Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕንፃ የሚገነቡ ኮንትራክተሮች የግንባታ ዋስትና እንዲያሲዙ ሊገደዱ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሕንፃ ግንባታ ለማከናወን ውል የሚገቡ ማናቸውም ኮንትራክተሮች፣ የሕንፃ ግንባታው ከሚፈጀው ጠቅላላ ዋጋ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ዋስትና ለማስያዝ ሊገደዱ ነው፡፡

ከግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ማሳሰቢያ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የግንባታና ቁጥጥር ቢሮ የተላለፈ ሲሆን፣ በየክፍላተ ከተሞች የግንባታና የቁጥጥር የሥራ ሒደቶች አማካይነት ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡ ማሳሰቢያው ማንኛውም የሕንፃ ግንባታ ለማከናወን ውል የገባ ኮንትራክተር በውል ሰነዱ መሠረት ግንባታው በሚከናወንበት ወቅት፣ በግንባታ ጥራትና በጥንቃቄ ጉድለት ሊደርስ ለሚችል ጉዳት ማካካሻ የሚሆን ዋስትና ማቅረብ አለበት፡፡ ሕንፃ የሚገነቡ ኮንትራክተሮች ዋስትናውን ይዘው መቅረብ ያለባቸው ከፈቃድ ጥያቄ ጋር ተያይዞ መሆን ይኖርበታል፡፡

ዋስትናው ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ለሚቆይ የጉዳት ማካካሻ ሲሆን፣ ዋስትናው የሕንፃ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡

የሕንፃ አዋጁን ተንተርሶ የወጣውን ደንብ ቁጥር 26 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት ያደረገውና የዋስትና መጠኑን የሚያሳይ መረጃም ተያይዟል፡፡ ከሪል ስቴት ውጪ ያሉ የምድብ ‹‹ለ›› የሕንፃ ኮንትራክተሮች የግንባታው ግምት እስከ 10 ሚሊዮን ብር ከሆነ 20 በመቶ ወይም ሁለት ሚሊዮን ብር፣ ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት የሚቆይ ዋስትና ከታወቀ የመድን ሰጪ ድርጅት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

ለሪል ስቴትና ለምድብ ‹‹ሐ›› ሕንፃ ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቱ ሊፈጅ የሚችለው ወጪ ተገምቶ 10 ሚሊዮን ብር ከሆነ 30 በመቶ ወይም ሦስት ሚሊዮን ብር፣ 15 ሚሊዮን ብር ከሆነ 25 በመቶ ወይም 3.75 ሚሊዮን ብር፣ 25 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ የሕንፃ ግንባታ ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና ማቅረብ አለባቸው፡፡ ኮንትራክተሮች ግንባታ ከመጀመራቸው በፊት ዋስትናውን በፐርፎርማስ ቦንድ ማቅረብ አለባቸው፡፡

በክፍላተ ከተሞቹ ተፈጻሚ የሚሆነው ይህ ማሳሰቢያ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሚት አካባቢ ከደረሰው የሕንፃ መደርመስ በኋላ ተፈጻሚ እንዲሆን መደረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡

የሕንፃ ግንባታዎችን የተመለከተው አዋጅ ግን ከሰባት ዓመታት በፊት ነው የወጣው፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም የተለያዩ መመርያዎችና ደንቦች ወጥተዋል፡፡ በመመርያዎቹና በደንቦቹ ውስጥ ከተጠቀሱት አንቀጾች ውስጥ አንዱ ኮንትራክተሮች ዋስትና ማስያዝ እንዳለባቸው የሚያመለክተው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ሥራ ላይ ሳይውል ቆይቷል፡፡  

የሕንፃ አዋጁን ተከትለው በወጡ መመርያዎችና ደንቦች አንድ የሕንፃ ግንባታ መከናወን ያለበት በተመዘገበ ተቋራጭ ብቻ እንደሆነ ከመገለጹም በላይ፣ ኮንትራክተሩና አስገንቢው የሕንፃ አዋጁ ባስቀመጣቸው መሥፈርቶች መሠረት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ማረጋገጫ ሊኖር ይገባል፡፡

የሕንፃ አዋጁን ተከትለው በወጡት ደንብ ቁጥር 243/2003፣ መመርያ ቁጥር 5/2003 እና በሌሎች ተያያዥ መመርያዎች ተፈጻሚ መሆን የሚገባቸው ተግባራት እንዳሉ ቢታወቅም፣ አሁን ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ የተሠራጨው ማሳሰቢያ ግን ዋስትና ላይ ብቻ ነው የሚያተኩረው፡፡

ከግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ግንባታ መጠናቀቅ ድረስ ተግባራዊ መሆን የሚገባቸው ሥራዎች ተፈጻሚነታቸው የሚረጋገጠው፣ በአዋጁና በመመርያዎቹ መሠረት አስፈጻሚ አካላት ሲከታተሏቸው ነው በማለት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ከአስተዳደሩ የግንባታና ቁጥጥር ቢሮ የተገኘው መረጃ አዋጁን፣ መመርያዎቹንና ደንቦቹን ማስፈጸሚያ ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር እየተገባ ነው፡፡ ቢሮው ማኑዋሎቹን እስካሁን ሲሠራባቸው መቆየቱን ገልጾ፣ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ በሁሉም ደረጃ የሕንፃ ግንባታዎች ተፈጻሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አስታውቋል፡፡  

በሥራ ሒደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉ ከኮንትራክተሮች ማኅበርና መሰል ማኅበራት ጋር ለመምከርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች