Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጁፒተር ትሬዲንግ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ አማካይነት ፈጽሟል ያለውን ወንጀል እያጣራሁ ነው አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዕውቅና ከሰጣቸው 14 የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን አቅራቢ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ በሆነው ጁፒተር ትሬዲንግ ተፈጽሟል ያለውን ወንጀል እያጣራሁ ነው አለ፡፡

ባለሥልጣኑ ተፈጸመ ያለው ወንጀል መነሻው ጁፒተር ትሬዲንግ ዓመታዊ ዕድሳት እንዲያካሂድ በተሰጠው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ላይ፣ ከ800 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያለው ደረሰኝ ታትሞበት ለደንበኛው በመመለሱ ምክንያት ነው፡፡

ታተመ የታባለው ደረሰኝ ዛማይ ኢንዱስትሪያል ኩባንያ ሽያጭ ያላካሄደበት መሆኑን በመግለጽ ለባለሥልጣኑ ባቀረበው አቤቱታ መግለጹንና እንዲጣራለት መጠየቁን የገለጹት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታክስ ወንጀል ከፍተኛ ኦፊሰር አቶ ሀብታሙ ካሳሁን ናቸው፡፡ የወንጀል ይዘት ያለው ድርጊት በመሆኑ በይበልጥ እንዲጣራ እየተደረገ እንደሚገኝ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡  

ዓመታዊ ዕድሳት እንዲደረግለት ለጁፒተር ትሬዲንግ መሣሪያውን የሰጠው ዛማይ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡ የጁፒተር ትሬዲንግ ኩባንያ ቴክኒሻኖች ፈጽመውታል በተባለው ድርጊት ከ800 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያለው ደረሰኝች ታትሞ እንደነበር፣ ኩባንያው ካቀረበለት አቤቱታ መረዳቱን በከፍተኛ ግብር ከፋዮች የወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ አቶ ዝናቡ አበበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ወንጀል በመፈጸሙ ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው፡፡ አቅራቢው ብቻም ሳይሆን አገልግሎት ጠያቂውም እንደ ወንጀሉ አስገዳጅነት ምርመራ ይካሄድበታል፤›› ያሉት አቶ ዝናቡ፣ ሆኖም ወጀንል ስለመፈጸሙ አመላካች ፍንጮች በመታየታቸው ምክንያት ሁለት ተጠርጣሪ የጁፒተር ትሬዲንግ ቴክኒሻኖች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበርና በተደረገባቸው ማጣራት ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ እንደተለቀቁ ገልጸዋል፡፡

የምርመራው ሒደት ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት እንደሚቆጠቡ አስታውቀዋል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ የባልቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያም በጉዳዩ ላይ የወንጀል ምርመራ ለመጀመር እየተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዛማይ ኩባንያ ባለቤቶች ስለጉዳዩ ማብራሪያ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ በመግለጽ፣ ጉዳዩ በሕግ ፊት እልባት እስኪያገኝ እንደሚጠባበቁ አስታውቀዋል፡፡ የጁፒተር ትሬዲንግ ተወካይ  ግለሰብ በበኩላቸው ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ሆን ተብሎ ያልተደረገና ከኩባንያው ሠራተኞች በአንዱ በሥራ አጋጣሚ ሳይታሰብ የተፈጠረ መሆኑን በፍርድ ቤት ጭምር በማስረዳት ጉዳዩ እልባት እንዳገኘ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዕውቅና ከሰጣቸው መካከል ሌላኛው በሆነው ሐሮን ኮምፒዩተርና አብረተው በተከሰሱ አካላት አማካይነት ተፈጸመ በተባለ ወንጀል መሠረት፣ ሐሰተኛ ደረሰኞችን በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በማተምና የታክስ ሥወራ በመፈጸም ወንጀል ተጠርጥረው ክስ እንደተመሠረተባቸው ታውቋል፡፡ ሐሮን ኮምፒዩተርና አብረውት በወንጀል ተሳትፈዋል የተባሉ አካላት 167 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የሐሰተኛ ደረሰኞችን ሽያጭ በማከናወን፣ የ27 ሚሊዮን ብር የታክስ ስወራ ጉዳት ከማድረሳቸው በላይ፣ የ51 ሚሊዮን ብር የተጨማሪ እሴት ታክስና የገቢ ግብር ጉዳት እንዳደረሱ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክስ ይጠቁማል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች