Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ጅማሮ ወዴት ያደርሰን ይሆን?

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ጅማሮ ወዴት ያደርሰን ይሆን?

ቀን:

በተስፋዬ ሀቢሶ

‹‹ጨለማን ጨለማ አያጠፋውም፣ ጨለማን ማጥፋት የሚችለው ብርሃን ብቻ ነው፡፡ ጥላቻንም ጥላቻ አያጠፋውም፣ ጥላቻን ማጥፋት የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው፤›› ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ የጥቁር አሜሪካውያን 1960ዎቹ የነፃነት ታጋይ የተናገሩት።

ላለፉት 27 ዓመታት በመላ አገሪቱ የተዘረጋው የአንድ ኮሙዩኒስታዊ አውራ ፓርቲ የአምባገነንነትና የአፈና አገዛዝ ያንገሸገሸው ሰፊው ሕዝብ በተለይ 2008 ዓ.ም. አንስቶ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ ወዘተ. የተቀጣጠሉትን ሰላማዊ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ጫናና ግፊት ለመቋቋም ባለመቻሉ፣ የኢሕአዴግ መራሹ አገዛዝ እየተሸረሸረና እየተዳከመ ሄዶ ወደ ማይመለስበት መንግሥታዊ ውድቀት ተቃርቦ እንደነበር ሁላችንም በከባድ ሥጋት፣ ሐዘንና ጭንቀት የታዘብነው እውነታ ነበር። ይፍጠንም ይዘግይ መንግሥት አልባ ሆነን ወደ ከፋ ሥርዓተ አልበኝነት፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንደምንዘፈቅ የሚተነብዩ ከሩቅም ከቅርብም በብዛት ነበሩ።

ሆኖም ይህንን ከፍተኛ አደጋና የመላውን ሕዝብ የማያወላውሉ የፍትሕና የእኩልነት ጥያቄዎችና ፍላጎቶች የተገነዘቡ የኢሕአዴግ አመራሮች፣ የተለመደውን ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ባደረጉበት ሒደት እነ ለማ መገርሳ፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸውሌሎችም የለውጥ ደጋፊዎች ከበስተጀርባቸው የደም ዋጋ ከፍለው በተሠለፉላቸው የወጣቶች ድጋፍ (በዋነኝነት ‹‹ቄሮዎች›› ‹‹ፋኖዎች›› እና ‹‹ዘርማዎች››) የኢሕአዴግን ወሳኝ የአመራር ሚና በመቀዳጀት፣ ድርጅቱንም ሆነ አገሪቱን ለመታደግ የሚያስችሉ የለውጥ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ በቁርጠኝነት ተሠለፉ። በዚህም መሠረት  ዓብይ አህመድ (/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን በቃለ መሃላ ከተረከቡ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የማይታመኑ የሚመስሉ ፈጣንና ዘርፈ ብዙ ተግባሮችና እንቅስቃሴዎችን በመፈጸም፣ ለእኛ ከደርግ ዘመን አንስቶ በአፈና ሥርዓት 44 ዓመታት ያሳለፍን ኢትዮጵያውያን ብሩህ የተስፋ ዘመን የሚያጭሩ የተሃድሶ ንቅናቄዎችን አስጀምረዋል።

የአፈና ሥርዓቱን በመበጣጠስ የነፃነት ጎህ ቀደዱልን፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ከተለያዩ የማጎሪያ እስር ቤቶች በይቅርታ እንዲወጡ አደረጓቸው፡፡ በተከታታይም ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና መካከለኛው ምሥራቅ በመጓዝ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን አስፈቱ። የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደኅንነትና የእስር ቤቶች ተቋማትን ለለውጥ አመቺ በሚሆኑበት አቋም እንደገና እንዲደራጁ አደረጉ፡፡ ዕድሜያቸው የገፉ ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናትን ወደ ጡረታ አስወጡ። የምሕረት አዋጅ እንዲታወጅ በማድረግ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች በወንጀል ተከስሰው የተፈረደባቸውን ዜጎች የአዋጁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበቋቸው።

ቀጥሎም የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ተቃዋሚም ሆኑ ደጋፊዎች ወደ አገራቸው ገብተው በነፃነት በማንኛውም ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ የዘንባባ ዝንጣፊና የሰላም ጥሪ ከማቅረባቸውም በላይ፣ ወደ አሜሪካ በመጓዝ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በማሳመን እርስ በርስ እንዲታረቁ፣ እንዲደጋገፉና በኢትዮጵያዊነት ዜግነትናማንነታችን ዙሪያ በአንድነት እንዲቆሙ በአጽንኦት አደራ በማለት ወደ አገራቸው ለመመለስ በቅተዋል፡፡ የአብዛኛዎቹን ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ያልተቆጠበ ድጋፍና አድናቆት ተቀዳጅተው ተመልሰዋል፡፡ ይህ እጅግ ደስ የሚያሰኝ  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።  በዚህም የተነሳ ከመላው ሕዝባችን (ከወጣቱም ሆነ ከአረጋውያን፣ ከሴቱም ሆነ ከወንዱ፣ ከክርስቲያኑም ሆነ ከሙስሊሙ፣ ከዳያስፖራውም ሆነ ከአገር ቤቱም፣ ወዘተ.) የተሰጣቸው ድጋፍ መሬት አንቀጥቅጥ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ነገር ግን አሁንም አንዳንድ ተቃዋሚዎች በተለያዩ ክልሎች መኖራቸውን ደግሞ ለመካድ አይቻለንም። 

ከሁሉም በላይ ደግሞ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳዮች ከፊታችን ተደቅነዋል። በመጀመርያ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በሁሉም ክልሎችና ከተሞች የሥራ ዕድል በማጣት በከንቱ የሚጉላሉበት ሁኔታ በአስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ፣ እንዲሁም የሸቀጣ ሸቀጦችና የአገልግሎቶች እጥረትም ሆነ የዋጋ ንረት አስቸኳይ መፍትሔዎች ካልተበጀላቸው በስተቀር የሚያስከትሉዋቸው አደጋዎች የከፉ ይሆናሉ። በሁለተኛ ደረጃ ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ እስር ቤቶች ከፍተኛ ግፍ፣ ሰቆቃና መከራ የደረሰባቸው የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ተገቢውን የሞራልና የማቴሪያል ማካካሻ የሚያገኙበት ሥልትና ፕሮግራም በአፋጣኝ አለመነደፉ ነው። ይህ አሳሳቢ ፈተና ነው፣ ውሎ አድሮ የሚፈነዳ ቦምብ መሆኑ አይቀርምና።  የሆነ ሆኖ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኗቸውን አስደናቂ ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ሥራዎችና በዚህም ረገድ ያስመዘገቧቸውን አንፀባራቂ ድሎች (በተለይም ከኤርትራ ጋር ለሃያ ዓመታት የወገብ ቅማል ሆኖ ሲያሰቃየን ለነበረው የጠላትነት ነቀርሳ አፋጣኝ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ድል በማስመዝገብ) የታዘበ ማናቸውም ዜጋ፣ በደስታና በእልልታ የሚያጅባቸው አስደናቂ ክንውኖችና መልካም ጅማሬዎች እንደሚሆኑ ከቶውንም አይጠራጠርም፡፡ የእኔም ስሜት ይኸው ነው።

የሆነ ሆኖ ማንኛውም ብሩህ ተስፋ የሚያጎናፅፍ መልካም ጅማሮ ወደ መልካም ፍፃሜ ያደርሰን ይሆናል በሚል ተስፋ እንጂ፣ በአሁኑ ወቅት አንዳችም ተቋማዊ ዋስትና ያለው ሁኔታ ገና አልተፈጠረም፣ ገና አልተረጋገጠልንም፡፡ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት (የፕሬስ ቦርድና የፕሬስ ነፃነት ተቋማት፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን፣ የሲቪል ሶሳይቲ ማኅበራት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋምና የፈጣን ዳኝነት የፍትሕ ተቋማት/ፍርድ ቤቶች፣ ወዘተ.) ገና አልተገነቡም፣ ገና ወደ ዳበረ መድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልተሸጋገርንም፡፡ የተፍረከረከ ፓርቲም ቢሆን የኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም በሚመራ የአምባገነንነት ሥርዓት ሥር አሁንም በሞኖፖል እየገዛን ነው። ይህ በእዚህ እንዳለ ቢሆንም፣ ዛሬ ዕድሜ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን አፋጣኝና ተከታታይ በጎ ዕርምጃዎች የተነሳ የኢሕአዴግ የቀድሞ አፋኝና ጨፍጫፊ ተግባሮቹ ቀስ በቀስ እየተወገዱ ናቸው፡፡ ስያሜው አሁንም ኢሕአዴግ ቢሆንም አስከፊ ተግባሮቹ እየተገረሰሱ ናቸው።  ይበል የሚያሰኝ ቆራጥነት ነው፣ ይቀጥል ዘንድም በፅኑ እንሻለን።

 ከሁሉም በላይ በመላ አገሪቱ ካለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት በተለይም 2008 ዓ.ም. የጊንጪ ወጣቶች አመፅ ወዲህ  ባልተቋረጠና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የተቀጣጠሉት፣ የሕዝባዊ እምቢተኝነትና የወጣቶች (የቄሮዎች፣ የፋኖዎች፣ የዘርማዎችና ገና ግልጽ ስያሜ ያልወጣላቸው የተለያዩ ክልሎች የዘውግ ወጣቶች) ሰፊ ንቅናቄዎች በአብዛኛው የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር፣ የሕገ መንግሥት፣ የሕግ የበላይነትና የመንግሥት የተጠያቂነት፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና የነፃነት ዋስትና የማስከበር ሰላማዊ ትግሎች እንደነበሩ ለመካድ አይቻልም። ክርስቲያኑንም ሆነ ሙስሊሙን፣ ወጣቱንም ሆነ ሽማግሌውን ሁሉ ከዳር እስከ ዳር ያስተባበሯቸው አንገብጋቢ የህልውና ጥያቄዎች የሰብዓዊ መብቶች፣ የመሬት ባለቤትነትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እንደነበሩ መገንዘቡ ለአዲሶቹ መሪዎች የወደፊት የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ ቀረፃና የትኩረት አቅጣጫ  ያግዛል ብዬ እገምታለሁ። 

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መለኮታዊ ተሰጥኦ እንዳላቸው ተደርገው የሚወደሱ መሪዎች (Charismatic Leaders) ሁሉ ከአማላይ ዲስኩሮችና መግለጫዎች ባሻገር፣ ዋስትና ያላቸውን የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋማዊ መደላድሎችንና ፍኖተ ካርታ ካልዘረጉ፣ ግልጽ ራዕይ ካላመላከቱ፣ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች የተቀጣጠሉትን ብሔረሰብ ተኮር የእርስ በርስ ግጭቶችንና መፈናቀሎችን በአስቸኳይ በማስቆም በተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ ሥር ከሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ማኅበራዊ ድርጅቶች መሪዎች ጋር በመወያየትና በመደራደር የወደፊቱን የለውጥ አቅጣጫ የሚያመላክት አስተማማኝ የጋራ ራዕይና ፍኖተ ካርታ (Road Map) በስምምነት ነድፈው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ በግልጽ ካልተዘረጋ በስተቀር፣ ይዋል ይደር ባልታሰቡ ድንገተኛ ክስተቶች የተነሳ በሚፈነዱ ያልተጠበቁ ደንቃራዎች ሳቢያ እነዚህን ለማስወገድ በሚወስዷቸው ዕርምጃዎች የተነሳ ወደድንም ጠላን ተመልሰው ወደ ፍፁም አምባገነንነት ሊለወጡ የሚችሉበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ሰፊ ዕድል ይኖራል፡፡ እኛምዓብይ  አህመድ (ዶ/ር) ‹‹የመለኮታዊ ስጦታነት አመራር›› እና የመልካም ራዕይ መግለጫዎች ላይ ብቻ በመተማመን ልንዝናና፣ ወይም ልንዘናጋ የምንችልበት ሁኔታ አይታሰብም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት የመላዕክት ሳይሆን የሰዎች አገዛዝ ስለሆነ ፍፁም የሚያስተማምን ሁኔታ ሊያረጋግጥልን አይችልም፡፡

በየክልሎቹ ‹‹በቄሮዎች›› ‹‹በፋኖዎች›› ‹‹በዘርማዎች›› እና በሌሎች የወጣት ቡድኖች የሚፈጸሙትን ግብታዊና ሕገወጥ ድርጊቶችን በጥሞና የሚታዘብ ዜጋ ለማረጋገጥ እንደሚችለው፣ እነዚህ ግብታዊ የሥርዓተ አልበኝነት እንቅስቃሴዎችና ሕገወጥ ድርጊቶች በአስቸኳይ ካልተገቱ የምንመኘው የዴሞክራሲና የነፃነት የለውጥ ጉዞ ሊደናቀፍ እንደማይችል አንዳችም ዋስትና አይኖረንም፡፡ የለውጥ አራማጆችና መሪዎች መሆናቸውን ተቀብለን ‹‹ከእናንተ አመራር ጋር ወደፊት›› ብለን ቃል ኪዳን የገባን ዜጎች ይህንን ቃላችንን አጥፈን ከበስተጀርባቸው እነዚህን ቀልባሽና ከላሽ፣ ሕገወጥና ጋጠወጥ ዕርምጃዎችን ስንወስድ ምን ይሆን ዓላማችንና ግባችን?

ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ከተለያዩ የዜና ምንጮች እንደምንሰማው ከሐረር ከተማ የሚወገደው ቆሻሻ ወደ ሚወሰድበት የቆሻሻ መቅበሪያ ሥፍራ እንዳይጫን በክልሉ መስተዳድር ሳይሆን በቄሮዎች ውሳኔ ተከልክሏል፡፡ አሁንም በቄሮዎች ጣልቃ ገብነት የተነሳ የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራውን አቁሟል፡፡ የባህር ዳር ፋኖዎች ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ሊጓጓዝ የነበረ እህል የጫነ ተሽከርካሪ በባህር ዳር ከተማ ውስጥ አስቁመው እህሉን ዘርፈዋል፡፡ የተርጫዳውሮ ወጣቶች በፈቃደኝነት ከዳውሮ ወደ ዱርጊና ዱራሜ የሚወስደውን የገጠር መንገድ በጉልበታቸው ለመሥራት የተነሳሱበት እንቅስቃሴ በዞኑ የመገናኛ ብዙኃን አሉታዊ ሽፋን ተሰጥቶታል በሚል ቅሬታ ተነሳስተው በርካታ የዞኑን መንግሥታዊ ተቋማትን አውድመዋል፡፡ በከፋ ዞን በጨና ወረዳ ማዶ ለማዶ በሚኖሩ አጎራባች መንደሮች ባልታወቀ ምክንያት የአንደኛው መንደር ወጣቶች በቁጣ ተነሳስተው፣ የሌላኛውን መንደር በርካታ ቤቶች በአንድ ጀንበር አውድመዋል፡፡ ንብረቶችን አቃጥለዋል፡፡ በሸካ ዞንም በቴፒ ከተማ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ከባድ ጥቃቶች ተፈጽመው በርካታ ወገኖች ለከፍተኛ ጉዳቶች እንደተዳረጉ ነሐሴ ሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በተላለፈው የኢቲቪ ዜና ተገልጿል፡፡ እሑድ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የኦኤምኤን ቡድን በኦቦ ጃዋር መሐመድ መሪነት ወደ ሻሸመኔ ከተማ ከደረሰ በኋላ፣ እኚህን ታዋቂ አክቲቪስት ለመቀበል በርካታ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ በወጣበት ሥነ ሥርዓት ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ‹‹ቦምብ! ቦምብ!›› ብሎ በመጮሁ የተደናበረው ሕዝብ ወደ አመቸው አቅጣጫ በሚሯሯጥበት ወቅት በመረጋገጥ ብቻ አራት ሰዎች እንደሞቱ፣ ስምንት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው አልበቃ ያለ ይመስል ቦምቡን ይዟል ተብሎ የተጠረጠረው ምስኪን ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎና በእንጨት ግንድ ላይ ተዘቅዝቆ ተሰቅሏል።

ኧረ ጎበዝ ወዴት እየተጓዝን ነው? ለነፃነትና ለፍትሕ የተዋደቀው፣ በሕይወቱና በአካሉ ቁጥር ስፍር የሌለውን ሰቆቃ ከፍሎና አሳልፎ ለዚህች የተስፋ ቀን ያበቃን ወጣት ያስገኘልንን ነፃነት እንዴት ራሱ መልሶ ሊቀብረው ይሯሯጣል? ነፃነት እኮ ሥርዓተ አልበኝነት አይደለም፡፡ ነፃነት ደግሞ ነፃ አይደለም፡፡ መሪር ዋጋ ተከፍሎበታልና።  ልብ ያለው ልብ ይበል! እነዚህ ግብታዊና ሕገወጥ ዕርምጃዎችስ የእነ  ዓብይ አህመድን (/) የለውጥ ተባባሪዎቹን ዓላማ ያሳልጣሉ/ያፋጥናሉ ወይስ ያዘገያሉ? ወይም ደግሞ ከእነ አካቴው ይቀለብሳሉ? ንፁህ ህሊናችን ይፍረድ!   ያለፉት ዘመናት ታሪክ እንደሚያረጋግጥልን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ ቀውሶችን ተከትለው የሚነሱ እንደ ዓብይ ያሉ ገናና/ተወዳጅ መሪዎች አንዳንዶቹ  ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ሽብርተኝነት አምርተዋል፡፡

ለምሳሌ ‹‹ነፃነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት›› የሚሉ አማላይ የሪፎርም አጀንዳዎች አውጀው የተነሱት እ.ኤ.አ. 1789 የፈረንሣይ አብዮት መሪዎች በገጠሟቸው ተቃውሞዎች የተነሳ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋና ሽብር ተዘፍቀው፣ ብዙም ሳይቆዩ ሥልጣናቸውን በአምባገነኑ መሪ በናፖሊዎን ቦናፓርቴ ተነጥቀዋል፡፡ አብዮቱንም ከግብ ሳያደርሱ ከሽፎባቸዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ ወደ ናዚ ዘረኝነትና ወደ ፋሺዝም የጥፋት ጎዳና አምርተው ሕዝቦቻቸውን ወዳልታሰቡ የመከራና የውድመት አዘቅቶች አስገብተዋል (ለምሳሌ፣ ሒትለርና ሙሶሎኒ)፡፡ ሌሎች ደግሞ የነፃነትና የታሪክን ጥሪ ተንተርሰው ብቅ ያሉት ገናና መሪዎች ደግሞ (እነ ማህተመ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ወዘተ.) አገሮቻቸውን ለነፃነት፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት አብቅተዋል።

ስለዚህ ዛሬ በአገራችን ያለው ሁኔታ ገና በጭጋግ ውስጥ የተሸፈነ ነው። በፍፁም አልጠራም፡፡ እነ  ዓብይ አህመድና (/) ጓዶቹ ገና ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለማቸው አልተቆራረጡም፡፡ ይህ አሳሳቢ ማነቆ ነው ለመሪዎቹም ሆነ ለሁላችንም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት 27 ዓመታት እንደተሰቃየንበት ሁሉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የጥቂቶች የፍፁም አምባገነንነት አገዛዝ ነውና። በተጨማሪም የእነ ዓብይ አህመድና (/) ጓዶቹ ‹‹የመደመር፣ የይቅርታ፣ የፍቅርና የኢትዮጵያዊነት›› ፖለቲካ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ እንደሚያቀነቅን በአደባባይ ታውጆልን ሳለ ‹‹በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት›› ላይ የተመሠረተው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ወይም በልዩ ሕገ መንግሥታዊ ኮሚሽን አማካይነት ተጠንቶና በፖለቲካ ኃይሎች ውይይትና መግባባት ላይ ተመርኩዞ ሳይሻሻል፣ ወደ ዴሞክራሲና ወደ መድበለ ፓርቲ ምርጫ የምናደርገውን የለውጥ ጉዞ እንዴት ሆኖ ወደፊት ለማራመድ ይቻለናል? የምርጫ ወቅት 2012 ዓ.ም. እየተቃረበ ነው፣ የሁለት ዓመታት ጊዜ ብቻ ነው የቀረን።

ታዲያ ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጥሪ ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመላው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የተለያዩ አጀንዳዎችንና የርዕዮተ ዓለም መርሆዎች የሚያራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ያላንዳች ግጭት ሰላማዊና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸውን ምርጫዎች ለማካሄድ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ እጅግ አስጨናቂ  ነው፡፡ ካለፈው ልምዳችንና ተሞክሯችን ስንነሳ። አዎን ወደ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓትና ወደ ብልፅግና ዘመን እንደምናመራ ከተወዳጁ ወጣት መሪያችን ከተበሰረልን የተስፋ መግለጫዎች በስተቀር፣ ስለምንተማመንበት ሁኔታ ግን እርግጠኞች አይደለንም። ዛሬ ‹‹ክርስቲያኑም ሙስሊሙም›› ተስፋ አይቆርጥም እንዲሉ፣ ሁላችንም በተስፋ መጠባበቅ ብቻ ነው፡፡ ወደ ነፃነትና ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እንዲያመራም የየበኩላችንን ያላሰለሰ ትግል ማፋፋም ነው የሚጠበቅብን፣ ወዳጄ ልቤ። ፕሌቶ የሚባል የግሪክ ፈላስፋ እንደተናገረው፣ ‹‹በሰዎች የሕይወት ቴአትር ውስጥ ተመልካች የሚሆኑት አማልክትና መላዕክት ብቻ ናቸው፡፡››

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...