Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አኃዝ የመቀጠሉ አስፈላጊነት

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አኃዝ የመቀጠሉ አስፈላጊነት

ቀን:

በሪፖርተር ጋዜጣ ቅፅ 23 ቁጥር 1894 (ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም.) ዕትም፣ ‹‹እኔ እምለው›› በሚለው ዓምድ ሥር አቶ ጌታቸው አስፋው ለኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ለመንግሥት ባቀረቡት የግል አስተያየት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ለቀጣይነቱ፣ ለሰላምና ለማኅበራዊ መረጋጋት፣ እንዲሁም ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲባል፣ እስካሁን ከሚያስመዘግባው የአሥርና አሥራ አንድ በመቶ ዕድገት መጣኞች በግማሽ ቀንሶ ለተወሰኑ ዓመታት ወደ አምስትና ስድስት በመቶ ዕድገት መጣኞች ዝቅ ማለት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ጸሐፊው ያቀረቡትን የፖሊሲ ንድፈ ሐሳብ ትክክለኛነት ለማሳመን ሰባት ኢኮኖሚያዊ ትንተናዎችን አቅርበዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አቶ ጌታቸው ባቀረቡት የፖሊሲ ንድፈ ሐሳብና ትንተናዎች ላይ የግል ዕይታን ለማካፈል ነው፡፡ 

  1. መዋዕለ ንዋይን ከቁጠባ ጋር ማስተካከል

መዋዕለ ነዋይን ከቁጠባ ጋር በማስተካከል የኢኮኖሚ ዕድገትን መቀነስ ለሚለው ሐሳብ መነሻ የሆነውንና የመጀመርያውን ዘመናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ንድፈ ሐሳብ የተቀመረው ሐሮልድና ዶማር በተባሉ የእንግሊዝ ኢኮኖሚስቶች ሲሆን፣ በእነሱ ንድፈ ሐሳብ መሠረት የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ከአገራዊ ቁጠባ ጋር ቀጥተኛ አዎንታዊ ግንኙነት አለው፡፡ የአንድ አገር ቁጠባ ሲጨምር ለመዋዕለ ንዋይ የሚያስፈልግ ፋይናንስ/ገንዘብ በቀላሉ ስለሚገኝ የመዋዕለ ንዋይ ዕድገት ይከሰታል፡፡ መዋዕለ ንዋይ ዕድገት አኮኖሚ ዕድገትን ያስከትላል፡፡ የሐሮድና ይመር የአኮኖሚ ዕድገት ንድፈ ሐሳብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነው የታዳጊ አገሮች አኮኖሚ ያለው ተግባራዊነት እጅግ ውስን ነው፡፡ ለሐሮድና ይመር ንድፈ ሐሳብ ተግባራዊነት በቂ የሆነ አገራዊ ቁጠባ መኖር የግድ ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች እንኳን በቂ የሆነ ቁጠባ ሊኖር በልቶ ማደር አስቸጋሪ ነው፡፡ ቁጠባ ቢኖር እንኳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የአንድ አገር ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት በአገራዊ ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ መሀል ባለው ልዩነት ይወሰናል፡፡ በመዋዕለ ንዋይና በአገራዊ ቁጠባ መሀል ያለው ልዩነት ሲቀንስ የተንቀሳቃሽ ሒሳብን ጉድለት ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን የተንቀሳቃሽ ሒሳብን ጉድለት ለማስወገድ በሚል ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን መዋዕለ ንዋይ በጣም ትንሽ ከሆነው አገራዊ ቁጠባ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረግ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መግታት ብቻ ሳይሆን ወደ ዜሮ ደረጃ ሊያወርድ ይችላል፡፡ እንደ አጠቃላይ በታዳጊ አገሮች ለመዋዕለ ንዋይ የሚያስፈልገው ካፒታል የሚገኘው ከአገራዊ ቁጠባ ሳይሆን ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ነው፡፡ ሌላው በአቶ ጌታቸው የቀረበው ምክረ ሐሳብ ፍጆታንና የመዋዕለ ንዋይ ድምር ወጪን ከጥቅል አገራዊ ምርት ጋር ተስተካካይ ማድረግ ነው፡፡ ባቀረቡት ቀመር ውስጥ የመንግሥትን ወጪ ረስተዋል፡፡

  1. የሠራተኞችን/የግለሰብ ገቢ መቀነስ

የኢትዮጵያን ነበራዊ ሁኔታ ስናይ በተለይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች (የግል ተቋማትም ቢሆኑ የተሻሉ አይደሉም) የሠራተኞች ገቢ መጠን ከሚሠሩት ሥራ ጋር እንኳን ሊመጣጠን አጠገቡም የሚደርስ አይደለም፡፡ ሠራተኞች ብዙ ይሠራሉ፣ ያመርታሉ፡፡ ነገር ግን ገቢያቸው በጣም የወረደ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የዩኒቨርሲቲ ዶክትሬት ዲግሪ ያለው መምህር አጠቃላይ ደመወዝ 13,140.00 ብር ሲሆን፣ የተጣራ ገቢው ግን 9,000.00 ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ አቶ ጌታቸው እንዳሉት ለየትኛው የሥራ ዘርፍ ነው 150,000.00 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር) የሚከፈለው? ቢኖር እንኳ ቁጥሩ ስንት ነው? የኢትዮጵያ ሠራተኛ በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች ተበዝባዥ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ግን ይህም በቂ አይደለም በማለት የዜጎች ገቢ እንዲቀንስ ለመንግሥት ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የአቶ ጌታቸው ምክረ ሐሳብ ስህተት ለመሆኑ የኢኮኖሚክስ ዕውቀት የሌለው ሰው እንኳ ያለ ብዙ ትንተናና የሚገነዘበው ይመስለኛል፡፡ ሌላው የአቶ ጌታቸው ሐሳብ፣ የግለሰብ ገቢ መጨመር ለሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብ ብቸኛ ምክንያት አድርገው ማቅረባቸው የተጠቀሰበት ነው፡፡ ለሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብ እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሱት የፍላጎት መጨመር፣ የአቅርቦት እጥረት፣ የገንዘብ አቅርቦት መጨመር፣ መዋቅራዊ ለውጥና የመሠረተ ልማት አለመሟላት ናቸው፡፡

  1. ኢኮኖሚዊ ኪራይን ማስወገድ

በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን፣ የካፒታሊስቱ የሀብት ምንጭ ነው፡፡ ለካፒታሊስቱ ከሚያስገኘው ትርፍ አንፃር የአገልግሎት ዘርፍ ትልቁን ድርሻ ሲይዝ በተቃራኒው ለአገራዊ ሀብት ክምችት የሚኖረው ድርሻ አናሳ ነው፡፡ ለአንድ ካፒታሊስት ግቡ አገራዊ ሀብትን ማከማቸት ሳይሆን፣ የራሱን ትርፍ ማሳደግ ነው፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮዊ ባህርይ የግሉን ጥቅም ማሳደግ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ከአገልግሎት ዘርፍ የሚገኘው የበዛ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ ጥቂቶች የሚሰበስቡት ስለሆነ መንግሥት የዚህን ዘርፍ ዕድገት ቢቀንስ ለሰፊው ሕዝብ ምንም ጉዳት እንደሌለው ይነግሩናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እሳቤ የኢትዮጵያዊያን ዓይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ እኛ ካልተጠቀምን (ብንጎዳም) እነሱ አይጠቀሙ፡፡ ሰፊው ሕዝብ ሳይጎዳ ግለሰብ እጅግ የበዛ ትርፍ ቢያገኝ ችግሩ ምንድነው? የመንግሥት ኃላፊነት አቶ ጌታቸው እንዳሉት ሳይሆን፣ አግባብነት ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች በማውጣትና በማስፈጸም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማረጋገጥ ነው፡፡

  1. የካፒታል ክምችትን መዛባትን መቀነስ 

የአቶ ጌታቸው አራተኛው ምክረ ሐሳብ ከማኅበረሰብና ግለሰብ ንቃተ ህሊና ጋር በጣም ይገናኛል፡፡ ሰነፎች ገንዘባቸውን ባንክ ሲያስቀምጡ፣ ገንዘብ የሌላቸው ነገር ግን የነቁ ብልሆች፣ ከባንክ ሰነፎች የቆጠቡትን በመበደር ሕንፃ ቢሠሩበት፣ ነግደው ቢያተርፉበት፣ ሀብታም ቢሆኑ ችግሩ ምንድነው? ወንጀሉ ምኑ ላይ ነው? አቶ ጌታቸው ‹‹በአዲስ አበባ የተገነቡት ሕንፃዎች ሁሉ የተሠሩት ደሃው አንጀቱን አስሮ ባደረገው ቁጠባ ነው፤›› በማለት በአዲስ አበባ የተሠሩት ሕንፃዎች ለደሃው እንዲከፋፈሉ ሐሳብ ያዋጣሉ፡፡ ግለሰቦች ከባንኮች ተበድረው በገንዘቡ በመሥራት ሀብታም እንዳይሆኑ ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ምክረ ሐሳባቸውም ግለሰቦች ለተበደሩት ገንዘብ የሚከፍሉትን የወለድ ምጣኔ ከፍ በማድረግ የብድር ፍላጎቶችትን መቀነስ ነው፡፡ በመሠራቱ የወለድ ምጣኔ የሚወሰነው በገንዘብ አቅርቦትና ፍላጎት ነው፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ሲቀንስ የወለድ ምጣኔ ይጨምራል፡፡ የገንዘብ አቅርቦ ሲጨምር የወለድ ምጣኔ ይቀንሳል፡፡ መሠረታዊ የወለድ ምጣኔ ወሳኝ ኃይሎች ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት መሆናቸው እየታወቀ መንግሥት የቁጠባ ወለድ ምጣኔን ቢያንስ ከዋጋ ንረት በላይ እንዲያደርግ የሚቀርብ ምክረ ሐሳብ ከመሠረታዊው የኢኮኖሚክስ ሳይንስ ሕጎች በጣም ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት በጣም የሚጎዳ ነው፡፡ ደሃ ቆጣቢዎች በዋጋ ንረት ምክንያት የቆጠብነው ገንዘብ የመግዛት አቅም (Real Value) ይቀንሳል ብለው ካሰቡ፣ ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተው መንገድ ወይም ሕንፃ መሥራት መብታቸው ነው፡፡

  1. የዋጋ ንረትን መግታት

የገንዘብ አቅርቦት መጨመር ወይም ተስፋፊ የገንዘብ  ፖሊሲ የሸቀጦችንና የአገልግሎቶችን ዋጋ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትንም ያፋጥናል፡፡ የሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ ከፍ ማለት ሸማቾች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲኖረው፣ አምራቾች ላይ ግን አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ የመንግሥት (ብሔራዊ ባንክ) ሚና መሆን ያለበት፣ አግባብነት ባለው ሁኔታ ሸማች ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመቀነስ ለአገራዊ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲን መከተል ነው፡፡

  1. የውጭ ምንዛሪ ለኢኮኖሚ ዕድገት

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ባለው የዕድገት ፍጥነት ወደፊት እንዲጓዝ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት በኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ ከሆኑት ኃይሎች አንዱ የሆነው የካፒታል ሸቀጥ ከውጭ የሚገዛ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል፡፡ ለካፒታል ሸቀጥ ግዥ የሚስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ ተልከው ከሚሸጡ ሸቀጦች፣ ከብድር፣ ከዕርዳታና ከውጭ ሐዋላ ገቢ ይገኛል፡፡ ወደ ውጭ ተልከው ከሚሸጡ ሸቀጦች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ (ወጪ ንግድን ለማበረታታት) የብርን የመግዛት አቅም ከዶላር አንፃር ማዳከም አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ የብር የመግዛት አቅም መዳከም ለአገር ውስጥ ሸማች የሸቀጦች ዋጋ ውድ ሲያደርግ ለዓለም አቀፍ ሸማች ርካሽ ያደርጋል፡፡ የዓለም አቀፍ ዋጋ መቀነስ የዓለም አቀፍ ሸማችን የመግዛት ፍላጎት ስለሚጨምር ወደ ውጭ የሚላከው ሸቀጥ መጠን ይጨምራል፡፡ ከተላከው ሸቀጥም የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ስለሚጨምር ለሚፈለገው ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ለሆነው ካፒታል ሸቀጥ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ ይገኛል፡፡ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም የሚያመጣው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መታየት ያለበት ከረዥም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ግቦች አንፃር እንጂ፣ ከጊዜያዊ አሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር መሆን የለበትም፡፡ የተሻለ ነገር ለማግኘት አግባብነት ያለው መስዋዕትነት ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት ሁኔታ የውጭ የኢኮኖሚ ጉድለትን በአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማስተካከያ ለማረም መሞከር የካፒታል እጥረት ውስጥ የሆነችው የአሁኗ ኢትዮጵያ ዘላቂም ሆነ ጊዜያዊ መፍትሔ አይሆንም፡፡

  1. የሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገትና የአገር አንድነት

አቶ ጌታቸው ቀጣይነት ያለው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት የአገሪቱን መበታተን ሊያስከትል ይችላል በሚል ሐሳብ ራሳቸውን በጣም አስጨንቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚወድ ማንኛውም ዜጋ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም መጨነቅ ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆን፣ ምክንያታዊነትም ነው፡፡ ነገር ግን የዓለምን ታሪክ ስንመረምር በኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት ምክንያት የተበታተነ አንድም በታሪክ የተመዘገበ አገር የለም፡፡ በተቃራኒ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት የአገራችን አንድነት ያጠናክራል፡፡

እንደ ማጠቃለያ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላምና ማኅበራዊ መረጋጋት ለዴሞክራሲ ዕድገትና ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነቱ ወሳኝ ነው፡፡

(እንዳለ ፀጋዬ፣ ከሐዋሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...