Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞቹን ችግር መፍታት ያልቻለው በማስፈጸም አቅምና በግብዓት አቅርቦት ችግር...

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞቹን ችግር መፍታት ያልቻለው በማስፈጸም አቅምና በግብዓት አቅርቦት ችግር ነው አለ

ቀን:

በዓለም ባንክና በቻይና ድጋፍ እየተከናወነ ያለው ፕሮጀክት አልተጠናቀቀም

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞቹን ችግር መፍታት ያልቻለው፣ የሰው ኃይል የማስፈጸም አቅም ውስን በመሆኑና በግብዓት አቅርቦት ችግር እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን በሚመለከት ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በርካታ ደንበኞቹን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ መስመሮችን መቀየር፣ መስመሮቹን ለማሻሻልና ለመቀየር ደግሞ ከፍተኛ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ ሥራውን የሚመጥን በጀት ደግሞ ለማግኘት አልቻለም፡፡ በመሆኑም የመስመሮቹን አቅም ለማሻሻል የሚያስፈልጉ የግብዓት አቅርቦቶችን ከአገር ውስጥ ማግኘት ግድ እንደሆነበት፣ ያም ቢሆን ችግሩ ሊቀረፍ አለመቻሉን መግጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ፣ የሥርጭት ሲስተም ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስናቀ ታምሩና ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌቱ ገረመው አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

ከአገር ውስጥ ይገኛል ተብሎ የታቀደ የግብዓት አቅርቦት በብዛትና በጥራት ወቅቱን ጠብቆ ባለመቅረቡ፣ ከፍተኛ የሆነ እጥረት እንደገጠመው ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ የደንበኞቹን ችግር መፍታት ካለመቻሉም በተጨማሪ፣ ደረጃውን የጠበቀ መከላከያ በሥራ ወቅት ማቅረብ ባለመቻሉ፣ በሰውና በእንስሳትም ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በአገር ውስጥ በተወሰኑ አቅራቢዎች ይሟላል ተብሎ የነበረው የግብዓት አቅርቦት ሊሳካ ባለመቻሉ፣ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም መሥፈርቱን ማሟላት የሚችል ተሳታፊ ተወዳድሮ ማቅረብ እንዲችል ጨረታ ወጥቶ በማወዳደር ላይ እንዲሆኑም ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በስምንት ከተሞች ማለትም አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ ሐዋሳ፣ ደሴ፣ ባህር ዳርና አዳማ ከተሞች ያለባቸውን የኃይል መቆራረጥና የኃይል ብክነት ለመቀነስ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ደንበኞችን ለማግኘት ከቻይና ኤግዚም ባንክና ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር በመከናወን ላይ ያለው ፕሮጀክትም አለመጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባን የኃይል ሥርጭት ችግር 50 በመቶ ይቀርፋል የተባለውን ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ 162 ሚሊዮን ዶላር በፓወር ቻይና ኩባንያ በመከናወን ላይ የሚገኘው ፕሮጀክት መጠናቀቅ ያለበት በ2010 ዓ.ም. ቢሆንም፣ እስካሁን የተከናወነው 72 በመቶ መሆኑን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአየር ላይ የሚያልፍ የመስመር ዝርጋታና መሬት ለመሬት በ140 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋ ኬብል እንዳለው ይታወቃል፡፡ 85 በመቶ የሚሆነው ወጪ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘ ብድር ሲሆን፣ 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ስምንቱ ከተሞች ያለባቸውን የኃይል መቆራረጥና የኃይል ብክነት ለመቀነስ፣ እንዲሁም አዳዲስ ደንበኞችን ለማግኘት የሚከናወን ፕሮጀክት ከዓለም ባንክ በተገኘ 62 ሚሊዮን  ዶላር ሲሆን፣ ከ400 በላይ ትራንስፎርመሮች እንደሚተከሉ ተገልጿል፡፡ ያም ሆነ ይህ የአገልግሎቱ ደንበኞች ግን ከኃይል መቆራረጥና አልፎ አልፎም ለቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸው እንደሚቆይ እየታየ ያለ ችግር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 420 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለመገንባት ዕቅድ ይዞ 139 ማዕከላት መገንባቱን፣ በገጠርና በመልሶ ግንባታ ለ618 ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ አቅዶ 567 ከተሞች ማግኘታቸውንና 75 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የቆዳ ሽፋን ከዋናው መስመር (ግሪድ) የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ 58 በመቶ ማሳካቱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በአጠቃላይ 2.952 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ በበጀት ዓመቱ ለ468 ሺሕ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ ለ321,781 መስጠቱንና 57,000 የኮንዶሚኒየም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙ ከኃይል ሽያጭ 6.15 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አስቦ 5.091 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ለአገልግሎቱ 40 በመቶ ወስዶ 60 በመቶውን ለኃይል አቅራቢው ተቋም ስለሚሰጥ፣ የሚገኘው ገቢ የኦፕሬሽን ወጪ እንኳን መሸፈን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተነጋግሮበት የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ በተወሰነ መጠን የሚያሻሽለው እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ጭማሪው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማይጎዳ እንደሚሆንና ለሌላውም ቢሆን የተጋነነ እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡ ውዝፍ ዕዳ ያለባቸው የመንግሥት ተቋማት በአስቸኳይ ቀርበው በመነጋገር ክፍያ የማይፈጽሙ ከሆነ ኃይል አቋርጠው በሕግ የሚጠይቁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት የተጀመሩ የኔትወርክ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች፣ አሠራሩን በቴክኖሎጂ የዘመነ ማድረግና ለሌሎች በርካታ ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎቱን በተቀላጠፈና ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ ለመስጠት ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙና ተቋሙን ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...