩል ለላኪዎች የተሸጠ በመሆኑ፣ ልንጠየቅ አይገባም መጠየቅ ካለባቸው ቡና ላኪዎቹ ናቸው፤›› የሚል ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡

የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባላቸው ወንበር እንዳይገበያዩ ስለማድረግ›› በሚል ርዕስ በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለደንበኞች ወንበር በማዘጋጀት መሥፈርቶችን ያሟሉ፣ የአባልነት መቀመጫ በመያዝ አባሉ በቀጥታ ለራሱ የሚገበያይ ወይም ደግሞ በአባልነት መቀመጫው ውልን መሠረት በማድረግ ሌሎች ቡና ላኪዎች እንዲገበያዩ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሠረት ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2008 በጀት ዓመት አጋማሽ ድረስ፣ 24 የምርት ገበያው አባል ነጋዴዎች ግብይት የፈጸሙላቸው 54 ቡና ላኪዎች ለኤክስፖርት የገዙት 19,343,84 ሜትሪክ ቶን ቡና የሰወሩ መሆኑ ተረጋግጧል›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ድርጊት ደግሞ የቡና ግብይት በሚመራባቸው ሕጎች የተከለከለና በወንጀል የሚያስቀጣ ከመሆኑም ባሻገር፣ በቡና ግብይት ሥርዓትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያስከትላል፡፡ በአባልነት ወንበራቸው ቡናው እንዲሰወር የተባበሩ አካላት በፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ተባባሪነት በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የምርት ገበያው አባላት (24) ግብይት እንዳይፈጽሙ እንዲታገዱ፤›› በማለት ሚኒስትር ዴኤታው የጻፉት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

የተሰጣቸውን ዕውቅና በአግባቡ ባልተጠቀሙ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ኃላፊነት ነው በማለት፣ ነጋዴዎቹ ንግድ ሚኒስቴር ሊያግዳቸው እንደማይገባ መከራከርያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡

በእርግጥ ንግድ ሚኒስቴር ይህ ሥልጣን እንደሌለው ዘግይቶ በመረዳቱ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ይህንን ኃላፊነት ወስዶ በሥሩ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማድረጉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በአግባቡ ሥራቸውን የማያከናውኑ አባላትን እስከ 180 ቀናት ለማይበልጥ ጊዜ የማገድ ሥልጣን አለው፡፡ የታገዱት ነጋዴዎች በበኩላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፍት ቤት ባቀረቡት አቤቱታ፣ አዋጁ የሰጣቸው የመስማት መብት እንደተጣሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 19 የባለሥልጣኑ መመርያዎችና ድንጋጌዎች በግብይት ፈጻሚው መጣሱን በማሳየት ከ180 ቀን ላልበለጠ ጊዜ ዕውቅናን የማገድና የመሰረዝ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ዕውቅና በሚታገድበት ወይም በሚሰረዝበት ጊዜ ለዕውቅና ያመለከተ ማንኛውም ሰው ወይም ዕውቅናው የታገደበት ወይም የተሰረዘበት የምርት ግብይት ፈጻሚ፣ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ያለው ሐሳብ የመስማት ዕድል ይሰጠዋል ይላል፡፡

ነጋዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት አቤቱታ የመደመጥ መብታቸው እንደተጣሰ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ልንጠየቅና ሐሳባችንን እንድናስረዳ መደረግ ነበረበት፤›› በማለት ነጋዴዎቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ የነጋዴዎቹ ቅሬታ በመቀጠል 24 ኩባንያዎች ቡና ለምርት ገበያ የሚያቀርቡ ሆነው፣ ከእነሱ ቡና የገዙ 54 ቡና ላኪዎች ደግሞ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ተጠያቂ የተደረግነው ከገበሬ ቡና ሰብስበን ለምርት ገበያ የምናቀርበው መሆናችን አግባብ አይደለም፤›› የሚል ቅሬታም አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል 7.6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ከ19 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ተሰወረ የተባለው ከ2000 ዓ.ም. እስከዚህ ዓመት አጋማሽ ድረስ ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ለስምንት ዓመታት የት ነበር? ምን ሲሠራ ከረመ? የሚል ጥያቄም እየተነሳ ይገኛል፡፡

የዘርፉ ተዋናዮች ቡና የመሰወር እንቅስቃሴ መኖሩን በተደጋጋሚ ቢገልጹም ሰሚ አለማግኘታቸውን እየተናገሩ ነው፡፡

የታገዱት የምርት ገበያ አባላት በርካታ ውል ያሏቸውና ይህ ዕግድም የገነቡትን መልካም ስም የሚያበላሽ በመሆኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፍት ቤት ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...