Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢሕአዴግ የሰመመን መርፌ!

የኢሕአዴግ የሰመመን መርፌ!

ቀን:

በይናገር ጌታቸው

1940ዎቹ ጋምቤላን የጎበኘው አገር አሳሽ ኢቫን ፕሪቻርድ ኙዌርን የራስ አልባ ፖለቲከኞች ምድር ይላታል፡፡ የፕሪቻርድ አገላለጽ ኙዌር ምንም ዓይነት ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ተዋረዳዊ መዋቅር እንደሌላት ለማሳበቅ ያለመ ነበር፡፡ ዛሬ ይህ እውነት ከኙዌር ወጥቶ የመላው ኢትዮጵያውያን የሆነ ይመስላል፡፡ በዚች አገር በየቀኑ አዕላፍ ዜጎች የብሔር ፖለቲካ በሚሉት መዓት ሕይወታቸውን ይነጠቃሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሎ የሚላስ የሚቀመስ በማጣቱ ዛሬን ስለማደሩ እንኳን እርግጠኛ አይደለም፡፡ አገራዊ ተስፋን ያጫረው የህዳሴ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ በአደባባይ ተገድሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት መድረክ ቦምብ ይወረወራል፡፡ ምክንያቱ ባልተወቀ ግርግር የአዕላፍ ዓመት ልፋት ወደ አመድነት ይቀየራል፡፡ ሰው በድንጋይ ተውግሮ ይሞታል፡፡ በአደባባይ ይሰቀላል፡፡

ፌርማታው የማይታወቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁንም ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር አምባጓሮ ውስጥ ገብቷል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሩብ ጉዳይ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሆነ ሥርዓት ውስጥ መተዳደር ጀምሯል፡፡ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አደባባይ ተሰይሟል፡፡ የአዊ ማንነት ጥያቄም ማቆጥቆጥ ጀምሯል፡፡ አፋር ክልል ያዝ ለቀቅ የሚሉ አለመረጋጋቶች ሥጋት ፈጥረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ዓመታት ያስቆጠረው ተቃውሞ አሁንም አልከሰመም፡፡ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የህልውና ሥጋት ውስጥ ገብቻለሁ የሚል የድረሱልኝ ደብዳቤ ለፌዴራልና ክልል መንግሥታት ልኳል፡፡ የትግራይ ክልል መሪ ድርጅት ሕወሓት በፌዴራል መንግሥቱ አካሄድ ላይ ተደጋጋሚ መግለጫ እያወጣ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ሥር ያልተለመዱት እነዚህ ሁነቶች ብዙ ሊያነነጋግሩ እንደሚችሉ መገመቱ አዳጋች አይደለም፡፡ በተለይም አሁን ካለው የለውጥ ንፋስ ጋር ተያይዞ እንዲህ ያለው አገራዊ አለመረጋጋት ሲታሰብ፣ ንግግራችንን ወደ ንትርክ እንደሚቀይረውም ለማወቅ ነብይነት አይጠይቅም፡፡ ነገር ግን ንትርካችንን ወደ ሰከነ ውይይት ለማምጣት የሚከተሉት ጥያቄዎች ወሳኝ የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሽግግር ውስጥ ነውን? ሽግግሩስ ፖለቲካዊ ዕድገትን ያመጣል? የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታስ በኢሕአዴግ እጅ ምን ሊሆን ይችላል?

ለውጥ ያተረፈው ነውጥ!

ፍራንሲስ ፉኩያማ ፖለቲካ ዕድገትና ንቅዘት በተሰኘ መጽሐፉ አገራዊ ቀውስ ሁሌም ፖለቲካን ለማዘመን ዕድል ይፈጥራል ሲል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ፉኩያማ ነውጥ የፖለቲካ ማዘመኛ መንገድ ነው ሲለን ከሁለት መሠረታዊ መከራከሪያዎች በመነሳት ነው፡፡

የመጀመሪያው ነውጥ ከተከሰተ ሁሌም ነውጡን የሚደግፍና የሚቃወም የፓርቲ አመራር መፈጠሩ ስለማይቀር ነው፡፡ ሁለተኛው ማኅበረሰቡ ገዥውን አካል አስጨንቆ ከያዘው ለውጡ የግድ ስለሚሆን ነው፡፡ ይህን መሰሉ የፉክያማ መከራከሪያ በእሱ ብቻ ሲቀነቀን የኖረ አይደለም፡፡ ቤድ ፎርድ ኒው አቡዝ ‹‹ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና የፖለቲካ ዝመና›› በተሰኘ ጽሑፉ ነውጥ ዘመናዊነት እየመጣ ስለመሆኑ አመላካች ነው ይላል፡፡ እንደ ኒው አቡዝ ገለጻ ማኅበረሰቡ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ንቃተ ህሊናው እየተለወጠ ሲሄድ፣ የትናንቱን በመንቀፍ ለአዲስ ሥርዓት ማበብ ትግል ይጀምራል፡፡ ኒው አቡዝ ይህ ዓይነቱን ማኅበረሰብ በሽግግር ላይ ያለያየዋል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱንም የሽግግር ፖለቲካ ሲል ይጠራዋል፡፡

በእርግጥ የካርል ማርክስን የማኅበረሰብ አከፋፈል ላየ ሰው የኒው አቡዝ መከራከሪያ ውኃ የሚያነሳ መሆን አያከራከርም፡፡ ማርክስ ማኅበረሰብ ሦስት ደረጃዎች አሉት የሚል ሲሆን እነሱም ትውፊታዊ፣ ሽግግራዊና ዘመናዊ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ሽግግራዊ ማኅበረሰብ ትውፊትና ዘመናዊነት የሚገኛኑበትና የለየለት ትንቅንቅ የሚያደርጉበት በመሆኑ፣ በአገሮች ታሪክ ውስጥ ማርሽ ቀያሪ ተደርጎ የሚታሰብ ነው፡፡ የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነትና የፈረንሣይ አብዮት ለዚህ አብነት ናቸው፡፡

ይህ ዓይነቱን ሽግግራዊ ባህሪ ከፓርቲ ፖለቲካ አንፃር ሊተንትነው የሞከረው ሳሙኤል ሃንቲንግተን፣ የሽግግር ጊዜ ፖለቲካ አገር በሚመራው ፓርቲ ውስጥ ልዩነትን መፍጠሩ የተለመደ ነው ይላል፡፡ ሃንቲንግተን ከላይ በፉክያማ ከተነሳው መከራከሪያ ጋር የተመሳሰለ ሐሳብ ይሰነዝራል፡፡ የፖለቲካ ሽግግር በሚኖር ጊዜ ፓርቲው ውስጥ ሁለት ጎራ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ጎራዎች እርስ በርሳቸው መገፋፋት ሲጀምሩ ደግሞ የአገሮች ፖለቲካ ውጥረት ይበዛበታል፡፡ ነውጥም ይከተለዋል፡፡

ከዚህ ነባረዊ ሁኔታ በመነሳት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለመመልከት እንሞክር፡፡ ባለፉት ዓመታት የነበረው አገራዊ አለመረጋጋት ማኅበረሰቡ ለውጥ እንደሚፈልግ የሚጠቁም ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ግፊት ግን ከሕዝቡ ብቻ ሳይሆን በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥም በጊዜ ሒደት እየተፈጠረ የሄደ ይመስላል፡፡ በዚህ ምክንያት በገዥው ፓርቲ ውስጥ የለየለት አምባጓሮ መነሳት ጀመረ፡፡ የክልል መንግሥታት ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር አብሮ መሥራታቸው ቀርቶ የፌዴሬሽን አባል መሆናቸውን በተቃውሞ ለማረጋገጥ ባተሉ፡፡ የፌዴራሊዝም መጥፎ ጎን የሆነው በአንድ አገር ሁለት መንግሥት እሳቤ በአገሪቱ ተንሰራፋ፡፡ የፌዴራሉና የክልል መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቡት መረጃ ለየቅል ሆነ፡፡ ይህ አሳሳቢ ሁኔታም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝን በእጃቸው ያለችውን አገር ህልውናዋ ሳያከትም እንኩ ተረከቡኝ እንዲሉ አስገደዳቸው፡፡

በዚህ የታሪክ አጣብቂኝ መሀል የተገኘው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም መሪ አልባ ይመስል አስቸጋሪ የሚባለውን ጊዜ በብልኃት ለማለፍ ሞከረ፡፡ የኢሕአዴግ ምክር ቤትም ተስብሰቦ ፓርቲው ያለበትን ሁኔታ ገመገመ፡፡ ይህ ግምገማ የእህት ድርጅቶችን ቁመና በውሉ በመፈተሽ የነገውን ኢሕአዴግ ዳግም ለመውለድ ያሰበ እንደነበር ይገመታል፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ካፈርኩ አይመልሰኝ ብሎ ስለስብሰባው ውጤታማነት አብዝቶ ለፈፈ እንጂ፣ የታሰበውን ያህል መግባባት የተመዘገበበት እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ይህን ደግሞ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በቅርቡ ለክልላቸው ምክር ቤት በይፋ አረጋግጠዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ተህድሶው ለምን እንደከሸፈ ባያብራሩም መላምቶችን ግን ለማስቀመጥ አዳጋች አይመስልም፡፡ የመጀመሪያው አሁን በአገሪቱ የነገሰው የዘር ፖለቲካ በኢሕአዴግ ቤትም ትልቅ ቦታ መያዙ ይመስላል፡፡ ሁለተኛው በእህት ድርጅቶቹ መካከል መተማመን መጥፋቱ ሲሆን፣ እንደ ሦስተኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ፓርቲው ርዕዮተ ዓለማዊው ዥንብር ውስጥ መዘፈቁ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ምክንያቶች የኢሕአዴግ ምክር ቤትን የግምገማ ውጤትና የአዲሱን ሊቀመንበር መምጣት እንደ ሰመመን መርፌ አናያቸው እንደሆን እንጂ፣ ሥር ነቀል ለውጥን እንዳንጠብቅ ያደርጉናል፡፡

በእርግጥ ዓብይ አህመድ (/) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የሆኑበት ድምፅ ከተከታዮቻቸው ሰፊ ልዩነት ያለው ቢሆንም፣ አጠቃላይ የጨዋታውን ውጤት ግን የሚያሳይ አልነበረም፡፡ በተለይም በምክር ቤቱ ግምገማ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ከፍተኛ ትችት ከተሰነዘረበት ኦሕዴድ መምጣታቸው የዓብይ አህመድን (/) ሊቀመንበር መሆን አብዝተው የሚኮንኑ አባላትን ቁጥር አነስተኛ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

እነዚህ ወገኖች በአደባባይ ወጥተው አይቃወሙ እንጂ ኦሕዴድም ሆነ አዲሱ ሊቀመንበር ርዕዮተ ዓለማዊ ክህደት ሲፈጽሙብን ኖረዋል ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ የዚህ ጎራ አባላት የኦሕዴድ አመራር በክልሉ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ እንደ ለም መሬት በመጠቀም የሥልጣን ተረኛነትን አስተሳሰብን ይዞ ወደ ስብሰባ አዳራሽ መግባቱን ነውር አድረገው ይቆጥራሉ፡፡ በዚህ ሳያበቁም በአንድ የፖለቲካ ፕሮግራም እየተዳደርን ሥልጣንን የሕዝብ ማገልገያ እናድርግ ባልንበት ማግሥት፣ ለእኔ ወንበሩ ይገባኛል ብሎ መቅረብም ተገቢ አይደለም የሚል ሙግት ይሰነዝራሉ፡፡ እንዲህ ያለው ሙግታቸው ታዲያ በአዳራሽ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ከአዳራሽ ውጭም ኩርፊያቸው ያሳብቃል፡፡

ኢሕአዴግ የዓብይ አህመድም (/) ሆነ በሒደቱ ደስተኛ አልነበሩም ያልናቸው ግለሰቦች ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም የነገውን ኢሕአዴግ ስናስብ ሁለቱንም ወገኖች ከግምት ማስገባት የግድ ይሆናል፡፡ በኢሕአዴግ ቤት የዶ/ር ዓብይን ወደ መሪነት መምጣት የደገፉ የመኖራቸውን ያህል፣ የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም አስኳል ተደርገው የሚታሰቡ ወገኖችም ተቃውሞ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ተቃውሟቸው ደግሞ በምርጫው ሒደት ብቻ ሳይሆን ከምርጫው በኋላ ዓብይ አህመድ (/) ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑ ማግሥት በሥሯቸውም ሥራዎች ላይ የሚያተኩር መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ የተለያዩ ዋቢዎችን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መኳረፋቸው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሐዱ ብለው ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ንግግራቸው ላይ ከሕገ መንግሥቱ የራቀ አገራዊ አንድነትን የሚሰብክ ሐሳብ እንሰተዋል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ በመሠረቷት ፌዴሬሽኖች ህልውና የሆነች አገር እንጂ፣ መሬት ላይ የራሷ ግዛት እንደሌላት ይገልጿል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ይህን አስተሳሰብ ንደው ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ሲሉ ተደመጡ፡፡

ይህ አገላለጽ ለማኅበረሰቡ ከፈተኛ ደስታን የፈጠረ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ይከበር ለሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን ግን የሚዋጥ አልነበረም፡፡ በተለይም አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከግዛታዊ አንድነት አላቀን በብሔሮች መፈቃቀድ ላይ መሥርተናል ለሚሉ የኢሕአዴግ ግንባር ታጋዮች የሚዋጥ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ስለመደረጉ በተደጋጋሚ ሲያወሩ ይደመጣሉ፡፡ ይህ ሐሳብ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ምን ዓይነት የሥልጣን ሽግግር ተደረገ? ማን ነው ለማን ሥልጣን ያሸጋገረው? የሚል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 73/2 በግልጽ እንደሠፈረው መንግሥታዊ ሥልጣን የሚመሠረተው በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ባለው ፓርቲ አማካይነት እንጂ በግለሰብ አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነ የአቶ ኃይለ ማሪያም በዶ/ር ዓብይ መቀየር በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለ የአመራር መተካካት እንጂ የሥልጣን ሽግግርን አያመለክትም፡፡ እነዚህ ማሳያዎች አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕገ መንግሥቱ ላይ ያላቸው አቋም ለዘብተኛ መሆኑን የሚጠቁም ይመስላል፡፡

በእርግጥ የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ሳይወያዩበትና የተወካዮች ምክር ቤትም ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል ሐሳብ ሳያቀርብ፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 104 በመጣስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻላል ሲሉ መደመጣቸውም ለዚህ ዓይነቱ መከራካሪያችን ጠንካራ ማስረጃ መሆኑ የሚቀር አይደለም፡፡ ይህን መሰሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕገ መንግሥቱ ለዘብተኛ አቋም ማሳየት ሕገ መንግሥቱ አገር አፍርሷል ለሚለው የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ትልቅ ድል ቢሆንም፣ ለታዳጊ ክልሎች ግን የራስ ምታት ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተንቀሳቀሱባቸው ታዳጊ ክልሎች መሠረታዊ ጥያቄ ሁኖ የተገኘው ይህ የሕገ መንግሥቱ ቀጣይነት ጉዳይ፣ በሰሜን አሜሪካ ቆይታቸውም ወቅት በታዳጊ ክልል ተወላጆች በኩል ሲደመጥ ተስተውሏል፡፡ እንዲህ ያለው ጥያቄ ግን በፖለቲካ ልሂቁ በኩል ተነስቶ የሚያባራ አልሆነም፡፡ የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በይፋ ሕገ መንግሥቱ ይከበር የሚል ደብዳቤ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት እንዲጽፍ አስገድዶታል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም በርዕስ መስተዳደሩ በኩል ፌዴራሊዝሙ ያቀዳጀንን ሕገ መንግሥት ማክበር የውዴታ ግዴታ ነው ሲል ተሰምቷል፡፡ ትግራይ በሕዝባዊ ሠልፍ ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የኦነግ አመራርም ሕገ መንግሥቱ ያቀዳጀውን የራስን ዕድል በራስ መወስን እስከ መገንጠል መብትን ለማስከበር ትግሉን እንደሚያጠናክር ይፋ አድርጓል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባድ የቤት ሥራ የሚጀምረውም እዚህ ላይ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከኦሮሚያ የተገኙ የአገር መሪ ናቸው፡፡ በዚህም ክርስቶፎር ክላፋም የሚያነሳውን የኦሮሞ አገር የመምራት ታሪካዊ ጥያቄ መልሰዋል፡፡ ያለፉት ዓመታት የፖለቲካ አለመረጋጋት ግን ከኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ከአማራም የሚቀዳ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ ገፊ ምክንያትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን  የአማራ ፖለቲካ ልሂቃንን ማሸነፊያ መንገድ እንዲፈልጉ የሚያስገድድ ነው፡፡

ለእንዲህ ያለው አጣብቂኛቸው መፍትሔው ደግሞ የአማራ ፖለቲካ ልሂቃንን ጭንብል መዋስ ነው፡፡ ለዚህም ነው እውነተኛ ፌዴራሊዝም ይስፈን በሚለው ወጣት ትግል ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ የግዛት አንድነት ጉዳይን በማንሳት በቀላሉ የአማራ ፖለቲካ ልሂቃንን ቀልብ ለመሳብ የቻሉት፡፡ ይህ ዓይነቱ መንታ ሰብዕናን ለመላበስ መሞከርም የአገሪቱን ሁለት ሦስተኛ ሕዝብ የሚሸፍነውን የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ቀልብ ለማሸነፍ ረድቷቸዋል፡፡

ይህ እውነት ደግሞ ባለፉት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያልተስተዋለ መሆኑን መካድ አይገባም፡፡ አንዲህ ያለው ታሪክ ጠቀስ ጉዟችን ግን በአንድ ጥያቄ ይገታል፡፡ ባለፉት መቶ ዓመታት የኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ ፖለቲካ ልሂቃንን በኅብረት አስታርቆ መሄድ እንዴት አልተቻለም? ማርካኪስ ኢትዮጵያ በመቶ ዓመታት ታሪኳ ውስጥ የሦስቱን ብሔር ፖለቲካ ልሂቃ አስታርቃ ለመሄድ አለመታደሏ ብዙ መስዕዋትነት አስከፍሏታል ይላሉ፡፡ ማርካኪስ ይህን ታሪክ ያለመለስውን ጥያቄ ለዛሬ ዘመን ፖለቲከኞች ትተው ወደ ሌላ ትንቢት ያልፋሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው የነገዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ግጭት ምንጩ የቆላውና የደጋዋ ኢትዮጵያ ፀብ ነው ይላሉ፡፡ “Ethiopia The Last Two Frontires” በተባለ መጽሐፋቸው እንዳብራሩት፣ የነገዋ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥጋት በታዳጊ ክልሎችና በአደጉት መካከል የሚነሳው ፀብ ነው፡፡ የታላቁ የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪ ትንቢት የሠራ ይመስላል፡፡ ዛሬ ታዳጊ ክልሎች የሕገ መንግሥቱ ጠበቃ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው የመሀል አገር ፖለቲከኛውና የአገሪቱ መሪ ሕገ መንግሥቱ ላይ አምጸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተቃርኖ ደግሞ የነገዋን ኢትዮጵያ ስናስብ ፅልመት እንዲውጠን ያደርገናል፡፡ እንዲህ ያለው ፀለምተኝነት ግን ከሽግግር ጊዜ ፖለቲካዊ ባህሪ ብቻ የሚቀዳ ሳይሆን፣ ከፖለቲካ ዕድገታችንም አንፃር የሚቃኝ ነው፡፡

የትኛውም አገር የፖለቲካ ዕድገት መመዘኛው መንግሥታዊ ጥንካሬ፣ ግልጽነትና የሕግ የበላይነት ነው፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች ያለፉትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  የአስተዳደር ጊዜያት ለመመልከት ስንሞክር፣ ምላሹ አዎንታዊ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን  ከላይ በወፍ በረር ስንቃኝ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳይደረጉ የተለያዩ ሕጎችን ሲጥሱ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር እንጂ የፖለቲካ ዕድገት አለመምጣቱን ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ከላይ ካነሳኋቸው ሦስት የፖለቲካ ዕድገት መገለጫዎች አንፃር ነገሩን በጥቂቱ ለማብራራት ልሞክር፡፡ 

የፖለቲካ ዕድገት መሠረታዊ መገለጫ ተደርገው ከሚታሰቡ ጉዳዮች መካከል  አንዱ የመንግሥት ጥንካሬ ነው፡፡ በዚህ መሥፈርት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት ጉዞዋ የተለየ ታሪክ አስመዝግባለች ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ያለውን ጊዜ ብንመለከት እንኳን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ተፈናቅሏል፡፡ ‹ድብቁ  የሰብዓዊ መብት ቀውስ› ተብሎ በዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እየተገለጸ ያለው የጌዴኦና የምዕራብ ጉጂ ግጭት አሁንም ነጋቸው የሚያስፈራ አዕላፍት በተለያየ ቦታ ተጠልለዋል፡፡ በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ቢሮና ዩኒሴፍም አስቸኳይ ዕርዳታ ካልተገኘ አሰቃቂ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚፈጠር እያስጠነቀቁ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግጭት ከወለደው ሰብዓዊ ቀውስ ባለፈ በየቦታው በሚነሱ አለመግባባቶች የበርካታ ዜጎቿ ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ ለማየት አይደለም ለማሰብ የሚዘገንኑ የፌዴራል ሥርዓቱን የሚገዳደሩ ወንጀሎች በየቦታው ተበራክተዋል፡፡  

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር ከጠቀስኳቸው የፖለቲካዊ ዕድገት መገለጫዎች ውስጥ የተሻለ ነጥብ የሚያስመዘግበው ፖለቲካዊ ተጠያቂነት በሚለው ነጥብ ይመስላል፡፡ በዚህ መመዘኛ ባለፉት አራት ወራት የተለያዩ መንግሥታዊ ተጠያቂነትን  የሚያሰፍኑ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ ያለ ጥፋታቸው ለዘመናት በማረሚያ ቤቶች አሰቃቂ ጉዳት የደረሰባቸው የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል፡፡ ባልተለመደ መንገድ የአገሪቱ መሪ ይቅርታ ሲጠይቁ ተስተውሏል፡፡ ይህ በአገሪቱ ታሪክ ሁሌም ሲወሳ የሚኖር ተግባር መሆኑ የሚያከራክር አይመስልም፡፡

ነገር ግን በይቅርታ ከማረሚያ ወጥተው ዳግም አገራዊ አለመረጋጋትን እየፈጠሩ ያሉ ግለሰቦች መኖራቸው ሲታሰብ፣ ይቅርታው የተደረገበት መንገድ ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከሰሞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ካሉ አለመረጋጋቶች ጀርባና ከሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ክስ እንደተመሠረተባቸው በመገናኛ ብዙኃን የምንስማቸው ዜጎችም፣ በቅርቡ ከማረሚያ ቤቶች የወጡ መሆናቸውም ለዚህ ማሳያ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥታዊ ተጠያቂነትን በማስፈን ደረጃ ሙከራዎች ቢኖሩም፣ አሁንም ወደ ኋላ የሚጎትቱ ነገሮችን አለመታጣታቸውን ያሳያል፡፡ በተለይም ከአርስቶትል የመንግሥታዊ ተጠያቂነት መርህ አንፃር ነገሩን ከተመለከትነው ብዙ ጉድለቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ አርስቶትል ሥልጣን ላይ ያለ አካል በግዛቱ ላለ ማንኛውም ወንጀል ተጠያቂ ነው ይላልና፡፡

ያለፉት አራት ወራትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጉዞ ከሌላው የፖለቲካ ዕድገት መመዘኛ የሕግ የበላይነት አንፃር ከተመለከትነውም የሰፌድ ላይ ሩጫው መቀጠሉን ያስገነዝበናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሕግ የበላይነት ደጋግመው ቢናገሩም፣ ከላይ ከጠቀስኩት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ከማፍረስ ጀምሮ እስከ ሞራላዊ ሕጎች የደረሰ ጥሰት በስፋት ተፈጽሟል፡፡

ወንድነት የተጠናወተው ፖለቲካ!

ዶናልድ ሌቪን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያመለጡ ወርቃማ ዕድሎች በሚለው ጽሑፉቸው አምስት አጋጣሚዎች የአገሪቱን ታሪክ የመቀየር አቅም ነበራቸው ይላሉ፡፡ ሌቪን ከ1953 .ም. መፈንቀለ መንግሥት እስከ ምርጫ 97 ለባከኑት ዕድሎች ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶችን ያነሳሉ፡፡ የመጀመሪያ የፖለቲካ ልሂቃን አለመተማመን ሲሆን፣ ሁለተኛው የውጭ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አምልኮ ነው። ለሌቪን ከዚህ ሁሉ የከፋው የክሽፈቶች መነሻው ግን ወንድነት ነው።

ወንድነት ጽንሰ ሐሳብ ነው። ወንድነት የእኔ እበልጥ የእኔ በልጥ ፖለቲካ ነው፡፡ ወንድነት ካሸነፉ በኋላ ሥልጣኑን ሁሉ ለራስ ወገን ማዳረስ ነው፡፡ ወንድነት የምን ታመጣለህ ጨዋታ መገለጫ ነው፡፡ ወንድነት ትናንትን አውግዞ አስወግዞ እኔን ተከተሉኝ ማለት ነው፡፡ የሌቪን የወንድነት ጽንሰ ሐሳብ አገር ያድናል፣ አገር ይገላል፡፡ መሠረታዊው ሐሳብ ግን እሱ አይደለም፡፡ መሠረታዊው ሐሳብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከበሽታው ድኗል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ዛሬም ወንድነት የሚሉት በሽታ በእጃችን የገባውን ዕድል ያሟሟዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የመሪነት ጎዳናም በመሆንና አለመሆን የተገራ ይሆናል፡፡ እንደ ቻይናው ዴንግ በሕዝብ ተሳትፎ የታጀበ ለውጥ አምጥቶ ታሪክ መሥራት፣ አልያም እንደ ሶቭየት ኅብረቱ ሚካኤል ጎርባቾቭ አገር መበተን፡፡ ኢትዮጵያ ለሁለቱም በቅርብ ርቀት ላይ ያለች አገር ናት፡፡ ከትናንት የተሻለ ታሪክን ለመሥራት የሚያስችል ተነሳሽነት ዛሬ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በዘመናዊ ታሪካችን ውስጥ ባልተለመደ መንገድ በአብዛኛው በሕዝብ ተወዳጅ የሆነ መሪ አግኝተናል፡፡ መንግሥትን ለማፅናትና ለብሔር ግንባታ አስፈላጊ የሚባለውን በአገር ተስፋ ማድረግንም ከትናንቱ በላቀ ሁኔታ እያስተዋልነው የምንገኘው ሀቅ ነው፡፡

ነገር ግን ከላይ ከተጠቀሱት ምቹ አጋጣሚዎች ባልተናነሰ የአርባ ቀን ዕድላችንን የሚወስኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ነገ አብረውን እንዳይቀጥሉ ማድረግ የምንችለው ደግሞ መጀመሪያ ምንጫቸው  ላይ ስንስማማ ይመስላል፡፡ በዛሬው ፖለቲካችን ውስጥ ለዚህ የሚያበቃን መሠረታዊው ጉዳይ አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷን በቅድሚያ ማመን ነው፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ ቆይታቸው ኢትዮጵያን ኦሮሞ ሲመራት ለምን ይህ ጥያቄ ይነሳል በሚል ሊለባበስ አይገባም፡፡ በእኔ ግምት ይህ ጥያቄ ከ27 ዓመታት በፊትም ይነሳ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥርዓት ችግርን ወደ ሕዝብ አውርዶ ለማስተሳሰር መሞከር እንደ አገር መሪ አደጋው የበዛ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚፈጠር ማኅበራዊ መሠረትም ከሕወሓት የባሰ አገርን ይፈጥር ካልሆነ በስተቀር ውጤቱ ውኃ ወቀጣ ይሆናል፡፡ ስለዚህም አገሪቱ ችግር ውስጥ መግባቷን ለማመንና ወደ ለውጥ የሚደረገውን ጉዞ ለመፈተሽ ይርዳል፡፡

ይህ ሲሆን ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ላይ መግባባት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ኢሕአዴግ መዳከሙን ማመን ነው፡፡ አስተያየቱ ከማንም ይምጣ ከማን ኢሕአዴግ በለየላቸው አንጃዎች ስለመከፈሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ደኢሕዴን ስድስት ወራት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስተኛውን ሊቀመንበር ሰይሟል፡፡  የማይገመቱ ሹም ሽሮች ኦሕዴድን ጨምሮ በስፋት ሲስተዋሉ ቆይተዋል፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴግን የሚተች መግለጫ በተደጋጋሚ አውጥቷል፡፡ ብአዴን ከወር በላይ መታገስ አልችል ብሎ የክልል ኃላፊ ሹመትን ሲሰጥ ሲነሳ ተመልክተናል፡፡ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የከተሙት ሀብሊና ኢሕሶዴፓ የማይሰማ ጩኸታቸው ቀጥሏል፡፡

እንደ ምንም ተጠጋግኖ ዛሬ ደጃፍ የደረሰው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉዳይ ከቅርብ ዓመታት በባሰ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የአገሪቱን አንድ ሦስተኛ የቆዳ ስፋት የሚሸፍነው ክልሉ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ሦስተኛው በርካታ ብሔር ያለው  አካባቢ እንደመሆኑ መጠን፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ነገው አሳሳቢ ይመስላል፡፡ ከ1987 ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም  ድረስ ክልሉን የመሩት ግለሰቦች በሙሉ በአንድም በሌላም መጨረሻቸው ማረሚያ ቤት መሆኑን ላየ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፖለቲካ የትናንት ብቻ ሳይሆን የነገም ፖለቲካዊ ሕመማችን መነሻ ስለመሆኑ  የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ማሳያዎች ኢሕአዴግ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከሩን የሚነግሩን አይደሉም፡፡ ይልቁኑም መንግሥታዊ ውድቀት ውስጥ ስለመሆናችን  ይጠቁማሉ፡፡

ሁለተኛው መሠረታዊ ችግር ከዘመናት በፊት የነበረ አሁንም የዘለቀ ነው፡፡ ይህ ችግር በመረራ ጉዲና (ዶ/ር) አገላለጽ የህልሞች ኩርፊያ ነው፡፡ ትናንት በኢትዮጵያ በፍላጎት ይጋጩ የነበሩት የፖለቲካ ልሂቃን ከኦሮሞ፣ ከአማራና ከትግራይ መሆናቸው የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ዛሬ የእነዚህ ልሂቃን ፍላጎት በውል ሳይፈታ ከታዳጊ ክልሎችም ሌላ ፍላጎት እየመጣ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የብሔር ግንባታ ሒደቱን የመቀልበስ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተስተዋሉ ያሉ የህልም ኩርፊያዎች  መዳረሻቸው አስፈሪ ነው፡፡

‹መደመር› በሚባለው የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ የተቀነበቡ አስተሳሰቦች እንደ ‹ፓንዶራ ቦክስ› ድንገት ቢከፈቱ አገር የማፍረስ አቅም አላቸው፡፡ ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ይዞ የሚወጣው ሰንደቅ ዓላማ መለያየት የአምሮት መገለጫ ሳይሆን፣ የተቃርኖ ማንነት  መንገዳችን ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ትናንቱ ቀላልና በጉልበት የማይፈታበት ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አገር ወደ መምራት እንዲመጡ ያስገድዳል፡፡ እስካሁን በርካታ አንጀት ሚያርሱ ንግግሮች የመንግሥታቸውን ፍኖተ ካርታ አብራርተዋል፡፡ ይህ ፍኖተ ካርታቸው ግን ገና ያልተፈተነ ነው፡፡

ፍቅርና አገራዊ አንድነት የአንድ ሥርዓት ግብ እንጂ መንገድ አይደሉም፡፡ ከዚህ በመነሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብን መንገድ የማድረግ ከባድ የቤት ሥራ ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡ ሽግግርን ግብ ከማድረግ ወጥተው ፖለቲካዊ ዕድገትን አሀዱ ማለትም  አስቸኳዩ ተግባር ነው፡፡  ይህ ካልሆነ ግን በሰመመን ውስጥ ያለው ሕዝብ  እውነተኛ ሕመሙን መጋፈጥ ይጀምራል። የእሱ ሞትም የአገር ሞት ይሆናል። ኦሮማይ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...