Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በአንድ ወቅት በምሠራበት መሥርያ ቤት ውስጥ መካሄድ ስላለባቸው መሠረታዊ ለውጦች እየተነጋገርን ነበር፡፡ መሠረታዊ ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ከለየን በኋላ እያንዳንዳቸውን በመተንተን ምን ያህል ድረስ ዘልቀን ለውጡን ማምጣት እንዳለብን ሐሳቦችን ተለዋወጥን፡፡ በውይይታችን ወቅት የተነሱት መሠረታዊ ችግሮች የግልጽነት አለመኖር፣ የተጠያቂነት ወሰን አለመታወቅ፣ ዳተኝነት፣ የብቃት ማነስ፣ አሉባልታ፣ የዲሲፕሊን ችግርና ሌብነት ነበሩ፡፡ የእነዚህን ችግሮች መነሻ ምክንያቶች መተንተን ስንጀምር ግን በመካከላችን ውዝግብ መነሳት ጀመረ፡፡ ውዝግቡ ሁለት ጎራዎችን ቁልጭ አድርጎ አሳየን፡፡

የመጀመርያው ጎራ መሠረታዊ ለውጥ መኖር አለበት በማለት ያጋጠሙንን ችግሮች ያለምንም ይሉኝታ ለመፍታት የሚጣጣር ሲሆን፣ ሁለተኛው ጎራ ደግሞ ያሉትን ችግሮች በማድበስበስ ለማለፍ የሚሞክር ነው፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ፈላጊዎችና አድበስባሾች በተፋጠጡበት በዚህ ውይይት ላይ መግባባት ሊደረስ ባለመቻሉ፣ ሁለቱን ጎራ በማስማማት ወደ ማዕከላዊ ነጥብ ሊያመጣ የሚችል የድርድር ኮሚቴ እንዲቋቋም ጥያቄ ተነሳ፡፡ ሁለቱም ወገኖች የያዙትን አቋም ሳያረግቡ እያመነቱ ድርድሩን ለመቀበል ለጊዜው ተስማሙ፡፡ ይኼንን ድርድር ያመቻቹት ገለልተኛ ሰዎች መካረሩ የትም ስለማያደርስ ውጤት ሊገኝ ይችላል ብለው በማሰብ ነበር፡፡

ከሁለቱም ወገኖች የተመረጡት አደራዳሪዎች መሠረታዊ የተባሉ ችግሮችን አንስተው የመነጋገሪያ አጀንዳ መምረጥ እንደሚኖርባቸው መነጋገር ሲጀምሩ፣ ዋናው ስብሰባ ላይ ያልተግባባንባቸው ችግሮች እዚህም መታየት ጀመሩ፡፡ አደራዳሪዎቹ ከሁለቱም ጎራዎች የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው የመጡ ይመስል የማደራደር ኃላፊነታቸውን ዘንግተው በበፊቱ ጭብጥ ላይ ተነታረኩ፡፡ ይህን ጊዜ በልምድም በዕድሜም ጠና ያሉ አንድ የሥራ ባልደረባችን ቆጣ ብለው፣ ‹‹የእኛ ተግባር የምንወግንለትን ፍላጎት ማንፀባረቅ ሳይሆን፣ ለተቋማችን ይበጃል የሚባለውን ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ አማራጮችን ማሳየት ነው፡፡ ሁለት ጎራ ፈጥረን ንትርክ ስንጀምር ገለልተኛ የሆነ የድርድር ኮሚቴ መቋቋሙ፣ ውዝግቦችን በማጥበብ አማካይ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ቡድናዊ አስተሳሰባችንን ትተን የጋራ መነጋጋሪያ መድረክ እናመቻች፤›› አሉ፡፡

በእሳቸው መሪነት ቀደም ሲል የተነሱትንና የተነተኑትን ነጥቦችን ይዘን የሚያቀራርቡና ወደ ጋራ መፍትሔ የሚያመሩ ሐሳቦችን ማቅረብ ስንጀምር፣ የተወሰኑ የኮሚቴ አባላት ተንቀሳቃሽ ስልኮች መጮኸ    ጀመሩ፡፡ የአንዳንዶቹ ደግሞ የጽሑፍ መልዕክት ያስተናግዱ ጀመር፡፡ ለስልኮቻቸው ጥሪዎችና መልዕክቶች ምላሽ ለመስጠት የአምስት ደቂቃ ዕረፍት በስምምነት ተደረገ፡፡ ከዕረፍት ተመልሰን የጀመርነውን ሥራ ለመቀጠል ስንዘጋጅ ያቀድናቸው ሐሳቦች ምስቅልቅላቸው ይወጣ ጀመር፡፡ የኮሚቴው አባላት ከየጎራው አለቆች ጋር በ‹‹ቴክስት ሜሴጅ›› እየተነጋገሩ ለካ ውይይታችን በሪሞት ኮንትሮል ይመራ ኖሯል፡፡ የሁለቱም ጎራ አለቆች በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት የድርድር ኮሚቴው ሥራ ተደነቃቅፎ ሳንስማማ ተበታተን፡፡

ስለገጠሙን መሠረታዊ ችግሮች ተነጋግረን ድርጅታችንን ከገባበት ችግር ማውጣት ሲገባን መስማማት አልቻልንም፡፡ አለመስማማቱን በድርድር ለመፍታት ኮሚቴ ብናቋቁም እንዲበተን ተደረገ፡፡ እንዲህ ዓይነት አደናቃፊ ችግሮች ሲያጋጥሙን በሰጥቶ መቀበል መርህ ተስማምተን መፍታት ካልቻልን ሰው የመሆናችን ትርጉሙ ምን  ሊሆን ነው? ለውጥ እንፈልጋለን ብለን ስንነሳ ግማሹ ለውጥን ሲሸሽ፣ ለውጥ ፈላጊው ያሉትን ዘዴዎችና አማራጮች ለመጠቀም ብልጠት ሲያጣ ምን ዓይነት መፍትሔ ሊኖር ነው? በአሻጥርና በተንኮል መረብ የተተበተበው አኗኗራችንና ባህሪያችን በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን?

ይህ የነገርኳችሁ ገጠመኝ እየከነከነኝ ሳለ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ከድርጅቱ ሊለቅ መሆኑን ሰማሁ፡፡ ይህ ከፍተኛ ዕውቀትና ችሎታ ያለው ሰው ድርጅቱን እንደሚለቅ አልነገረኝም፡፡ እንዲያውም በርካታ ዕቅዶች እንዳሉት ነበር የማውቀው፡፡ የእሱ የመልቀቅ ዜና እያበሳጨኝ ላናግረው ወደ ቢሮው ስሄድ ጓዙን ሲሸካክፍ አገኘሁት፡፡ ‹‹ምን ተፈጠረ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹ላለፉት ዓመታት ጥርሴን ነክሼ ሥሠራ የነበረው ይኼንን ድርጅት ከማጥ ውስጥ በማውጣት የስኬት ምሳሌ ለማድረግ ነበር፡፡ አሁን ግን እንደማይቻል ስለታወቀኝ በቃኝ፤›› አለኝ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ መታገስ እንዳለበት በወዳጅነት መልክ ስነግረው፣ ‹‹ወንድሜ አንተም ይብቃህ፡፡ ለውጥ ከማይቀበሉ ኃይሎች ጋር ትግል ሰልችቶኛል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ እየሰመጠ ካለ ጀልባ ጋር ለምን ጊዜዬን አጠፋለሁ?፤›› ሲለኝ፣ የራሴ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም መከራ አሳሰበኝ፡፡

የሆነስ ሆነና ጀልባዋ ብቻ ሳትሆን አገር ስትሰምጥስ ማነው የሚታደጋት? ይኼንን ገጠመኝ ለመጻፍ የተነሳሳሁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማያቸው አሳሳቢ ድርጊቶች ምክንያት ነው፡፡ አገር ለውጥ ፈልጋ ሕዝባችንም የለውጡ አካል በሆነበት በዚህ ወቅት፣ አደገኛ የሆኑ አዝማሚያዎች ሲታዩ ዝም ማለት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ የገዛ ወገንን በአደባባይ መግደልና በጭካኔ የተሞሉ ድርጊቶችን አለማውገዝ፣ ምን አገባኝ በማለት ችላ ማለትና የከፋ ከመጣ ቅራቅንቦ ሸክፎ እግሬ አውጪኝ ለማለት ልብን ማንጠልጠል አያዋጣም፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ ሕገወጦችን እንዳላዩ መሆን አያዛልቅም፡፡ አለበለዚያ እንደ ዋዛ የምንነታረክባቸው አላስፈላጊ ነገሮች ለውጡን አደናቅፈው ልክ እንደኛ መሥሪያ ቤት ሁላችንም ጥጋችንን ያስይዙንና እናርፈዋለን፡፡ መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም ያልቻለ ትውልድ መራራውን መከራ ይጋፈጣል፡፡ ያኔ ያመለጠው የለውጥ ባቡር ይናፍቃል፡፡ ናፍቆት ያብሰለስላል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ማስተዋል እየጎደለን ብዙ ነገሮችን ስናበላሽ መቆየታችን አንዘንጋ፡፡ ይኼ ለውጥ ካልተሳካና ተመልሰን ወደ አፈና የምንገባ ከሆነ ማፈር ያለብን በራሳችን መሆኑን በጥሞና እናስብ የስሜታዊነት ሰለባ አንሁን፡፡ ሰላም!

(ግሩም ተውህቦ፣ ከላፍቶ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...