የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚቀጥለውን አዲስ ዓመት የ114 ችግረኞች መኖሪያ ቤት በማደስና 96 የቆሻሻ ቦታዎች በማፅዳት፣ ተምሳሌታዊ ሥራ በማከናወን ለመቀበል ማቀዱን አስታወቀ፡፡
አስተዳደሩ ይህንን ተምሳሌታዊ ሥራ ለማከናወን ያቀደው፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ከበጎ አድራጊ ወጣቶች ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማኅበራዊ የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የቤቶቹ ዕድሳት በ15 ቀናት ውስጥ፣ የቆሻሻ ቦታዎችን ማፅዳት ደግሞ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ይካሄዳል ብለዋል፡፡
የበጎ አድራጎት ተምሳሌታዊ ሥፍራው የችግኝ ተከላ በማካሄድ፣ 30 ሺሕ ለሚሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችና የደንብ ልብስ በመሟላት፣ ሰባት ሺሕ ሕፃናት ምግብ ቋጥረው ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉ በመሆናቸው ድጋፍ እንዲያገኙ መመቻቸቱ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በበዓሉ ዋዜማ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡
የአዲሰ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ነብዩ ባዬ እንደገለጹት፣ ቀጣዩን አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ ለማክበር የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ትልቅ ብርታት ይሰጣል፡፡
‹‹እንዲህ ዓይነት በጎ ተግባራት ግን በዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣይነት ባለው መንገድ በዕቅድ ሊከናወን ይገባል፤›› ሲሉም ቀጣዩን የአስተዳደሩ ዕርምጃ አመላክተዋል፡፡