Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ 2.2 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እያደረግን ነው››

አቶ ሐይድሩስ ሐሰን፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአቅርቦትና የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለችግር የሚዳረጉ ወገኖችን ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ በግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የሰው እጅ ማየታቸው ግን እንግዳ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በነሐሴ 2007 ዓ.ም. በኤልኒኖ ምክንያት የአየር ንብረት በመዛባቱ 4.5 ሚሊዮን ወገኖች ለምግብ ዋስትና ችግር ተዳርገው ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ የኤልኒኖ ክስተት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የዝናብ እጥረት እንዲያጋጥም በማድረጉ፣ በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. የተረጂዎች ቁጥር 10.2 ሚሊዮን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተፈጥሮ አደጋ የተረጂዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ፈታኝ ጉዳይ ነበር፡፡ በተለይ ለዕርዳታ አቅርቦት የሚሆን ሀብት ማሰባሰብ፣ የመጋዘን አቅርቦትና የተሽከርካሪ አቅርቦት ከወደብ አቅም ማነስ አንፃርም ፈተና እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ለአገሪቱም ሆነ ለብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በድርቅ ምክንያት ለችግር ከተዳረጉ ወገኖች ይልቅ፣ በግጭት ምክንያት እየተፈናቀሉ የሚገኙ ወገኖች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ከመድረሱም በላይ፣ ዕርዳታ ለማቅረብም ከተፈጥሮ አደጋ ይልቅ ፈታኝ ክስተት ሆኗል፡፡ በግጭት ምክንያት እየተፈናቀሉ የሚገኙ ወገኖች ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ የሚገኝ ሲሆን፣ ችግሩ ገፍቶ መጥቶ ዕርዳታ ፈላጊ ተፈናቃዮች አዲስ አበባ ንፋስ ስልክ አካባቢ የሚገኘውን የኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት እስከ ማጥለቅለቅ ደርሰዋል፡፡ ባሉበት መርጋት ሳይችሉ ይልቁኑም ወደ ኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት የሚመጡ የግጭት ተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር ያሠጋው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ተፈናቃዮች ወደ ኮሚሽኑ መምጣት እንደሌለባቸው ጥሪ አስተላልፏል፡፡ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአቅርቦትና የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ሐይድሩስ ሐሰን፣ በወቅታዊ የኮሚሽኑ ሥራዎች ላይ ከጋዜጠኞች ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ከሪፖርተር ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ውድነህ ዘነበ አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ለሚፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚሰጥበት አሠራር ምንድነው? ብዙም ባልተለመደ መንገድ ወደ ኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት እየመጡ ያሉ ድጋፍ ፈላጊ ወገኖች ስላሉ እዚህ ላይ ኮሚሽኑ ያለው አቋም ምንድነው?

አቶ ሐይድሩስ፡-  ከድርቅ አደጋ ጋር ባለው አሠራራችን በመጀመርያ የዳሰሳ ጥናት ይደረጋል፡፡ በጥናቱ የተጎጂዎች ቁጥር ከተለየ በኋላ ችግሩ ካለባቸው ክልሎች ጋር የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል፡፡ ተጎጂዎቹ ባሉበት ምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዲደሳቸው ይደረጋል፡፡ በግጭት ሲሆን ደግሞ እንደሚታወቀው ግጭት በደረሰበት አካባቢ ክልሉ በሚያቀርበው ሪፖርት፣ በዚያ ሪፖርት ላይ ተመሥርተን የራሳችንን የቴክኒክ ኮሚቴ አሰማርተን የዳሰሳ ጥናት እናካሂዳለን፡፡ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከተረዳን በኋላ የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ይህን እንግዲህ ክልሎች በራሳቸው የሚሸፍኑ ከሆነ ራሳቸው ይሸፍናሉ፡፡ ከአቅማቸው በላይ ከሆነ እንደ ፌዴራል ተቋም ጣልቃ በመግባት ከክልሎች አቅም በላይ የሆነውን ድጋፍ እናደርጋለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው በተለይ በሶማሌ ክልል በተከሰተው ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋና በሐረር ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑን እየታየ ያለው ደግሞ ቀጥታ ከተፈናቀሉበት ቦታ ተነስተው፣ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ወደ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት እየመጡ ነው፡፡ ይኼ በእኛ አሠራር ተቀባይነት የለውም፡፡ በእኛ አሠራር የተፈናቀሉ ወገኖች ክልሉ የሚያስተናግድ ከሆነ ያስተናግዳል፡፡ ከክልሉ አቅም በላይ ከሆነ ክልሉ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለት አሠራሮች አሉን፡፡ አንደኛ መጠለያ ጣቢያ ተዘጋጅቶላቸው ወደመጡበት እስከሚመለሱ ድረስ የተለያዩ ድጋፎ ይደረጋሉ፡፡ አሁን ግን ከጅግጅጋ፣ ከቀብሪደሃር፣ ከጎዴ፣ ከደገብሃርና ከመሳሰሉት አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሐረር ሠፍረዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ አዲስ አበባ በመምጣት ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ከዚያም ወደ እኛ መጥተዋል፡፡

ወደ እኛ ከመጡ በኋላ አሠራራችንን ገልጸንላቸዋል፡፡ ወደመጡበት እንዲመለሱ ነው፡፡ ድጎማ እየተደረገላቸው ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ አላቆሙም፡፡ አሁንም በቀጥታ ወደ እኛ እየመጡ ነው፡፡ እኛ ባሉበት በፍጥነት እንደርሳለን፡፡ ለእኛ ሪፖርት ቢቀርብ ቢበዛ በ72 ሰዓት፣ ከዚያ በ48 ሰዓት፣ ከዚያ በ24 ሰዓት፣ ከዚያ በ12 ሰዓት፣ ከዚያ በሦስት ሰዓት ውስጥ እናደርሳለን፡፡ ይህ ስታንዳርዳችን ነው፡፡ እዚህ የሚያስመጣ ነገር የለም፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የውኃ ሙላት፣ የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ አደጋ፣ አውሎ ንፋስና ሌሎች አደጋዎችም ቢሆኑ እዚያው ሄደን ነው የምንደግፈው፡፡ ስለዚህ ወደ ኮሚሽኑ መምጣት አያስፈልግም፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ እየደረሱ ላሉ ችግሮች በፍጥነት እየደረሳችሁ አይደለም፡፡ በሶማሌ ክልል ችግር ሲያጋጥም በፍጥነት እንዳልደረሳችሁ ይነገራል፡፡ ስለዚህ ድጋፍ ፈላጊ ዜጎች ወደ ኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ቢመጡ ምን ያስደንቃል? ድጋፍ ፈላጊ ዜጎች ወደ እናንተ ቢመጡ የሚፈጠረው ችግር ምንድነው?

አቶ ሐይድሩስ፡- በሶማሌ ክልል በፍጥነት አልደረሳችሁም የሚለውን ነገር ሁላችሁም እንደምትረዱት የአገራችን የቆዳ ስፋት ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ደግሞ ያለን የሎጂስቲክስ ምልልሳችን ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን በፍጥነት አልደረሳችሁም የሚለው ጉዳይ ለእኔ አዲስ ነው፡፡ እንደ አገር፣ እንደ ምሥራቅ አፍሪካና እንደ አኅጉር ጥሩ ተምሳሌት መሆናችን ነው የሚነገረው፡፡ ልምድም ከእኛ እየተወሰደ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል ቶሎ አልደረሳችሁም ለተባለው ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በ2009 ዓ.ም.፣ በ2010 ዓ.ም. በሔሊኮፕተር፣ አሁን በተከሰተው ችግር ደግሞ በአንቶኖቭ ነው የደረስነው፡፡ ቀብሪደሃርና ጎዴ የደረስነው በአንቶኖቭ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ቶሎ አልደረሱም ለሚባለው ጉዳይ ለምሳሌ ጌዴኦ ዞን ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ ሶማሌ ክልል ደግሞ ቀላፎና ሙስታሂል አካባቢ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ ባሉን ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ እነዚህ ሥፍራዎች ለመድረስ የሚወስድብን ጊዜ ካልሆነ በስተቀር፣ ትልቁ ተደራሽነታችን 72 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ የለም፡፡    

ሪፖርተር፡- ከተፈጥሮ አደጋ ይልቅ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ለመድረስ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ፍጥነቱን ለማሻሻል የምትወስዷቸው ዕርምጃዎች ይኖሩ ይሆን?

አቶ ሐይድሩስ፡- ግጭት በመሠረቱ ከሌሎች አደጋዎች በተለየ ውስብስ ባህርያት አሉት፡፡ የተፈጥሮ አደጋን ብትወስዱ በ2008 ዓ.ም. 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ ዋስትና ችግር ተዳርጎብን ነበር፡፡ አሁን በግጭት ምክንያት 2.2 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሎ ለተመሳሳይ ችግር ተዳርጎብናል፡፡ 10.2 ሚሊዮን ከ2.2 ሚሊዮን በታች ነበር ፈታኝነቱ፡፡ ምክንያቱም በኤልኒኖ ክስተት ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች ዕርዳታ በምናደርስበት ወቅት የመንገድ ላይ ችግር አልነበረም፡፡ የፀጥታ ችግር አልነበረም፡፡ የዕርዳታ ምግብና ቁሳቁስ በሰላም ሲደርስ ነበር፡፡

በግጭት ጊዜ ግን በመንገድ ላይ የደኅንነት ጉዳይ አለ፡፡ አሽከርከሪዎች የተወሰነ ቦታ ይደርሱና አጃቢ ኃይል ይፈልጋሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር መዘግየት የለም፡፡ መቶ በመቶ የተሟላ ነው ባይባልም፣ በተለያዩ ችግሮች ለምሳሌ ድልድይ ሲሰበርና የመሳሰሉት ካልሆኑ በስተቀር ተደራሽ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- በሶማሌ ክልል ያጋጠመው ግጭት ከረር ያለ ነው፡፡ ዜጎች ከዚያ ወጥተው ወደ ኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት የመጡት ለዕለታዊ ድጋፍ ብቻም ሳይሆን በዘለቄታ በሰላማዊ ቦታ መሥፈር ፈልገውም ይሆናል፡፡ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተከሰተው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች፣ በተለይ በኦሮሚያ በኩል በ11 የዞን ከተሞች በዘላቂነት እንዲሰፍሩ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን አልተመለከታችሁትም?

አቶ ሐይድሩስ፡- አንደኛው የግጭቱ ክስተት ባህርይ የተለየ ነው፡፡ ሰዎች ለሕይወታቸው ስለሚሠጉ ተረጋግተው አይቀመጡም፡፡ ሁለተኛ በተፈጠረው ግጭት ብዙ አቁሳይ የሆኑ ክስተቶች ይደረስባቸዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭትም ሆነ አሁን በተከሰተው ግጭት፣ በእኛ በኩል ያደረግነው ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመነጋገር የመከላከያ ሠራዊት ሥፍራው እንዲደርስና ችግሩን እንዲቆጣጠር፣ ይህም ቢሆን ግጭት ባለበት ቦታ የነበሩ ሰዎች ችግር የለም ተረጋግታችሁ ተቀመጡ ቢባልም ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጉዳት አንፃር ለመረጋጋት ይቸገራሉ፡፡

ከዚህ አንፃር እንደ መንግሥት እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ችግሩ ከደረሰበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተወስደው ተረጋግተው እንዲቀመጡ እየተደረገ ነው፡፡ ከክልሉ መንግሥት፣ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመነጋገር ሌሎች ዜጎች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት እየተደረገ ነው፡፡ አረጋግቶ ከማስቀመጥ አንፃር ከመሀል አገር ወደ ሶማሌ ክልል የሄዱ ወገኖች ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ፣ ከባህሉና ከሚፈጠሩ ችግሮች በመነሳት አመቺ ስላልሆነ ሰዎቹን ተረጋጉ ብለናቸው እንኳ ተረጋግተው የመቀመጥ ስሜት አይታይባቸውም፡፡

ስለዚህ ወዴት ይመጣሉ? ወደ ከተሞች በተለይም ወደ መሀል አገር መምጣት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እንደ መንግሥት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በተለይ የመከላከያ ሠራዊታችን ባለበት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ እየተሠራ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ከኦሮሚያ አንፃር ያነሳኸው ትክክል ነው፡፡ በመሠረቱ ወሳኞቹ ክልሎች ናቸው፡፡ አንድ ክልል ተፈናቃዩን በራሱ ከወሰደ በኋላ በተለያዩ መንገዶች የማስፈር ሥልጣን የክልሉ ነው፡፡ ክልሎች ሉዓላዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ እኛ የድጋፍ ሥራ እንሠራለን፡፡

የኦሮሚያ ክልል በ11 ዞኖች ተፈናቃዮቹን አስፍሯል፡፡ እኛ ደግሞ በየወሩ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ክልሉ በራሱ ጥረት ከከተሞችና ከኅብረተሰብ ጋር ሆኖ ቤቶች እንዲሠሩላቸው አደረገ፡፡ እኛ ደግሞ ጊዜያዊ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ወደ ኮሚሽኑ ዋና ጽሕፈት ቤት መምጣት አይጠበቅም፡፡ ክልሉ በዘላቂነት ሊያሠፍር ይችላል፡፡ እኛ እስኪቋቋሙ እንደግፋለን፡፡    

ሪፖርተር፡- ከተፈጥሮ አደጋ ውጪ በግጭት እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከኮሚሽኑ ጋር የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተፈናቃዮቹ ቁጥር 2.8 ሚሊዮን አድርሰውታል፡፡ የእርስዎ መሥሪያ ቤት ደግሞ 2.2 ሚሊዮን እያለ ነው፡፡ የቁጥር ለውጥ እንዴት መጣ?

አቶ ሐይድሩስ፡- በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ ዞን መጀመርያ የነበረው 280 ሺሕ፣ ቀጥሎ 500 ሺሕ ሕዝብ ተፈናቅሏል እየተባለ እያለ የአካባቢውን ፀጥታ የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ ቡድን ተዋቅሮ አካባቢው ላይ ሲደርስ፣ ተደብቀው የቆዩ ሰዎች እየወጡ ቁጥሩ ወደ 900 ሺሕ ደረሰ፡፡ ይህንን እኛ ብቻ ሳይሆን ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ ስለምንሠራ ቀድመው መረጃ የመልቀቅ ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ቢሆን ሥራው በዋናነት በመንግሥት ስለሚመራ አሁን የተፈናቃዮች ቁጥር ግን 2.2 ሚሊዮን ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ 615,381 ተፈናቃዮች ሰባት ዙር ድጋፍ አድርገናል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ 241,941 ተፈናቃዮች፣ በጌዴኦ የመመለስ አዝማሚያ ስላለ 800 ሺሕ ተፈናቃዮች፣ ከዚህ ውጪ አሁን ከጂቡቲ ከ5,000 በላይ ወገኖች ተፈናቅለው መጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሲደመሩ ቁጥራቸው 2.2 ሚሊዮን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ለተረጂዎች ድጋፍ ለማድረግ ያላችሁ አቅም ምን ያህል ነው?

አቶ ሐይድሩስ፡- በእኛ በኩል ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ቁጥሮች ላይ ተመሥርተን ነው ከመንግሥት በጀት የምንጠይቀው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ከውጭ ተገዝቶ እንዲገባ ከተደረገው የምግብ እህል ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ወደ አገር ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ግዥ የተፈጸመው አራት ሚሊዮን ኩንታል ነው፡፡ ከተለያዩ የአገር ውስጥ አምራቾችም ግዥ እየተፈጸመ ነው፡፡ ማዕካለዊ መጋዘኖቻችን ለዚህ ዝግጁ ናቸው፡፡ ሌላው ቁሳቁስ ነው፡፡ ቁሳቁስን በተመለከተ በጀት ተመድቦ ዕቅድ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ለስድስት ወራት የሚሆን እስከ ሚቀጥለው ታኅሳስ ወር ድረስ የትኛውም አደጋ ቢከሰት ዕቅድ ተዘጋጅቶ የሎጂስቲክስ ጉዳይ ዝግጁ ነው፡፡ ሁሉም መጋዘኖች በእህል የተሞሉ ናቸው፡፡ የሚመጣውንም ለመያዝ እየተጠባበቁ የሚገኙ መጋዘኖች አሉ፡፡       

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል›› አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ ባንክ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ብርቱ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጥ ተወስኖ፣ ከዚያም ከለውጡ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከወለድ...