Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአገር ላጋጠማት ችግር ምን መደረግ አለበት?

አገር ላጋጠማት ችግር ምን መደረግ አለበት?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አገራችን ባልተጠበቀ፣ በሚደንቅ፣ በሚያሳሳና በሚያሳስብ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች፡፡ አዲሱን ምዕራፍ ያልተጠበቀ የሚያደርገው ከኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወጣቶች ትግልና ከገዥው መንግሥት የረገጣና የድቆሳ መስተጋብር ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣ በመሆኑ ነው፡፡ ለውጡን የሚያስደንቅ የሚያደርገው ደግሞ የለውጥ ኃይሉ ቅንብር ነው፡፡ የለውጥ ኃይሉን ቦታ የያዙት ከኢሕአዴግ ከራሱ ውስጥ የተመዘዙና ከተቃዋሚ ውስጥ የተፈለቀቁ የዴሞክራሲ ወገኖች፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወጣቶች ጋር አንድ ላይ ገጥመው ነው፡፡

ለውጡን እጅግ በጣም አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ አሁን አገራችን ውስጥ በየቦታውና በየቀኑ የሚታየውን አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ ውድመት፣ ጥቃት፣ ሁከትና ግርግር እያመነጨ የሚዘረግፈው ሁኔታችንና አሠላለፋችን ነው፡፡

የለውጥ ተቃዋሚዎች መፈክርና ዓላማ፣ እንዲሁም ዝርዝር ምክንያት ገና ፈርጦ የወጣ ባይሆንም የዚህ ጎራ ችግር ለ‹‹እናሸንፋለን›› ‹‹አንጠራጠርም›› ብቻ የሚተው ቀላልና ተራ ነገር አይደለም፡፡ የተጀመረውን ለውጥ አሳሳቢ የሚያደርጉትና ለአደጋም ያጋለጡት የለየላቸው የለውጥ ተቀናቃኞች ብቻ አይደሉም፡፡ በለውጥ ፈላጊውም ረድፍ ውስጥ ኢሕአዴግን በመቀበል የተጠመዱና በዚህ የሰከሩ፣ የለውጡን ዋነኛ ባህሪና ፀጋ ማለትም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆኖ ለውጥ ማራመድንና ማምጣትን፣ ስለዚህም ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙ ትርጉም ስለሌለውና ሕገ መንግሥቱን አሽቀንጥረው ካልጣሉት በስተቀር ‹‹ዕውን›› ስለማይሆነው ‹‹የሽግግር መንግሥት›› የሚያወጉ፣ የለውጡ አደጋዎች አሉ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም በደም ፍላት ከታወረና ከሰከረ፣ ጥቃትን፣ ጥላቻን፣ ውድመትን የትግል ዘይቤው ካደረገ አፍላ ጊዜ ውስጥ ወጣን ብንልም፣ ሕግ የማስከበር ተግባር በጉልበተኞች እጅ ሲገባ በዓይናችንና በሕይወት ጭምር እየመሰከርን ነው፡፡  ሕገወጥነትን ለመግታት መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ የፈራ ተባ፣ የግብር ይውጣ፣ የዘፈቀደ ሥራ ሆነ እያልን አሁንም መሥጋታችንና ማማረራችን ሳያንስ፣ የመንግሥት የሕግ አስከባሪነት ዕርምጃ የራሱንም የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ አስገምቶና አስገምቶ የፍትሕ ሥርዓቱ በአጠቃላይ ማፈሪያ መሆኑ ሳይበቃ፣ ግለሰቦች በዚህ ‹‹ግርግር›› ውስጥ ከሕግ በላይ ሲሆኑ፣ አፄ በጉልበትነታቸውን ሲያውጁ፣ ከዚያም አልፈው እንደ ግል ኩባንያ እናዝበታለን የሚሉን የብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ፣ ‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለውን መብት›› እናረጋግጣለን ብለው ሲሞክሩ ሁሉ ዓይተናል፡፡

አምባገነንነት አይዞህ ባይ እንዲያጣ፣ አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን መፍራት እንዲጀምር፣ ለአድራጊ ፈጣሪነት ሕጋዊነትን ማቀዳጀት እንዲቀር እንጂ፣ የሕግ አስተዳደር ድራሹ ጠፍቶ ዘልማድ እንዲሻርና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ አልታገልንም፡፡ በትግሉ ውስጥ የታየው ጥቃት ጥላቻና አውዳሚነት የወንጀል መከላከል፣ የፍርድና የፍትሕ ሥርዓቱ አካልና መሣሪያ ይሁን አላልንም፡፡ ከስደት የተመለሱና የሚመለሱ የለውጥ ኃይሎችም ከስደት ሲመሉና አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ተቀበሉን ሲሉ፣ የአቀባበል ሥርዓትም ሲያዘጋጁ፣ የሕዝብ ስብሰባም ሠልፍም ሲጠሩ፣ የገንዘብም መዋጮ ሲያሰባስቡ ሕግ ማክበር ድሮ ቀረ እያሉ መሆን የለበትም፡፡

የኢትዮጵያን ዴሞክራሲም ሆነ መልካም አስተዳደር ከዚያም በላይ፣ የኢትዮጵያውያንን ተራ ውሎ ማደር ጭምር ለሥጋትና ለአደጋ ያጋለጡ ሕጎች፣ አሠራሮችና ልማዶች በእንዲህ ያለ የለውጥና የአብዮት ሁኔታ ውስጥ መነቃነቃቸውና መንቃታቸው የማይቀር ቢሆንም፣ በዚህ ምክንያት ግን ከመሠረታዊና የትም ቦታ መከበር ካለባቸው ሕጎች ውጪ መሆንና ወንጀል መፈጸም የሚያስችል መብት የሚያቀዳጅ ነፃነት የሚባል ነገር የለም፡፡ በዚህ ረገድ የሚታየው ክብረ በዓላዊ የፈንጠዝያና የሆያ ሆዬ ግርግር የሕግ አክባሪነትን የውኃ ልክ ከማስገመቱም ባሻገር፣ ለለውጥ ተጠናዋቾች አሻጥር መታገያና መደበቂያም ይሆናል፡፡ ሌላ ምክንያት መዘርዘር ሳያስፈልግ በገዛ ራሱ ምክንያት ትክልል አይደለም፡፡ ሻሸመኔ ላይ የታየውን አሰቃቂና አረመኔያዊ ወንጀል መፈጸም እስኪቻል ድረስ ከልካይና ሃይ ባይ የታጣው፣ በ‹‹እንቁላሉ ጊዜ ልክ አይደለም›› እያልን መናገርና ማሳፈር ባለመቻላችን ነው፡፡

በጣም አስቸጋሪና አደናቃፊ የሆኑ ሕጎች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ እነዚህንም ተራ ሕጎች የማቃናት ጉዳይ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን የማረም፣ የማከምና የመለወጥ ጉዳይ ዴሞክራሲን ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከዚህ በላይ ውስብስብ ነው፡፡ እንኳንስ ሕገ መንግሥቱን ኢሕአዴግን ራሱን ‹‹አስፈላጊ›› የሚያደርገው ብዙና የተወሳሰቡ ምክንያቶች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እንኳንስ ዛሬ ድኅረ መጋቢት 2010 ዓ.ም.  ከዚያም በፊት ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል ዒላማ ገዥው ቡድን (ኢሕአዴግ) አይደለም፡፡ በተለይ ዛሬማ የለውጥ ኃይሎች ከኢሕአዴግ/ከኢሕአዴጎች ከራሳቸው ውስጥ በሕዝቦች የትግል ምጥ ከተወለዱ በኋላ፣ የትግሉ ዒላማ ለብቻዬ ልግዛ ብሎ ልማቱም ዴሞክራሲውም ኢትዮጵያም ያለ እኔ አይኖሩም ብሎ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ የደረሰው ብልሽትና ጥፋት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥታዊ አውታሩ ከየትኛውም ቡድን ይዞታነትና ደባልነት ነፃ እንዲሆን፣ እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶችም ችሮታነት እንዲያከትም መታገል ነው፡፡ ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርጋቸውን ምክንያቶች በደንብ አብራርተን እንለፍ፡፡

ኢሕአዴግ በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ አዕምሮ ሙሽት ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አሻራውን አሳርፏል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መልከዓ ምድር ቀይሯል፡፡ የብሔረሰብ መብትን አነሰም በዛ የተመረኮዘ የአስተዳደር ይዞታ አሸናሸንን፣ የፓርቲ አደረጃጀትንና የሥልጣን አያያዝን ያመጣ ሕገ መንግሥት ተክሏል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአገሪቱ የልማት ግስጋሴ ጀማሪም ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ተቃውሞና ድጋፍ እንዳፈራ ሁሉ፣ ሕገ መግሥቱም ደጋፊና ተቃዋሚ አፍርቷል፡፡ እንዲያውም የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩትንና ‹‹ሕገ መንግሥቱ ሊያሠራ ይችላል፣ ተግባራዊ የሚያደርገው ታጣ እንጂ›› የሚሉትን የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ወስደን፣ ‹‹ለሰላማችን ጠንቅ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ነው›› ከሚሉት የተቃዋሚ ክንፎች ጋር ስናነፃፀር፣ እነዚህኞቹ በቁጥር የሚያንሱ ናቸው፡፡ ወይም የሚያንሱ ይመስላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በራሱ ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ወደ ጎን የማይባሉ አስፈላጊ ሰበዞች ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ዴሞክራሲን ተጋግዞ የመገንባት ዕድል ዕውን የመሆን ተስፋ የሚኖረው፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› በሚል ጥያቄ በኩል ሳይሆን ያለውን ሕገ መንግሥት የጋራ መገናኛ በማድረግ በኩል እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ እናም በሽግግር መንግሥት ጥያቄ አማካይነት ካለው ሕገ መንግሥት ለማምለጥ መሞከር ለተከፋፈለ የፖለቲካ ንጠት በር መክፈት ነው፡፡

ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርጋቸው ሌላም ሰበዝ አለ፡፡  ኢሕአዴግ በሥልጣን አወጣጡና ‹‹በአዲስ›› አገዛዝ ግንባታው የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ ኃይል ከእነ ርዕዮተ ዓለሙ በዋናነት የተጠቀመ መሆኑ አውታረ አገዛዙን ገለልተኛ እነፃ የጎደለው መንታ ተፈጥሮ (ከውስጥ ባሻ/በጨነቀ  ጊዜ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችል ኢሕአዴጋዊ ቡጥ፣ ከውጭ ደግሞ ‹‹የዴሞክራሲ›› ቅርፊት) እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችን ተግባራዊ ሕይወት ከሲታ እንዲሆን ያደረገው፣ የኢሕአዴግንም በሥልጣን ላይ መቆየት በሕዝብ ድምፅ ብቻ የማይወሰን እንዲሆን ያደረገው ይኸው የቡጥና የቅርፊት አለመጣጣም (ቡጡ ቅርፊቱን መጫን መቻሉ) ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፓርቲ በምርጫ ድምፅ ቢሸነፍና ሽንፈቱን ተቀብሎ ከሥልጣን ለመውረድ የተስማማበት ሁኔታ ቢከሰት እንኳ፣ ከአገዛዙ የሥልጣን ኃይል ውስጥ ዘራፍ ብሎ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ምናልባት ሁሉ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ማለት ዛሬም ያልታለፈ ፈተና ነው፡፡ በአጭሩ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የኢሕአዴግ ሰበዝ (ፋክተር) እንዳያያዛችን ለበጎም ለክፉም ውጤት መዋል ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የሁሉም የዴሞክራሲና የለውጥ ኃይሎች የጋራ መነሻና መገኛ መሆን አለበት የሚባለው፣ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች በጭራሽ የሉም ተብሎ አይደለም፡፡ ወይም ኢሕአዴግ ላለፉ 23 ዓመታት እንደሚለው ሕገ መንግሥቱ እንከን የለሽና በዓለምም በአፍሪካም አንደኛ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን እናሻሽል ከማለት በፊት ለዴሞክራሲ ድል ግድና ተቀዳሚ የሆኑ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚቻሉ ተግባሮች አሉ፡፡ አዘላለቃችንን የሚወስኑና አደጋዎችን ለማምከን የሚረዱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሳይረባረቡ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻል አወዛጋቢ ጉዳይ መግባት፣ የትግሉን ኃይል ክፉኛ ይከፋፍላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ በሆነው ፓርቲያዊነት ባልተጠናወታቸው አውታሮች ላይ፣ ዴሞክራሲን መሠረት በማስያዝ ለውጥ ላይ ትኩረትን ማሰባሰቡ በጣም ተመራጭ ነው፡፡ ይህም ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ ከኢሕአዴግ የለውጥ ኃይሎች ጋር የሚቻል ነው፡፡

እሳትና ጭዳቸው ወጥቶ የነበሩ ቡድኖች አገር ቤት እየገቡ ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ውስጥ በሕግ ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁ፣ በፍርድ የሞት ቅጣት የተወሰነባቸውን መሪዎቻቸውም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊካንና አገርን መገንባትን ጉዳያችን ብለው የተሰባሰቡበት፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱበት፣ ነፃ የብዙኃን ማኅበራትና ነፃ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎዎች የሚፍለቀለቁበት መልካም የፖለቲካ አየር መፍጠር የመጀመርያው ግዳጃቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸውና የማይነካኳቸው፣ የዴሞክራሲ ተቋማትንና አውታራትን ማሰናዳት የሚቻላቸው እንዲህ ያለ የፖለቲካ አየር ሲፈጠር ነው፡፡ ሕግ ማክበርንና ማስከበርን፣ ሕገወጥነትን መግታትን ባልዘነጋ በዚህ የፖለቲካ አየር ውስጥ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከቡድኖች የፖለቲካና የድምፅ ትርፍ ይልቅ ለጤናማ፣ ደህነኛ የምርጫ ዘመቻና ላልተጭበረበረ ነፃ የድምፅ አሰጣጥ ሥር መያዝ መጨነቅን ያበለጠ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊናንና ግንዛቤን የማጎልበት ሥራ ማከናወን ይቻላል፡፡ ቀላልም ይሆናል፡፡

አገር ውስጥ ያሉና ውጭም የነበሩ ስለመከረኛው የሽግግር መንግሥት፣ ስለብሔራዊ የዕርቅ መንግሥት፣ ወዘተ. ጥያቄ/ስብሰባ ጉባዔ ሲያነሱና ሲጥሉ ይሰማሉ፡፡ ይህን ጥያቄ ‹‹ውድቅ›› የሚያደርገው ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥትን ጥያቄ ያጥላላው ስለነበር፣ አሁን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአሜሪካ/ዋሽንግተን ስብሰባ መልስ ላይ ‹ግዴላችሁም አያዋጣም እኔ ሽግግር እሆናችኋለሁ› ስለተባለ ብቻ አይደለም፡፡ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ እንደ እውነቱ ከሆነ ያለውን ሕገ መንግሥት እንዝለለው፣ እንለፈው ማለትን መንደርደሪያውና ግቡ ያደረገና ሁኔታው ከባሰም በሥርዓት ቅልበሳና ወይም በፀረ ሕገ መንግሥትነት መከሰስ/መኮነንን ስለሚያስከትልም ጭምር ነው፡፡

ዛሬም በአዲሱ የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጅምር የለውጥ ሒደት ውስጥ በሥርዓት ቅልበሳና በፀረ ሕገ መንግሥትነት ውግዘትና ፍረጃ ማምጣት የቻሉ አንዳንድ ‹‹ያልተወደዱ ባህሪዎች››፣ ኢሕአዴጎች ውስጥ (በኢሕአዴጎች መካከል) ቃላትና መግለጫ መወራወርን ሲያመጡ ዓይተናል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ እንዲያውም ቀደም ብለን ከላይ እንደገለጽነው የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ፣ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩና በለውጡ ውስጥ አሠላለፋቸው ገና ያልለየላቸው ወገኖች በሕገ መንግሥት ይከበርና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን በማስተግበር ስም በአገር ህልውና ላይ አደጋ ሊጠሩ፣ የሚንቀለቀል እሳት ሊጭሩ ይችላሉ፡፡ ከሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሶማሌ ክልል የሆነው የዚህ ሙከራ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ይህንን አደጋ ደግሞ ይበልጥ ያባባሰውና የሚዘገንን ግፍ እንዲያስመዘግብ ያደረገው በተለይም የታጠቀ የክልል ኃይል፣ ብሔርተኛና ፖለቲከኛ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ግን ሕገ መንግሥቱ ራሱ ያፈራው ዕዳ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዚህ ሁሉ የምዕራፍ ሦስት ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎቹ ተመሽጎ እያለ፣ እያንዳንዱን ክልል ከሌላው አንፃር ‹‹እኛ›› እና ‹‹እናንተ››፣ በእያንዳንዱም ክልል ውስጥ በራሱ ባለቤትና ባዳ፣ ነዋሪና መጤ ያደረገ ሥርዓት መነሻ በጭራሽ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይህን አደጋ ያመጣው ከይዘቱ ይልቅ የሕገ መንግሥቱ ‹‹አያያዝ›› ነው፡፡  ይህንን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ማሻሻል ይቻላልም የምለው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከታች ጀምሮ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ደረጃ ያሉ የሥልጣን አካላት በሕዝብ ወሳኝነት እንዲደራጁና እንዲመሩ ይደነግጋል፡፡ ክልል ገብ ጉዳዮችን ለክልሎች፣ ክልል አለፍና ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለፌዴራል ማለትም ለማዕከላዊ ለያይቶ የሰጠ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አስማምቶ ለማስተዳደር በፍፁም አያንስም፣ አይጠብም፡፡ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት በተለይም አንቀጽ 39ን የማይወዱና የሚቃወሙ ብዙዎቹ ለዚህ ያበቃን፣ ለልብ መከፋፈል የደረገን ባሻ ጊዜ የራስ ክልል ከመፍጠር አንስቶ ከአገሪቱ እስከ መለየት ድረስ የሰፋና የከፋ መብቶችን የሰጠው ሕገ መንግሥት ነው ይላሉ፡፡ ዴሞክራሲ ላይ ቆመን ወደፊት ስለሕገ መንግሥቱ በአጠቃላይ መነጋገራችን አይቀርም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የተነሳው ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ግን እነ እንቶኔን ምን አካሰሳቸው ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ከመፈለግና ከመምከር ይልቅ፣ የመክሰስ መብትን ጥፋተኛ በሚያደርግ መንገድ ውስጥ የሚነጉድ በመሆኑ የሥር የመሠረት ችግራችንን ወደ መረዳትና ማወቅ አያደርሰንም፡፡

ችግራችን ያለው ግን እኛ ሰዎቹ ዘንድና ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ አሟልተን አለማክበራችን ላይ ነው፡፡ መንግሥት ከሕግ በላይ በመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በመላ በሕዝቦች ባለቤትነት ውስጥ ገብቷል ብሎ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት መቆንጠጥ፣ አጠቃላይ የሕዝብ እምነት በጭራሽ መሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሥልጣን በአንድ ፓርቲ እጅ ውስጥ ወድቋል ማለት የሕዝብ እምነት ነው፡፡ እንዲያውም ያለማድበስበስ የኢትዮጵያ አገዛዝ ‹‹ሲም ካርድ›› ሕወሓት ነው እስከ ማለት የሄደና በተራ ሰው ደረጃ የሚታመንበት ግንዛቤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ የአንዱን ክልል ብሔራዊ ድርጅት ቦታ ሌላው (ኦሕዴድ) እንዳይተካው መፈራቱ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጭምር የተነሳና እሳቸውም ዋስትና እሰጥበታለሁ ብለው ሙከራ ያደረጉበት ሥጋት ነው፡፡

ይህ የፈለቀው ግን ከተንኮለኛ አዕምሮ አይደለም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የሥልጣን መዋቅርና አውታሮች ከአንድ ፓርቲ (ለዚያውም የክልል ብሔርተኛ ፓርቲ) ወገናዊነት ተላቀው ባለመደራጀታቸውና ጭራሹኑም ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በፓርቲ መቃኘታቸውን ትክክለኛና አስፈላጊ አድርጎ፣ ከመዋቅሮችም ባለፈ የሕዝቦችን ማኅበራዊ ህሊና በአስተሳሰቡ መቆጣጠርን ትግሌና ሥራዬ ብሎ በመያዙ ነው፡፡ የችግሮቻችን አናት የሆነው ችግር ይኸው ነው፡፡ የፓርቲዎች ፖለቲካ ከጠላትነት እንዳይወጣ አድርጎ የቀሰፈው፣ የምርጫ ሜዳዎች ከፓርቲ ጫናና ተፅዕኖ ነፃ እንዳይሆኑና የምርጫ ሒደቶች እውነተኛ የውድድር ነፍስ እንዳይዘራባቸው ያደረገው፣ ምክር ቤቶች ከወረዳ እስከ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ የእኛ አለኝታ ከመባል ይልቅ፣ በኢሕአዴግ ይዞታነት እንዲታዩ ያደረገው፣ በአጠቃላይም ለመንግሥት የተቀባይነት ጉድለት (ጎዶሎነት) ምክንያት የሆነው ይኸው ችግር ነው፡፡ መታረምና መስተካከል ያለበት ይኸው ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ፖለቲካዊ ሰላምና ነፃነት ከልማት ጋር የተገናኙበት ሕይወት ውስጥ የሚያስገባውን መንገድ በመፈለግ ተግባር ውስጥ በተጠመድንበት በዚህ ወቅት፣ ፖለቲካችንና አካሄዳችንን ማሳመር አለብን፡፡ በቁጣ መታወር፣ በጥላቻ መብከንከንና እልህን በግዑዝ ንብረትና በዜጎች ላይ መወጣት በጭራሽ ፖለቲካ አይደለም፡፡ እያሳሳቀ ሥርዓት አልባ ቀውስ ውስጥ ሊከት በሚችል የጋጋታና የውድመት ተቃውሞ ውስጥ መግባትም ፖለቲካ አይደለም፡፡

ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ከአፈና መዳፍ የመፈልቀቅ፤ ዕድሜ የማራዘም ሆነ የመቅጨት ውጤቶች በሁለቱ ወገኖች ድርጊታዊ መስተጋብር የሚወሰኑ መሆናቸውን ምን ጊዜም ቢሆን አለመዘንጋት ነው፡፡ መንግሥት ማነቆ አላልቶ፣ ለአደባባይ ሠልፍ፣ ለሕዝባዊ ስብሰባ፣ ለነፃ ንግግርና መንቀሳቀስ ዕድል ሲሰጥ፣ እንደምንገኝበት ዓይነት አብዮታዊ ሁኔታዎች ተፈጥረው አድራጊ ፈጣሪነት ለጊዜውም ሆነ ለወረት ሕዝብን መፍራት/መሰለል ሲጀምር፣ ወዘተ በመብቱና በነፃነት አላውቅበት ማለት፣ ከዚያም አልፎ ከቁጥጥር በወጣ ግንፍልታ ታውሮ የጥፋት ድርጊት ውስጥ መግባት የገዛ መብትን ማብረርና ማባረር ነው፡፡ በተቃራኒው ኃላፊነት በተሞላበት አኳኃን በመብት መገልገል ያ መብት እንዲሰፋና ሥር እንዲይዝ መሥራት ብልህነት ነው፡፡ የፖለቲካና የፖለቲከኛነት ትንሽ ዕውቀት ከዚህ ይጀምራል፡፡ የሕዝብ አታጋዮችም አዲስ መጦችም ሆኑ ነባሮቹ ከዚህ የበለጠ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑን ማወቅና አረማመዳቸውና ፖለቲካቸውን በዚሁ ልክ ማሳመር አለባቸው፡፡

በተለይ ከዚህ ቀደም ውድመትን፣ ጥቃትን በትግል ዘዴነት ባርከው ለወጣቱ ሰጥተው የነበሩ አመራሮች ጥፋትን ይዞ የሚመጣ የእነሱ ሠልፍ፣ ስብሰባ፣ ጉብኝት፣ ወዘተ ውስጥ ከወዲሁ ካልሠጉና ካልተጠናቀቁ ተከታዮቻቸውንም ከዚህ ማዕዘን ካልገሩ፣ የሻሸመኔው ዓይነት አፄ በጉልበቱነት ሳይጠየቁ መቅረትን ይዞ ላለመደጋገሙ አገር ዋስትና የላትም፡፡ የትኛውም የመንግሥት የአስተዳደር አካባቢ/ዕርከን በሆነ ሥፍራና ጊዜ ሠልፍ እንዲካሄድና አቀባበል እንዲደረግ፣ ወዘተ ዕውቅና ሊሰጥ፣ በዚያው ተግባሩ የተሠላፊውን/የተሰብሳቢውንም ሆነ ከሠልፉ ውጪ የሆኑ ዜጎችን/ሰዎችን ደኅንነት የመጠበቅ ድርሻንም ለራሱ እየሰጠና እየተቀበለ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የዚህ አንድ ሳንቲም ሌላው ገጽታ የተጠቀሰው የአዘጋጆች ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የለውጥና የዴሞክራሲ ትግል ከዚህ በላይ ብዙ ይጠይቃል፡፡ የወጣቶች ትግል ከጥፋት፣ ከግርታና ከጋጋታ ዕርምጃ ጋር እንዲታይ፣ አሻጥረኞች ሊያቀናብሩትና ሊያደርሱት ለሚችሉት ውድመትና ዕርምጃ ሁሉ ማላከኪያ እንዲሆን ማገዛቸው የማይገባቸው፣ የአንድ ሕዝብ/ብሔረሰብ ትግል ከውድመት ጋር መዛመዱ ቀሪው ወይም ሌላው ሕዝብ ያንን ብሔር በሥጋት እንዲመለከት ያደርጋል፣ ይህም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ትግል መጥፎ የወገብ ስብራት ይሆናል ብሎ ኃላፊነት የማይቀበሉ አመራሮች ‹‹ተደመርን› ባይሉ ይሻላቸዋል እላለሁ፡፡    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...