Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ሐሳብ ቀረበ

ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ጥረት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፣ የአምራች ኢንዱስትሪዋ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪውን የ2010 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው ውይይት ላይ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በበጀት ዓመቱ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኤክስፖርት 997.9 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 487.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

በ2012 ዓ.ም. የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ዘመን ከዘርፉ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ታቅዷል፡፡ የአምራች ዘርፉ 21 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ያደገው 11 በመቶ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 109 ሚሊዮን ዶላር፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች 133.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ሥጋና ወተት 107.6 ሚሊዮን ዶላር፣ ምግብና መጠጥ 59.2 ሚሊዮን ዶላር፣ ፋርማሲዩቲካል 2.4 ሚሊዮን ዶላር፣ ኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች 28.2 ሚሊዮን ዶላር፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ 27.4 ሚሊዮን ዶላርና ኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ 42.9 ሚሊዮን ዶላር ማስገባታቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም የኢኮኖሚ ዕድገት በመመዝገብ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪና የግብዓት እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥና የፀጥታ ችግር በአምራች ዘርፍ ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን አስረድተዋል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች የልማት አርበኞች እንደሆኑ ገልጸው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት መንግሥት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንና የፖለቲካ ሁኔታውም በመረጋጋት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቦጋለ ፈለቀ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መረጋጋት የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰላምና መረጋጋት ቢኖር ኖሮ የአምራች ዘርፉ ከዚህ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘግብ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹አምራች ዘርፍ ባለሀብቱ በቀላሉ ገንዘብ የሚሠራበት አይደለም፡፡ ትርፍ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት ነው፤›› ያሉት አቶ ቦጋለ፣ በአሁኑ ወቅት በባለሀብቱ አካባቢ የግንዛቤ ችግር እንደሌለ፣ ባለሀብቱ ወደ አምራች ዘርፍ መግባት የማይፈልገው ፈተናዎቹን በመፍራት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹እኛ አሁን መሥራት ያለብን የማስተዋወቅ ሳይሆን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን እየለየን መፍታት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ግልጽ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ንዑስ ዘርፍ የተጋረጡበትን ችግሮች በዝርዝር አስረድቷል፡፡ በተለይ በርከት ያሉ ቆዳ አምራቾች ብሶታቸውን አሰምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቆዳ አምራቾች ተወካይ በጥሬ ቆዳ ኤክስፖርት ላይ ማዕቀብ በመጣሉና የአገር ውስጥ ቆዳ ፋብሪካዎች ቆዳ በበቂ መጠን ስለማይገዙ፣ የአገር ውስጥ ዋጋ እንደወደቀ ተናግረዋል፡፡ የቆዳ ዋጋ በመውደቁ ነጋዴዎች መሰብሰብ እንዳቆሙ የገለጹት ተወካዩ፣ የኢትዮጵያ ቆዳ ገዥ አጥቶ እየበሰበሰ ከውጭ ቆዳ እየተገዛ መግባቱ እንዳሳዘናቸው አስረድተዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. 24 ሚሊዮን ቆዳ አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን፣ 2.5 ሚሊዮን የሚሆነው ከውጭ ተገዝቶ የገባ ነው፡፡ የቆዳና ሌጦ፣ ቅመማ ቅመምና ጥጥ አምራቾች ለንዑስ ዘርፎች ትኩረት እንዲሰጡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ጠይቀዋል፡፡

ሥጋ ላኪዎች በበኩላቸው የአገር ውስጥ የሥጋ ዋጋ ከውጭ ገበያ የላቀ በመሆኑ፣ ሥጋ ለመላክ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የበሬ ዋጋ የሚቀመስ ባለመሆኑ የበሬ ሥጋ መላክ አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የኮንትሮባንድ ንግድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አብዛኛዎቹ ዘመናዊ ቄራዎች የፍየልና የበግ ገበያ ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ተነግሯል፡፡ አብዛኛው የበግና የፍየል ሥጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚላክ ታውቋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የማስፈጸም አቅም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የጻፈላቸውን ደብዳቤ ይዘው ወደ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲሄዱ እንደሚሳቅባቸውና ሚኒስቴሩ ጥርስ የሌለው አንበሳ እንደሆነ እንደሚነገራቸው አስታውቀዋል፡፡

የኬሚካል ግብዓቶች አምራቾች ማኅበር ተወካይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትና አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት አድርገው መሥራት ያለባቸው በግብዓት ልማት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብዓት ከውጭ አስገብተው በማምረት ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ የገለጹት ተወካዩ፣ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ሊተኩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ምርምር መሥራት አለብን፤›› ያሉት ተወካዩ፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን እንዲደግፍ ከስድስት ዓመት በፊት የተቋቋመው የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት አንድም ቤተ ሙከራ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪውን እንዲደግፍ መጀመርያ የኢንስቲትዩቱ የራሱ አቅም ሊገነባ ይገባል ብለዋል፡፡

በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲና የክልል የሊዝ ፋይናንስ ኢንተርፕራይዞች የማሽነሪዎችና ብድር አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር አውስተዋል፡፡ የልማት ባንክ በሚሰጠው የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ማሽነሪዎች ገዝቶ ለአምራቾች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ የፋይናንስ አቅራቢ ሆኖ ሳለ ማሽነሪዎቹን ከውጭ ገዝቶ የሚያቀርብ በመሆኑ ሒደቱ ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅበት ተገልጿል፡፡ ባንኩ ብድር አቅራቢ ነው፡፡ በዚህ ላይ ማሽኖች ገዝቶ የሚያቀርብ በመሆኑ አጠቃላይ ሒደቱ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ይፈጅበታል ያሉት ኃላፊዎቹ፣ ባንኩ ብድሩን ቢያቀርብ በማሽን ግዥና አቅርቦቱ ላይ የግሉ ዘርፍ ቢሳተፍ የግዥውን ሒደት የተቀላጠፈ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት በማሽነሪዎች አቅርቦት በኩል መዘግየት ይታያል፡፡ ‹‹ከሌሎች አገሮች ልምድ እንዳየነው ብድሩን ባንኩ ቢያቀርብ፣ የግሉ ዘርፍ በማሽኖች አቅርቦት ላይ ቢሳተፍ የተቀላጠፈ አሠራር መዘርጋት ይቻላል የሚል እምነት አለ፡፡ ይህን ሐሳብ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለመንግሥት እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡

የክልል ሊዝ ፋይናንስ ኢንተርፕራይዞች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንዳያበድሩ የተጣለባቸው የብድር ጣሪያ ሊያሠራቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ በክልል ከተሞች በመገንባት ላይ ያሉት ‹ተርንኪ› ወርክሾፖች ግንባታቸው ለአራት ዓመታት በመጓተቱ፣ ለግንባታው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለወሰዱት ብድር ወለድ በመክፈል ላይ በመሆናቸው ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እንደገባ በምሬት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች