Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ መሳተፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጨረታ ብቻ እንዲስተናገዱ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– 6,000 ሜጋ ዋት አመነጫለሁ ያለው ኩባንያ የመጨረሻ ውሳኔ እየጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች በጨረታ ብቻ እንዲስተናገዱ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ መሠረት ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው ሲደራደሩ የቆዩ ኩባንያዎች ድርድሮች መሰረዛቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዚህ በኋላ የውኃ፣ የፀሐይ፣ የንፋስና የጂኦተርማል ፕሮጀክቶችን ጨረታ በማውጣት ብቁ ሆነው ለተገኙ ኩባንያዎች ይሰጣል ተብሏል፡፡

ከ14 በላይ ኩባንያዎች በኃይል ዘርፍ ለመሰማራት ለውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበው ይሁንታ በማግኘታቸው፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሲደራደሩ ቆይተዋል፡፡

ሁነኛ ኃይል አመንጪ ኩባንያ ለማግኘት ጨረታ ተመራጭ መንገድ ነው ተብሎ በመታመኑ፣ የድርድር ሒደቶች እንዲቋረጡና ከዚህ በኋላም በጨረታ ብቻ የኩባንያዎች መረጣ እንዲካሄድ ቦርዱ መመርያ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት ካሳዩ ኩባንያዎች መካከል አገር በቀል ኩባንያ የሆነው ደን ኢንጂነሪንግ ኔትወርክ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ከጀርመኑ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጌልፎርስ ጋር በመሆን ከአውሮፓ ፋይናንሰሮች በሚያገኘው 7.2 ቢሊዮን ዩሮ፣ ከተለያዩ አማራጭ የኃይል ምንጮች ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ይህ ኩባንያ በመጀመርያው ዙር በአዲስ አበባ ዙርያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ አካባቢ ከንፋስ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ በቴክኒክና በፋይናንስ ላይ ሲደራደር ቆይቷል፡፡

ይህ ድርድር ሁለት ዓመት ተኩል ያስቆጠረ ሲሆን፣ ኩባንያው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሲያካሂድ የቆየው ድርድር ተጠናቆ ለቦርድ ቀርቦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከደን ኢንጂነሪንግ ጋር ሲያካሂድ የቆየው ድርድር ረዥም ጊዜ መውሰዱንና ኩባንያው የተሻለ ቴክኖሎጂና ዋጋ ማቅረቡን አመልክቶ፣ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ ድርድር ሲያካሂዱ የነበሩ ሁሉም ኩባንያዎች በጨረታ እንዲያልፉ በሰጠው ውሳኔ መሠረት፣ ይህም ፕሮጀክት ጨረታ እንደሚጠብቅ አስገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጻፈው ደብዳቤ እንዳብራራው፣ ደን ኢንጂነሪንግ ይዞት የመጣው ቴክኖሎጂ እስካሁን በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ከዋሉት የተለየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በዋጋ ደረጃ የኩባንያው ሞዴል ተወስዶ ቴክኖሎጂውና አደረጃጀቱ ምን እንደሚመስል ለመረዳት ጊዜ መውሰዱን አመልክቷል፡፡

በደብዳቤው እንደተብራራው ደን ኢንጂነሪንግ ለአንድ ኪሎ ዋት በሰዓት ያቀረበው ዋጋ 0.76 ዩሮ ነው፡፡ ይህ ዋጋ ከሌሎች የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለም የንፋስ ኃይል አማካይ ዋጋ በአንድ ዋት በሰዓት 1.3 ዶላር መሆኑም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በማስተር ፕላኑ ያስቀመጠው ደግሞ 1.8 ዶላር በመሆኑና ደን ኢንጂነሪንግ ካቀረበው ዋጋ ጋር ሲተያይ በኩባንያው የቀረበው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን በመተንተን አስረድቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በደን ኢንጂነሪንግ መካከል የተካሄደው ድርድር በስምምነት የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ በጨረታ ላይ ትኩረት በማድረጉ ስምምነቱ ያለውጤት ተንጠልጥሎ መቅረቱን ኩባንያው እንዳሳሰበው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ደን ኢንጂነሪንግ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ለሚመራው የኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹ብዙ ሒደቶችን ተጉዘን እየተግባባን ከሄድን በኋላ የታሪፍ ሥሌቱ ማጠቃለያ ላይ ለመድረስ፣ የቴክኖሎጂ ባለቤቱና ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ባደረግነው ውይይት ታሪፉ 0.76 ኪሎ ዋት በሰዓት ሆኖ ፀድቋል፡፡ ይህ ታሪፍ በመፅደቁም ከሳምንት በኋላ ቦርዱ ስምምነቱን ያፀድቀዋል ተብሎ ተነግሮን ነበር፤›› በማለት የተደረሰበትን ደረጃ አመልክቷል፡፡ ደን ኢንጂነሪንግ በመጨረሻ ለዶ/ር ደብረ ጽዮን ባቀረበው ጥያቄ የቴክኖሎጂው ጠቀሜታ፣ የተገኘው ፋይናንስና ለሁለት ዓመት ተኩል ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋጫ እንዲበጅለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለጨረታ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሚወጡት ጨረታዎች የሚሳተፉ ኩባንያዎች ከራሳቸው ምንጭ ፋይናንስ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች