ባለፉት ሦስት ዓመታት በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ሰፋፊ ሁከቶች፣ ተቃውሞዎችና አመፆች በነበሩበት ጊዜ የደቡብ ክልል ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር በአብዛኛው ሰላማዊ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በወቅቱ በተለይ በኮንሶና በሰገን ሕዝቦች ዞኖች አካባቢ ከታዩ ግጭቶች በላይ ጎልቶ የወጣ ግጭት በክልሉ አልተስተዋለም ነበር፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች አካባቢዎች ሲታዩ የቆዩ አመፆችና ተቃውሞዎች ሲረግቡና ወደ መረጋጋት ሲመለሱ፣ የደቡብ ክልል ተረኛ የሆነ ይመስላል፡፡ በክልሉ ከሐዋሳ እስከ ወላይታ፣ ከጉራጌ እስከ ስልጤ፣ ካፋና ሸካ ዞኖች የዘለቁ ግጭቶች ተስተውለዋል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል፡፡
በሰኔ ወር በሐዋሳ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት ከአሥር በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ ዘጠኝ ሰዎች ከባድ፣ ከ80 በላይ ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ከ3,000 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡ በተመሳሳይ በሐዋሳ የወላይታ ተወላጆች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው በማለት ተቃውሞ በወጡ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ሁከት ሦስት ሰዎች ሲሞቱ፣ ከአሥር በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በርካታ ንብረቶችም ተቃጥለዋል፣ ወድመዋል፡፡
በሌላ ወገን በደቡብ ኢትዮጵያ የክልሉ ዞኖች፣ በተለይም በካፋና በሸካ ዞኖች ግጭቶች የተስተዋሉ ሲሆን፣ የሰዎችን ሕይወት እስከ ማጥፋት፣ ንብረቶችንና የኢንቨስትመን ፕሮጀክቶችን ማውደምና እስከ ማቃጠል የደረሱ ግጭቶችም ተስተውለዋል፡፡
አሁን ደግሞ ካለፈው ሰሞን ጀምሮ እየተስተዋለ ያለው ግጭት በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ነው፡፡ በዚህ ግጭት ሦስት ሰዎች ሲሞቱ፣ በርካታ ንብረቶች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማትና የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡
በአካባቢው የተከሰቱ ግጭቶችንና በስፋት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎትና ሌሎች ጥያቄዎችን በቅርበት ለመስማት የክልሉ ገዥ ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንበርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ በደቡብ ምዕራብ ሦስት ዞኖች በመዘዋወወር ሕዝቡን አወያይተዋል፡፡ ወ/ሮ ሙፈሪያት ባወያዩዋቸው የደቡብ ምዕራብ ሦስት ዞኖች ማለትም ካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ የተለያዩ ጥያቄዎችን ተነስተዋል፡፡ በተለይ የአስተዳዳሪዎች ብቃት ጥያቄና የአድልዎ አሠራሮች፣ የመንግሥት አገልግሎት አቅርቦትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ በሦስቱም ዞኖች በሸካ ቴፒ፣ በካፋ ቦንጋና በቤንች ማጂ ዞን ሚዛን አማን ከተሞች በተደረጉ ውይይቶች ከተሳታፊዎች የክልልነት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪያት ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ወጣቱ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ማንም አልወከልንም የሚል ጥያቄ ያነሳ ሲሆን፣ በተለይ ቴፒ ከተማ ከአዳራሽ ውጪ በመሰብሰብ ድምፁን ሲያሰማ የነበር፡፡ ከአዳራሹ ውጪ በተሰበሰቡ ወጣቶች መሀል በመግባት ወ/ሮ ሙፈሪያት ጥያቄያቸውን ሲያዳምጡም ታይተዋል፡፡
በየቴፒ ከተማ ግጭት የተከሰተው አፈ ጉባዔዋ በአካባቢው በመገኘት ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. አወያይተው ከተመለሱ በኋላ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ የተናገሩ ግለሰቦች ሰድበውናል በሚሉ ቡድኖች ቅራኔ የተጀመረ እንደሆነም ከአካባቢው ሪፖርተር ያናገራቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለቀናት በአካባቢው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ያልነበረ ሲሆን፣ ከከተማው ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ተዘግተውም ነበር፡፡
በከተማውም የመከላከያ ኃይል በመግባት ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. መንገዶችን የማስከፈትና ሕዝቡን የማወያየት ተግባራት እንደተከናወኑ፣ በሥፍራው ሰላም ለማስከበር የገባው ሬጅመንት የ53ኛ ሞተራይዝድ አዛዥ ኮሎኔል ፀጋዬ አብርሃ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ኃይሉም መንገዶችን እንዳስከፈተና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር እየጣረ እንደነበር አዛዡ አስታውቀዋል፡፡
ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ያደረጉት የመከላከያ ኃይል አባላት ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በፖለቲካ አመራሩ የሚመለሱ እንደሆኑ፣ በዋናነትም የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ተያያዥ ጥያቄዎች እንደሆኑ በመግለጽ ተሰድበናል በሚል መነሻ የመጣ ግጭት እንደሆነ አዛዡ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ መድረኮች ከልማት፣ ከመሠረተ ልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከመንግሥታዊ አገልግሎቶች ጎን ለጎን ግጭቶች በተከሰቱባቸው ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
ካሁን ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግጭት ተከስቶባቸው ባወያዩዋቸው የሲዳማ፣ የወላይታና የጉራጌና የቀቤና ማኅበረሰብ ተወካዮች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የክልልነት ጥያቄ ነበር፡፡ በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ ከተሞች የተዘጋጁ ሦስት የምክክር መድረኮች የክልልነት ጥያቄዎች ቀርበውባቸዋል፡፡
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳው ውይይት በሰጡት ምላሽ ለምን የክልል ጥያቄ እንዳስፈለገ የክልሉ ነዋሪዎች በሁሉም ደረጃ እንዲወያዩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ደረጃም ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀው ነበር፡፡
በወቅቱ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) በወላይታ በተደረገው ውይይት ላይ የክልልነት ጥያቄ እንደተነሳ በማውሳት፣ ‹‹የወላይታ ሕዝብ እንኳን ክልል ቀርቶ አገር መሆን እንደሚችል አምናለሁ፡፡ በትክክል ሕዝቡ የሚፈልገው ከሆነ ተወያይተን ጥያቄውን ለክልል እናቀርባለን፤›› ብለው ነበር፡፡
በወልቂጤው መድረክ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎቹ ሕገ መንግሥታዊ አግባብ ተከትለውና ሕዝቡን በማሳተፍ እንዲቀርቡ አስታውቀው ነበር፡፡
ይህ ጥያቄ በተለይ በሲዳማ ክልል የቆየ ቢሆንም፣ በፓርቲው መዋቅር ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መፍትሔ እየተሰጠው ሲንከባለል የመጣ እንደሆነ የሚገልጹት የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰርና የፌዴራሊዝም ጥናት ባለሙያው አስናቀ ከፋለ (ዶ/ር)፣ በፊት እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች በፓርቲ አሠራር የሚታዩ ነበሩ ይላሉ፡፡ ነገር ግን የሲዳማ ዞን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄውን ማፅደቁ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ዓርብ ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የደቡብ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከትና የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በተወያየባቸውና ውሳኔ ባስተላለፈባቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ‹‹ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ስለሆነ ለምን ተነሳ ማለት አይቻልም፤›› ብለው፣ በተለይ የሲዳማ ዞን ያፀደቀው የክልልነት ጥያቄም ሆነ ሌሎች ገና ያልበሰሉና በሒደት ላይ ያሉ በመሆናቸው ብዙ ሊባልባቸው እንደማይቻል ሪፖርተር ላነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በሌሎቹ አካባቢዎች የታየው ጥያቄ የጥቂት አካላት መሆኑንና ወካይ ነው ለማለት እንደሚያስቸግር አክለዋል፡፡ እሳቸው ባወያዩዋቸው አካባቢዎች ከዚህ ይልቅ የአገልግሎት፣ የአመራርና የአገልግሎት ጥያቄዎች እንጂ ክልልነት የተሳታፊዎች ጥያቄ እንዳልሆነ መረዳት መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ዋነኛው ጥያቄ የመሠረተ ልማት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና የመልካም አስተዳደር ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ለማንሳት ይጠቅማሉ፡፡ ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ ሁሉንም ጥያቄዎች አንስተን ማስመለስ እንችላለን የሚሉ ምልከታዎች አሉ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ አፈ ጉባዔዋ ገለጻም፣ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እንዲቻል አገልግሎቶችን ለወረዳና ለዞን ማዕከላት ለማቅረብ በክልሉ አዲስ አደረጃጀት እንደሚኖር ጠቁመው፣ የፀጥታ አካላትን የማጠናከር ሥራም እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም አመራሮች እየተተኩ እንደሆነም ገልጸው፣ እስካሁንም አመራሮች በተተኩባቸው አካባቢዎች ለውጦች መታየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ራስን በራስ ማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደሆነ የሚስማሙት የፌዴራሊዝም ባለሙያው አስናቀ (ዶ/ር)፣ በአገር ደረጃ ያሉት ዘጠኝ ክልሎች አነሱ ከተባለ የትኛው ክልል ይሁን የሚለው በጥናት ላይ ተመርኩዞ በቆዳ ስፋትና በተያያዥ መመዘኛዎች ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን ይኼንን መተግበር አሁን ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ላይ ተጨማሪ አለመረጋጋት አይፈጥምርም ወይ?›› የሚለው ሊታሰብበት ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡
እንደ እሳቸው ምልከታ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 መሠረት በማንነት ላይ የተመሠረተ የክልል ምሥረታ ስለሚፈቀድና መብትም ስለሆነ፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በየትኛውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 አራት ንዑስ አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሦስት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስለመመሥረት መብት የተደነገጉ ናቸው፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሁለት የተዘረዘሩት ዘጠኝ ‹‹ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፤›› የሚል ሲሆን፣ ንዑስ አንቀጽ ሦስት ደግሞ ይህ መብት ሥራ ላይ የሚውልባቸውን ሒደቶች ያትታል፡፡
በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥቱ፣ ‹‹የማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ሥራ ላይ የሚውለው የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ፣ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፣ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ፣ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣ የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብና በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው፤›› ይላል፡፡
ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር መታየት አለባቸው ሲሉም አስናቀ (ዶ/ር) ያሳስባሉ፡፡ አዲስ ክልል ሲፈጠር የፌዴራል ድጎማ ይጨምራል፡፡ የክልል ካቢኔ ማደራጀትና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች ስለሚፈጠሩ እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚለው ሁኔታ ከአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅም አንፃር መታየት አለበትም ይላሉ፡፡
‹‹ይህ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል፤›› ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡ ‹‹አሁን ያለውን የመንግሥት መዋቅር መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ እንኳን አለ ወይ ብሎ ማጤን ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች የውክልና፣ የአስተዳደርና ፓርቲው ተዳክሟል ከሚሉ እሳቤዎች የሚመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው እንደሚገምቱ፣ ባለፉት 27 ዓመታት በፓርቲው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሰፍኖ የቆየ ስለሆነ አሁን ሲነሱ ግልጽ ውይይቶችን ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
‹‹ይህ የፖለቲካ ጥያቄ ስለሆነ ለምን ተጠየቀ ማለት አይቻልም፡፡ የሚያስፈልገው መወያየት ነው፡፡ ጥቅምና ጉዳቱን ምንድነው የሚል ውይይት ማድረግ ነው፡፡ የግድ የተነሳ ጥያቄ ሁሉ መመለስ አለበት ማለት ግን አይደለም፤›› ሲሉም ያስገለዝባሉ፡፡
አንድ የፌዴራል መንግሥት መዋቅር ባለበት ይቀጥላል ማለት ሳይሆን፣ የጊዜውን ሁኔታና አስፈላጊነት በማየት ሊቀየር የሚችል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአፍሪካም እንደ ናይጄሪያ ያሉ የፌዴራሊዝምን የመንግሥት አደረጃጀት የሚከተሉ አገሮች እንዲህ ዓይነት ለውጦችን ማድረጋቸውን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያም ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
ይሁንና አሁን አገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ትኩሳት አንፃር እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ወዳልተፈለገ ብጥብጥና ተጨማሪ ግጭቶች ሊያመሩ ይችላሉ በማለት ያስጠነቅቃሉ፡፡
የደቡብ ክልል ከ58 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ክልል ሲሆን፣ በዘጠኝ ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የተዋቀረ ነው፡፡ ክልሉ አምስት የቀድሞ ክፍለ አገሮችን በመቀላቀል የተፈጠረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2007 የክልሉ ሕዝብ ብዛት 14,929,548 እንደነበረ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡