Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የለውጥ ጣር!

ከወራት በፊት የኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ አሳሳቢና አብዛኛውን ሕዝብ የተስፋ ዕጦት ውስጥ የከተተ እንደነበር የሁላችን ትዝታ ነው፡፡ የነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት የአገሪቱን አቅጣጫ ለመገመት ያላስቻለ ስለነበር፣ ዜጎች በጭንቀት ተወጥረው እንዲሰነብቱ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህም በዜጎች ኑሮና ሕይወት ላይ ብቻም ሳይሆን፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይም ጠባሳውን አሳርፏል፡፡

ይሁን እንጂ የተፈራው ሳይሆንና ሳይደርስ ያልተጠበቀው ሆነና አገርና ሕዝብ ከሥጋት ውጥረት ተንፈስ ያሉበት ድባብ ተፈጠረ፡፡ የዜጎችን ጭንቀት የሚያቃልል ‹‹መደመር››ን መርህ ያደረገ ሐሳብ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊት አውራሪነት ሲቀነቀን፣ ቀድሞ ያንዣበበው ሥጋታቸውን ፍቆታል ማለት ይቻላል፡፡ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ተሰበከ፡፡ ዜጎች የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ተስፋ በማድረግ ከጨለመው ይልቅ ብሩህ ተስፋ ሰንቀው መራመድ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በእርግጥም በጥቂት ወራት ውስጥ የማይጠበቁና የማይታሰቡ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይሁንታ የተቸረው የለውጥ መንገድ ስለመጀመሩ ብዙኃን መስክረዋል፡፡

 አብዛኛው ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለነገዋ ኢትዮጵያ የሰጡትን ተስፋ አምኖ በመቀበል ዛሬስ ምን ያስደምጡን፣ ምንስ ያሳዩን ይሆን? እስከማለት መደረሱም፣ ኢትዮጵያዊያን የመሪዎቻቸውን ንግግር የጓጉበት አዲስ ታሪክ ክስተት ሆኖ አብዛኛውም ሕዝብ ከለውጡ ጋር አብሮ እንዲከንፍ ያስገደደውን ስሜት የፈጠረ መግነጢስ ነው፡፡

ይሁንና በመልካም አስተሳሰብና በአገር ፍቅር ስሜት የተጀመረው ለውጥ ግን አልፎ አልፎ በሚታዩ ዘግናኝ ተግባራትና አደናቃፊ ግጭቶች መደብዘዙ እየታ ነው፡፡ በደስታ የሞላውን መንፈስ የሚበርዝ ድርጊት እዚህም እዚያም መታየቱ በርካቶችን እያሳዘነ ነው፡፡

ፍቅርና አንድነት በሚሰበክበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታየው ግጭትና በስሜት ግብታዊነት የሚፈጸመው ተግባር በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ማየት ያማል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ሰበብ የሆኑ ግጭቶች በአስቸኳይ መቆም እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ የሕፃናት ስቃይና ሞት፣ የእናቶች፣ አረጋውያንና የደካሞች መንከራተት ከግፍም በላይ ነውና መንግሥትም ሕዝብም ሊያተኩሩበት የሚገባ የአገር የውርደት ማቅ ነው፡፡   

መንግሥት ሁኔታውን በማጤን ቆንጣጭ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባው የሚያመላክቱ የሕዝብ አስተያየቶች ጠንክረው መደመጣቸውን ልብ ይሏል፡፡ አንዳንዱ እስከ ደም መፋሰስና የሃይማኖት ተቋማትን እስከ ማውደም መድረሱ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነትም ድርጊቱን አምኖ ለመቀበል ይከብዳል፡፡ ህሊናን ያኮማትራል፣ ልብ ይሰብራል፡፡ ዜጎች በስንት ድካም ያፈሩት ንብረትና ጥሪት ዓይናቸው እያየ ሲወድም፣ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ የለማዳ ሰው መሰል አውሬዎችን ድርጊት በማውገዝ ብቻ መታቀቡ ውሎ አድሮ የሚያስከፍለው አደጋ ከዚህም የከፋ ላለመሆኑ መተማመኛ ማግኘት አንችልም፡፡ ጥፋት ከመከሰቱ በፊት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ቢታመንም፣ ከግጭቱ በኋላም የሚታየው የማስተካከያና የማረቂያ ዕርምጃ ፈጣን አለመሆኑ ለምን? ማሰኘቱ ተገቢ ነው፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተከሰተው ጥፋት ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ከወደ ሻሸመኔ የሰማነው ድርጊት፣ በደቡብና በሌሎች አካባቢዎችም የተፈጸሙት የግፍ ተግባራት የእኩዮች መገለጫዎች ቢሆኑም፣ በጥቂቶች የተነሳ ብዙኃኑ ሰለባ መሆናችን ግን አሳዛኝ ነው፡፡ በርካታ ሠራተኞች የሚያስተዳድሩ፣ ለመንግሥት ታክስ የሚከፍሉ ፋብሪዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በጠራራ ፀሐይ ወድመዋል፡፡ በርካቶች በአንድ ጀንበር ወደ ተረጂነትና ጥገኝነት ደረጃ እንዲወርዱ ተገደዋል፡፡ ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ጫናም ከፍተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእርስ በርስ ግጭት ሰበብ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸውንና መንገላታታቸውን ዓለም ሁሉ ተቀባብሎታል፡፡

እዚህም እዚያ የተነሱ ግጭቶችና ያስከተሉት አደጋ በቶሎ እንደሚያገግም ተስፋ የተጣለበት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መልሶ እንዲሸማቀቅ አስገድዶታል፡፡ ደጋግመን እንደምንለው፣ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚበረግገው የአገራችን ኢኮኖሚ ከቅርብ ጊዜ በሚታዩ ግጭቶች ሳቢያ ከውጭ የሚወጣውን ኢንቨስትመትም ሊያስቆመው ይችላል፡፡

የእርስ በርስ ግጭትና ሁከት መበራከቱ ከምንም በላይ በኢትዮጵያዊያን ሕይወትና ህልውና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንዳለ ሆኖ፣ ወደ አገሪቱ በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያለውን የውጭ ባለሀብት በዚያው እንዲቀር፣ ኢትዮጵያንም በክፉ እንዲያነሳት ማድረጉ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለው በመምጣት ኢንቨስት ያደረጉትም ቢሆኑ የአገሪቱ ሕዝብ እርስ በርሱ የሚባላ ነው የሚል ስሞታ በማስተጋባት ቀድሞም ዳር ዳር የሚሉትን የውጭ ኢንቨስተሮች ይበልጡን እንዲሸሹ ሊያደርግ የሚችል ትልቅ አደጋ ተደቅኖብናል፡፡ ጉዳቱ ሰፊ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለውጡ ያመጣውን ዕድል ተጠቅመው ወደ አገራቸው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንም እንደልባቸው ተዘዋውረው አገር እንዳያዩ ሊያስገድዳቸው፣ ጭርሱኑ ሳይመጡ ሊያስቀራቸው ይችላል፡፡ በመልካም የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዘመን ተሻጋሪ እንዳይሆን እያሰናከሉ ያሉት እኩይ ድርጊቶችን በመምከርና በመገሰጽ ብቻም ሳይሆን፣ ተበዳይም ፍትሕ እንዲያገኝ ገደብ ማበጀቱ ግድ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉትን አስፈሪና አሳፋሪ ድርጊቶች ለማስቆም ሕጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መንግሥት ግዴታ አለበት፡፡

ሕዝብ ዳር ከዳር የደገፈውን ለውጥ ለመቀበል ፈራ ተባ የሚሉ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ ሹመኞች ላይ የሚታየውም ዳተኝነት ለችግሩ መፈጠር ሚናውን ተጫውቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ ተራ የሌብነት ድርጊቶች መባባሳቸው እየታየ ነው፡፡ ይህንን በአግባቡ ለመከላከል እየተሠራ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ደግመን ደጋግመን ማንሳት፣ ማስተጋባት ይኖርብናል፡፡

ችግሮች በፍትሕም በአስተዳደርም በፖለቲካውም ዕልባት ሲያገኙ፣ የተዳከመውን ኢኮኖሚ መታደግ የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ጤናማ ገበያ እንዲፈጠርም ዕድል ይሰጣል፡፡ ለችግሮች ምክንያታዊ መሆን ያሻል፡፡ ለግጭቶች መፈጠር የሕግ አስከባሪ አካላት መዘናጋት አሊያም መዝረክረክ፣ አመራር መስጠት የሚጠበቅባቸው ኃላፊዎች ቸልተኝነት አስተዋጽኦም እንዳለበት መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡

በአብዛኛዎቹ ተቋማት ውስጥ ከለውጡ ጋር ያልተሰማሙ አመለካከቶች መኖራቸው፣ በቀድሞ አመለካከትና አሠራር የተቃኙ አመራሮች ምንቸገረኝ የማለታቸው፣ አያገባኝም የሉበትም ማብዛታቸው፣ ሲብስም ሆን ብለው ግጭቶችን ማነሳሳታቸው ለሰላም መደፍረስ አስተዋጽኦ እንዳለው ዕሙን ነው፡፡ የተፈጠረውን መልካም ድባብ ከእስካሁኑም ለከፋ አደጋ እንዳያጋልጡ መንግሥት ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ሰዎችም በአንድነትና በአብሮ ነዋሪነታቸው እንጂ በጥቅም ተደልለውና በፖለቲካ ተደልድለው የገዛ ጎረቤታቸውንና ዘመዳቸውን መግደላቸውም በሰውም በፈጣሪም ሕግ የበደል በደል ነውና ይህን በሰከነ ህሊና ማየቱ ይበጀናል፡፡ ከመንግሥት በላይ ኅብረተሰቡ በገዛ ሰላሙና ጉርብትና ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለውጡ እንዲመጣ የደከመ ሕዝብ፣ ለውጡን ሊያደናቅፍ ከሚችል ስሜታዊነትና ግብተኝነት መቆጠብ፣ የሕግ የበላይነትን በማወቅ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ እንጂ፣ ሕይወት እስከማጥፋት መድረሱ ሠርቶ ማበላሸት እንዳይሆን ሁሉም የየራሱን በጎ ተግባር ይፈጽም፡፡

የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ታላላቆች፣ እናት አባቶች ባሉበት፣ ሽበት በሚከበርበት አገር፣ ከእንስሳ የማይጠበቅ ዘግናኝ ድርጊት በፈጣሪ አምሳል ላይ ሲፈጸም መመልከት የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ማንነት፣ ከየት የተማሩትና የወረሱት ተግባር ነው ያሰኛልና አገር ወዳዶች ሆይ ልጆቻችሁን፣ ደመ ሞቃቶቹን አርቁ፡፡ ገስጹ፡፡ ቆንጥጡ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት