Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በውብሸት ሙላት

የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በውብሸት ሙላት

ቀን:

የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት

በውብሸት ሙላት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሆነው ከተሰየሙ በኋላ በእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሲኖዶስ ውስጥ የነበረውን የመከፋፈል ችግር በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴን በማስማማት በአንድ አመራር እንዲመራ ለማድረግ ቢያንስ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ብዙዎቹ የሽብር ድርጊት እንደፈጸሙ ተደርገው ታስረው ነበር፡፡

በኦርቶዶክስ ክርስትናም ለሃያ ሰባት ዓመታት ለሁለት ተከፍሎ መንበረ ፕትርክናቸውን አንዱ በውጭ ሌላው በአገር ውስጥ ሆነው የቆዩቱን ሲኖዶሶች አንድ እንዲሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለቱም ሃይማኖቶች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ከአሜሪካ ከመጡ በኋላም መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ጎብኝተዋቸዋል፡፡ ለወትሮው ከሃይማኖት አመራሮች ጋር ሲወያይና ሲያወያይ የነበረው የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር በእነዚህ የማስማማት ሒደት ውስጥ አልታየም፡፡

የሁለቱ ሃይማኖቶችን አመራር እንዲከፋፈል ወይም ስምምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ረገድ የመንግሥት ድርሻም እንደነበረበት አንዳንድ የሃይማኖት አመራሮቹ ይናገራሉ፡፡ እርግጥ ነው እርስ በራሳቸው የተጣሉ ቢሆን ኖሮ በቀላሉ ታርቀው አንድ ቀን ባልሞላ ውይይት ወይም ድርድር አንድ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ ጽሑፍ በመጅሊሱ ወይም በሲኖዶሱ ውስጥ የተከሰተውን አለመግባባት በሚመለከት የመንግሥት ሚና እንዲህ ወይም እንዲያ ነበር የሚል ክርክር ማቅረብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሁነቶቹ በመነሳት የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት ሕገ መንግሥቱን ምርኩዝ በማድረግ መፈተሽ ነው፡፡

የጽሑፉ አካሄድ በአገራችን የመንግሥትና የሃይማኖትን ያለፈውን ግንኙነታቸውን በሕግ አንፃር በጥቅሉ በመገምገም፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን በማብራራት፣ በጉዳዩ ላይ አግባብነት ያላቸውን መርሆችንም በመጠቀም የአንዳንድ አገሮችንም ልምድ ከግምት በማስገባት ነው፡፡

 በመሠረቱ ሃይማኖት የግል ነው፡፡ በግለሰብ ምርጫ ይወሰናል፡፡ የግል በመሆኑ ማንም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት መከተል ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሃይማኖት የቡድን መልክና ጠባይ ስላለው ሌሎች ተቋማት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍ ማለቱ አሌ አይባልም፡፡ በአብዛኛው የማኅበራዊ ማንነት መገለጫም ሲሆን፣ በአንዳንድ አገሮች ዘንድ ደግሞ የብሔራዊም (አገራዊ) ማንነትም መገለጫም ጭምር ነው፡፡

ሃይማኖት በራሱ ተቋም ነው፡፡ የተለያዩ የሃይማኖት ዓይነቶችም ስላሉ ይኼንን ሀቅ ከግምት ያስገባ ግንኙነት መኖር አለበት፡፡ ስለሆነም የመንግሥትና የሃይማኖትን ግንኙነት በሕገ መንግሥት ትኩረት ከሚደረግባቸውና ስምምነት ላይ መደረስ ካለበቸው ነጥቦች አንዱ ነው፡፡

የመንግሥት ዓለማዊነት

የበርካታ አገሮች ጥንታዊ መንግሥታት ሃይማኖታዊ ነበሩ፡፡ ሃይማኖትና መንግሥት ሁለቱም በአንድነት የሚመሩ ነበሩ፡፡ አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አገሮች ሰፋ ባለ መልኩ ደግሞ በዓረብ ዓለም እንደቀጠለ ነው፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት ተነጣጥለው አይመሩም፣ አይተዳደሩም፡፡ የተለያየ ሕግ የሚያወጣም የሚያስፈጽምም አካልም የለም፡፡

የሃይማኖትና የመንግሥትን ግንኙነት በሕገ መንግሥትም ይሁን በሌላ ሕግ አማካይነት ምን መምሰል እንዳለበት ለመወሰን ከግምት መግባት ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ሁኔታዎቹ እንደ ሃይማኖቶቹ ዓይነትም እንደ አገሩ ሕዝብ የሃይማኖት ስብጥርም፣ እንደ አገሮቹ ልዩ ባህርያትም የተለያዩ እንደሚሆኑ መገመትም ይቻላል፡፡ ከየአገሮቹ ልማድም ማወቅ ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች መንግሥታቸው ዓለማዊ እንዲሆን በማድረግ ሃይማኖት ደግሞ ለብቻው እንዲመራና እንዲተዳደር አድርገዋል፡፡ ሕግ አውጪዎቻቸውም አስፈጻሚዎቻቸውንም ለያይተዋል፡፡  

አገሮች የመንግሥታቸውንና የሃይማኖትን ግንኙነት ወደ አምስት ጎራዎች ማጠቃለል እንደሚቻል በርካታ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

ሀ. የከረረ (ጠንካራ) ዓለማዊነት

እንደ ፈረንሣይ ዓይነት ሕገ መንግሥትና አተገባበር የሚከተሉ አገሮች መንግሥታቸው ፍጹም ዓለማዊ ነው፡፡ የአገራቸውም መለያ ያደርጉታል፡፡ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች፣ አስተምህሮዎች፣ መገለጫዎች በመንግሥታዊ ተቋማትም በሕዝባዊ አደባባይም እንዲንፀባረቁ አይፈልጉም፡፡ ተማሪዎች ሃይማኖታቸውን የሚገልጽ አለባበስም አይፈቀድላቸውም፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችም እንዲሁም፡፡ የመንግሥት ሹመኞችም ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ዝግጅት ሲያደርጉ የትኛውንም ሃይማኖታዊ ተግባር መፈጸም አይችሉም፡፡

ማንም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት መከተልና ማመን ቢችልም፣ እምነቱን በሕዝባዊና በመንግሥታዊ ተቋም ማንፀባረቅም ማሳየትም አይችልም፡፡ የሃይማኖት ግላዊነትን መንግሥት በጥብቅ ይከታተላል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቶቹ አገሮች ዜጎቻቸው ሃይማኖታዊ ከሚሆኑ ይልቅ ባይሆኑ ይመርጣሉ ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም ነገር ዓለማዊ ይሆን ዘንድ ሕገ መንግሥታዊ ምርጫቸው ነው፡፡

ለ. ገለልተኛ (ደካማ) ዓለማዊነት

አንዳንድ አገሮች ደግሞ የትኛውንም ሃይማኖት አይደግፉም፣ አይተቹም አይነቅፉም፣ አይረዱም፣ አያደናቅፉም፣ ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ ልዩ ጥቅምም መገለልም አይኖርም፡፡ መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ገለልተኛ ነው፡፡ መንግሥታቸውም አገራቸውም ሃይማኖታዊ አይሆንም፡፡ የአንዱን ሃይማኖት ጠባይም አያንፀባርቅም፡፡

ይኼንን ዓይነት አካሄድ ከሚከተሉት መካከል አሜሪካ በግምባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናት፡፡ በሕገ መንግሥቷ ‹‹አንድን ሃይማኖት አይመሠረትም፣ በነፃነት ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን መፈጸምንም አይከለክልም፤›› በማለት ተደንግጓል፡፡ ማንም ሰው ከነሃይማኖታዊ መለያው በየትኛውም መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተግባራት ላይ መሳተፍ ይችላል፡፡ ሹመኞችም እንደ ሃይማኖታቸው ቃለ መሐላ መፈጸምን አይከለከሉም፡፡

መንግሥትም በትምህርትም ይሁን በሌሎች ዘርፎች ውስጥ አንድን ሃይማኖት አስተምህሮ ነጥሎ ማካተት አይችልም፡፡ በዓለማዊ ብቻ በመተካት ሃይማኖታዊውን ማጣጣል አይፈቀደም፡፡ ለአብነት ስለሥነ ፍጥረት ትምህርት ሲሰጥ መለኮታዊ የፍጥረት ታሪክን በመተው የዝግመተ ለውጥን ትክክል በማድረግ መውሰድ ወይም በተገላቢጦሹ ማድረግን ይከለክላሉ፡፡ ሁለቱንም በእኩል ማየትና ለሐሳቦቹ ተመጣጣኝ ቦታ መስጠትን ይጠይቃሉ፡፡

ሐ. ብዙኃዊ አስተናጋጅ ዓለማዊነት

አንዳንድ አገሮች ደግሞ ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ ሲባል ምንም ዓይነት ድጋፍ ካለማድረግ ይልቅ ሁሉንም እኩል መደገፍንና አድልኦ የሌለበት እንክብካቤን ይመርጣሉ፡፡ መንግሥት በእኩልነት ሁሉንም ይደግፋል፡፡ ሃይማኖት አገራዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሕዝቡም ሃይማኖታዊ የሆነባቸው አገሮች ይኼንን አካሄድ ይመርጣሉ፡፡

የሃይማኖት ተቋማትም ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለሚያበረታቱ መንግሥታቸው እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች የሃይማኖት ግብር እንዲሰበስቡ ይፈቀድላቸዋል አሊያም ተሰብስቦ ይሰጣቸዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱም እንደ አንድ ሕዝባዊ ድርጅት (ማኅበር) መብትና ግዴታ ኖሮት፣ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ ፖለቲካዊ ተቋም ይቆጠራሉ፡፡ መንግሥትና ሃይማኖትም ለጋራ ማኅበራዊ ጥቅም (Common Goods) የሚሠሩ ሸሪኮች እንደሆኑ ራሳቸውን በመውሰድ በትብብር ይሠራሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ጀርመን ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካና ህንድ ይኼንኑ አካሄድ መርጠዋል፡፡

መ. በመንግሥት የተመሠረተ ሃይማኖት ያለበት ዓለማዊነት

አንዳንድ አገሮች አንድን ሃይማኖት ነጥለው ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊም አድርገውታል፡፡ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልን ነፃነት ያረጋግጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ርዕሰ ብሔሩ (ብዙ ጊዜ ንጉሡ ወይም ንግሥቲቷ) በሕገ መንግሥት ዕውቅና የተለገሰውን ሃይማኖት ብቻ እንዲከተሉ ግዴታ ይጥላል፡፡ ለሃይማኖት ተቋሙ በጀት ይመድባል፡፡

ይህ አካሄድ በራሱ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ አገሮቹ በሕገ መንግሥታቸው አንድን ሃይማኖት ዕውቅና ይሰጡና ጠቅለል ባለ መልኩ ብቻ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚገልጹ አሉ፡፡ የዚህ ጥሩ ምሳሌ አርጀንቲና ናት፡፡ ፕሬዚዳንቷ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንዲሆን የሚያስገድደውን ድንጋጌ ካነሳች በኋላ የቀረው ለካቶሊክ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል የሚለው ብቻ ነው፡፡ ቄሶችን የመንግሥት ኃላፊነት እንዳይዙም ከልክላለች፡፡ ይህ ላላ ያለ ወይም ደከም ያለ ድጋፍ ያለበት በመንግሥት የተመሠረተ ሃይማኖት ያለበት ሆኖ ዓለማዊነትን የሚከተል አካሄድ ነው፡፡

ከላይ ከተገለጸው ለየት ባለ መልኩ ደግሞ፣ አንዳንድ አገሮች በሕገ መንግሥት ለተመሠረተ (ዕውቅና ለተቸረው) ሃይማኖት ብዙ ድጋፍ ይደርጋሉ፡፡ ቁርኝታቸውም የጠበቀ ነው፡፡ የተወሰኑ የሹመት ቦታዎች ለዚሁ ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ እንዲሆን የሚያስገድድ አንቀጽም አላቸው፡፡ ሕግ አውጪው ላይም እንዲወከሉ ያደርጋል፡፡ ኖርዌይ፣ ብሪታኒያ፣ ኢራን፣ ግብፅን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

አገሮች ከላይ የተጠቀሱት የግንኙነት አካሄዶችን ሲመርጡ የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ከአገሪቱ ሕዝብ ውስጥ በጣም ብዙው አንድ ሃይማኖት የሚከተል ሲሆን፣ መንግሥት ለዚያ ሃይማኖት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ግንኙነትን የመሠረተ አካሄድን ሲመርጥ ይስተዋላል፡፡ ሩሲያና ግሪክ ለኦርቶዶክስ ክርስትና፣ ግብፅ ለእስልምና፣ ሊባኖስ ለእስልምናም ለክርስትናም ልዩ ቦታ እንደሰጡት ማለት ነው፡፡

የአገሬው ሕዝብ ማንነት መገለጫው ሃይማኖቱ በሆነባቸው ዘንድም ሃይማኖቱን መንግሥታዊ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ማጣጣል ወይም ከመንግሥታዊ አገልግሎት የማራቅ አካሄድን አይከተሉም፡፡

በርካታ ብሔሮች የሚገኙባቸው አገሮች ደግሞ ሃይማኖትን ሲያበረታቱ ወይም በጋራ መሥራትን ሲመርጡ ይስተዋላል፡፡ የብሔር ማንነትን መሠረት አድርጎ መከፋፈል እንዳይኖር ወይም ለመቀነስ ሃይማኖት የማስተሳሰሪያ ገመድ እንዲሆናቸው ስለሚፈልጉ ነው፡፡ የብሔር ክፍፍልን በሃይማኖት በማስተሳሰር አንድ ማድረግን ስለሚጠቅማቸው ሆን ብለው የሚያደርጉት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙኃናዊ አስተናጋጅ አካሄድን ይመርጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ አካሄድ

 እስከ 1966 አብዮት ድረስ የነበረው የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሌላውን ለጊዜው እንተወውና ከ1923ቱ ሕገ መንግሥት መውጣትን ተከትሎ ያለውን ግንኙነት እንመልከት፡፡ በ1923ቱም ይሁን 1948ቱ ሕገ መንግሥቶች ላይ እንደተገለጸው ንጉሠ ነገሥትነት የተሰጠው ከአንድ ትውልድ ለሚወለድ ሃይማኖቱም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለሆነ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በእርግጥ በ1923ቱ ሕገ መንግሥት ላይ የመንግሥትና የሃይማኖትን ግንኙነት በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ አንቀጽ አናገኝም፡፡ ይሁን እንጂ ከመግቢያው ጀምሮ ስለንጉሠ ነገሥቱ የተጻፉትን አንቀጾች ስንመለከት ከላይ የተገለጸው እውነት መሆኑን እናውቃለን፡፡ የ1948ቱ ግን ከአንቀጽ 126 እስከ 128 ድረስ እንደተገለጸው ንጉሠ ነገሥቱም ኦርቶዶክስ መሆን አለበት፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖትም ናት፡፡ ድጋፍም ይደረግላታል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ የቤተ ክርስቲያኗን ሥጋዊ አስተዳደር በሚመለከት ሕግ ያወጣል፡፡ የጳጳሳትንም ምርጫ የማፅደቅ ሥልጣን የንጉሠ ነገሥቱ ነው፡፡ ይህ ማንም ሰው የመሰለውን ሃይማኖት መከተልን አይከለክልም፡፡ ዕውቅናም ሰጥቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ እንደ አንድ ማኅበርም (ድርጅትም) በፍትሐ ብሔር ሕጉ አማካይነት ተመሥርታለች፡፡ ከእነዚህ ኩነቶች አንፃር እንኳን ብንመለከተው ጠንካራ በመንግሥት የተመሠረተ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት ያለውን የዓለማዊነት አካሄድን የመረጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡

አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ግን ይህ የመንግሥት ሃይማኖት የግንኙነት ፈለግ ተለውጧል፡፡ ወታደራዊው መንግሥት፣ በአንድ በኩል ሁሉንም ሃይማኖቶች እኩል ዕውቅና መስጠት በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አብዛኛው ኅብረተሰባዊነትን እንደሚከተሉ አገሮች ለሃይማኖት አዎንታዊ አመለካከት አልነበረውም፡፡ የሃይማኖት አባቶች ተገድለዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ንብረቶች ተወርሰዋል፡፡ ሃይማኖታዊ ተቋማት አገዛዙን እንዲደግፉ ተደርገዋል፡፡

ኋላም ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ አንቀጽ 46 (2) እንደተገለጸው መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል፡፡ እንደ ማንኛውም ሕዝባዊ ድርጅት የሃይማኖት ድርጅቶችም የሶሻሊዝምን መርሆች የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ከሕገ መንግሥቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለሃይማኖት ምንም ዓይነት ድጋፍ አያደርግም፡፡ አማኞችም ቢሆኑ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ በርካታ ግዴታዎችን እንዲፈጽሙ ስለሚጠየቁ ከላይ ካየናቸው አካሄዶች አኳያ ጠንካራ ዓለማዊነትን ፈለግን መርጦ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ግን ሶሻሊስት አገሮች ስለሃይማኖት ያላቸውን (በአብዛኛው ፀረ ሃይማኖት) የተለየ ፈለግና አመለካከት በመዘንጋት አይደለም፡፡

የደርግ መውደቅን ተከትሎ የመጣው አገዛዝ (አስተዳደር) ከደርግ የለዘበ የዓለማዊነት መርህን መርጧል ማለት ይቻላል፡፡ እስኪ ሕገ መንግሥቱ የሚለውን እንመልከት፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖቶች የሚኖሩባት ስለሆነች ከዚህ አንፃር ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ በመሠረታዊ መርሆነት ካስቀመጣቸው አንዱ ልክ በደርግ ዘመን እንደነበረው ሕገ መንግሥት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን ነው፡፡ የሁለቱን ግንኙነት የወስነው አንቀጽ 11 ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረትም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖትም አይኖርም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም የመንግሥት ጉዳይን በተመለከተ እንዲሁ፡፡

የዜጎችን መሠረታዊና ሰብዓዊ መብቶችን ዕውቅና የሰጠ ሕገ መንግሥት ለአንድ ሃይማኖት የተለየ ጥበቃ የማድረግ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ የበለጠ ዕድሉን ዝቅተኛ የሚያደርገው ደግሞ በርካታ ሃይማኖቶች ያሉባት አገር መሆኗ ነው፡፡ የሁለቱ መለያየት ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሥርዓተ መንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው ለሰብዓዊ መብት መከበር የተደረገው ትግል አንዱና መሠረታዊ መብት የዕምነት ነፃነት መከበር ነው፡፡

የሃይማኖትና የዕምነት ነፃነት ሐሳብን በነፃ ከመግለጽ መብት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የዕምነትና የራስን ሐሳብ የመግለጽ መብት በተከበረበት ሁኔታ የሃይማኖት ነፃነት መከበርም የግድ ነው፡፡

ሃይማኖት በመንግሥት ሥራ ውስጥ የሚገባ ከሆነ መንግሥት የአንድ ሃይማኖት መንግሥት ይሆናል፡፡ መንግሥት የአንድ ሃይማኖት ተከታይ በሆነበት፣ የዕምነት ነፃነት ላይ የተጣለ ሸክም መሆኑ አይቀርም፡፡ 

በሌላ አነጋገር የአንደኛው ዕምነት ማስፋፊያ መሣሪያ ሲሆን፣ የዜጎች እኩልነት ላይ ደንቃራ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ መንግሥት ከያዘው ዕምነት የተለየ ዕምነት ያለው የማይሳተፍባቸው የሹመት ቦታዎች፣ የሥልጣን ማማዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የሌላ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ዜጎች በእኩል የማይወከሉበት ወይም እኩል ዕድል የማያገኙበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡

 

የተወሰነውን የኅብረተሰብ ክፍል ሃይማኖት የሚወክል መንግሥት የሁሉም ሕዝብ መንግሥት ስለማይሆን መንግሥትና ሃይማኖት ባልተለያዩበት ሁኔታ የሕዝብ ሉዓላዊነት ሊከበር አይችልም፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንቅፋት ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆን ይኖርበታል፡፡  ይህ ማለት ከላይ እንዳየነው የመንግሥት ኃላፊዎች የራሳቸው ሃይማኖት አይኖራቸውም ማለት አይደለም፡፡ ይሁንና ሃይማኖታቸው የመንግሥት ሥራ መምራት የለበትም ማለት ነው፡፡

 ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር እንደመሆኗ መጠን መንግሥትና ሃይማኖት መለያየቱ የአገሪቱን ነባራዊ የሃይማኖት ስብጥር የዋጀ ነው፡፡

ሌላው በሕገ መንግሥቱ የተገለጸው ቁምነገር መንግሥታዊ ሃይማኖት እንደማይኖር መደንገጉ ነው፡፡ ይህ ንዑስ አንቀጽ በ1948ቱ ሕገ መንግሥት ላይ ከነበረው አካሄድ የተለየ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እንደቀድሞው መንግሥታዊ ሃይማኖት እንዳይኖር ዋስትና የሰጠ ነው፡፡

በደርግ ዘመን የወጣው ሕገ መንግሥት ከዚህ አገላለጽ ጋር አቻ የሚሆን ድንጋጌ ባናገኝም፣ እንኳንስ መንግሥታዊ ሃይማኖት ሊኖር ቀርቶ የትኛውም ሃይማኖት ቢሆን ሶሻሊስታዊ መርሆን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ስለተገለጸ ከደርግ ዘመን የተሸጋገረን ያልተመለሰ ጥያቄን የመለሰ አዲስ ሐሳብ ባይሆንም፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት እንዳይኖር ግን ዋስትና የሰጠ አንቀጽ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዳይኖሩ ለመከልከል መነሻ የሚሆን አንቀጽ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን ከመጡ እንደሃይማኖታቸው አገርን መምራት ተከልከሏል፡፡ መምራት የሚችሉት ዓለማዊ መርሕን ተከትለው ነው፡፡ 

በአንቀጽ 11 ንዑስ ቁጥር ሦስት ላይ ሠፍሮ የምናገኘው ሌላው ቁምነገር ደግሞ አንደኛቸው በሌላው ጣልቃ አለመገባባትን ሕጋዊ ዋስትና መስጠቱ ነው፡፡ ሁለቱም የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው ይመራሉ፡፡ ይህ ግን እርስ በርስ መተባበርን አይከለክልም፡፡ በመንግሥትነት ካባ ሃይማኖትን ማወክ አይቻልም፣ በሃይማኖት ሰበብም መንግሥትን መበጥበጥንም ይፈቅዳል ማለት አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው አንዱ በሌላው ጣልቃ መግባት አይቻልም ሲባል ሃይማኖትን ከለላ አድርገው የሚነሱ የአመፅ እንቅስቃሴዎችን መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ማለት አይደለም፡፡ አመፅና የጉልበት ሥራ የአንዱን ፍላጎት በሌላው ላይ መጫን ስለሆነ ይህ ማለትም የአንዱን የሃይማኖት ዕምነት በሌላው ላይ ለመጫን የሚደረግ እንቅስቃሴ በመጀመርያ ደረጃ የሃይማኖትና የዕምነት ነፃነትን የሚፃረር ስለሚሆን፣ መንግሥት የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ግዴታ ስላለበት እንዲህ ዓይነት በሃይማኖት ከለላ የሚነሱ የአመፅ ድርጊቶችን መቆጣጠርና ማስቆም መንግሥታዊ ግዴታው ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ መንግሥት በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ ብዙ ጊዜ በስበብ አስባቡ ዘው ብሎ ሲገባ ተስተውሏል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከላይ እንደተገለጸው ይበል እንጂ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን ልክ በደርግ ዘመን እንደወጣው ሕገ መንግሥት የአሁኑን መንግሥት ፖሊሲዎች ዕውቅና መስጠት ለእነሱ መገዛትን ይፈልጋል፡፡ እንደውም በአደባባይ ውዳሴና ሙገሳ እንዲደረግለት ሲፈልግ ኖሯል፡፡ አስደርጓልም፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሚያደርገውን ነገር ከኮነኑ ጣልቃ እንደገቡ በመወሰድ ማሳጣትና በተራው ሲኮንን ኖሯል፡፡ 

ከላይ በአጭሩ የቃኘነው የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበትና በኢትዮጵያም ምን እንደሚመስል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ መቶ በመቶ በተጠጋ መጠን ሃይማኖት አለው፡፡ ሃይማኖት ከመብት አንፃር ግላዊ ምርጫ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም የወል ጠባዩ ከፍ ያለ ነው፡፡ ቤተሰባዊነቱ ደግሞ ያይላል፡፡ ለልጆች ሳይቀር ወላጆች ሃይማኖታቸውን ሊመርጡላቸው እንደሚችሉ የማስገደድም ሥልጣን ጭምር ሊኖራቸው እንደሚችል በሕግ ሳይቀር ድጋፍ አለው፡፡

ከግላዊ ምርጫ አልፎ ቤተሰባዊ፣ ወላዊ ባሕርይ ስላለው አገራዊ ማንነት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖ የጎላ ነው፡፡ በቋንቋና በሌሎች ማንነቶች የተከፋፈለን ማኅበረሰብ ሃይማኖት ያቀራርበዋል፡፡ ሰናይ ባሕርያትን፣ ግብረ ገብነትን ያሳድጋል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ ብቻ እንኳን በአገራችን የተስተዋሉትን ግጭቶች ላጤነ ሰው የትኞቹም ሃይማኖቶችና አማኞች ያደርጓቸዋል ተብለው የማይገመቱ የጭካኔ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ ዜጎች በዜጎች የፈጸሙት፣ በእምነት ተቋማት ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች ለኅሊና ዘግናኞች ነበሩ፡፡ መንግሥትም ጥበቃ ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡

የመንግሥትና የሃይማኖት ተግባራዊ ግንኙነት ድጋሜ ሊጤን ይገባዋል፡፡ መንግሥትም ለሃይማኖት ድርጅቶችና አማኞች ያለበትን ግዴታ ቆም ብሎ ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡ እነዚህን ሁለት ነጥቦች ማጠንጠኛ በማድረግ በሌላ ጽሑፍ በዝርዝር እንመለስባቸዋለን፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...